የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /8/

“ልጆቼን ትዳሬን ሳስብ እኔ ባልኖር ምን ይሆናሉ ? እያልሁ እጨነቃለሁ ። ባየኋቸው ጊዜም እረበሻለሁ” እያልህ ይሆን ? ነቅተህ ራስህን ብትጠብቅ ስትዘናጋ እና ስትተኛ የሚጠብቅህ ማነው ? አንድ ራስህን መጠበቅ ያልቻልህ ሌላውን መጠበቅ እንደምን ትችላለህ ? እግዚአብሔር የቤተ ሠሪዎች ቤት ሠሪ ፣ የጠባቆች ጠባቂ ፣ የዳኞች ዳኛ እንደሆነ አታውቅምን ? ከገዛ ተፈጥሮህ አስበህ የማታዝዛቸው ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉ አታውቅምን? በራስህ ላይ ማዘዝ ሳትችል እንዴት ሌላው አልተገዛልኝም ብለህ ትጨነቃለህ? ከአካላትህ ያንተ የሆነ የትኛው ነው ? የእኔ የምትለው አካል ሳይኖርህ ሰዎችን የእኔ ብለህ መጨነቅህ የሚገርም ነው ። ትላንት ላይ ቆመህ ዛሬ ለመድረስህ እርግጠኛ ነበርህ ወይ ? ለዛሬ እርግጠኛ ሳትሆን ለነገ እርግጠኛ ሁነህ እንዴት ታስባለህ ? ከትዳርህ በፊት ከልጆችህ አስቀድሞ የሚያውቅህ እግዚአብሔር ነው ። አንተን ሌጣውን ያበዛህ ፣ ሞኙን ባለ ንብረት ያደረገህ እርሱ ነው ። በብልሃትህ እንዳልኖርህ ረስተህ አሁን ስለ ነገ ታስባለህ ? ዘመድ ፣ ልጅና ገንዘብ የማያሳልፈውን ያን ቀን አልፈህ የመጣኸው በእግዚአብሔር ነው ።
ካንተ በፊት የነበረው ፣ አንተን ወደ ህልውና ያመጣው ፤ ካንተ በኋላ የሚቀረው ፣ ያዝረከረከውን የሚሰበስበው እግዚአብሔር ነው ። ደግሞም እሞታለሁ ባይ ቀባሪ ይሆናል ። ሰው የተወለደበትን ቀን እንጂ የሚሞትበትን ቀን አያውቀውም ። ሰው የት እንደ ተወለደ እንጂ የት እንደሚሞት አያውቅም ። ሰው ስላዋለዱት እንጂ ስለሚቀብሩት ሰዎች አያውቅም ። ሞቼ በነፍሴ የት እገባለሁ ? ሳይሆን የት እቀበራለሁ ? የሚል ብዙ ነው ። ከሕይወቱ ሞቱን የሚያከብር አያሌ ነው ። ሰዎች የሚቀብሩህ ለጤናቸው ብለው እንጂ ላንተ አዝነው አይደለም ። ከሞትህ በኋላ ስምህ እንዳይነሣ ሁሉንም ሥርዓት አሲይዝ ። ሁለት ቤት ከመሠረትህ ከሥጋህ ጨርሰህ በነፍስህ ስትወቀስ ትኖራለህ ። ሁለት ትዳር የመሠረተ ሰው አጽሙ እንኳ አያርፍም ። ኑሮህን ልጆችህን ከአንድ ምንጭ አድርግ ። እነርሱም እንኳ ከተፋቀሩልህ ዕድለኛ ነህ ። ለልጆችህ የሚገባውን አድርግ እንጂ ዘላለማዊ ተረጂ አታድርጋቸው ። ለልጅ እውቀት እንጂ ገንዘብ አይሰጥም ። እውቀት ሌባ የማይሰርቀው ሀብት ነውና ልጅህን በቅጡ አስተምር ። አንተ የድሀ ልጅ ስለሆንህ ገንዘብ ክፉ አያሠራህ ይሆናል ፣ ልጅህ ግን የአንተ የባለጠጋው ልጅ ነውና በገንዘቡ ይጠፋል ። ብዙ እንቅፋትን የተሻገሩ ሰዎች ገንዘብን መሻገር አልቻሉም ።
በቁምህ ያልሰጠኸውን ስትሞት ለመስጠት አትፈልግ ። ይህ ከፍተኛ ስስት ነው ። ታስረህ ከመስጠት ዛሬ በተፈታ እጅ መስጠት ይሻላል ። ልጆቼ ነገ ቢቸገሩ ብለህ ዛሬ አትዝረፍ ። እኔ ብሞት ምን ይሆናሉ ብለህ ሌላውን ገድለህ ለቤትህ አትሰብስብ ። የነገሥታት ልጆች አባቶቻቸው ያስቀመጡትን ወርቅና ብር አልበሉትም ። ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ መሰብሰብ ይቻላል ፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ግን መብላት አይቻልም ። ቤትህ ሲፈርስ እግዚአብሔር ምሰሶውን ይጨብጣል ፣ አንተ ስታልፍ ለልጆችህ እግዚአብሔር አባት ይሆናል ። እግዚአብሔር የፈጠራቸው አንተን ተማምኖ ሳይሆን ክንዱን አይቶ ነው ።
“እኔ ከሌለው ምን ይሆናሉ ?” እያሉ የሚጨነቁ ሰዎችን እግዚአብሔር በብርቱ ያስተምራል ። ሥራ ፈትተው ፣ በወኅኒ ወድቀው ፣ በአልጋ ተጥለው ቤታቸው ሲቀጥል በዓይናቸው ያሳያቸዋል ። የምንኖረው የተፈቀደልንን ነው፤ የተፈቀደልንን ጠላትም ሆነ የራስ ፍርሃት አያስቀረውም ። ቤተሰብህ ያላንተ ይኖራል ፣ ያለ እግዚአብሔር ግን አይኖርም ። ዋናው አንተ አትሙት ሁሉም ለራሱ የሚያውቅ ጎበዝ ነው ። ቁርጡን ሲያውቅ ሁሉም ራሱን ችሎ ይቆማል። ልጆቹን የሚወድ ወላጅ ራሱን መጠበቅ አለበት ። ቀድሞ መብላት ፣ ቀድሞ መታከም አለበት ። ምክንያቱም ልጆቹን የሚጠቅመው የወላጅ መኖር እንጂ ምግብ አይደለም ። ምግብ ከእርዳታ ተቋማትም ይገኛል ። የወላጅ ፍቅር ግን የትም አይገኝም ። በሩ ክፍት ሲሆን ለልጆች ተስፋ ነው።ደግሞም ጭንቀት ወደ ልጆች የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ ነው ። ያንተን መጨነቅ የሚያዩ ልጆችህ በጭንቀት የሚጎዱ ይሆናሉ ።
ነገ ስላንተ ቤት ይቅርና ስለ ሰፊው ዓለም ምንም ዋስትና የለም ። በአልፋነቱ ያስጀመረን እግዚአብሔር በዖሜጋነቱ የተዋበ ፍጻሜ እንደሚሰጠን እናምናለን። ሳሉ መዋደድ እንጂ ሲሞቱ መላቀስ ከንቱ ነው ። ለተዋደደ ሰው መከዳዳት እንጂ መሞት አያሳዝንም ። ቢያሳዝንም ጨርሶ አያስከፋም ። ያለ እኔ ምን ይሆናሉ ማለት ራስን ጣዖት አድርጎ ማምለክ ነው ። በእግዚአብሔር ፈንታ ሁኖም በድፍረት መናገር ነው ።
ከአቅምህ በላይ ምንም ነገር አታድርግ ። ያንተን ቤት ለመሥራት ብለህ የሰው ቤት አታፍርስ ። የአንዱ ፈርሶ የአንዱ አይለማምና ። ጭንቀቴ ቢቀለኝ ብለህ ወደ ትዳር አትግባ ። የራሱ ኃላፊነት አለውና መጀመሪያ ራስህን አረጋጋ ። አንዳንድ ጭንቀት ግን “ቆሜ ልቀር ነው” የሚል አሳብ የወለደው ነውና ስትገባ ይለቅሃል ። ላለው ከምትጨምር ፣ ለሌለው ብትሰጥ በረከት ይሆንሃል ። ድሀ ብትሰጠው ይመርቅሃል ። እኩያህ ግን ብትሰጠው እንዴት በዚህ ገመተኝ ብሎ ይጣላሃል ። እንዲወዱኝ ብለህ አትባክን ። ፍቅር ጸጋ እንጂ ግዢ አይደለምና ። እንደ ባከንህ ስትቀር “አላውቅበት ብሎ ነው” ይሉሃል እንጂ “ለእኛ ብሎ ነው” አይሉህም ። በአምፑል ዘመን ሻማ አትሁን ። በልኩ ኑር ። ደስታህ ሙሉ ይሆናል ።
አንዲት ሴት በጣር ሰዓቷ አንድ ነገር አደራ አለችኝ ። “እኔ የማስበው ለልጄ አይደለም ፣ ለባሌ ነው ። ልጄን የዚያች የሟቿ ልጅ እያሉ ሁሉም ይንከባከበዋል ። ባሌን ግን ሁሉም ይረሳዋል ። አንተን ይሰማሃልና መልካም ሴት ቆመህ ዳረው ። በምድር የሰጠሁህን በሰማይ እቀበልሃለሁ” አለችኝ ። የዚህች ሴት ጽናት ይገርመኛል ። ባልም በሚስት ይጽናናል ፣ ልጅም በቤተሰብ ያድጋል ማለቷ ነው ።
ሴትዬዋ ነፍስዋ ከሥጋዋ ተለይታ ወደ ገነት ትሄዳለች ። ከታላቁ ዙፋን እንደ ደረሰች እጅ ነሣች ። ባለ ዙፋኑም ቤቷን አሳያት በማለት መልአኩን አዘዘው። መልአኩም ይዟት ሲሄድ በጣም የተዋቡ ቤቶችን በማየት ትደነቃለች ። አንዱ ውስጥ በገባሁ ስትል የእርስዋ እንዳልሆነ ይነግራታል ። በጣም ደሳሳ የሆነ ከከተማው ዳር አንድ ቤት ውስጥ ወሰዳት ። “ቤትሽ ይህ ነው” ሲላት “እንዴት” ብላ ደነገጠች ። መልአኩም ፡- “በምድር ሳለሽ በላክሽኝ ገንዘብ የሠራሁት ቤት ይህ ነው” አላት ይባላል ። በመልካምነታችን መጠን የሚቆየን ነገር ይኖራል ። ዮናታን በጣም መልካም ስለ ነበር ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዘሩን ፈልጎ ረድቶታል ። ለልጅ የሚቀመጥ ሀብት መልካምነት ነው ።
በዚህ ዓለም ላይ በጣም ደፋር ሰው ወልዶ ግፍ የሚሠራ ሰው ነው ። የእኛ ኃጢአት ሦስትና አራት ትውልድን ያጎዳል ። በአባታቸው ግፍ አገር ጥለው የሸሹ የሉም ወይ ? የአባት ኃጢአት አገር ያስጥላል ፣ የእናት ኃጢአት ኅሊና ያስጥላል ። የእንጀራ ልጆቻቸውን ያሰቃዩ የነበሩ ፣ የገዛ ልጆቻቸው ኅሊናቸውን ጥለው ሲወድቁ አይተናል ። መልካም ሠርቶም የሚያስጨንቅ ዓለም ነው ፣ እንኳን ክፉ ሠርቶ ። ጽድቅ ለልጆቻችንም ርስት ነው ። በመልካም ኖሮ ማለፍ ይሁንላችሁ ፣ ይሁንልን !!
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 13
ተጻፈ አዲስ አበባ
ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ