እግዚአብሔር እንደሚያይህ ሁነህ ሥራህን ሥራ እንጂ የሰዎችን ጭብጨባ አትጠብቅ ፤ ነቀፋቸውንም አታዳምጥ ። እንኳን ዙሪያህን ይቅርና የገዛ እግርህንም እያየህ ከሮጥህ ትወድቃለህ ። ማንነትህንና ታሪክን ትተህ እግዚአብሔር ላንተ ያለውን ፍቅር ዋስትና አድርገህ ሥራህን ሥራ ። መሥራት ማለት በማይሠሩና የሚሠራን በማይወዱ ሰዎች መጠላትና መነቀፍ ማለት ነው ። ሰዎች በእኔ ላይ ምን እያሰቡ ይሆን ? ብለህ በመናገራቸው እንደ ተጨነቅህ በዝምታቸው አትጨነቅ ። አምላክህ እንኳን ከታሰበ ከተወረወረ የሚያድን ነው ። ስትዘናጋ ደግሞም ራስህን ጥለህ ስትተኛ የሚጠብቅህ ማን ነው ? በትጋቱ እንደ ኖረ ፣ በራሱ ጥረት ዛሬን እንዳየ ሁነህ አትፍራ ። እግዚአብሔር የዕውራን መሪ ነውና ለመጀመር አትፍራ ። በማታውቀው አገር ፣ አገር አላማጅ እግዚአብሔር ነው ። የድካምንም ፍሬ በመስጠት የሚባርክ ነው ።
የእግዚአብሔር ፊት እንዳይሰወርብህ የሰው ፊት እያየህ ተግባርህን አትፈጽም። ሰው የሚፈልገውን ራሱ አያውቀውምና ለሰው ፍላጎት አትኑር ። በአቅምህ ልክ ሥራ ፣ በገባህ መጠን ተመላለስ ። ስለመሞከር እንጂ ስለ አለመሳካት አታስብ ። በንጉሥ ፊት ከመቆም የበለጠ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆምህ አስብ ። ግፍንና መገፋትን ታገሥ ። በትዕግሥት ውስጥ የሚገለጠውን የመለኮት ክብር በሕይወትህ ተለማመድ ። ለሁሉም ነገር መልስ አይሰጥም ። ሰዎች እስኪገባቸውም ሥራ አይቆምም ። እየተራመድህ ተጣራ እንጂ ቆመህ ማንንም አትጥራ ። መቆም የጨው ሐውልት ፣ የሚሟሟ መታሰቢያ ያደርጋል ። እግዚአብሔር ስለሚናገርልህ አንተ መናገር አያስፈልግህም ። አንተ ስለ እግዚአብሔር መስክር ፤ አንድ ቀን እግዚአብሔር ስለ አንተ ይመሰክራል ። ሰዎችን በማሰባቸው እንጂ በድርጊታቸው መጠን አትንቀፋቸው ። የተሳሳተ ድርጊት ባልተሳሳተ አእምሮ ሊያቀርቡ ይችላሉ ። የሰማኸውን ሁሉ አታስተላልፍ ። ከእገሌ እገሌ ይሻላል አትበል ፤ የተሻለውን ለዓለም አበርክተህ እለፍ እንጂ አንተ ደረጃ መዳቢ አይደለህም ። ከዚህኛው ዓመት ያለፈው ይሻል ነበር አትበል ፤ ዘመን እንደ መክሊት ነው ፤ ገንዘብ በራሱ ጽድቅና ኩነኔ የለውም ። በጎ ብትሠራበት ሕንፃ ሥላሴን/ሰውን ትገነባበታለህ ፣ ምርጫህ ክፉ ከሆነ ሕንፃ ሥላሴን ታፈርስበታለህ ። ዘመንም እንደ መክሊት ነውና በራሱ ክፉና ደግ አይደለም ። ዘመንን አትርፍበት እንጂ አትክሰርበት ።
የመልካሞቹ መልካም እግዚአብሔር ካንተ ጋር እንዳለ እመን ።
የምትፈልገውን ለማግኘት መጀመሪያ የምትፈልገውን እወቅ ፤ ጊዜ እያለህ ጊዜ አትጠብቅ ። ትልቁ ድሀ ተሰጥቶት የሚጠብቅ ነው ። ድህነት ያለንን አለማወቅ ነው ። ዘወትር ከእግዚአብሔር ምሕረት ተቀበል እንጂ ስለ ዓለም አታስብ ። ምን ይሉኛል ? ብለህ አትጨነቅ ሰዎች የሚኖሩት ለማለት ነውና። ይሉኝታና ጽድቅ ዓይንና ጢስ ናቸው ። ይሉኝታ የሰውን ሽልማት ሲፈልግ ፣ ጽድቅ ግን የእግዚአብሔርን ሽልማት ይጠብቃል ። የምትጠላውን ስለ ጠላልህ የምትከተለውን ወገን አንድ ቀን ክፉኛ ትጠላዋለህ ፤ ክፉኛ ይጎዳሃልና ። እውነተኛ ፍቅር ሌሎችን በመጥላት ላይ አይመሠረትም ። ስሙ የሚነሣ የቆመ እንጂ የሞተ አይደለምና ስምህ ሲነሣ ደስ ይበልህ ። መንገዱ ሩቅ የመሰለህ ጉዞ ስላልጀመርህ ነው ። ወደ በጎ አንድ እርምጃ መራመድ ፣ ከክፋት አንድ ርምጃ መራቅ ነው ። ሰዎች ትልቅ የመሰሉህ ተቀምጠህ ስለምታያቸው ነው ። ብትነሣ የተሻለ ነገር ትሠራለህ ። ፈተናዎች የሚያስደነግጡህ ዕድሜ ስላልጠገብህ ነው ። ዕድሜ ሁሉም እንደሚያልፍ ያስተምራል ። ገንዘብ ትልቅ የሆነብህ የድህነት ጠባይ ስላልለቀቀህ ነው ። ጉልበት ሠሪ የመሰለህ ታመህ ስላላየኸው ነው ። በአንድ ቀን ትኩሳት እንደምትሟሽሽ ምነው ባወቅኸው ። ሰው ቋሚ የመሰለህ ሞትን ዘንግተህ ነው። ጠላት የበረታ የመሰለህ አንተ እንደምትፈልገው ስላልተቀጣ ነው ።
የምትሠራውን ሥራ ሁሉ ጸሎት ለእግዚአብሔር አስቀድመህ አሳውቅ ። የእግዚአብሔር ፈቃድ የልብ ሙላት ፣ የጉልበት ኃይል ነውና ። አብዝተህ ሥራህን ሥራ ። ነገ የሚኖረው ወሬ ሳይሆን ሥራ ነውና ። ስለሚያልፈው ሳይሆን ስለማያልፈው አስብ ። ምኞት የሚያሰክርህን ያህል ሥራ አያደክምህም ። መኝታህን በጊዜ አድርግ ፣ ማልደህም ተነሣ ። ማልደው የተነሡ ሴቶች የጌታን ትንሣኤ እንዳዩ እወቅ ። የሀገርም ትንሣኤ ማልዶ በመነሣት የሚገኝ ነው ። እንድትሠራ ስለተፈጠርህ አለመሥራት የእግዚአብሔርን ዓላማ መዘንጋት ነው ። ያንተን ተግባር ሰዎች እንዲሠሩልህ አትከጅል ፤ ይህ ሞት ነውና ። ለራስህ ሳትበቃ ለአገር አትተርፍምና ንጽሕናህን ጠብቅ ። ትጉ ስትሆን የትጉሃን ማኅበር የመላእክት ዘመድ ትሆናለህ ። መላእክት ሥራህን በትጋትና በጥንቃቄ ስትሠራ በደስታ ያዩሃል። ዕረፍት ሥራ ፣ ሥራም ዕረፍት እንዳለው አትዘንጋ ። ነገር ግን ራስህን የምታዳምጥበት ፣ መጻሕፍት የምታነብበት ፣ ወዳጆችህን የምታገኝበት ከሁሉ በላይ አምልኮተ እግዚአብሔርን የምትፈጽምበት ጊዜ ይኑርህ ። የጊዜ ባለቤት ለአምልኮት የሚያንስ ጊዜ አልሰጠህምና ።
ኃጢአት ሁሉ ሥራ ፈትነት አለው ። ስካር ፣ ሱስ … በሥራ ፈትነት ውስጥ የሚፈጸሙ ናቸው ። ሔዋን የሞት በር የሆነችው ሥራ በመፍታት ነው ። ሦስት ነገሮች ጉዳት አላቸው ፡- ሥራ ፈትነት ፣ መክሮ አለመሥራትና አምልኮተ እግዚአብሔርን ማጓደል እነዚህ ሦስቱ ለሰይጣን ፈተና አሳልፈው ይሰጣሉ ።
አዳም ገነትን እንዲንከባከብ ከተፈጠረ ይህችን እሾህና አሜኬላ የበቀለባት ምድር መንከባከብ በጣም ይገባናል ማለት ነው ። ካልተንከባከቡት ገነትም ይደርቃል ፣ ከተንከባከቡት በረሃም ይለማል ። ሥራ ስትለምደው የሱስ ያህል ነው ። ከማድረግህ በላይ አለማድረግህ ቅር ይልሃል ፣ ያደክምሃል ። ሥራ የሚሠሩ ደስተኞች ናቸው ። እንቅልፋቸው የጣፈጠ ነው ። ለነገርና ለሐሜት ጊዜ የላቸውም ። ሥራ ከአጉል ጭንቀትም ያድናል ። እየሠራህ ዕረፍ ፣ እያረፍህ ሥራ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 3
ተጻፈ አዲስ አበባ
መስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም.