የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዳለ ያለ

“አንተ ግን ያው አንተ ነህ ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ።”

መዝ. 101 ፡ 27 ።

ከሳ ደረቴ መነመነ ፣
የድሮ መልኬ ምንድን ሆነ ?
የድሮ መልኬ ጠፋኝ ወይ ?
ሰው ኑሮውን መሳይ ።

በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተነሣው ታላቅ ረሀብ አንዲት የተጎዳች ሴት መልኳን በመስተዋት አይታ ድሮና ዘንድሮ ሲምታታባት የገጠመችው ግጥም ነው ይባላል ። ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ራስዋ ለራስዋ እንደ ጠፋት የገለጠችበት ነው ። ቆንጆ ነኝ ማለት ሐሰት ነው ። የጨበጡት የሚመስል ነገር ገና በፍለጋ ላይ ያለ ነው ። “ሰው ማንን ይመስላል ?” ቢሉ “ኑሮውን” ይባላል ። ይህች ሴት በደህና ዘመን መልኳ ደህና ነበር ፣ በረሀብ ዘመን ደግሞ ቅላቷ ጠቁሮ ፣ ውፍረቷ ከስቶ ፣ ወዟ ደርቆ ፣ ደም ግባቷ ርቆ ፣ ውበቷ ረግፎ ፣ ማማሯ አስፈሪ ሁኖ አየችው ። በጥጋብ ዘመን የሕይወት መልክ ፣ በረሀብ ዘመን የሞት መልክ ይዛለች ። በቁም ፈርሳ ፣ ሳትቀበር የሙታን አምሳያ ሁናለች ። ስለዚህም ይህን ልብ የሚነካ ግጥም ገጠመች ። ውበት ሐሰት ፣ ደም ግባትም ከንቱ መሆኑን ለመናገር ታሪክ ማጣቀስ ፣ መጽሐፍ ማንበብ ፣ ፎቶ መፈለግ አያሻም ። ረሀብተኞች ጋ መሄድ ፣ ሕመምተኞችን መጎብኘት በቂ ነው ። ዓለም የተሠሩትን ቆንጆዎች ለማፍረስ ዛሬም አልደከማትም ። በመቃብር የሚፈርሱ የአንድ ጊዜ ዕዳ አለባቸው ። በቁም እየተሠሩ መፍረስ የሚገጥማቸው ብዙ ናቸው ። እኛም ብዙ መልክ የያዝነው በዚህች ትንሽ ዕድሜአችን መሆኑ ይገርማል ። መልክ አድራሻ አይሆንም ። ቆሞ የማይጠብቅ በራሪ ነገር ነው ። እንዳማሩ ያሉ ፣ እንዳማሩ የሞቱ ጥቂቶች ናቸው ። ሰው ኑሮውን ሲመስል መልኩ ይጠፋዋል ፤ እግዚአብሔርን ሲመስል ግን መልኩን ያገኘዋል ። እግዚአብሔር ግን በማይጠፋ ውበት ፣ በማይደፈር ግርማ ፣ በማይናወጥ ዙፋን ፣ በማይጎድል ጌትነት ፣ በማይነጥፍ ምስጋና ፣ በማይለወጥ ባሕርይ ፣ መገዛት በሌለበት መለኮት ፣ በማይፋለስ አንድነት ፣ በማይጣፋ ሦስትነት ለዘላለም ይኖራል ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ ይላል ።

ረጅም መቀነት ሳይስቡት ይጠብቃል ፣
የዘመኑ ፍቅር ሳይጀምሩት ያልቃል ።
አሁን ምን ይባላል ሐተታ መናገር ፣
እየሰሙ መቻል ሳለ ደግ ነገር ፤
ከዚያም ከዚያም አትበይ እንደ ቆዳ ገድጋጅ ፣
አምላክ ከወደደው ይበቃል አንድ ወዳጅ ።

የድሮ ዘፈን ነው ። ዓለም ዓለምን የታዘበችበት ግጥም ነው ። ሰዎች በተዋወቁ ቅጽበት በቁልጫ የሚጠራሩበት ፣ ካልተገባበዝን ብለው ሸብ ረብ የሚሉበት ፣ የኑሮአቸውን ምሥጢር ዘክዝከው የሚናገሩበት ይህ ዘመን ነው ። ቁልምጫም ፣ ግብዣውም ፣ ምሥጢር መካፈሉም መልካም ነበር ። ያ ሰው ዞር ሲል ግን ህልውናውን ለመርሳት መቸኮል ምን የሚሉት ፍቅር ነው ? ፍቅር ካለበት ሰዓት ይልቅ የሚታወቀው መለያያው ሲደርስ ነው ። ሲለያዩ መረሳሳት ይህ ፍቅር አይደለም ። ፍቅር በአካል ሲርቁ በልብ መጨዋወት፣ በመንፈስ መስመር መገናኘት ነው ። በእኛው ዘመን በፌስ ቡክ ፍቅር ይጀመራል ፣ ድምፅ ሰምቶ ሰው በፍቅር አበድኩ ይላል ። ሲገናኝ ግን አንድ ቀን ለመቆየት አቅም ያጣል ። ድምፁ የውሸት ፣ መልኩ የውሸት ፣ ፎቶው የውሸት ነው ። አንድ አባባል እውነት ከሆነ ልጥቀሰው፡- “የውሸት ፀጉር ይዘሽ የእውነት ወንድ አትፈልጊ” የሚል ነው ። በዚህ የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ በሆነ ዘመን ፍቅር ከጃንሆይ ጋር ተቀብሯል የሚሉ ብዙዎች ናቸው ። ፍቅርን ብቻ ሳይሆን አምላክንም ድሮ ቀርቷል የሚሉ እየበዙ ነው። “የጃንሆይ ጊዜ እግዜር አንተ ታውቃለህ” የሚሉ አሉ ። እግዚአብሔር ግን ፍቅሩን ወረት ፣ አባትነቱን ክዳት ሳይጎበኘው አለ ። ፈተና ያልገጠመው ፍቅር ፣ ሞት እንቅፋት ያልሆነው መውደድ የእግዚአብሔር ብቻ ነው ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ ተብሎለታል ።

ጠማማውን እንጨት እየቆረጣችሁ ፣
ወልጋዳውን እንጨት እየቆረጣችሁ
ይህም ማገር ሁኖ ቤት ትሠራላችሁ

የሚል ቅኔም አስታውሳለሁ ። ሌላም ግጥም አለ፡-

ምን ያስመርጣል ጥሩ እንጨት ፣
ለመሰንበቻ ቤት ።

በዚህ ዓለም ላይ እያለፍን እንጂ እየኖርን አይደለም ፣ እያቋረጥን እንጂ መሠረት እየጣልን አይደለም ። የዛሬ ሰው የነገ አፈር ነን ። ለራሳችን የሰሰትነው ሀብት ንብረት ፣ ጤናችንን አደጋ ላይ የጣልንበት ቤት ለማንም ይሆናል ። እኔም አለሁ ማለት በማይቻልበት ዓለም አንድ የጸና አለ ። ሁሉም ነገር ሲወዛወዝ ትክል የሆነ ነገር መፈለግ ግድ ነው ። ሁሉም ነገር ሲፈናቀል አድራሻ ያለው የሰማይ መቅደስ ብቻ ነው ። የሐጊያ ሶፊያ ድንቅ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ኢስታንቡል ውስጥ የእስላም መስጊድ ሁኗል ። ዓለምን የምትገዛ የነበረች ሮም ዛሬ ኢኮኖሚዋ ይዋዥቃል ። በግዛቷ ፀሐይ አይጠልቅም የተባለች እንግሊዝ ዛሬ ደሴት ሁናለች ። ሶቅራጥስ ፣ ፕሌቶ ፣ አሪስቶትል ዛሬ የሉም ። ቄሣር ፣ ፈርዖን ፣ ታላቁ እስክንድር ስማቸው አይጠራም ። እኛ ግን እኛ አይደለንም ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ ብለን እናመሰግናለን ።

ሁሉም ነገር በሚለዋወጥበት ዓለም የማይለወጠውንና የማይናወጠውን አምላክ ያዙ ።

የጸናው ክርስቶስ ያጽናችሁ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ