“ጓደኞች ቢኖሩኝ ደስ ይለኛል ፤ ነገር ግን የሚዘልቅ ጓደኛ እየጠፋ ነው ። ሁሉም ነገር ወረትና ጥቅም ብቻ ሁኗል ። የትላንቱ ይደገማል ብዬ ስለምሰጋ ጓደኛ አያስፈልገኝም እላለሁ ። አሁንም ጓደኛ ይዤ ቢከዳኝስ ?” እያልህ ይሆን ? እግዚአብሔር የፈጠረህ ለማኅበራዊ ኑሮ ስለሆነ ብቸኝነት ይጎዳሃል።አንተ የተሸከምኸው ተፈጥሮ ለራስህ ብቻ ቢሆን ኑሮ ተፈጥሮ ባክኗል ። የሚቀበል እጅ ብቻ ሳይሆን የሚሰጥ እጅም ተቀብለሃል ። ሀብሀብ የተባለ ፍሬ የምታውቅ ከሆነ አንድ ጣፋጭ ለማግኘት መቶ ጊዜ ትሞክራለህ ፣ ጓደኞችም ልክ እንደዚህ ናቸው ። አንዱን መልካም ለማግኘት መቶ መሞከር ግድ ይላል ። በዚህ ዓለም ላይ ጓደኝነት የምታፈራበት የዕድሜ እርከን አለ ። የልጅነት ጓደኛ ፣ የትምህርት ቤት ጓደኛ ፣ የወንድም ጓደኛ ፣ የቤተ ክርስቲያን ጓደኛ ፣ የሥራ ጓደኛ ፣ የሻይ ቡና ጓደኛ ፣ የምክር ጓደኛ ፣ የፍቅር ጓደኛ ፣ እያልን መዘርዘር እንችላለን ።
የልጅነት ጓደኛ ጥብቅና ትዝታው በልብ ተቋጥሮ የሚቀር ነው ። የልጅነት ጓደኛ ግን ሰፈሩን ስትለቅ የሚያበቃ ነው ። የትምህርት ጓደኛ ትምህርት እስኪፈጸም ድረስ አብሮ የሚቆይ ነው ። ገብስ ፣ ገብሱን የሚያወራ ጥንቃቄ ያለው ኅብረት ነው ። የወንድም ጓደኛ ብዙ መንታዎች ላይ የሚንጸባረቅ ነው። የሥጋ ብቻ ሳይሆን የአሳብ ቁርኝትም ያለው ነው ። የቤተ ክርስቲያን ጓደኛ ሃይማኖት የሚያገኛኘው ነው ። ሲለያይ ጥላቻው ከዓለም የከፋ ነው ። የክርስቶስ ፍቅር ብቻ የሚያስቀጥለው ነውና ። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያገኘኸውን ሰው የትኛውም የኑሮ ዘርፍ የማያገናኝህ ወንድም ነው ። ከቤተ እግዚአብሔር ስትርቅ በመንገድ እንኳ አታየውም ። የሥራ ጓደኛ የጋራ ጥቅም የሚያገናኘው ነው ። የሻይ ቡና ጓደኛ ቢያሙት የማይከሳውን መንግሥትን ለመቦጨቅ የሚያገለግል ነው ። ሰው አባወራነት ሲያቅተው የሚደበቀው ንጉሡን በማማት ነው ። የምክር ጓደኛ አስተዋይ ወይም የሃይማኖት መምህር ነው ። ለጭንቅ ቀን እንደ መድኃኒት የሚፈለግ ነው ። እውነተኛ ወዳጅ ይህ ሳለ በምቾት ቀን ግን አትፈልገውምና ምስኪን ነህ ። አንተ ሆይ ! ደስታም መካሪ ያሻዋል ። የፍቅር ጓደኛ ካንጀት የምትወደውና የሚወድህ ሲሆን ያለ ፕሮቶኮል የምትቀርበው ነው ። እውነተኛ ነጻነት የምታገኘው የማይታዘብህ ይህ ሰው ጋ ነው ።
ጓደኝነት ከሥጋ ይልቅ የአሳብ ዝምድና ነው ። ጓደኝነት ሁለት ሰዎች ለአንድ ዓላማ ሲሰለፉ የሚገኝ ኅብረት ነው ። ዓላማ የሌለው ጓደኝነት እንዳልታሰረ ነዶ የተዘራበት ጋ ረግፎ ይቀራል ። በዓለም ላይ ጓደኛ መፈለግ ከባድና ሩቅ ነው ፤ ጓደኛ መሆን ግን ቀላልና ቅርብ ነው ። በዓለም ላይ ጓደኛዬ ማነው ማለት አድካሚ ነው ። እውነተኛው ጥያቄ ጓደኛ ልሆንለት የሚገባው ማነው ? የሚለው ነው ። ጓደኛህ ዛሬ የአንተ እርዳታ የሚያስፈልገው እርሱ ነው ። ጓደኝነት ብርቱ ነው ። ሰው ከወንድሙ የደበቀውን የሚያወራው ለጓደኛው ነው ። ጓደኛ የንስሐ አባት ነው ። ለንስሐ አባት አንኳሩን የሚናገረው ሰው ለጓደኛው ግን ዝርዝሩን ይናገራል ። ጓደኛ ነቀፋው እንኳ የምርቃት ያህል ነው ። ጓደኛ ራስን የሚገልጡለት እውነተኛ ሸፋኝ ነው ። ያንን ጓደኛ የት አገኛለሁ ? አትበል ፤ ያንን ጓደኛ ዛሬ ሁን ። ጓደኛ ምሥጢርን ጠባቂ መሆን አለበት ። ጓደኛ ይቅር መባባል አለበት ። ጓደኛ ፣ ጓደኛውን ለቁምነገር ማድረስ አለበት ። ጓደኝነት ኪዳን ያለው ሊሆን ይገባዋል ።
የንጉሥ ሳኦል ልጅ ፣ አልጋ ወራሽ ልዑል ዮናታን እረኛውን ዳዊትን ከልቡ ይወደው ነበር ። ከቤተ መንግሥት ወጥቶ በሜዳ ያጫውተው ነበር ፤ መድረሻው ትልቅ እንደሆነም ለእረኛው ለዳዊት ይነግረው ነበር ። እውነተኛ ጓደኛ ከኑሮ ደረጃ በላይ ነው ። እውነተኛ ጓደኛ ተስፋውን በመንገር የጓደኛውን አቅም የሚያነሣሣ ነው ። ተስፋው የላላውን ፣ ሁሉ ጠላት የሆነበትን ዳዊትን አንተ ንጉሥ ትሆናለህ ይለው ነበር ። ምቀኛ ጓደኛ አይሆንም ፤ ቅን ግን ጓደኛ ይሆናል ። ዮናታን ዙፋኑን ለዳዊት ለቀቀለት ። ጓደኝነት ከዙፋን በላይ ነው ። ዮናታን በሞተ ጊዜም ዳዊት ለዮናታን ዘር ቸርነት አደረገ ። ጓደኝነት ከሞት በላይ ነው ። ሁለት ጓደኛ የሆኑ ወታደሮች አንዱ ሲወድቅ አንደኛው አፈር ሳላለብስ አልሄድም ብሎ ከሞት ጋር ይፋጠጣል ። ጓደኛ ጓደኛው በሌለበት ስለ ጓደኛው የሚመሰክር ነው ፤ ወይም ለጓደኛው አምባሳደር ነው ። ጓደኛውን የሚያሳማ እርሱ ርካሽ ነው ። ጓደኛ ሸፋኝ ነው ። ሁለት ሰዎች ያደረጉት ነገርም በምንም መንገድ ለሦስተኛ ሰው አይወጣም ። ጓደኝነት የምሥጢር መቃብር ነው።
“ጎጃም ተሸምቶ ይበላል በጌምድር
እየከዳ እንቢ አለ ዘመድና ምድር”
እንደ ተባለ ጓደኝነት ቢመናመንም ዛሬም ጨርሶ አልጠፋም ። ጓደኝነትን የሚጎዳው ነገር ምንድነው ? ቅናት የጓደኝነት ፀር ነው ። በችግር ዘመን ታማኝ የነበረ ጓደኛው ሲያገኝ የሚጣላ ከሆነ ቀናተኛ ነው ። ይህ ሰው ችግር እንዳይወጣ ዘብ የቆመ ነው ። የሞት ወኪልም ነው ። ጓደኝነትን ወረት ይጎዳዋል ። አዲስ ሰው ሲመጣ ከዚያ ጋር እፍ ማለት ጓደኝነትን ይሰብራል።ሐሜት ትልቁ የጓደኝነት ፀር ነው ። ጓደኛ አካል ነውና አይታማም ።
መክዳት እንጂ መከዳትን አትፍራ ። የማይሄደው እግዚአብሔር ሁልጊዜ ካንተ ጋር ነው ። ሊሰማህ ይችላል ፣ ሊሰብርህ ግን አይገባም ። ሐሰተኛ ሰዎች ሁሉን ሰው ሐሰተኛ አድርገው እንዳይስሉብህ ተጠንቀቅ ። ነጻ ፍቅርን ሁልጊዜ ስጥ እንጂ የሚገባው ለማን ነው ? አትበል ። በየዕለቱ በቀንና በሌሊት የሚጠብቁህ መላእክት አሉ ። ስለዚህ ብቸኛ አይደለህም ። ቅዱሳን ከበውሃል ። ፀሐይ የምታበራው ላንተ እንጂ ለራስዋ አይደለም ፣ እህትህ ናትና ደስ ይበልህ ። ያንተ የተቃጠለ አየር ለእጽዋት ሕይወት ነው ፤ ያንተ መጎዳትም ለብዙዎች ትምህርት ነው ። እጽዋትም አዲስ አየር ይሰጡሃል ።በዚህ ዓለም ላይ የማይሰጥ ምስኪን ድሀ ፣ የማይቀበልም ኩሩ ባለጠጋ የለም። በዚህ ሁሉ ቤተ ዘመድ ውስጥ የምትኖር ነህ ።
ክፉዎች ስለሚገኑብህ እንጂ ከሚጠሉህ የሚወዱህ ይበዛሉ ። በርሜል ሙሉ ውኃ ውስጥ ጠብታ መርዝ ቢጨመር የሚወራው ስለ መርዙ ነው ። ዓለም ሁሉ ቢወድህም የምትኖረው ከሁለት ሰው ጋር ነው ። ዓለም ሁሉ ቢጠላህም የምትኖረው ከሁለት ሰው ጋር ነውና ደስ ይበልህ ። ያለፉት ዘመናት ያስተምሩህ እንጂ አያስደንብሩህ ። ሽንኩርት እስከ መጨረሻው ብትልጠው ክፍል አለው ፤ ሰውም ተጠንቶ የሚያልቅ አይደለም ። ሰው ባለመውደቁ ሳይሆን በመማሩ የሚመሰገን ፍጡር ነው ። ትምህርት ሁሉ ዋጋ ያስከፍላልና ያለፈውን ለትምህርትህ አድርገው ። ዛሬ ግን ውደድ ። ፍቅር አማራጭህ ሳይሆን ግዴታህ ነው ። የክርስቶስ ሰላም ይፍሰስብህ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 9
ተጻፈ አዲስ አበባ
ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.