የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነቱ ያለው ማን ጋ ነው ?

“በእርግጥ ሰምታችሁታልና ፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል ፤” ኤፌ. 4 ፡ 21።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ የዋለው እውነት ስለሆነ ነው ። እውነት ከፍ ብላ ትሰቀላለች ። ሰቃዮች አዋረድን ብለው እውነትን ከፍ አድርገው ይሰቅሏታል ። ከፍ ካላለ ሰንደቅ ዓላማ አይታይም ። ክርስቶስም ከፍ ብሎ ባይሰቀል ክርስትና አይታይም ነበር ። እውነት ሽፍንፍን የለውም ። ስለዚህ ክርስቶስ ዕርቃኑን ተሰቀለ ። ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ፍጹም ግልጽነት አስፈላጊ ነው ። እግዚአብሔር ምን ያህል ብቁ ነህ ? ሳይሆን ምን ያህል ግልጽ ነህ ? የሚል አምላክ ነው ። ክርስቶስ ክፍ ብሎ መሰቀሉ ሁሉ ያየውና ያምንበት ዘንድ ነው ። ክርስቶሰን አለማመን ሊኖር ይችላል ፣ አለመስማት ግን እንዳይኖር ወንጌል ሊሰበክ ይገባዋል ። ዓለም ለእውነት የመደበችው ስፍራ መስቀል ነው ። የመጨረሻ ውርደት በነበረው መስቀል ላይ እውነት የሆነው ክርስቶስ ቢሰቀል መስቀል የመጨረሻው የክብር ዙፋን ሆነ ። መስቀል ዙፋን ነው ፣ ክርስቶስ ውሎበታልና ። መስቀል ጻሕል/ገበታ ነው ፣ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ሰጥቶበታልና ። መስቀል ሰንደቅ ነው ፣ ዓላማ የሆነውን ክርስቶስ ያሳያልና ። መስቀል ማካፈያ ነው ፣ ጻድቅና ኃጥእ ተለይቶበታልና ። ዓለማት የማይችሉት በማኅፀነ ማርያም ሲወሰን መስቀል ነው ። መስቀል የማይወሰነው ለመወሰን መፍቀድ ነው ። መስቀል ብዙ ፍቺ አለው ። ዕድሜ ልካችንን የምኖረው ነውና ትርጉሙን ሁሉ አሁን ማወቅ አያሻንም ።

ብዙ ሰዎች ብዙ ነገር ይሰማሉ ። ያለንበት ዘመን የምንሰማውንና የምናየውን ካልመረጥን ብዙ አማራጭ ያለበት ዘመን ነው ። የሚያስፈልገንን ሽተን ስናስስ የምንፈልገው ጋ ሳንደርስ ሰዓታችንን የሚበላ ፣ አንጎላችንን የሚያናጋ ብዙ ወሬ አለ ። የምፈልገው ምንድነው ? ለምፈልገውም የመደብኩት ሰዓት ስንት ነው  ማለት ያስፈልጋል ። የማንፈልገውን በተለጠጠ ሰዓት በማየትና ራስን በማድከም መኖር የዕድሜን አጭርነት አለመገንዘብ ነው ። ሰዎች ፍቅርን በለስላሳ ጆሮ ይሰማሉ ፣ ጥላቻን ግን በድምቀት ያደምጣሉ ። ያበበውን ነገር በማየት በእርግጥ የሰማነውን ማወቅ ይቻላል ። ወንድማማችነት ካበበ ፍቅርን በእርግጥ ሰምተናል ማለት ነው ። ባለመስማት ውስጥ መስማት አለ ። በመስማት ውስጥም አለመስማት አለ ። በመስማት ውስጥም በእርግጥ መስማት አለ ። በእርግጥ ልንሰማው የሚገባውን መለየት ያስፈልጋል ።

በእርግጥ የምንሰማው አሽሙርን ከሆነ የሚራመደው እግራችን ይወላከፋል ። በእርግጥ የምንሰማው አሉባልታን ከሆነ የተነቃቃው ራእያችን ይከስማል ። በእርግጥ የምንሰማው ሰዎች የሚሰጡንን መደብ ከሆነ ጽንፈኛነት ያጠቃናል ። በእርግጥ የምንሰማው ራሳችንን ከሆነ ግምታችን ያደናግረናል ። በእርግጥ የምንሰማው ጀማውን ከሆነ ሁሉም ነገር ያለቀ ይመስለናል ። በእርግጥ የምንሰማው ጠብ ዘሪዎችን ከሆነ እሳቱ እንዳይጠፋ እንጨት አቀባይ ያደርጉናል ። በእርግጥ የምንሰማው ትሞታላችሁ የሚሉንን ከሆነ ሕይወት የእግዚአብሔር ቀመር መሆንዋን ያስረሱናል ። በእርግጥ የምንሰማው የክፉን ፉከራ ከሆነ የያዝነውን ያስጥለናል ። በእርግጥ የምንሰማው ትላንትን ከሆነ ጸጸት በእሳት ጅራፍ ይገርፈናል ። በእርግጥ የምንሰማው ዛሬን ከሆነ ዜናው ያውከናል ። በእርግጥ የምንሰማው ነገን ከሆነ ተስፋ ያጥርብናል ። በእርግጥ የምንሰማው ኢኮኖሚውን ከሆነ እየበላን ይርበናል ። በእርግጥ የምንሰማው ነፋሱን ከሆነ የረገጥነው መሬት ይከዳናል ። በእርግጥ የምንሰማው ሰይጣንን ከሆነ የእግዚአብሔርን ፍቅር ያጠራጥረናል ።

ክርስቶስን በእርግጥ የሰሙ ለዛሬውም ለዘላለሙም ያርፋሉ ። በእግዚአብሔር የተፈጠረ ዓለም የሚድነው በእግዚአብሔር ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ይህን ዓለም ሲያበጀው የሌለውን ወደ መኖር እንደሚያመጣ አሳየን ፣ በዚህም ከየት ታመጣዋለህ ? የማይባለው አምላክ ሊረዳን እንደሚችል አስተማረን ። እግዚአብሔር ይህን ዓለም በለቢሰ ሥጋ ሲያድነው ጥፋታችንን መጨረሻ አድርጎ የማይጥለን አምላክ መሆኑን ነገረን ። ይህን ዓለም ሊያሳልፍ ዳግም ሲመጣም የአደባባይ ተግባራችን የአደባባይ ፍርድ እንደሚሰጥበት ያስተምረናል ። በእርግጥ እርሱን ሰምተናል ወይ ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ።

“እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል ፤” ይላል ። ብዙ ሰዎች ሃይማኖት በዛ ማንን እንመን ? ይላሉ ። ብዙ ሰዎች በግራና በቀኝ ዓይናቸውን አፍጥጠው የሚናገሩ ሰዎችን በማየት ትክክሉ የማን ነው ? ግራ ገባን ይላሉ ። ሽምግልና የተቀመጡ ባልና ሚስትን የሚያዳምጡ ሁለቱም ተመርረው ሲያለቅሱባቸው እውነቱ ማን ጋ ይሆን ? ብለው ይጨነቃሉ ። ሲለያዩ የሚቦጫጨቁ ፣ ሲገናኙ የሚሳሳሙ ሰዎችን በማየት ሰዎች እውነቱ ፍቅር ነው ወይስ ጥላቻ ? ብለው ግራ ይጋባሉ ። እገሌም የሚናገረው እገሊትም የምትለው ሳይሆን እውነት ያለው ክርስቶስ ጋ ብቻ ነው ። እውነቱን አውቀው ቢሞቱም የማይቆጫቸው ሰዎች አሉ ። እውነትን መጠማት እስከዚህ ድረስ ያስመኛል ። እውነቱ ግን ያለው እግዚአብሔር ጋ ነው ። እግዚአብሔር ሁላችሁም ዝም በሉ ብሎ እውነትን ሲናገር ያን ቀን እንደነቃለን ። ተጋርዶ የሚቀር ቀን ፣ መሽቶ የሚቀር ሌሊት የለም ። እግዚአብሔር ትልቅ ነውና እኛ እየለፈለፍን እርሱ አይናገርም ።

ክርስቶስ በእርግጥ የምንሰማው ነው ። ይዋሸናል ብለን አንጠራጠረውም ። ክርስቶስ እውነት ነው ፣ ይከዳናል ብለን አንሰጋውም ። ክርስቶስ ትምህርት ነው ፣ እንደሚያሳርፈን እርጠኞች ነን ።

አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፣ የተራቆተችውን ነፍስ በእውነትህ ክዳን አልብሳት ። አሜን።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም.

ያጋሩ