የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንኳን 2015 ዓ.ም. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

የእርሱ የሆኑትን ሕዝቦች ፣ እረኝነቱ የሚያስፈልጋቸውን በጎች ፍለጋ አማኑኤል ወደ ዮርዳኖስ መጣ ። ንስሐ የሚገቡት የከበሩ መሆናቸውን ሊያሳይ የንስሐ ጥምቀት ወደሚጠመቁት ዘንድ ሄደ ። ከሁሉ የከበረ አገልግሎት ሰዎችን ለይቅርታና ለንስሐ ማብቃት መሆኑን ሊያሳይ ወደ ንስሐ ሰባኪው ወደ ዮሐንስ መጥምቅ ዘንድ ገሰገሰ ። በእውነት የምእመናን ቍጥር ሳይቀንስ በጥምቀቱ መታሰቢያ ቀን ይታያል ። ወትሮም ወደ እውነተኛዋ ዮርዳኖስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ ክርስቶስ ይጣራል ። ጎዳናውን የሚያጸዱ ቡሩካን ናቸው ፣ ክርስቶስ የሚያልፍበትን ልባቸውን ከቂም ከበቀል የሚያነጹ ጻድቃን ናቸው ። ብዙ ሕዝብ በጥምቀቱ መታሰቢያ ቀን ይታያል ። የተለያየ እንዲገናኝ ፣ ብቸኝነት “የሰው ያለህ” ያሰኘው በሕዝብ ግፊያ ፣ ሙቀትና ኃይል እንዲሰማው ጥምቀቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል ።

ጭንቀት የሚሰማው እልል ሲልና እልልታ ሲሰማ የወጠረው ክፉ ስሜት ይበናል ። ሁሉም ሰው በየቤቱ ሆ ማለት ይችላል ። አደባባይ ወጥቶ ሆ የሚለው ለእግዚአብሔር ነው ። አምልኮቱ እንዳይቀር ፣ በዓሉና ባሕሉም እንዲጸና ቤተ ክርስቲያን ትመክራለች ። የእግዚአብሔር ቤት ሲሞላ ከማየት የበለጠ የሚያስደስት ምንም ነገር የለም ። ለዘመናት ጥበቃ የማያስፈልገው በዓል በዓለ ጥምቀት ነው ፤ ምክንያቱም ሁሉም ሕዝብ በአምልኮ ልብ ይወጣልና ማን ሊረብሽ ይችላል ! ይህ የአደባባይ በዓል ኢትዮጵያ በነጻነት የመኖርዋ ምልክት ነው ። ሃይማኖትም እንዲህ ባላገር ሁኖ በጎዳናው ሞልቶ መታየቱ ኢትዮጵያን ልዩ ያደርጋታል ።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ሁሉ በአንድ ቀን ፣ በተመሳሳይ ሰዓት ፣ በአንድ ዓይነት ዝማሬና ሥርዓት በዓሉ ይከበራል ። የአንዱ ደብር በዓል ከሌላው አይበልጥም ። በሃይማኖት ውድድር የለምና ።

ወዳጆቼ ሆይ ስሙኝ !

እናንተ እንዲህ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስትመጡ የአባቶችና የአገልጋይ ዲያቆናት ልብ በደስታ ይሞላል ። የእግዚአብሔር እንግዳ የሆናችሁትን እናንተን ለመቀበል ካህናት ይተጋሉ ። ታላቅ ቅንዓት ሊሰማን ይገባል ። የዛሬው ምእመን ነገም እንዲመጣ ፣ አምና ያለፈው ዘንድሮ ንስሐ እንዲገባ ፣ ቀጠሮ ያበዛው ቀጠሮውን ሰብሮ ሥጋና ደሙን እንዲበላ ቅንዓት ይሰማናል ።

በዓለ ጥምቀቱን የሰላም የደስታ ያድርግልን !

ይቆየን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ