የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …?

“መማር እፈልግ ነበር ፣ ነገር አእምሮዬ በብዙ ነገሮች ተይዟል ። ትምህርቱን ጀምሬ ባቆመውስ ?” እያልህ ይሆን ? አንተ ስለ አሁን እንጂ ስለሚመጣው የማታውቅና የማትጠየቅ ነህ ። አንተ የዛሬ ሳይሆን አንተ የአሁን ሰው ነህ ።በጀቱን በትክክል ያልተጠቀመ ተቋም በጀቱ ይመለስበታል ። ዕድሜህንም በትክክል ካልተጠቀምህ ተመላሽ ይሆናል ። ማቱሳላ በዚህ ዓለም ተገኘ ፣ እንጂ ይህን ሠራ አልተባለም ። 969 ዓመት ኖረ እንጂ ይህን በጎ ነገር ፈጸመ ተብሎ አልተጻፈለትም ። በዚህ ዓለም ላይ ዛፎችም ዓለቶችም ተገኝተዋል።አንተ ግን የተገኘህ ብቻ ሳይሆን የኖርህም ልትሆን ይገባሃል ። ሞቶ መኖርና ኑሮ መሞት ልዩነት አለው ። የቀረህ አንድ ቀን ቢሆንም ትምህርት ቤት አትቅር ። ትምህርት በራሱ ዋጋ ነውና ዋጋ አገኝበታለሁ ብለህ አትማር  ። ትምህርት በራሱ ምግብ ነውና እበላበታለሁ ብለህ አትማር ። ትምህርት ብዙ አሳብህን ይወስድልሃል ። አሳብህን ለመርሳት መሞከር የበለጠ ማስታወስ ነው። ሌላ ማሰብ ግን መርሳት ነው ። ትምህርት ሌላው አሳብ ነው ። ትምህርት በጠባዩ ልጅ ያደርጋልና ለመታደስ ከፈለግህ ተማር ።
ደግሞም ትምህርት የዕድሜ ገደብ የለውም ። ለትምህርት ብለህም የምትበላው ተጨማሪ ምግብ የለም ። ለመኖር የምትበላው ለትምህርት ይሆናል ። ፍርሃትህ በእግዚአብሔር ጸጋ አንተን ይፍራህ እንጂ ፍርሃትን አትፍራው ። ለልጅ ከሳቁለት ፣ ለውሻ ከሮጡለት ፣ ለውኃ መንገድ ከለቀቁለት ፣ ለባለጌ ፊት ካሳዩት ፣ ለሌባ ከሰጡት መቆሚያ የለውምና ደፍረህ ቁም።
በአገራችን ሰው ቤት ሲገዛ ስላማረው አይገዛውም ፣ ወደፊት ዋጋ ያወጣ ይሆን ወይ ? ብሎ ነው ። መኪና ሲገዛ ደስ ስላለው አይገዛውም ወደፊት ከእጄ ይወጣ ይሆን ወይ ? ብሎ ነው ። ገና አንድ ቀን ሳታድርበት ስለ መሸጥ ለምን ታስባለህ ? ገና አንድ ቀን ሳትሳፈርበት ስለ መሸኘት ለምን ትጨነቃለህ ። መቼ ነው የምትኖረው ? ሁሌ አውታታ ፣ ሁሌ መንገደኛ ነህ። ከአገር ውጭ የሚያምር የአንገት መስቀል አየሁና ወደድኩት ። አጠገቤ የነበሩትን ትልቅ አባት ፡- “ብፁዕ አባታችን ወድጄው ነበረ ፣ ቢለቅስ ብዬ ፈራሁ” አልኳቸው ። እርሳቸውም፡- “ካማረህ ግዛው ፣ እንኳን እርሱ እኛም እንለቃለን” አሉኝ ። ይህ መልስ ከዚያን ቀን ጀምሮ ለብዙ የሕይወት ገጠመኜና ለማዘገየው ደስታዬ መልስ ሁኖልኛል ። አዎ ስለሚፈርሱ ቤቶች ስናስብ እኛም እናልፋለን ፣ ስለሚለቁ ጌጦች ስናስብ እኛም መልካችንን እንጥላለን ብለን ማሰብ መልካም ነው ። ያለቀ ነገር ሁሉ የተጀመረ ነውና ያሰብከውን በጎ ነገር ጀምረው ። እግዚአብሔር ይረዳኛል በል ። አምላክህ ባታየውም ሊረዳህ በአጠገብህ ቁሟል ። ጉዳዩን በጥልቅ አስበው ፣ ጸልይበት ፣ ፈጽመው ። መለኮት ያግዝህ !
ይቀጥላል
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 6
መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
ተጻፈ አዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ