የትምህርቱ ርዕስ | እውነት ክርስቶስ ነው

“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።” ዮሐ. 14 ፡ 6-7 ።

እውነት በዘመናውያን አስተሳሰብ መሬት የረገጠችና የተረጋገጠች አይደለችም ። እውነት የግል ምልከታና እሳቤ ተደርጋ ትቆጠራለች ። ያንተ እውነት ላንተ ፣ የእኔ እውነት ለእኔ በሚል ያለመነካካት ሥልጣኔ ውስጥ ላለ ትውልድ ፣ እውነት እንደ ሰዉ የምትለያይ ናት ። ዘመናዊነቱ እያየለ ሲመጣ አንተ ትክክል አይደለህም ብሎ ሌላውን በፍቅር መውቀስ ፣ በሥልጣን መገሠጽ እንዳይኖር ያደርጋል ፣ ስብከትም መታገዱ አይቀርም ። እውነት ነፋስ እንደ ተሞላ ፊኛ የምትንቀዋለል ፣ ከምድር የለቀቀች ፣ ብትወርድም የማትጠቅም ፣ አቅጣጫዋን በነፋሱ መንገድ የምትለዋውጥ አይደለችም ። የሰው ልጆች እውነትን በየዕለቱ እየፈለጉ ከእውነት ግን እየራቁ ይመጣሉ ። ፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ እውነትን ይፈልጋሉ ። እውነተኛ ፍቅርን ሲሹ ዘመናቸውን የጨረሱ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ። እውነተኛ ኑሮ የሌላቸውን ሰባክያን ሲወቅሱ የሚታዩ አያሌ ናቸው ። በትልልቅ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ሲዋሹ የሚሰማቸው ሰው ያፍርላቸዋል ። ትልቅነት ያለ እውነት ትንሽነት ነው ። ሽንገላን ብንወዳጅም ሸንጋዮችን ግን አንወድም ። ልቡ እና ቃሉ የተለያዩበት ሰው ወዳጅ እንዲሆነን አንፈልግም ። እኛ ጋ እየበሉ ጠላት ጋ የሚውጡ ሰዎችን መቀበል ይከብደናል ። ሃይማኖት ለዋጮችም ሥራቸው ያጸይፈናል ። ሰው እሞትለታለሁ ላለው ዓላማ መኖር እንዴት አቃተው? የሚል ትዝብት በውስጣችን ይጮኻል ።

ያለ እውነት ፣ ፍርድ ገዳይን አወድሳ ሟችን የምትኰንን ናት ። ያለ እውነት ፍቅር የላይ ጥርስ እንጂ የልብ ግብዣ የሌለባት ናት ። ያለ እውነት እውቀት ውስጣዊ መዝገብን ማጣበብ ነው ። ያለ እውነት ወዳጅነት ሲገናኙ መወዳደስ ሲለያዩ መቦጫጨቅ ነው ። ያለ እውነት አገር መውደድ ሰውዬውን እየገደሉ ተራራ ሸለቆውን ማምለክ ነው ። ያለ እውነት አገልግሎት ሰማይን እያዩ ምድር ላይ መቅረት ነው ። ያለ እውነት ንግግር የውኃ ማስተላለፊያ ቦይ መሆን ፣ ሌላውን ማራስ ለራስ ግን መድረቅ ነው ። ያለ እውነት ትዳር በድብብቆሽ ዕድሜን መፍጀት ነው ። እውነት ሁሉን ነገር እርግጥ ፣ የታመነ ፣ የሚኖርለት ፣ የሚሞትለት መሆኑን ማኅተም የምታሳርፍ ናት ። ያለ እውነት ዙፋን አይጸናም ። ያለ እውነትም የሰው መንገድ ፍጻሜ የለውም ። በዚህ ዘመን ሰዎች ውሸትን ከእውነት በላይ እየኖርዋት ነው ። ውሸታቸውን እውነት ለማሰኘት ሲጥሩ እውነት የማድረግ አቅም ግን አላገኙም ። ሁልጊዜ ሰውን ማታለል እንደማይቻል ፣ የብልጣብልጥነት መጨረሻ ሞኝነት መሆኑን እያየን ነው ። የእውነት አገርዋ ወዴት ነው ? የምንልበት ዘመን ላይ ነን ።

እውነትን በድርቅና ብቻ የያዙ እውነትን ምሕረት የለሽ ያስብሏታል ። እውነትን ያለ ፍቅር የያዙ እውነትን ሰይፍ ያሰኝዋታል ። እውነትን የግል ገንዘባቸው ያደረጉ የሚመስላቸው ሌላው ከሀዲ እነርሱ ብቻ አማኒ እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ላይ ይገኛሉ ። እውነት ግን የእግዚአብሔር ገንዘብ ፣ የመለኮት ወኪል ናት ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ከእውነት ጋር የተያያዘ ነው ። እርሱ በእውነት ሰው ሆነ እንጂ ሰው አልመሰለም ። ሞቱም አማናዊ እንጂ ተመስሎ ያለበት ተውኔት አይደለም ። በርግጥ ቤዛችን በመሆኑ ድነናል ። አማኑኤል እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ፣ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው ።  አዳም የበደለው በሐሰት ተታሎ ነው ፣ በእውነተኛ ተዋሕዶ ክርስቶስ አድኖናል ። የክርስቶስ ሰው መሆን እውነትና ምሕረት የተስማሙበት ነው ። እውነት ነጻ ታወጣለች ። እውነቱ የተገኘላቸው ሰዎች ከፍርድ ቤት በነጻ ሲለቀቁ ይታያሉ ። እውነት ሰውን ከአእምሮ እስር ቤት ትፈታዋለች ። ዳኛ ቢፈርድበት እንኳ ውስጡ ነጻ ነህ የሚለው ነጻ ነው ። ዳኛ በነጻ ለቆት ውስጡ እስረኛ ነህ የሚለው እሱር ነው ። ሕሊናም በሐሰት የሚወቅስበት ጊዜ ይኖራል ። ከአእምሮ መታወክ ምክንያቶች አንዱ ሕሊና በሐሰት ሲወቅስ የሚሰማ ሕመም ነው ። ከሁሉ የሚበልጠው በአንድ ልጁ ሰው መሆን እኛን የተዛመደው ፣ በአንድ ልጁ ሞትም እኛን የታረቀው የእግዚአብሔር እውነት ነው ።

እውነቱ የት ነው ( ግራ ገባን የሚሉ ሰዎች አሉ ። እውነትን አለማወቅ ግራ ያጋባል ። ይልቁንም የደቦ ፍርድ ባለበት በዚህ ዘመን እውነቱ የት ነው የሚለው የአደባባይ ጥያቄ ነው ። እውነት ከኑሮአችን ሩቅ በሆኑ አገራትና ሰዎች ላይ ስትጓደል እንኳ የሕመም ስሜት ይሰማናል ። የነፍስ መከራዋም እውነት ሲጓደል ማየት ነው ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ሆኖ መጥቷል ። ግራ መጋባትን የሚያርቅ ፣ መደናገርን የሚያስቀር ፣ እስራትን የሚፈታ ፣ ፍርጃን የሚያነሣ የእውነት አዋጅ ሆኖ ተገልጧል ። ከመጻሕፍት የምትበልጠውን ወንጌል ፣ ከሃይማኖት የከበረችውን ክርስትና ሰጥቶናል ። የእኔ መጽሐፍ ይበልጣል ፣ የእኔ ክርስትና ይልቃል ብለን ሌላውን እንድናሳንስበት ግን አልሰጠንም ። የሰጠን ነገር ሁሉ ለመዳን የተሰጠን ነው ። የፍለጋ ሁሉ ማብቂያ እውነት ክርስቶስ ነው ። ዕርቃኑን ተሰቅሎ ያላፈረው እውነት ስለሆነ ነው ። ደግመው የሚናገሩት ፣ ጠፍተው የሚመለሱበት እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። በዘመናት ሁሉ የነበሩ ፈላስፎች እውነት ምንድነው ? በማለት ፈልገዋል ፣ በዱር ገብተዋል ፣ መናኔ ንብረት ሆነዋል ። እውነት የጠቢባን ፣ የነገሥታት ፣ የባለጠጎች ጥልቅ ጥያቄ ናት ። ይህንን የነፍስ ሸለቆ የሞላው እውነት የሆነው ፣ በጲላጦስ ፊት የተከሰሰው ክርስቶስ ነው ። በችሎት አደባባይ እውነተኞች ሲከሰሱ ኖረዋል ፣ በቀራንዮ ግን ራሱ እውነት ተከስሶ ቆመ ። ለእውነት ስፍራ በሌላት ዓለም ክርስቲያንነትህን አበባ ይዞ የሚቀበለው የለም ።

ምስጋና ብርሃን ለምታወጣው እውነት ይሁን ! አሜን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም