የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንደገመትነው አይደለም

ያኰረፈን ስለ ኮራ፣ ዝም ያለን ጊዜው የእኔ ነው ብሎ አይደለም፤ እኛ ከማናውቀው ከራሱ ችግር ጋር እየታገለ ስላለ ነው። ፊቱ የተጨማደደው ፣ ዝም ብሎን የሄደው እኛን ጠልቶ አይደለም፤ የሕክምና ውጤቱ ደስ የማያሰኝ ስለ ነበረ ነው። እርሱ ስለ ካንሰር ያስባል፣ እኛ ስለ ፈገግታ እናስባለን። ያልመጣው፣ ቀጥሮን መንገድ ላይ ያቆመን የተሻለ ስላገኘ አይደለም። አደጋ ገጥሞት ፣ ራሱን ስቶ ነው። ስልካችንን ያላነሣው ይለምኑኛል ብሎ ሰግቶ አይደለም ፣ በአካል ለማግኘት ፈልጎ ነው።

ያልመጣው ጥሪያችንን ንቆ አይደለም፣ ያሠራልን ያገር ልብስ አልደርስ ብሎት ነው። የእናቱን ሞት ሰምቶ ከምቾት አገር ያልመጣው፣ አልነገረንም እንጂ በወረቀት ምክንያት ስለ ታሰረ ነው። ያላገለገለው ትንሽና ድሀ ስለሆንን ንቆን አይደለም፤ ልጁ ሞታበት ቀብር ላይ ስለ ነበረ ነው። ያልሰጠን ስለ ሰሰተ አይደለም፣ ንብረቱ ሁሉ ታግዶ ችግር ላይ ስለነበረ ነው። ጠይቀነው ዝም ያለን የራሳቸው ጉዳይ ብሎ አይደለም፣ ስለ እኛ ሰዎችን እየለመነ ስለ ነበረ ነው። ልቅሶአችንን ያልደረሰው ውለታ በላ ስለሆነ አልነበረም፣ የስምንት ዘመዶቹን መርዶ ሰምቶ ኀዘን ላይ ስለ ነበረ ነው። እየጠጣ ወደ ቤቱ የሚገባው በጣም ስለ ተመቸው አይደለም፣ መደበቅ የሚፈልገው ውስጣዊ አባራሪ ስለ መጣበት ነው። ሳይነግረን የመጣው ቀጠሮ ማስያዝ እንደሚገባው ረስቶ አይደለም፣ ከሞት ጋር እየታገለ ስለ ነበረ ነው። የጠባይ ለውጥ ያመጣው ምን ያመጣሉ ብሎ በእጁ ስላስገባን አይደለም፣ ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት ገጥሞት ለመዋል ለማደር ተቸግሮ ነው። ዝምታን ያበዛው አስጠልተነው አይደለም፣ ብነግራቸው ይጎዳሉ ብሎ ነው ። ለመክፈል የዘገየው ብልጥ ሆኖ አይደለም፣ ከሥራ ስለ ተባረረ ነው።

ከሰው የሚሸሸው በደሉኝ ብሎ አይደለም፣ የገጠሙት ክፉዎች ሁሉን እንዳያምን ስላደረጉት ነው። አገር ካገር የሚዞረው ስለ ደላው አይደለም፣ የገዛ ትዳሩና ልጆቹ ጠላት ሆነውበት ነው፡፡ የሚነጫነጨው ሌላ ለምዶ አይደለም፣ ትሞታለህ የሚል ድምፅ ሰምቶ ነው። የሚቆጣው ሥራችን ስላላስደሰተው አይደለም፣ ከራሱ ጋር ያለውን ትግል ማንም ስላልተረዳለት ነ ው። ያመሸው ትዳሩ ላይ እየባለገ ስለ ነበር አይደለም፣ የደረሰበትን አደጋ ቢነግረን ይደነግጣሉ ብሎ ነው።

እንደገመትነው አይደለም። እርሱን ብንሰማውና እውነቱን ብናውቀው ራሳችንን ክፉ ነህ እንለው ነበር። ራስን ብቻ ማዳመጥ ትንሽ ሰው እንደሚያደርግ ይገባን ነበር። እኛን ስለ ልጃችን ጠባይ የሚመክረን እርሱ ልጅ ቀብሮ ነው። በነጻ የሚፈልገን ያለሁላቸው እኔ ብቻ ነኝ ብሎ ስላሰበ ነው ። እንዳላውካቸው ብሎ የሚሸሸን እርሱ የእኛን ችግር ሲካፈል የኖረ ነው። የዛሬውን ሳይሆን የትላንቱን ፣ ተራራ አብረን የገፋንበትን ቀን እናስብ ። ሃያ ዓመት የሳቀልን አንድ ቀን እንዲያኮርፍ እንፍቀድለት ። ዛሬ ደክሞት ነው ፣ መፈለግ የኛ ተራ ነው እንበል። ወዳጅ እንዲሁ አይጣልም። ወዳጅ በገንዘብ አይለወጥም። ደጉን ቀን እያሰቡ ያልፉታል እንጂ በአንዲት ሰባራ ቃል አይሸኙትም። ብቻ እንደገመት ነው አይደለምና እግዚአብሔር ሆይ ይቅር ይበለን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ