የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ጾም

የጾም ፍቺው መከልከል ማለት ሲሆን ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ ፣ ለዘላለም ከኃጢአት መታቀብ ማለት ነው ። ለአዳም የተሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ “አትብላ” የሚል የጾም ወዝ ያለው አንቀጽ ነው ። በዚህ ዘመንም አትብላ የሚል ትእዛዝ በብዛት እየተሰማ ነው ያለው ። በሽታ አፋፍ ላይ ያሉ ፣ በበሽታ ውስጥ ያሉ አትብላ ይባላሉ ። ምግብ ለመኖር የሚጠቅመውን ያህል መኖርንም ሊያጨናግፍ ይችላል ። ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ሰዎች እንዳይበሉ ይመከራሉ ። ባዶ ሆድ መሆናቸው ሥራውን የተሳካ ያደርገዋል ። በሩቅ ምሥራቅ ባሉ ሕዝቦች ለረጅም ቀናት ከምግብ ተከልክሎ በውኃ ብቻ መቆየት በሰውነት ውስጥ ያለውን መርዛም ነገር ለማስወገድ ይረዳል ብለው ያምናሉ ፣ ያደርጋሉ ። በአገራችንም በውኃ ብቻ እንጾማለን የሚሉ ግን ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችን እናያለን ። ይህ ዓለም ሲሠራ የልክ ዓለም ሁኖ የተበጀ ነው ። ምግብም ከልክ ሲያልፍ ሥጋን ታማሚ ፣ አእምሮን ድፍን ያደርጋል ። ሰውም ለኃጢአት ፣ ለእንስሳ ግብር ፣ ለአራዊት ጭካኔ ተላልፎ የተሰጠ ይሆናል ። በዚህ ዓለም ላይ ካሉት የእምነት ሥራዎች ጸሎትን የሚያህል የለም ። ጸሎትን በተሰበረ ልብ ወደ እግዚአብሔር እንድናቀርብ የሚያደርግ ጾም ነው ። የተሰበረ ልብ ማለት የተሰበረ ሽቱ ማለት ነው ፤ የተሰበረ ሽቱ አካባቢውን ሁሉ ያውዳል ፣ የተሰበረ ልብም ሰማይን ያውዳል ።

ጾም በሁሉም ሃይማኖቶች ትልቅ ዋጋ ያለው ፣ ዘመናዊነትም ከርሞ መንቃት ልማዱ ቢሆንም አሁን ደረስኩበት ያለው ነው ። የተመራማሪዎቹ ነገር በጣም ይደንቃል ። ዓለም ለሺህ ዓመታት የተቀበለውን ነገር ሲኰንኑ ከርመው ፣ በዚህ ሰሞን ደረስንበት ይላሉ ። እውነቱ ግን ከዓለም ሁሉ ሕዝብ ይልቅ ደንቁረው የከረሙ እንጂ ሊቅ የነበሩ አይደሉም ። እናቶቻችን በጥብጠው የሚያጠጡንን ቅጠል ዛሬ ተመራማሪዎች ደረሱበት ተብሎ ከበሮ ይመታል ። የደረሱበት ግን እናቶቻችን ነበሩ ። ሊቁ ሌላ ፣ ሊቅ ተብሎ የሚሸለመው ሌላ ነው ። ዓለም ጥቂት ሰዎች ተሻርከው የሚዘርፏት የወንበዴዎች ዋሻ ናት ። ጾም መልካም መሆኑን የነገረን ይህን ሥጋና ነፍስ ያዋቀረው እግዚአብሔር ነው ። ዓላማውም ከእርሱ ጋር ኅብረት ለማድረግ ነው ።

ሰዎች ጾምን በተለያየ መንገድ ሊጾሙት ይችላሉ ። ጾም የራሱ የሆነ ትሩፋትና የጤና በረከት ቢኖረውም ለዚህ ብሎ መጾም ፣ የሰውነት ቅርጽን ለማስተካከል ከምግብ መከልከል ድፍረት ነው ። ጾም ርእስ ፣ ዓላማ ፣ ሥነ ሥርዓት ፣ ግብ ያስፈልገዋል ። ርእሱ በአባቶች መሰጠት አለበት ። አጽዋማት የመታሰቢያ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ። ነገር ግን ርእስን መስጠት የሚችሉት አባቶች ናቸው ። ሕዝቦች በአንድነት ሲዋጉ የአገር አንድነትን ይገልጻሉ ፣ በኅብረት መጾምም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ፣ ተባብሮ ክፉን የመጣል ምልክት ነው ። ጾም ርእስ ያስፈልገዋል ። ዓላማው እግዚአብሔርን ማግኘት ነው ። እግዚአብሔር ተገኝቶም የሚፈለግ የስስት/የናፍቆት አምላክ ነው ። የእግዚአብሔርን ገጸ ምሕረት ማየት የጾም ዓላማው ነው ። በዚህ ዓላማ ውስጥ ንስሐና ይቅርታ ወሳኝ ናቸው ። ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ ፣ ከሰው ጋር በይቅርታ መስማማት የጾም ዓላማ ነው ። ጾም ከጸሎትና ከምጽዋት ጋር ሲደረግ ከራስ ፣ ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቃል ።

ጾም ሥነ ሥርዓት ያስፈልገዋል ። አንዳንድ ሰዎች እንደ ጌታ ዐርባ ቀን እጾማለሁ ብለው በዋሻ ገብተው ፣ በቤት ውስጥ መሽገው አደጋ ደርሶባቸዋል ። ጾምን ልዩ የሚያደርገው መጎዳታችን ሳይሆን እግዚአብሔርን መናፈቃችን ፣ ምሕረቱን ደጅ መጥናታችን ነው ። ደግሞም የድሆችን ረሀብ እንድናስብና ችግረኞችን እንድንረዳበት ነው ። ችግረኛን መርዳት የሌለበት ጾም ከረሀብ አድማ አይለይም ። ጾም ሥነ ሥርዓት ያለው እንጂ ከእነ እገሌ ጋር የምንወዳደርበት አይደለም ። በበሽታ የሚሰቃዩ ፣ አቅማቸው የደከሙ ሰዎች ከአባቶች እየተመካከሩ ሊበሉ ግን አብዝተው ሊጸልዩ ይገባል ። ጾም እልህ አይደለምና ። እግዚአብሔርንም በፍቅሩ የምናይበት እንጂ እንደ ጨካኝ የምንቆጥርበት አይደለም ። ነገር ግን እንዳንጾም የጠላት ፈተና ሊኖር ስለሚችል ጸንተን ማሸነፍ አለብን ።

ጾም ግብ ያስፈልገዋል ። ግቡም የነደደው እሳት መብረድ አለበት ። በእውነት የጾምን ዓላማ ከተረዳንና ንስሐ ከገባን ኃጢአትን እንተዋለን ፣ ደግሞም ከወንድማችን ጋር እንታረቃለን ። ንስሐና እርቅ ካለ የነደደው እሳት በርግጥ ይጠፋል ። በአገራችን በዚህና በዚያ ሆነው የሚዋጉ ሁለቱም ወገኖች ይጾማሉ ። ወደ ጾም ዓላማ እንመለስ ቢሉ በግድ ይታረቃሉ ። ጾም ከኃጢአት መከልከል ሲኖረው እውነተኛ ይሆናል ።

ወርሃ ጾሙን የበረከት ያድርግልን !

ደካማውን ወንድማችሁን በጸሎታችሁ አስቡኝ!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ