የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ፍቅር

“የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው” 1ጢሞ. 1፡5
አይሁዳውያን በአንድ እግርህ ቆመህ የምትናገረው የሚል አባባል አላቸው ። በአንድ እግር ቆመው የሚናገሩት እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ መውደድና ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ነው ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ቃል ደግማችሁ አስቡት ። ባልንጀራን እንደ ራስ የምትወዱ ከሆነ እግዚአብሔርን ከራሳችሁ በላይ መውደድ አለባችሁ ማለት ነው ። እግዚአብሔርን አልጠላም ማለት እግዚአብሔርን መውደድ አይደለም ። እግዚአብሔርን የምንወዳቸውን ያህል መውደድም እግዚአብሔርን ትልቅ ለማለት መፈተን ነው ። እግዚአብሔርን የራስ ያህል መውደድም ራስንና እግዚአብሔርን ማምለክ ነው ። እግዚአብሔርን ከራስ በላይ መውደድ እርሱ እውነተኛ አምልኮ ነው ። የሮማን ፍሬ አንድ ነው ፤ በውስጡ ግን ብዙ ፍሬዎችን ይዟል ። የምንጠራው ግን አንድ ሮማን ብለን ነው ። ፍቅርም እንደ ሮማን ፍሬ ነው ። በውስጡ ብዙ የሕግና የትእዛዝ ፍጻሜዎች አሉ ። ፍቅርን ገንዘብ ያደረገ ሁሉንም ትእዛዛት ፈጸመ ። ፍቅር አባ ጠቅል ነው ።

ሕግ ማለት የአታድርግ መመሪያ ነው ። ትእዛዝ ግን የአድርግ መመሪያ ነው ። ባለማድረግ መቀደስ አለመስረቅ ፣ አለመግደል ነው ። በማድረግ መቀደስ ግን መስጠት ፣ ለሌሎች ቸርነት ማድረግ ነው ። ሐዋርያው ስለ ሕግ እየነገረን አይደለም ። ሕግን የጨዋ ልጆችም ይጠብቃሉ ። አይገድሉም ፣ አይሰርቁም ፣ አይሳደቡም ። ከክርስቲያን ከዚያ ላቅ ያለ ነገር ይፈልጋል ። በእውነት ክርስትና ከጨዋነት በላይ ነው ። ክርስቲያን የሆነው ፖሊስ ላለማስቸገር አይደለም ። የዓለምን ሕመም ለመቀነስም ነው ። የዓለምን ሕመም የምንቀንሰው የሚያለቅሱትን እንባቸውን በማበስ ፣ ያዘኑት በማጽናናት ፣ የወደቁትን በማንሣት ነው ። በፍቅር ሕግን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ትእዛዛትን መፈጸም እንችላለን ።
ፍቅር ከሦስት ምንጮች ከተቀዳ ያን ጊዜ እውነተኛ እየሆነ ይመጣል ። ትእዛዛትንም ይፈጽማል ። እነዚህ ምንጮች ንጹሕ ልብ ፣ በጎ ኅሊናና ግብዝነት የሌለበት እምነት ናቸው ።
በየዕለቱ ልባችን እየደፈረሰ ተቸግረናል ። አንደኛውን ስህተት ይቅር ለማለት ታግለን እንደ ምንም ይቅርታ ካደረግን በኋላ የዚያኑ ቀን ሰዎቹ ሌላ ጥላሸት ይቀቡናል ። እንደ ገና ይቅርታ ባይገባቸውም ለራሳችን ሰላም ስንል ያንን ጥቁር ቀለም ለማጥፋት በጸሎት ፣ በቃሉ ፣ በምክር ፣ ያልበደሉንን ሰዎች በማሰብ ፣ የቀደመውን ጥሩ ጊዜ በማስታወስ ለማጽዳት እንሞክራለን ። ሰዎቹ ግን መልሰው አሁንም ልባችንን ያቀልሙታል ። ተሰብረን ስለምንኖር ይሰብሩናል ። ካልፈቀድንላቸው ግን አይሰብሩንም ። ሞተን ካልጠበቅናቸው አይገድሉንም ። ሞተን ስንጠብቃቸው ግን ገደልን ብለው ይፎክራሉ ። ንጹሕ ልብ በየቀኑ የምንቸገረው ነገር ሁኗል ። ያለፉት ዘመናት የጣዖትና የዓለማዊነት ትዝታዎችም ድቅን እያሉብን ንጹሕ ልባችንን እንከስራለን ። የምናየውና የምንሰማውን ስለማንመርጥም ልባችን ይቆሽሻል ። ሁልጊዜ በተግባር አንበድልም ። በአሳብ ግን ስንበድል እንኖራለን ። አሳባችን ሁሉ ቢከናወን አወይ ሰው ነኝ ለማለት ባልበቃን ነበር ።
እጅ እግር የሌለው ፣ ተግባር የጎደለው ፍቅር በዓለም ላይ አለ ። ይህ ፍቅር ንጹሕ ልብ ስለሌለው ነው ። በጥርጣሬ የሚታመስ ፍቅር በጎ ለማድረግ ይዘገያል ። “እባብ ያየ በልጥ ይደነብራል” እንዲሉ በትላንት ገጠመኙ የዛሬ ፍቅሩን የሚለካ ሰውም አፍቅሮም ፈሪ ነው ። ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል ማለት ብከዳ ፣ ብጎዳ አይልም ማለት ነው ። ምክንያቱም ምንጊዜም ተጎጂው አፍቃሪው ሳይሆን ፍቅርን የገፋው ሰው ነው ። ልቅሶ ቦታ ተለዋውጦ እንጂ ማልቀስ ያለበት ከዳተኛው ነው ። ከንጹሕ ልብ የማይወጣ ፍቅር በጎነት የለውም ። በእጁ አይሰጥም ፣ በእግሩ አይደርስም ። ንጹሕ ልብ የሌለው ፍቅር አካለ ጎዶሎ ነው ።
ፍቅር ማለት ቃላት ሳይሆን ተግባር ነው ። እውነተኛ ፍቅርም ከስሜት ይልቅ ለተግባር የሚያደላ ነው ። ሰዎች ተግባራዊውን ፍቅር አይወዱትም ። ከዚያ ይልቅ የሚያቆላምጣቸውንና የሚያጫውታቸውን ዱርዬ ይወዳሉ ። እውነተኛ ፍቅር ግን ተግባራዊ ነው ። እግዚአብሔር ከረዳን የቃልና የስሜትን ፍቅር ትተን ተግባራዊውን ፍቅር መከተል አለብን ። ወላጆቻችን አንድ ቀንም እወዳችኋለሁ ብለውን አያውቁም ። ፍቅራቸው ግን ተግባራዊ ነው ። ቀላል ልብ ያለው ሰው በድለላ ይሸፍታል ። ዛሬ እስቲ እናስተውል በተግባር የሚወዱን እነማን ናቸው ? ብለን እናስብ ። እኛም በተግባር የምንወዳቸውን ለማሰብ እንሞክር ። እውነተኛ ፍቅር ተግባራዊ ነው ። “እንደምትወደኝ አትንገረኝ ፣ እንደምትወደኝ አሳየኝ” የሚል አባባል አስታውሳለሁ ።
ፍቅር ተግባራዊ እንዳይሆን ሁለተኛው መሰናክል “በጎ ኅሊና” ማጣት ነው ። ዛሬ በዓለም ላይ ትልቁ የሰላም ምሥጢር በጎ ኅሊና እንደሆነ ታምኗል ። የዘወትር ጸሎታችንም ሊሆን የሚገባው፡- አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” የሚለው ነው መዝ. 50፡10 ። ደጋግመን እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እንደምንለው ደጋግመን ይህን ጸሎት መጸለይ ይገባናል ። የቀና መንፈስ ፣ ቀናነት ፣ ለነገሮች በጎ ትርጉም መስጠት የደስታ መሠረት ነው ። ቀናነትን በተፈጥሮ የታደሉ ጥቂቶች ናቸው ። ቀናነትን ለማግኘት ብዙ ተጋድሎ ያስፈልጋል ። ንጹሕ ልብ ለራስ ሲሆን ቀናነት ግን ሰዎችን የምናይበት መነጽር ነው ። በሰለጠነው ዘመን “ሰዎች ለምን ክፉ ሆኑ ? ምን ዓይነት ጉዳት ቢደርስባቸው ነው ?” ተብሎ ታሪካቸው ይጠናል ። እርዳታ ለማድረግ ይሞከራል ። ክርስትናችን ግን ከሥልጣኔ አንሶ ቅንነት አልባ ሁኗል ። በጎ ኅሊና ከምቹ ትራስ ይልቅ ዕረፍት እንደሚሰጥ ይነገራል ። አዎንታዊነትን ማዳበር ከክርስትና አልፎ ዘመናዊነት እየሆነ ነው ። ፍቅር ተግባራዊ እንዲሆን በጎ ኅሊና አጋዥ ነው ።
ግብዝነት የሌለበት እምነት ለተግባራዊ ፍቅር ወሳኝ ነው ። ተዋንያን በሰዓት ሲሠሩ በሃይማኖት ስፍራ ያሉ ግብዞች ግን ለዘመናት የመተወን አቅም አላቸው ። ተውኔት በመድረክ እንጂ በሕይወት ሲሆን ከባድ ነው ። ከእውነተኛነት ግብዝነትን የሚያከብር ማኅበረሰብ ቢፈጠርም እውነት ግን ከእግዚአብሔር ጋር የምታገናኝ ድልድይ ናት ። ጽድቃቸውን ከሚነግሩን ድካማቸውን የሚነግሩን እውነተኞች እነርሱ ተስፋ ይሰጡናል ። መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአተኞችን የሚረዳ መጽሐፍ የሆነው ስለ ሰዎች ፍጹምነት ሳይሆን ስለ ድካማቸው ስለሚነግረን ነው ። የዳዊትን መግደልና ምንዝርና ፣ የጴጥሮስን መካድ ፣ የጳውሎስን ፀረ ክርስቲያንነት የሚነግረን ፤ ውድቀት መጨረሻ አለመሆኑን ተረድተን እንድንነሣ ነው ።
“በፍቅር ኃጢአቶቻችን ሁሉ ይቅር ይባሉልናል ።” ፍቅር ካለንም የሌሎችን ኃጢአት ይቅር እንላለን ። እውነተኛ ፍቅር ሦስት ምንጮች አሉት ። ንጹሕ ልብ ፣ በጎ ኅሊናና ግብዝነት የሌለበት እምነት ናቸው ። እኛ የጎደለን የቱ ይሆን ? 
1ጢሞቴዎስ /10/
ኅዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ