“እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ ።” ኤፌ. 4፡17።
ትምህርት ያለው ከሕይወት እንጂ ከሞት አይደለም ። ሰው የሚለወጠው በሕይወቱ እንጂ በሞቱ አይደለም ። የትላንት ስህተት በዛሬ ንስሐ ይካሳል ። እያንዳንዱ ቀን አዲስ ጉዞ ለመጀመር የተሰጠ ተጨማሪ ዕድል ነው ። ዛሬ ሲጨመርልን እግዚአብሔር በእኛ ተስፋ እንዳልቆረጠ እንረዳለን ። የተሸከማቸው ጌታ ሳይደክመው ላየናቸው የሚደክሙን ሰዎች ካሉ የስህተት መንገድ ላይ ነን ። ሰይጣን በሚያንሰው ኃጢአት ንጹሕ አድርጎ በሚበልጠው በትዕቢት የሚይዛቸው ሰዎች አሉ ። መፍረድ ወድቄ አላውቅም ፣ አልወድቅምም ብሎ እንደ ማሰብ ነው ። “እንዳይለመድህ” ብሎ መግደል ትርጉም የለውም ። እንዳይለመድህ የሚለው ቃል ስህተት ላይ ቆሞ የሚነገር ሲሆን ስህተትህን ልማድህ አታድርገው ማለት ነው ። እንዳይለመድህ ብሎ መቅጣት ግን የወላጅ ፣ የመምህርና የወዳጅ መሣሪያ ነው ። ወላጅም ወልዶ አሳድጓልና ፣ መምህርም አስተምሯልና ወዳጅም ለወዳጁ ዋጋ ከፍሏልና የመቅጣት መብት አላቸው ። ያልወለዱ ፣ ያላስተማሩ ፣ ያልወደዱ ሰዎች የመቅጣት መብት የላቸውም ። ልደት ፣ ትምህርት ፣ ፍቅር ሥልጣን ይሰጣሉ ። አባትነት ፣ መምህርነት ፣ ወዳጅነት ሥልጣን ነው ።
ቅጣት በቀል ከሆነ ፣ ቅጣት ጠላቴን አሁን አገኘሁት የሚል የሥጋ ደስታ ከሆነ መንፈሳዊ አይደለም ። ቅጣት ለረጅምና ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ደወል ነው ። ደወልነቱም ሕመም አለው ። ሕመሙን እያስታወሰ ወደ ቀደመ ክፉ ተግባሩ እንዳይመለስ ቅጣት ያግዳል ። እንዳይለመድህ ተብሎ በደለኛ በትር ይመዘዝበታል ። የቅጣቱ መሠረት ፍቅር ፣ ግቡም የዚያ ሰው የሞራል ልዕልና ነው ። ዓላማውም ሰብሮ ማስቀረት ሳይሆን የተሻለ ሰው እንዲሆን መናፈቅ ነው ። አንተ በሥጋ ስትወድቅ እኔ በተስፋ ወድቄአለሁ ፣ አንተ ስትሰበር እኔ በልቤ አንክሻለሁ በማለት ወዳጅ ይቀጣል ። ቅጣት ወላጅ ሲያደርገው እንዴት እንዳሳደገው በማሰብ የትላንቱ መልአክ ልጅ እንዴት ሰይጣን ሆነ ? ብሎ ነው ። መምህር ሲያደርገው ከወላጆቹ እያለቀሰ የተቀበልሁት ያ የፍቅር ብላቴና እንዴት ከፋ ? ብሎ ነው ። ወዳጅ ሲቀጣ ለእኔ መልካም ማድረግ እየቻለ ሌላ ቦታ መልካም መሆን እንዴት አቃተው ? ብሎ ነው ። ቅጣት የተቀጪውን መልካምነት የሚናፍቅ ነው ። የሚከናወነውም በር ዘግቶ ነው ። ምክንያቱም ቀጪው ቢረሳው ጎረቤት የዚያን ሰው ጥፋት አይረሳውምና ። ቅጣት በር ዘግቶ ካልሆነ ጉዳት አለው ። የተናጋን አጥንት የበለጠ ማናጋት ነው ። በርግጥ ሕዝብን የበደለ ከሆነ በሕዝብ ፊት ቅጣት ይተላለፍበታል ። ቢሆንም እንዳይለመድህ ብሎ መግደል የጠላት እንጂ የወዳጅ ግብር አይደለም ።
እንዳይለመድህ የሚለው ቃል ዕድል የሚሰጥ ፣ ነገ ሌላ ሰው ሆነህ ላይህ እፈልጋለሁ የሚል ተስፋ ያዘለ ነው ። እንዳይለመድህ ብሎ መግደል ተገቢ አይደለም ። ዜማቸው መንፈሳዊ የሆነ ግጥማቸው ግን ሰይጣናዊ የሆነ ሰዎች የቀጣነው ለእግዚአብሔር ቤት ቅድስና ብለን ነው ይላሉ ። ያ ሰው በመውደቁ ግን ደስተኛ ናቸው ። ውድቀቱንም ያሰናዱት እነርሱ ሊሆኑ ይችላሉ ። እንዳይለመድህ ሲሉ አገልጋይ ይመስላሉ ፣ ሲገድሉ ደግሞ ከሰይጣን ይከፋሉ ። ወንድሞቻችንን ሰብረናቸው ተሰበሩ ብለን ስናወራባቸው ቅር አይለንም ። እንቅፋት በመንገዳቸው ትክክል አስቀምጠን ፣ የሚያጠምዱ ነውረኛ ሰዎችን ልከንባቸው ሲሰናከሉ በልባችን ደስ እያለን በአፋችን እናለቅሳለን ። ፖለቲከኞች ይህን ክፋት አያውቁትም ። ዓለማውያን እስከዚህ አይጠላለፉም ። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉ የሰይጣን የውስጥ ካድሬዎች ግን ያመነውን ለማስካድ ፣ የደከመውን ለመግደል በንቃት እየሠሩ ነው ። “አገልግሎት ሕይወቴ ነው ፤ በሕይወቴ የገባውን በሕይወቱ እገባበታለሁ” ብለው ሲናገሩ ሐፍረት አይሰማቸውም ። ክርስቶስ ሕይወታችን ካልሆነ አገልግሎት ሕይወታችን ቢሆንም ከመግደል አንመለስም ። ዛሬ በአገልግሎቱ ዙሪያ ያለው ጠብ የሱቅ ጠብ ነው ። ደምበኛዬን ወሰድክብኝ የሚል ክርክር ነው ። ባለሱቅም አቅርቦቱን ያሻሽላል እንጂ የእኛን ያህል አይጣላም ።
ሐዋርያው ግን “በጌታ ሆኜ እመክራለሁ” ይላል ። ቅዱሳን ሰዎች ሌላውን ሲመክሩ ቀድመው ንስሐ ይገባሉ ፣ ያለቅሳሉ ። “ጌታ ሆይ ፣ እኔ እርሱን ለመምከር ማን ነኝ ? በምክሬ እንዳልሰብረው እርዳኝ” ብለው ተማጽኖ ወደ ተሰቀለው ጌታ ያቀርባሉ ። ማንንም ሰው ሲያዩ የሚታያቸው የሰውዬው ክፋት ሳይሆን እግዚአብሔር ሲፈጥረው በእርሱ ላይ የነበረው አርአያ ሥላሴ ደግሞም የክርስቶስ የደሙ ዋጋ ነው ። ሐዋርያው በጌታ ሆኜ እመክራለሁ ማለቱ ብዙ ፍቺ አለው ። እኔ ሳልሆን የሚመክራችሁ በእኔ ያለው የፍቅር ጌታ ነው ማለቱ ነው ። እኔም በጌታ ምሕረት ተርፌ ለመምከር በቅቼ እመክራችኋለሁ ማለቱ ነው ። በደሌ የተተወልኝ ፣ የኋላ ታሪኬ አሳዳጅ የሆንሁት በክርስቶስ አክናፈ ምሕረት ተሸሽጌ እመክራችኋለሁ ማለቱ ነው ። ዛሬ በምክር ስም የሚሳደቡ ፣ በቅድስና ስም ሌላውን የሚያረክሱ ፣ በትዕቢት ተይዘው እገሌን በሌብነት ያዝሁ የሚሉ ምስኪኖች አሉ ። “ጦጣ ታስራ ትዘፍናለች” ይባላል ። መታሰሯን ረስታ ። እነዚህም በትልቅ ማዕሠረ ኃጢአት መያዛቸውን ረስተው ነጻ ነኝ ብለው ይዘፍናሉ ።
ሐዋርያው የትላንት ኑሮአችሁን የቅድሙን አስተሳሰባችሁን ፣ የቀደመ ጣዖታዊነታችሁን ደግማችሁ አትኑሩት ። ይህች ሰዓት የመለወጥ ዕድል ናትና ተለወጡ እያለ ነው ። እናንተ አሕዛብ ፣ እናንተ ርኵሳን እያለ የቀደመውን ታሪክ የስድብ ርእስ አላደረገባቸውም ። ሰውን የመምከር እንጂ የማስገደድ መብት ማንም የለውም ። መንገድ ማሳየት እንጂ በዚህ ካልሄድህ እንዲህ አደርግሃለሁ የሚባል ሰው ሊኖር አይችልም ። ስለ ድንግል ማርያም ከዘመርህ ይህን ጉድ አወጣብሃለሁ እያሉ የሚያስፈራሩ የዘመናችን የኢየሱስ ፖሊሶች የሚያሳፍሩ ናቸው ። እነዚህ በኢየሱስ ስም አፍሪካን የወረሩ የቅኝ ገዢዎች ልጆች መሆናቸውን እያስመሰከሩ ነው ። በእነዚህ ጨካኞች የወንጌል ሥራ ይጎዳል ። ክርስትናም በክፉ ይታያል ። በእነዚህ ሰዎች የተጎዱ ወደ ዓለም ተመልሰው ክርስትናን ሲበቀሉ ማየት ያሳዝናል ።
ያለፈው አልፏል ። ሰው የሚጠየቀው እውነት ከገባው ሰዓት ጀምሮ ነው ። ከሰማበት ሰዓት ጀምሮ ሳይሆን ከተሰማው ሰዓት ጀምሮ ነው ። እያንዳንዱ ሰዓት የመጀመር ዕድል ነው ። በእልህ መጥፋት የራስን ነፍስ የእኔ አይደለሽም ማለት ነው ። የበደሉንን ሳይሆን ያልበደለንን ጌታ ማሰብ የተሻለ ነው ። ግር እንዳይለን በስንዴው እርሻ ላይ እንክርዳድም አለ ። እስከ መቼ ካልን በቤተ ክርስቲያን ክፉዎች እስከ ዕለተ ምጽአት ይኖራሉ ። ሰው በክርስቶስ ይለካል እንጂ ክርስቶስ በሰው አይለካምና በርቱ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም.