የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /7/

“የትዳሬ የወደፊት ሁኔታ ያጠራጥረኛል ፣ በርግጥ ባለቤቴ ጤናዋ የተሟላ አይደለም ፣ ውጤቱ ምን ይሆን ? እላለሁ ፤ የበሽታው ይሁን ወይም ያሰበችው አለመሳካቱ አላውቅም ብቻ በእኔ ደስተኛ አትመስለኝም ። ብዙ ነገሮችን ሳስብ የነገው ኑሮዬ ያሰጋኛል” እያልህ ይሆን ?
ትዳር ከእግዚአብሔር ነው ። የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምተህ የገባህበት ከሆነ ጥያቄ አይኖርህም ። ከጊዜያዊ ችግሮች ለማምለጥ ብለህ ፣ ቃሉን ገሸሽ አድርገህ ፣ የጠንቋይና የደላሎችን ንግርት ሰምተህ የገባህበት ከሆነ የምትማርበት ነው ። በዘመናት እግዚአብሔር የእገሌ ሚስት እገሊት ነች ብሎ አያውቅም ። ትዳር በሕይወት መንገድ ላይ የሚገኝ ፣ መርሕን የሚያከብር ጸጋ ነው ። ቀጥ ያለ ኑሮ እንኳን ከሰው ጋር ፣ ብቻህን ብትሆንም ሊኖር አይችልም ። ሕይወት ከፍና ዝቅ ያለ መንገድ ነው ። ተራራውን ስትጨርስ መስክ ታገኛለህ ፣ መስኩን ስትጨርስ ተራራ ይገጥምሃል ። ሁልጊዜ ተራራ የለምና አትጨነቅ ፤ ሁልጊዜም መስክ የለምና አትቦርቅ ። ደስታንም ኀዘንንም የምትሸከምበት ትዕግሥት ከእግዚአብሔር ለምን ። ወደ ትዳር የገባኸው ኪስህን ተማምነህ ከሆነ አደገኛ ነው ። ገንዘብ የሚመልሰው የገንዘብ ጥያቄን ብቻ ነው ። ለትዳር አቅም አስፈላጊ ነው ፤ በአቅም ብቻ ግን ትዳር አይመራም ። ያ ቢሆንማ የባለጠጎችና የባለሥልጣናት ትዳር የቀና በሆነ ነበር ። ትዳርን ኃላፊነት ብለኸው ቢያስደስትህ ወጉ ነው ፤ ደስታ ብቻ ነው ብለህ ከገባህ ግን ኃላፊነትንም እንደ ዕዳ ትቆጥረዋለህ ። ድምፅዋ ደስ ስላለኝ ነው ብለህ ብትገባ በዜማ የዛሬው ቁርስ አይታለፍም ። መመዘኛህ የላቀ ካልሆነ የምትኖረው ዝቅ ያለ ነው ። ነገሮችን በጣም መንፈሳዊ ለማድረግ አትሞክር ፣ ተመጻዳቂ ትሆናለህ ። የተበደርከውን ለመክፈል ጌታ ተናግሮኛል አትበል ፤ መመለስ ግዴታህ ነው ። ቤትህንም በግጥምጥሞሽ አትምራ ፤ የእኔ ስም ሰይፈ ሥላሴ ነው ፣ የእርስዋ ሥርጉተ ሥላሴ ነው ፤ ለእኔ እንደ ተፈጠረች ምልክቱ ይህ ነው አትበል ። ይህ የወፍ በረሮች መራቀቅ ነው ።
በአእምሮው የሚያስብ ወንድ ልጅ ጥቂት ነው ። አብዛኛው የሚያስበው በኪሱ ነው ። በራሱ የማይተማመን ወንድ በገንዘብ ለመግዛት ስለሚያስብ ሌባ ይሆናል ። በሌብነት የመጣ ኑሮም ሚስትን በሽተኛ ፣ ልጆችን ዓመፀኛ ያደርጋል ። ወንድ ልጅ ለትዳሩ የሚያስፈልገው ዋና ነገር የመጀመሪያው ፍቅር ፤ ሁለተኛው፡- ማዳመጥ ፤ ሦስተኛው፡- በጋራ መወሰን ነው ። ፍቅር ለማዳመጥና በጋራ ለመወሰን አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም ፍቅር የሚወደውን ሰው ይሰማልና ፤ ዳግመኛም ከእኔ የተሻለ አሳብ አለው ብሎ ስለሚያከብር በጋራ ይወስናል ። ብዙ ወንድ ልጆች የእኔ የሚሉትን ሰው በስስት ስለሚይዙ የዚያን ሰው ትንሽ ችግር መሸከም አይችሉም ። ማንኛውንም ወጪ አውጥተው ችግሩን ለመቅረፍ ያስባሉ ። ስለዚህ የማዳመጥ አቅም ያንሳቸዋል። ወንዶች ነፍሰ ገዳይ የሚሆኑት ብዙ ጊዜ ረጅም ሰዓት የማሳመንና የመታገሥ አቅም ስለሚያጡ ነው ። ሚስትህ ግን ከሁሉም በላይ መደመጥ ትፈልጋለች ። አንተ ርእስ ብቻ ተናግረህ ዝም ትላለህ ፣ እርሷ ግን ዝርዝሩን ተናግራ ማስረዳትና መታመን ትፈልጋለች ። ስለዚህ ማዳመጥ ይገባሃል ። ብዙ ዱርዬ ወንዶች ሴቶችን በጆሮ ያዳምጣሉ ፣ በውሸት ያሞግሳሉ ፣ ያጫውታሉ ። ብዙ የዋህ ሴቶች የሚታለሉት እውነተኛ ወዳጆቻቸው እነዚህ ስለሚመስሉአቸው ነው ። በትዳር አጠገብ የሚያደቡ ጨካኞች አሉና ተጠንቀቅ ።
ሚስትህ ከእጮኝነት ጊዜ ወደ ትዳር ስትገባ የመፈለግ ጊዜዋ ያቆመ ይመስላታል ። ስለዚህ ራሷን ትጥላለች ። አንተ ግን እንደ ቀድሞ ራሷን እንድትጠብቅና በእጮኝነት ጊዜያችሁ ወደምትዝናኑበት መልካም ቦታ ይዘሃት የመሄድ ልምድ ሊኖርህ ይገባል ። ስትወልድም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች ። በአገራችን አራስን አትለዩ የሚባለው ለዚህ ነው ። ስትወልድ የጥፋተኝነት ስሜት ፣ በጣም ስጉነትና ልጇን የማጣት ፍርሃት ይከባታል ። በዚህ ወቅትም አለመለየት በጣም ወሳኝ ነው ። በአጠቃላይ ትዳር የሚጸናው ጊዜ በመስጠት ነው ። አሊያ ፎቁን ሠርተህ ስትጨርስ ቤትህ ሊፈርስ ይችላል ።
ሚስትህ በሌለችበትና ከሚስትህ እውቅና ውጭ ከጓደኞችዋ ጋር ማሳለፍን በጥንቃቄ ማየት ይገባሃል ። እንደውም እርሷ ስላልተመቻት ቀጠሮው መሰረዙን ማብሰር አለብህ ። የኑሮው ጫና ፣ የመውለድም ድካም ስለሚጫናት ጤናዋን መከታተል ይገባሃል ። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የወደዳት እስከ ሞት ነውና አንተም የትዳር አጋርህን እስከ ሞት መውደድ አለብህ ። ጉድለት መቊጠር ከጀመርህ ፍቅርህ እየቀነሰ ነውና እንደገና ፍቅርን ይሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔርን ለምነው ።
ሚስትህን በሚመለከት ከሐኪም የሰማኸው ብርቱ በሽታ ካለ አትስጋ ። ሰው የሚሞተው በጥሪ እንጂ በበሽታ አይደለም ። “እግረ ቀጭን ይሞታል ሲሉ እግረ ደንዳና” የሚባለው ለዚህ ነው ። ራቁትህን ተወልደህ ራቁትህን ትሄዳለህና ካንተ በኋላ መጥቶ ካንተ በፊት ለሚሄደው ገንዘብ ሰስተህ ኋላ እንዳትጸጸት አስፈላጊውን ሁሉ አድርግ ። ጸጸት አለመሞከር እንጂ አለመሳካት አይደለም ። ይልቁንም የሚስትህን በሽታና ችግር እግዚአብሔር እምነትህን ሊፈትን ያመጣው ሊሆን ይችላልና በታማኝነት ተወጣው ። የአንዳንድ ሰው አገልግሎቱ የቅርብ ሰዎችን ማስታመም ሊሆን ይችላል ። ይህን እያዩ ብዙዎች እውነተኛ ፍቅርን ይማራሉ ። ከአርባ ዓመት በላይ ሚስታቸውን የሚያስታምሙ ወንዶችን አውቃለሁ ። ይህን የሚሰማ ሁሉ ይመርቃቸው እላለሁ ።
ሚስትህ ብትማር ፣ ብታገኝ ፣ ሥልጣን ላይ ብትወጣ የበታችነት ስሜት ተሰምቶህ እንቅፋት ልትሆናት አይገባም ። ራስህን መቀበል ካቃተህ ሚስትህም አትቀበልህም ። ዓለምን እያመሰ ያለው የበታችነት ስሜት ነው ።ያንተ የሆነ ሰው በማደጉ ደስ ሊልህ ይገባል ። ስለዚህ በሥራ ዓለም ያገኛሃትን ሚስት ልጅ አሳዳጊ አድርገህ ያለ ፈቃዷ ልትቆልፍባት አይገባህም። በመንፈሳዊ አገልግሎት አግኝተሃት አሁን ቤተ ክርስቲያን ልትከለክላት መብት የለህም ። ሰው ፍላጎቱን ተከልክሎ አብሮህ ሊኖር ይችላል ። ሰላም ግን ሊሰጥህ አይችልም ። ፍላጎቱን የተከለከለ ሰው ጋር መኖር በድን ታቅፎ እንደ መኖር ነው ።
እግዚአብሔር የቤቱ ራስ አድርጎሃልና ለአካልህ ተጠንቀቅ ። ቤትህንም በትክክል መምራት ብዙ ነገሮች ወደ መምራት ብቃት ያሳድግሃል ። ቤትህ ትንሹ አገር ነውና ። ሚስትህ ደጋግማ የምታነሣውን የከረመ ችግር በይቅርታ ዝጋው ። የሞተ ታሪክ የዛሬውን አዲስ ቀን እንዲረብሽ አትፍቀድ ። የስህተትህ እስረኛ እንዳትሆን አጠፋህ በተባልከው ነገር ይቅርታ ጠይቅ ። የይቅርታ ተቀባይ ሚስትህ ሳትሆን የሠራዊት ጌታ ነውና ክብርህ ነው ። በዓለም ላይ “ይቅርታ” እንደሚለው ቃል የሚጣፍጥ የለም ። ለአላዋቆች ደግሞ ይቅርታ መራራ ነው ።
ተገቢውንና እግዚአብሔር የሚደሰትበትን ነገር አድርግ እንጂ ሰውን ለማስደሰት አትሞክር ። ሰውን ላስደስትህ ስትለው የበለጠ እየተከፋብህ ይሄዳል ። እግዚአብሔርን ስታስደስት ግን እርሱን የሚያውቅ ሰው ይደሰትብሃል። ትዳርህን ወደ ዘላለማዊነት ካስጠጋኸው በሰማይም የክርስቶስ ሙሽራ ሆናችሁ ትቀጥላላችሁ ። የምድሩ ምሳሌ ነው ፣ አማናዊው በሰማይ ነው ። ምሳሌው ቢጎድል ወጉ ነው ። በሰማይ ግን ትልቅ ሰርግ ይጠብቀናል።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 12
ተጻፈ አዲስ አበባ
ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ