የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ልጅ

“በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ” /1ጢሞ. 1፡2/ ።
ይህን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሽንገላ ያልዞረበት ፣ አለባብሶ ማለፍን የማይወድ ፣ እውነትን ወገን ያደረገ የክርስቶስ ወታደር ነው ። የግንባር ሥጋ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ፣ የአደባባይ ስህተትን በአደባባይ የሚያርም ሰው ነበር ። በዚህ ዓለም ላይ ፍርሃትን የሚወልድ ሀብት ፣ አለማወቅና የክብር ጥማት ነው ። ሐዋርያው ግን መናኔ ንብረት ነው ። ከኅሊናውና ከእግዚአብሔር ውጭ የበላይ ተቆጪ ፣ ላስደስትህ የሚለው አልነበረውም ። አለማወቅ ፍርሃትን የሚወልደው “እንዲህ ተብዬ ብጠየቅ ምን እመልሳለሁ ?” ብሎ ነው ። ሐዋርያው ግን የብሉይ ኪዳንን እውቀት የአዲስ ኪዳንን መገለጥ አሟልቶ የያዘ ፣ በራሱ በክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ነው ። በገዳዮች ቦታ ቆሞ ሲያሳድድ የነበረ በመሆኑ የገዳዮች ዛቻ የሚያስፈራው ሰው አልነበረም ። የእጁን ሰንሰለት እንደ ወርቅ ፣ እግረ ሙቁንም እንደ አምባር ፣ ግርፋቱንም እንደ ካባ የሚቆጥር ሰው ስለነበር ክብሬን አጣሁ ብሎ መደንበር በእርሱ ዘንድ አልነበረም ። ይህ ሐዋርያ ልጄ ብሎ ጢሞቴዎስን ሲጠራው በእውነት እንጂ በሽንገላ አይደለም ። የተለመደ ቋንቋን የሚናገር ሳይሆን በአባትነት ስሜት ልጄ የሚል ቅዱስ ሐዋርያ ነው ። ጢሞቴዎስ እውነተኛ ልጅና እውነተኛ ደቀ መዝሙር ነበረ ። አንድ ራሳቸውን ብቻ ያተረፉ ልጆች ሲባሉ ፣ ሌሎችን ለማዳን የሚተጉ ግን ደቀ መዛሙርት ይባላሉ ። ጢሞቴዎስ እውነተኛ ልጅና እውነተኛ ደቀ መዛሙር ነበረ ። ይህ መልእክት ሲጻፍለት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ነበር ። በርግጥም እውነተኛ ልጅና ደቀ መዝሙር ነው ።

እውነተኛ ልጅነት በሌለበት እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት የለም ። ጌታችን ልጅነት እንደሚቀድም ደቀ መዝሙርነት እንደሚከተል በማቴዎስ 28፡19-20 ላይ ተናግሯል ። በሥላሴ ስም በመጠመቅ ልጅነት ሲገኝ ፣ በመማር ደግሞ ደቀ መዝሙርነት ይገኛል ። ልጅነት መሠረት ሲሆን ደቀ መዝሙርነት ግን ዕድገት ነው ። ሐዋርያው ለልጁ ለጢሞቴዎስ የደቀ መዝሙር ደብዳቤ ጻፈለት ።
አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት ብዙ ዓይነት አባትነቶች በምድር ላይ አሉ ። እነዚህን አባትነቶች ሁሉ የሰጠው እግዚአብሔር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ፡-
1-  በሥጋ የወለዱ አባቶች ፤
2-  አገር የሚመሩ ነገሥታት ፤
3-  በእውቀት የሚወልዱ መምህራን ፤
4-  በመንፈሳዊነት የሚወልዱ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ፤
5-  በዕድሜ የገፉ አረጋውያን አባቶች እነዚህ ሁሉ አባት ተብለው ይጠራሉ።
ከሁሉ የሚበልጠው አባትነት መንፈሳዊ አባትነት ነው ። ምድራውያን አባቶች ይህን ዓለም ለማየት ሲያበቁን መንፈሳውያን አባቶች ደግሞ ሰማያዊውን ዓለም ለማየት ያበቁናል ። ምድራውያን አባቶች የወለዱት ሥጋችንንም ነፍሳችንንም ሳለ የሚያስቡት ግን በአብዛኛው ለሥጋችን ነው ። መንፈሳውያን አባቶች ግን ነፍሳችንን ለማዳን ይተጋሉ ። ምድራዊ አባትነት ሞት ይሽረዋል ። መንፈሳዊ አባቶች ግን ዝምድናቸው ዘላለማዊ ነው ።
ጢሞቴዎስ በእምነት እውነተኛ ልጅ ነበረ ። እምነት በውስጡ ልደት አለው ። ከእግዚአብሔር እንወለዳለንና ውሉደ እግዚአብሔር ያሰኘናል ። የቤተ ክርስቲያን አባል ያደርገናልና መንፈሳዊ ቤተሰብ ይሰጠናል ። እንድናምን የረዱን መምህራንም ልጆቼ ብለው ሲጠሩን አያፍሩም ። ሐዋርያው በእምነት እውነተኛ ልጄ ያለው ለምንድነው ? ስንል በሥጋ እውነተኛ ልጄ የሚባሉ ስላሉ ነው ። እነዚህ ደም መላሽ ሁነው ሥጋውያን አባቶችን የሚያኮሩ ፣ ትልቅ ደረጃ ደርሰው ስም የሚያስጠሩ ፣ ሀብት አግኝተው የሚጦሩ ናቸው ። ጢሞቴዎስ ግን በእምነት እውነተኛ ልጅ ነበረ ። በእውቀት እውነተኛ ልጅ የሆኑ አሉ ። “ተቀመጥ በወንበሬ ፣ ተናገር በከንፈሬ” የሚባሉና አልጋ የሚወርሱ ናቸው ። የእገሌ ተማሪ ነኝ በማለትም በመምህራቸው ክብር ተከብረው የሚኖሩ ናቸው ። ሐዋርያው ግን ክብርን ሁሉ አጥቶ የተሰደደ ፣ ተፈርዶበት ሞቱን የሚጠብቅ ነው ። ይህን ደብዳቤ ሲጽፍ ሊሞት አራት ዓመት ያህል ቀርቶታል ። ጢሞቴዎስ በእምነት እውነተኛ ልጁ ነው ። ሰንሰለቱን ፣ ሞቱን የሚካፈለው ልጁ ነው ። የሥጋ ልጆች እልህን ያሟላሉ ፣ የእውቀት ልጆች ስም ያስጠራሉ ። የእምነት ልጆች መስቀል ይካፈላሉ ።
እውነተኛ ልጄ አለው ። ሐሰተኛ ልጆች አሉና ። ጳውሎስ ልጄ ሲለው ጢሞቴዎስም አባቴ የሚል ነበረ ። የአንድ ወገን ጥሪ ብቻ ሳይሆን ምላሽ የነበረው ጥሪ ነው ። አንዳንዶች ልጄ ሲባሉ ሳቃቸው ይመጣል ። በክርስቶስ እኩል ነን ፣ ወንድማማች ነን እንጂ የበላይ የለብንም ይላሉ ። ልጄ ሲባሉ አባቴ የማይሉ አዲስ ግርፎች ደግሞም ሐሰተኞች አሉና እውነተኛ ልጄ አለ ። ልጄ ሲባሉ ቁመት የሚለካኩ አሉና እውነተኛ ልጄ አለ ። ልጄ ሲባሉ እንደ ዴማስ የሚኮበልሉ አሉና እውነተኛ ልጄ አለ ። ያስተማሯቸውን ፍጹም ክደው “እኔ በቀጥታ የተገለጠልኝ ከእግዚአብሔር ነው” የሚሉ ከሰማይ ወረድን ለማለት ሩብ ጉዳይ የቀራቸው አሉ ። ተቀብያለሁ ለማለት የሚያፍሩ ምልዕ ነን ብለው የሚገምቱ እየበዙ ነው ። “አባት የሌለው አባት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው” የሚለውን ሁልጊዜ ማሰብ አለብን ። በሥጋ አባቶቻችን እየተጠራን መንፈሳውያን አባቶችን ማቃለልና አገልግሎታቸው ላይ አመድ ማፍሰስ ታላቅ ቅጣት የሚያመጣ ዓመፅ ነው ።
በዚህ ዓለም ላይ ልጅ ተብለው ነገር ግን ሐሰተኛ የሆኑ አያሌ ናቸው ። እነዚህ ሐሰተኛ ልጆች፡-
1-  ለጥቅማቸው ብቻ ወላጆቻቸውን የሚፈልጉ ፣
2-  ሌባና ሽፍታ ወደ ወላጆቻቸው የሚልኩ ፣
3-  በተበላሸ ሕይወታቸው ወላጆቻቸውን የሚያሰድቡ ፣
4-  ለዚህ ያበቋቸውን ወላጆች ዘንግተው ከዛሬ ጓደኞቻቸው ጋር የሚዘሉ ፣
5-  ለልጆቻቸው አስበው አባቶቻቸውን የሚረሱ ፣
6-  በመከራ ሰዓት ወላጆቻቸውን የሚክዱ ፣
7-  በክፉ ቀን ለክፉዎች ወላጆቻቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ፣
8-  የተደረገላቸውን ትልልቅ ነገር ዘንግተው በትንሽ ነገር ወላጆቻቸውን የሚወቅሱ፣
9-  ለወንድሜ የበለጠ ተደረገለት ብለው ረብሻ የሚያስነሡ ፣
10-         በቁም ንብረት አካፍሉኝ ብለው ወላጆቻቸውን የሚያስጨንቁ ናቸው ። 

ጢሞቴዎስ ግን እውነተኛ ልጅ ነበረ ። መንፈሳዊ አባቱን የሚያውቅ ፣ በወንጌል ነጋዴዎች እጅ ያልወደቀ እውነተኛ ልጅ ነበረ ። በሐዋርያው ሰንሰለትና መከራ ያላፈረ ፣ መስቀሉን ያገዘው ፣ በክፉ ቀን የጳውሎስ ጥረት እንዳይበላሽ የጠበቀ ትልቅ ልጅ ነው ። ዛሬ ልጄ የሚል አባት ፤ አባቴ የሚል ልጅ እንዳይጠፋ ያሰጋናል ። ወርደን ልናልቅ አልቻልንምና ።
እኛስ እውነተኛ ልጆች ነን ?
እግዚአብሔር ያገለገሉንን የምናከብርበት ማስተዋልና ዘመን ይስጠን !
1ጢሞቴዎስ /4/
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ