የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /5/

“በምን መስፈርት ይሁን አላውቅም ሰዎች እኔን ለማማከር ይመርጡኛል ። እኔም ሳላስበው የሰዎችን ችግር በመፍታት ሥራ ተጠምጄ ራሴን አገኘዋለሁ።ነገር ግን በምሰማው ነገር እንዳልፈተን እሰጋለሁ” እያልህ ይሆን ? ሰዎች በሥጋዊ ፣ በሥነ ልቡናዊና በመንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ ያልፋሉ ። ሥጋዊ ችግር ማጣት ፣ ሕመም ፣ ስደት ፣ እስራት … ነው ። ሥጋዊ ችግሮች የሥጋ ብቻ ሁነው የሚቀሩ አይደሉም ። መፍትሔ ካላገኙ የሥነ ልቡናና የመንፈሳዊ ጫናን ያስከትላሉ ። በችግር ምክንያት ጭንቀት ይፈጠራል ፣ ይህ የሥነ ልቡና ጉዳት ነው ። በችግሩ ምክንያት ወንጀል ውስጥ ሲገባ ደግሞ መንፈሳዊ ችግር ነው ። ሥነ ልቡናዊ ችግር የተለያየ ነው ። ጭንቀት ፣ ፍርሃት ፣ ከመጠን ያለፈ ድፍረት ፣ ይሉኝታ ፣ ጭካኔ ፣ ለመጀመር መፍራት ፣ ከትላንት ኑሮ ጋር መተሳሰር ፣ … ነው ። የሥነ ልቡና ችግር ሥጋዊ ችግር ያመጣል ። በጭንቀት ምክንያት አካል ይደክማል ። የምግብ ፍላጎት ይቀንሳል ፣ ወይም የምግብ ፍላጎት ይጨምራል ። የተጨነቀ ሰው ይህችን ካልጎረስኩ እሞታለሁ ብሎ ሲፈራ በጣም ይመገባል ። ከእንቅልፉ እየነቃም ሊበላ ይችላል ። አንዳንድ ሰው ጭንቀቱን ምግብ ላይ ይወጣዋል ። ፍርሃትም ከቤት እንዳይወጣ ፣ ሥራ እንዳይሠራ ምክንያት ሲሆን በዚህም የኑሮ መናጋት ይመጣል ። የሥነ ልቡና ችግር መንፈሳዊ ችግርም ያመጣል። ሰው መጨነቅ ሲጀምር እምነቱን እያጣ ይመጣል ። ሲፈራም ከእግዚአብሔር በላይ ሌላ ነገር እያከበረ ነው ማለት ነው ። ሰዎች ሁሉ ለእኔ መልካም አመለካከት የላቸውም ስለሚል የማያውቀውን ሰው ሳይቀር ለመበቀል ይነሣል።
መንፈሳዊ ችግር እግዚአብሔርን በአምልኮት ፣ ወንድምን በጥላቻ መበደል ነው ። መንፈሳዊ ችግር በመንፈሳዊ ነገር ካልሆነ በሌላ ነገር የማይደለል እውነት ፈላጊ ነው ። መንፈሳዊ ችግር ውስጥ የገባ ሰው ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የነቢይና የመነኩሴ ቃል ይፈልጋል ። ሲያልፍም ወደ ጠንቋይ ይሄዳል። እግዚአብሔርን ቢያገለግል እንኳ ሙያውን እንጂ እግዚአብሔርን ስለማይወድ ፍቅር የሌለው አገልግሎት ያገለግላል ። አንድ አገልጋይ ሲናገር የሰማነው ፡- “አገልግሎቴ ይበላሻል ብዬ እንጂ እገሌን መግደል እፈልግ ነበር” ብሏል ። ይህ ሰው የፈራው ዜናውን እንጂ ሥላሴን አይደለም ። ያለ መንፈሳዊነት ማገልገል ይቻላል ። እንደውም አገልግሎት ታክስ የማይከፈልበት ንግድ የሆነላቸው ብዙዎች ናቸው ። መንፈሳዊ ችግር ለቃሉ ፣ ለጸሎት ፣ ለኅብረት ጊዜና ልብ ማጣት ነው ። መንፈሳዊ ሕይወት ካነከሰ የማያነክስ የሕይወት ክፍል የለም ። መንፈሳዊ ችግር ለሥጋ ፈቃድ መገዛት ፣ በኃላፊ ዓለም ፍቅር መነደፍ ፣ በኃጢአት ኳስ መጫወት ነው ።
ሰዎች ወደ እኛ ለማማከር የሚመጡት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ይዘው ነው ። ለማማከር ለምን መረጡን ? ብለን መጠየቅ ጥሩ ነው ። መጠነኛ ዝምታችንን ሲያዩ ምሥጢሬን አያወጡም ብለው ነው ። መንፈሳዊ ምክር ስንሰጥ ሲያዩን የእኔ መፍትሔ እዚያ ይገኛል ብለው ነው ። ጥሩ ሰላምታ ስንሰጣቸው ጥሩ ሕይወት ያሳዩናል ብለው ነው ። በአጠቃላይ በትንሹ ስንታመን በብዙ አምነውን ነው ። የሚያማክሩን ሰዎች በዓለም ላይ ካሉት አክባሪዎቻችን የመጀመሪያዎቹ ናቸው ። ስለዚህ ልናከብራቸው ይገባል ። ምሥጢራቸውን ልንጠብቅ ፣ የተሻለ መንገድን ልናሳያቸው ፣ የሕይወት ሸክማቸውን ልንጋራላቸው ይገባል ። በአሳብ ብቻ ሳይሆን በገንዘብም ልንደግፋቸው ይገባል ። ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው ለዚህ ቀን ሊሆን ይችላልና ።
በማማከር ሂደት ውስጥ ከእኛ የሚጠበቀው የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር ማዳመጥ ነው ። ሰዎች ሲናገሩ ከግማሽ በላይ እፎይታ ያገኛሉ ። ሲናገሩ መንገዱ እየታያቸው ይመጣል ። ሰው አፉን ሲዘጋ አፉ መጥፎ ጠረን ይይዛል ፣ ሲከፍት ግን አዲስ አየር ይገባል ። በመናገራቸው ውስጥ የጠፋቸውን ውል ሊያገኙት ይችላሉ ። ለተጨነቁ ሰዎች ትልቁ እርዳታ ጆሮ ማዋስ ነው ። ችግራቸውን እያጋነንን መስማትና መግለጽ በፍጹም አይገባም።ከእግዚአብሔር በላይ የሆነ ችግርና ኃጢአት የለምና ። ተራችን ደርሶ ስናናግራቸው አንዳች የፍርድ ቃል መጠቀም የለብንም ። የሚያጽናና ቃልን ከእግዚአብሔር ቃል ፣ ከኑሮ ልምዳችን ልናካፍላቸው ይገባል ። በመጨረሻ አብረን መጸለይ ሁለታችንንም ይፈውሳል ። ከዚያ በኋላ ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው ። ችግሩን እየረሱት ከሆነ መቀስቀስ የለብንም ። ሌላ ነገር መጨዋወት ይገባል ። መናገር ከፈለጉ ግን መስማት ይገባናል ። የተቸገረ ሰው ተናግሮ አይረካምና ።
ሌላውን ሰው ስናማክር ራሳችንን ከፈተና ለመጠበቅ እንደ መርማሪ ፖሊስ መጠየቅ የለብንም ። የነገሩን ላይ ተመሥርቶ ማጽናናት ብቻ ተገቢ ነው ። የፍርድና በልብ የመታዘብ ስሜት ሊኖረን አይገባም ። እኛም ከቆምን የቆምነው በራሳችን አይደለምና ። ካማከርን በኋላ አብረን መጸለይ ሸክሙን እዚያው ለመጣል ይረዳል ። የአማካሪዎች አማካሪ ከሌለ አማካሪ እየተጎዳ ይመጣልና እኛ ደግሞ የምናማክረው የበላይ ሰው ያስፈልገናል ። ሌሎችን ለማማከር ጸጋ እንዳለን የምናውቀው ሰዎች ምርጫ እያደረጉን ወደ እኛ ሲመጡ ነው ። ያለንበት ዘመን የበዛ ችግር ሳይሆን ያነሰ አማካሪ ስላለ ችግሮች ገንነው ይታያሉ ። አማካሪ ከተገኘ ሕይወት ቀላል ነው ። ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ደግሞም ሕይወት ያለው የምክክር አገልግሎት እየጠፋ የቢሮ ሥራ ስለሆነ ፣ የክፍያ ምክርም ያን ያህል ስለማይረዳ ብዙ ሰዎች እየተቸገሩ ነው ።
አንተ ግን ብዙ ችግር ቢኖርብህም የሰዎችን ችግር ለመፍታት ስትጥር እግዚአብሔር ያንተን ፈተና እያራቀ ይመጣል ። መስጠት ብዙ መቀበል ነው።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 10
ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም.
ተጻፈ በአዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ