የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እኮ እንዴት ?!

ባለፈው ዘመን ተደርጎ ነበር ወይ ? ተደርጎስ ከሆነ የሰለጠነው ዘመን እንዴት ሊደግመው ደፈረ? ማወቅ በድንቁርና ፣ ዘመናዊነት በአራዊትነት እንዴት ተለወጠ ? እኮ እንዴት ?! ዘርን አጠፋለሁ ብሎ ፈርዖን ተነሥቶ ነበር ፣ የቅርብ ዘመን ጨካኞችም ይህን ፈጽመዋል ። እስራኤል ግን አልጠፋችም ። በመቃብር ላይ ነፍስ ዘርታ የዓለም ጥያቄ ሆናለች ። እግዚአብሔር የፈጠረውን አጨርሳለሁ ብሎ ማሰብ እኮ እንዴት ?! ሌላው ሲፈተን እኔ አልፈተንም ፣ ሌላው ሲቀብር የእኔ አይሞትም ብሎ ማሰብ እኮ እንዴት ?! የልደት መጨረሻ ሞት አይደለም ወይ ?

በመከራ ዓለም በመከራ መደንገጥ ፣ ሞተ ነፍስን አስቀምጦ በሞተ ሥጋ ጉድ ማለት እኮ እንዴት ?! በስደት ምድር ላይ ተደላድሎ መቀመጥ ፣ ለእነዚያ ያለፈች ዓለም ለእኔ አታልፍም ብሎ መረጋጋት እኮ እንዴት ?! በሌሎች ክፉ ቃላት ተሰብረን የእኔ ክፉ ቃል አይሰብርም ማለት ፣ የሌላውን እንደ ጦር የራስን ቃል እንደ መጦር ማሰብ እኮ እንዴት ?! መብል እየወደዱ ሥራን መጥላት ፣ ከሴት ተወልዶ ሴትን ማስጨነቅ እኮ እንዴት ?!

ጠብታው ውኃ ዓለትን ይሰነጥቃል ፣ የተኛውም በሬ ከቆሰቆሱት አውሬ ይሆናል ፣ ግለሰብ ሲጠቃ ቀጥሎ ሕዝብ ይጠቃል ። መጽሐፍ ሲቃጠል ቀጥሎ ሰው ይቃጠላል ። ክፋት በጥቂቱ ተጀምሮ በብዙ ያድጋል ። ወንዙም ከምንጭ ይጀምራል ። ክፉ ነገር በጽንሱ ካልቆመ ልደቱ ሞት ይሆናል ። የዘራውን ያህል የሚያጭድ ገበሬ የለም ፣ ከዘራው በላይ ግን ስለ አንዱ ሠላሳ ፣ ስድሳ ፣ መቶ ፍሬ ያጭዳል ። በእንቁላሉ ያልቀጡት ልጅ በሬ ሰርቆ ይመጣል ። የዘራነውን ለማጨድ መማረራችን እኮ እንዴት?!

ያሳደጉት ልጅ ሽማግሌ ሲገርፍ ፣ ያጎረሱት ወዳጅ እጅ ሲነክስ ፣ ጥግ የሆኑት ጥግን ሲያፈርስ ፣ አብሮ የኖረ ገዳይ ሲመጣ አሳልፎ ሲሰጥ ፣ ተማሪ ወንበዴ ሁኖ ሽፍታ እየመራ ሲመጣ እኮ እንዴት ?! ክርስቶስን በጭካኔ የተቀበለች ዓለም ለእኔ ትራራ ማለት እኮ እንዴት ?! ማስተማር የሚቀጥለው በመማር ነው ። የእናት ጡት የሚመነጨው እናቲቱ ስትመገብ ነው ። ምድር ፍሬ የምትሰጠው ዘር ሲጥሉባት ነው ። በአንድ እውቀት ለማርጀት ማሰብ እኮ እንዴት ?! እረኝነት በግ መሆን ፣ መሪነትም መመራት ያሻዋል ። ምንም ቢፈረጥም የሜዳ አህያ ጭነት አይችልም ። ትከሻው ቢያምርም አንበሳ ቀንበር አይሸከምም ። አባት የሚሆን ፣ ልጅ የነበረ ነው ። የሰው ችግር የሚያሳዝነው በችግር ያለፈ ጨዋ ሰው ነው ። አስቀድመህ ሳትታዘዝ ለማዘዝ መሞከር እኮ እንዴት?! ያልተማረ መምህር ተማሪ ያውር ። ያልተማረ ቄስ ሁሉን ያረክስ ። የተማረ ቄስ ርኵስ ይቀድስ ፣ ሕዝብ ይመልስ ! እኮ እንዴት ?!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ