የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /3/

“ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆኑ አምናለሁ ። በዛሬ ዘመን ግን መውለድ ያስፈራኛል ። ልጆቼ ከእኔ ፈቃድ ውጭ ቢወጡስ ብስጭቱን እችለዋለሁ ?” እያልህ ይሆን ? ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ብቻ ሳይሆኑ የእግዚአብሔር አደራም ናቸው ። ልጆችህን ከእውቀትህ ብቻ ሳይሆን ከሕይወትህም ልታስተምራቸው ይገባል ። በተፈጥሮ ካንተ የሚወስዱት ጠባይ እንዳለ ሁሉ በልምምድ ደግሞ ካንተ የሚወርሱት ነገር አለና ከመውለድ በፊት የሕይወት ለውጥ ወሳኝ ነው ። አንተ አልኮል እየጠጣህ መጠጥ ክፉ ነው ብትላቸው አንደኛ ስትስማቸው በትንፋሽ ታስለምዳቸዋለህ ፣ ሁለተኛ እንደ ተከለከሉ እንጂ መጥፎ እንደሆነ አይረዱምና ሲያድጉ የመጀመሪያ ሥራቸው አልኮል መቅመስ ይሆናል ። ልጆች የአዳሪ ተማሪ ናቸውና የሚማሩት ከሕይወትህ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የእነርሱ ንጉሥም ጳጳስም አንተ ነህና አንተን ያያሉ ። ልጆችህ ባንተ ላይ ስላላቸው እምነት እንኳ መለወጥ ግድ ይልሃል ።
ልጆች ላንተ የሚሰጡህ ብዙ ነገሮች አሉ ። ቅዱስ ፍርሃትን ያለማምዱሃል ።እንደ ድሮው ተቆጡኝ ብለህ ቡጢ መሰንዘር ፣ ተናገሩኝ ብለህ ሥራ መልቀቅ አይታሰብም ። ስለ ልጆችህ ስትል ትዕግሥትን ትለማመዳለህ ። እግዚአብሔር ትዕግሥትን የማይወደውን የሰው ማንነት መታገሥን ከሚያለማምድበት መንገድ አንዱ መውለድ ነው ። ስለ ፍቅር ግድ የሌለህና ስለ ፍቅር በሚያወሩ የምትስቅ ከነበርህ እግዚአብሔር በትንሹ ሕፃን ፍቅር አቅልህን/አእምሮህን ይቆጣጠረዋል ። አንተን ትልቁን ሰውዬ በትንሹ ሕፃን ቆዳ ጠቅልሎ ልክህን ያሳይሃል ። እንደሚወድህ ማረጋገጥ ሳትፈልግ የምትወደው ልጅህን ነውና ምክንያት የለሽ ፍቅርን በልጆች ትማራለህ ። ከመውለድ በፊት ያየኸው ልብስ ያምርህ ነበረ ፣ አሁን ግን ለልጄ ትላለህ ። ራስ ወዳድነትን እየጣልህ እንደሆነ እወቅ ። ትልቁ የገነት ኃጢአትና የሞት በር ራስ ወዳድነትን የምትጥለው አንዱ በመውለድ ነው ። የወላጆችህ ፍቅር ብዙም ግድ አይሰጥህም ነበረ ፣ እንደ ጤንነትም አትቆጥረውም ነበረ ፤ “ወልደህ እየው” ሲሉህም ምርቃት መስሎህ ነበረ ። አሁን ግን ወላጆችህ ላንተ የከፈሉት ዋጋ ይገባሃል ። መውለድ በወላጆችህ ላይ የነበረህን ግድ የለሽነት ያስጥልሃል ። መቼም ሁሉም ወላድ በዚህ መንገድ ይማራል ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ቀና ሰዎችን ሁሉን ለትምህርት ያደርግላቸዋል ማለት ነው ።
ልጆች ዋጋ እየከፈልህ የምትወዳቸው ናቸው ። እነርሱ ከመጡ በኋላ የቤት ወጪህ ጨምሯል ። የኖረው ብርጭቆ ይሰባበራል ። ነገር ግን ከሚያከስሩህ የሚሰጡህ ደስታ ይበልጣልና ደግመህ አታስበውም ። የመጀመሪያ ልጅህን ስትወልድ አዲስ ስለሆንህ አንተም ተጨንቀህ ልጁንም ታስጨንቃለህ ። ልጁን ብቻ ሳይሆን ነጻነቱንም ትወደዋለህ ። ልጄ ይህን መምሰል አለበት ብለህ የሳልከውን ሥዕል ከመጀመሪያ ልጅህ ትጠብቃለህና ዱላና ቁጣ ታበዛበታለህ። ገና እስከ ሰማንያ ዓመት የሚማረውን በሰማንያ ወራት እንዲማርልህ ትፈልጋለህ ። ስለዚህ የመጀመሪያ ልጅህ ሳታውቀው ትጎዳዋለህ ። ኋላ ላይም ትንንሾቹ አጥፍተው እርሱን ትገርፋለህ ። በሁለተኛው ልጅ ትንሽ ትበርዳለህ። ሦስተኛው ላይ ከፍቅር በላይ ስለ ምቾቱ ታስባለህ ። በአራተኛው ላይ ልጁን ወደህ ነጻነቱን ትተውለታለህ ። ብዙ ጊዜ የመጨረሻ ልጆች የማይነኩት ለዚህ ነው ። አንተም ይደክምሃል ፣ ሁሉም ነገር በጊዜው እንደሚሆን ታምናለህ ። የመጀመሪያ ልጅህ የጉብዝና በትርህ ስላረፈበት ገሸሽ ሲልህና ሲወቅስህ ፣ የመጨረሻው ግን ድካምህንና ፍቅርህን ብቻ ስለሚያውቅ ያዝንልሃል ። ሁሉም ልጆችህ የመጨረሻው ላይ ጥለው አንተን ይረሱሃል ። ብቻ መውለድ መልካም ነው ፣ የመውለድ መጨረሻው ግን መሐንነት ነው ። ሁሉም የራሱን ኑሮ ሲጀምር ቤትህ ፀጥ ይላል ። በድሀ አገር ልጆች የሚወለዱበት ምክንያት ይጦረኛል በማለት ነው ። የሚጦር ግን እግዚአብሔር ነው ።
እምነትህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ እንጂ ወርደህ በልጅ አትታመን ። ዳዊት ለልጆቹ በጣም ይሳሳ ነበር ። አምኖንን በጥፋቱ ትቶታል ፣ አቤሴሎም ወንድሙን ገድሎም መልሶ ባብቷል ። ነገር ግን የሳሱለት ዘመድ አይሆንምና ልጆቹን ከስሯል ። ደግ ነኝና ደግ ልጅ እወልዳለሁ ብለህ አታስብ ። እንዳንተ የሆንከው አንተ ብቻ ነህ ። ልጅህ ከባሕርይህ የተከፈለ እንጂ ተቀጥሎ የሚኖር አይደለም ። የራሱ ምርጫ አለው ። ደጉ ዳዊት ዓመፀኛ እንደ ወለደ አትርሳ ። የዓመፀኞቹ የአዳምና የሔዋን ልጅም አቤል መሆኑን አስታውስ ። ዓለም ለግምት አይሆንም ። ካህኑ ዔሊ ልጆቹን ለመቆጣት እንኳ ሳሳ ። በመጨረሻ ልጆቹንም አጣ ። እርሱም አጉል ሞት ሞተ ። አዎ ልጅህን ገሥጽ ፣ አስተምር ። ልጅህን በዱላ ስትቀጣ ግን በጣም ተጠንቀቅ ።ሰይጣን እያንዳንዱን ገጠመኝ የሞት ምክንያት እንዲሆን ይሠራልና በጣም አስብበት ። በጥፊ የሞቱ ፣ በአንድ አለንጋ እዚያው የቀሩ አሉ ።
ደግሞም በዚህ ዘመን እንዴት እወልዳለሁ አትበል ። በየትኛውም ዘመን ኃጢአት ነበረ ። ልጅ የእግዚአብሔር ሲሆን ላንተ ግን ስጦታ ነው ። በልጅ ምክንያት እምነት እንዳታጣ ተጠንቀቅ ።
አንድ ትልቅ ባለሥልጣን የነበሩ ሰው እንዲህ ብለው መከሩኝ ፡- “አሥራ ሁለት ልጅ ወልጃለሁ ፣ አንዱም አይመስለኝም ፣ ሁለት መጽሐፍ ጽፌአለሁ የእኔን አሳብ ያንጸባርቃሉ ። ልጅ እንደ ራሱ ነው ፣ መጽሐፍ ግን እንዳንተ ነው ። ስለዚህ ጻፍ “ ብለውኛል ። አዎ ልጅ የራሱን አሳብ ቢከተል ብዙም አትጨነቅ ። ወጉ ነው ። አንተ ግን የቀናውን መንገድ ምራው ። በጠዋት የመከርከው በማታም ይሰማሃል ። በልጅነቱ ያነጽከው በጎልምስናውም ያከብርሃል ። ላንተ ፍቅር እንዲኖረው እርሱን በጣም አትውደድ ፣ እናቱን ስትወድ ፣ ያን ጊዜ ላንተ ፍቅር ይኖረዋል ። ላንቺ ያለውን ፍቅር ልጅሽ የሚረዳው አባቱን ስትወጂ ነው ። ብዙ ባለ ትዳሮች ያልተረዱት ምሥጢር ይህን ነው ። ሲወልዱ የትዳር ፍቅራቸውን ሁሉ ለልጁ ይሰጣሉ ። በረከቱን ሕይወት አድርገው ይኖራሉ ። ቢሆንም መውለድ ስጦታ ነውና አለመውለድም ስጦታ ነው ። ሁሉ አይወልድም ፣ መውለድም አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም ። የተወለዱትን መታደግም መውለድ ነው ። ያልወለዳችሁም አመስግኑ ። እግዚአብሔር ያየውን አይቶ ይከለክላልና ። የማትወልዱት መንፈስ እየተዋጋችሁ ነው ከሚሉና ነጻ እናውጣችሁ ከሚሉ ተጠንቀቁ ። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው ከተባለ እግዚአብሔር ልኮ ማን ያስቀረዋል ?
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 8
ተጻፈ በአዲስ አበባ
መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ