ክፍል አንድ
ክርስቶስ በሥጋ ስለ መወለዱ የተዘመሩ መዝሙሮች
ቅዱስ ኤፍሬም
በዚህ ቀን ቃላቸው ተፈጽሟል ፣ የተናገሩትም ሁሉ ሆኗልና ይህ ቀን ነቢያትን ፣ ነገሥታትንና ካህናትን ደስ ያሰኛቸው ቀን ነው ። በዚህ ዕለት ድንግል አማኑኤልን በቤተ ልሔም ወልዳለች ። ኢሳይያስ በጥንት ጊዜ የተናገረው ቃል ዛሬ እውን ሆነ ። የአሕዛብን ቊጥር በጽሑፍ የሚናገረው እርሱ በዚያ ተወለደ ። በአንድ ወቅት ዳዊት የዘመረው መዝሙር ዛሬ ተፈጸመ ። በአንድ ወቅት ሚክያስ የተናገረው ቃል ዛሬ ሆነ ። ከኤፍራታ እረኛ መጥቷል ፣ በትሩም ነፍሳት ላይ ይገዛል ። ኦ ! ከያዕቆብ ኮከብ ወጣ ፣ ከእስራኤል ራስ ተነሣ ። በለዓም የተናገረው ትንቢት ዛሬ ተተረጎመ ። የተሰወረው ብርሃን መጣ ፣ ከሰውነቱም ውበቱ ፈነጠቀ ፤ በዘካርያስ የተነገረው ብርሃን ዛሬ በቤተ ልሔም በራ ።
የንጉሥ ከተማ በሆነችው በኤፍራታ የመንግሥቱ ብርሃን በራ ። ያዕቆብ የባረከው ቡራኬ ዛሬ ፍጻሜውን አገኘ ። ልክ እንደዚሁ ያች የሕይወት ዛፍ ሟች ለሆኑ ሰዎች ተስፋ አመጣች ። ስውር የሆነው የሰሎሞን ምሳሌ ዛሬ ተገለጠ ። ዛሬ ሕፃን ተወለደ ፣ ስሙም ድንቅ ነው ! እግዚአብሔር ራሱን እንደ ሕፃን መግለጡ ድንቅ ነውና ። መወለዱ ያለ ጋብቻ ነበርና መንፈስ ቅዱስ ትኩስ በሆኑ ቃላት አስቀድሞ በምሳሌዎች (ስለ እርሱ) ተናገረ ። መንፈስ ቅዱስ (አስቀድሞ) ያመላከተው ምሳሌ ዛሬ ትርጉሙ ተገለጠ ። ከእርሱ አስቀድሞ በደረቅ መሬት ላይ እንዳለ ሥር መጣ። በስውር የተነገረው ዛሬ በግልጽ ተደረገ ። በይሁዳ ተሰውሮ የነበረውን ትዕማርም ከጭኑ መካከል የሰረቀችው ስውር በሆነ ሁኔታ የወደደችው ንጉሥ ዛሬ ማራኪ የሆነውን ውበቱን ተነሣ ። ሩት በእርሱ የተሰወረውን የሕይወት መድኃኒት አውቃለችና በቦዔዝ ጎን ተኛች ። ለሁሉም ሕይወትን የሚሰጠው ከእርሷ ዘር ተነሥቷልና ዛሬ መሐላዋ ተፈጸመ ። እናታችን ሔዋን የተወለደ ካልሆነው/እናትና አባት ከሌሉት ከወንድ ወለደች። (እንዲህ ከሆነ) የሔዋን ልጅ እንዴት ያለ ወንድ ወልዳለች ቢባል አትታመንም ! ድንግሊቱ መሬት የምድር ንጉሥ የነበረውን አዳምን ወለደች ! ዛሬ ደግሞ ድንግል በሰማያት ላይ ንጉሥ የሆነውን አዳምን ወለደች ። የአሮን በትር አበበች ደረቋም እንጨት ፍሬ አፈራች ። ከድንግል ማኅፀን (ወንድ) ልጅ ተወልዷልና ምሥጢሩ ዛሬ ግልጽ ሆነ ።
አዳኛችን እስካልመጣ ድረስ ትንቢታቸው እውነተኛነቱ አልተረጋገጠምና ነቢያትን እንደ እውነተኞች የሚመለከት ያፍራል። የእውነት አባት ከሆነው (ከአብ) የመጣውና የእውነተኛ ነቢያት ትንቢት የፈጸመው እርሱ ይባረክ። ጌታ ሆይ ከሀብትህ ግምጃ ቤት ከቅዱሳት መጻሕፍትህ መዝገብ የአንተን መምጣት ለመመልከት የናፈቁትን (አስብ) ። ኖኅን የሸፈኑት ሁለቱ ወንድማማቾች በኩራት የሰከረውን የአዳምን ዕርቃን ሊሸፍን የሚመጣውን የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ ተመለከቱ። ሴምና ያፌት ደግና መልካም ሁነው ሊመጣ ያለውን ፣ ፣ ከነዓንንም ከኃጢአት ባርነት ነጻ የሚያደረገውን ደጉን (የእግዚአብሔር) ልጅ ፈለጉት።
መልከ ጸዴቅ ሊቀ ካህን እንደ መሆኑ የክህነት ጌታ የሆነውን ሂሶጱም ዓለምን የሚያነጻውን ይመለከት ዘንድ ጠበቀው። ሎጥ ተፈጥሮአዊ/እንደተለመደው ያልሆነውን ቅድስና የሚሰጠውን ጌታ ተመልክቷልና ሰዶማውያን ተፈጥሮን እንዴት እንዳጎደፏት አስተዋለ ። አሮን በትሩ እባቦችን የሚውጥ ከሆነ የክርስቶስ መስቀል ደግሞ አዳምና ሔዋንን የበላችውን እባብ እንደሚውጥ ተመለከተ። ሙሴ የእባቡን መርዝ የፈወሰውን የተሰቀለውን (የነሐሱን) እባብ ተመልክቷልና የጥንቱን እባብ ቊስል የሚፈውሰውን እርሱን አስተዋለ። ሙሴ እርሱ ብቻ ከእግዚአብሔር ብርሃን እንደተካፈለ ተመልክቶ በትምህርቱ (የጸጋ) አምላክነትን የሚሰጠውን እርሱን ፈለገ ።
ሰላዩ ካሌብ የወይን ዘለላ በመሎጊያ ይዞ መጣ ፣ ወይኑ ዓለም የሚያጽናናውን (እውነተኛውን) ዘለላ ያይ ዘንድ ናፈቀ። የመጠሪያ ስሙን ኃይል ያውቅ ዘንድ እርሱን የነዌ ልጅ ኢያሱ ናፈቀው ። (ኢያሱ ማለት መድኃኒት ማለት ነው) በኢየሱስ ስም በኃይል ድል ካደረገ ክርስቶስ በልደቱ ምን ያህል ድል ያደርግ ይሆን ? ይህ ፍሬ ሰብስቦና ተሸክሞ ይዞ የመጣው ኢያሱ ፍሬው ለሁሉም ሕይወትን የሚሰጠውን የሕይወትን ዛፍ ይናፍቅ ነበር ። እርሱን ረዓብም ትፈልገው ነበር ። ቀዩ ፈትል በምሳሌ ከቊጣ ባዳናት ጊዜ በምሳሌው ከእውነት ቀመሰች። እርሱን ኤልያስም ናፈቀው። እርሱንም በምድር ላይ ባላገኘው ጊዜ ይመለከተው ዘንድ እጅግ ንጽሕ በሆነ እምነት ወደ ሰማይ ዐረገ ። ሙሴ ተመለከተው ኤልያስም እንዲሁ ። ትሑቱ ሰው /ኤልያስ/ ከጥልቅ ወደ ላይ ወጣ ፣ ቀናዒውም ጌታ ከላይ ወደ ታች ወረደ ፤ በመካከልም (የእግዚአብሔርን) ልጅ ተመለከተው ። (ሙሴና ኤልያስ) የመምጣቱን ምሥጢር ተመለከቱ ። ሙሴ የሙታን ምሳሌ ኤልያስ የሕያዋን ሲሆኑ በምጽአቱ ይገናኙት ዘንድ ሄዱ ። ሞቱን የቀመሱ ሙታን ፊተኛ እንዲሆኑ የቀሩት ያልተቀበሩትም እርሱን ይገናኙት ዘንድ ኋለኛ ሆነው ይነጠቃሉ ።
ደካማ ፍጥረቶች በሆንነው በእኛ አንደበት ይቊጠር ዘንድ የማይቻለውን (የእግዚአብሔርን) ልጅ የፈለጉትን የጻድቃንን ቊጥር ሊቆጥር የሚችለው ማን ነው ? እንግዲህ ተወዳጆች በሚቻለኝ መጠን በሌላ ጊዜና በሌላ ትረካ አስቀድሞ ያዩትን እተርክ ዘንድ ጸልዩልኝ ። ወደ እኛ የመጣውን የእውነትን ልጅ ያመሰግን ዘንድ ብቁ የሆነ ማን ነው ? በትውልዳቸው ያዩት ዘንድ ጻድቃን የናፈቁት እርሱን ነው። እርሱ የኪሩቤል ጌታ ነውና አዳም እርሱን ፈለገው። አቤል በእርሱ ዘመን ይመጣ ዘንድ እርሱ ካቀረበው በግ ይልቅ የእግዚአብሔርን በግ ይመለከት ዘንድ እርሱን ናፈቀ ። እርሱን ሔዋንም ፈለገችው ። የሴቶች ዕርቃን መራራ ነበር ፣ እርሱም በቅጠል ያይደለ ባጡት ክብር ይከድናቸው ዘንድ የሚችል ነውና። ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ አንዱን እየተመለከቱ ብዙኃኑ የገነቡት ግንብ ወደ ምድር መጥቶ ወደ ሰማይ የሚያወጣውን ግንብ ገነባ። እርሱ ነፍሶች መጠለያ የሚያገኙባትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይገነባልና የሕያዋኑ መርከብ በምሳሌ ጌታን ተመለከተ ። በጥፋት ውኃ ቀን ምድር ተከፋፍላ ነበር ። እርሱ በእሳት ልሳኖች ምድርን ለሐዋርያት አከፋፈላት ። እርሱ ወደ ምድር መጣና ጥምቀትን (ባርኮ) ጀመረ፣ ሰዎች በእርሱ ወደ ሰማይ ሄዱ ። ሴትና ሄኖክ ከነዓንም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠርተው ነበር ። በጸጋ ወንድሞቹ ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔርን ልጅ ፈለጉ። ማቱሳላ ከሺህ ዓመት ጥቂት የጎደለውን ዕድሜ ኖረ ፤ እርሱም የማያልቀውን ሕይወት ወራሾች የሚያደርገውን (የእግዚአብሔር) ልጅ ናፈቀ ። ጸጋም ራሱ ስውር በሆነ ምሥጢር ጌታቸው በእነርሱ ዘመን ይመጣና ጉድለታቸውን ይሞላ ዘንድ ይለምን ነበር። መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ስለ እነርሱ በተመስጦ ይለምናል። (መንፈስ ቅዱስ) አነቃቃቸው በእርሱም የሚናፍቁትን ያንን አዳኝ ተመለከቱ ።
ይቀጥላል