የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግረ መንገድ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                              
                                                                                ዓርብ ነሐሴ 30/2006 ዓ.ም

(ማቴ. 9፡18-26)

ዎችን ያለልክ ብናምናቸው የገዛ እምነታችን ይጐዳናል፡፡ ምክንያቱም እምነታችንን ሊያሟሉ አይችሉምና፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ማድረግ ስለሚችል ያለ ወሰን ብናምነው እንዳመነው ይሆንልናል፡፡ እምነትን መለማመድ ያስፈልጋል፣ እግዚአብሔርን እንደ ቃሉ ለማየትና ኃይሉን ለመለማመድ ዕለት ዕለት መነሣሣት አለብን፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት የሚጨምረው እግዚአብሔር እንዲሠራ መንገድ ስንለቅለትና ሲሠራም ስናየው ነው፡፡ ለማንም ሰው እግዚአብሔር ሊፈውስ እንደሚችል ማመን እንኳ ዳገት ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ታሪኩ የተጻፈለት መኰንን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጁን ከሞት እንደሚያነሣለት አምኖ ነበር፡፡ የታመመች ልጁን ሳይሆን የሞተች ልጁን እንዲያድንለት ለመነው፡፡
ለወላጆች በልጆቻቸው ችግር መፍራትና መጨነቅ ፍቅርና ግዴታ በሚመስልበት ዓለም ለልጄ ከእኔ ይልቅ ጌታ ይቀርበዋል፣ ሊያድነውም ይችላል ማለት ትልቅ እምነት ነው፡፡ እኛ የምናምነው ወይም የምንደፍረው ለሩቅ ሰዎች ነው፡፡ ምክንያቱም ባይሳካም አያስጨንቀንምና፡፡ እግዚአብሔር ግን በጉዳያችን ውስጥ ደፍረን እንድንቆምና ጣልቃ ገብነቱን እንድናይ ይፈልጋል፡፡ በሕይወታችን ውስጥ “አሁንስ በቃ” ያልንባቸው ነገሮች ስንት ይሆኑ? እግዚአብሔር በቃ ሳይል ግን እኛ በቃ ማለት አይገባንም፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመኰንኑን ልጅ ከሞት ለማዳን ሲጓዝ ሳለ አንድ ጉዳይ መንገዱን አዘገየው፡፡ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችና ገንዘብዋን ለሐኪም ገፍግፋ ምንም መፍትሔ ያላገኘች ሴት ጉዞውን አዘገየችው፡፡ በበሽታዋ ምክንያት የተጠላችውና የተገለለችው፣ ሕመሟም አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ችግር ያስከተለባት ያች ሴት ብዙ ከሞከረች በኋላ የሰውን መንገድ ሁሉ ጨርሳ፣ ገንዘቧንም አንጠፍጥፋ ደክማት ቁጭ ብላ ሳለ ነው ጌታን ያገኘችው፡፡ በልብዋም የኢየሱስን የልብሱን ጫፍ ብቻ ብነካ እድናለሁ ብላ አሰበች፡፡ አመነች አየች፡፡ ማመን በእግዚአብሔር መንግሥት ማየት ነውና፡፡ በዓለም ግን ማየት ማመን ነው፡፡
ይህች ሴት ጉዳዬ እንኳን ለእርሱነቱ ለቀሚሱ ዘርፍም ቀላል ነው ብላ አሰበች፡፡ ለዓመታት ሊቃውንት ያደከመ ችግሯ፣ ገንዘቧን የጨረሰ በሽታዋ ለኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለቃሉ ሳይሆን ለቀሚሱ ዘርፍ ቀላል ነበር፡፡ ሁሉ አይታ በሰውም ተስፋ ቆርጣ መምጣቷ አላስወቀሳትም፡፡ እንደውም ሁሉን ስላየች ከእንግዲህ ወዲህ የትም አያምራትም፡፡ ምናልባት ልጅ የሞተችበት ይህ ሰው ይህች በሽተኛ ስላዘገየችበት አዝኖ ይሆናል፤ ለእርሱ የእርሱ ችግር ይበልጣልና፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ሁሉም ችግር ከባድ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡


ወደ መኰንኑ ቤት ሲደርስ በእምቢልታ፣ በዜማ ይለቀስ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን “ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው” እነርሱ ግን በጣም ሳቁበት፡፡ የማያምኑ ሰዎች ዛሬም በእምነት ነገር ይስቃሉ፡፡ በኋላ ግን በፀፀትና መልስ በማይገኝለት ጩኸት ያለቅሳሉ፡፡ የመኰንኑ ልጅ ግን ከሞት ተነሣች፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን! 
ዘመዶችና ጐረቤቶች ለዚያች ልጅ ለወጣት የሚሆን ግጥም ሲሰበስቡ፣ መልካም የቀብር አፈር ሲመርጡ፣ የሩቅ ዘመዶችን ሲያስጠሩ፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው መኰንኑ ግን ሕይወት ቀጣይ እንዲሆን ወደ ጌታ ኢየሱስ ዘንድ ሄዶ ነበር፡፡ ሞትን ለማውራት የሚሽቀዳደመው ዓለም የምሥራች ለመናገር ግን የዘገየ ነው፡፡ አንዳንዴ እኛ ባረፍንበት ጉዳያችን ሰዎች ቢታወኩ፣ እኛ ጌታን በምንጠብቅበት ነገራችን ሰዎች የሞት ጡሩንባ ቢያስነፉ፣ እኛ አላለቀም በምንለው ጉዳያችን ሰዎች የቀብር ጉድጓድ ቢያስቆፍሩ አሁንም ማመናችን በጌታችን ይበርታ! መንጫጫት ሲበዛ በፀጥታ እግዚአብሔርን እንጠብቅ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እግረ መንገዱን የዘመናትን ችግር እየፈታ ያልፍ ነበር፡፡ ለእርሱ አገልግሎት ሥራ ወይም ልዩ ሥፍራን የሚጠይቅ ነገር አልነበረም፡፡ የምንጣፍ መስተካከል፣ የአትሮንስ /ፑልፒት/ መዘጋጀት ጉዳይ አይደለም፡፡ ለእርሱ አገልግሎቱ ሕይወቱ ነበር፡፡ ሲቀመጥም፣ ሲነሣም፣ ሲሄድም ያገለግል ነበር፡፡ እኛስ ምስክርነታችን የተለዩ ሰዎችንና የተለየ ቦታ ይመርጥ ይሆን? እኛ የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ዕቅድ እኛ የምናስፈልጋቸውና ወንጌል የምንሰጣቸው ሰዎች መሆናቸውን ምን ያህል ተረድተናል?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱ በበጀት፣ ባማሩ መቅደሶች፣ በዘማሪ ቡድን የታገዘ አልነበረም፡፡ እርሱ በመገኘቱ ሁሉ ይሠራ ነበር፡፡ እኛም አገልግሎቱ ሕይወታችን ሲሆንልን እግረ መንገዳችንን እንኳ የዘመናትን ችግር እየመለስን ማለፍ እንችላለን፡፡ ታክሲ ስንጠብቅ፣ በጎዳና ስንሄድ፣ ልቅሶ ስንደርስ፣ ስለ መልካም ነገር አስተያየት ስንጠየቅ፣ ለተከፉ ድሆች ሣንቲም ስንወረውር… እግረ መንገዳችንን የምንሠራው የዘመናት ፍርስራሽ፣ የምንገፈውም የዓመታት ጨለማ አለ፡፡ ከተወሰኑ ሰዓቶች ይልቅ ያልተወሰኑ አጋጣሚዎች ለወንጌል ልዩ መድረክ ናቸው፡፡
ጌታችን ከመንገድ እስከ ቤት ችግሮች ተዘርግተው ይጠብቁት ነበር፡፡ ከመንገዱ ይልቅ የቤቱ ችግር ሬሳ ነበር፡፡ ዛሬም የተሸፈኑ የቤቶች ችግር ከተገለጠው የአደባባዩ ችግር እየበለጠ ነው፡፡ ያ ችግር ሲገነፍል ልጆች ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋሉ፣ ፍቺ ይበረክታል፣ በቃል ኪዳን የተሳሰሩ ተጋደሉ ሲባል ይሰማል፡፡ አንዳንዱ ችግር እኛ በማለፋችን ብቻ ሊቃለል ይችላል፡፡ እኛን በማየት ብቻ የሚጽናኑ አሉ፡፡ እርሱን የሚመስል ሰው በማየት ተመለሰልኝ የሚል ብቸኛ አለና፡፡ ሌላው ችግር በመቆምና በማነጋገር ይወገዳል፡፡ ሰዎች የሚያደምጣቸው በማጣት ብቻ በእሳት እየነደዱ ይሆናል፡፡ ስንሰማቸው ግን ይወጣላቸዋል፡፡ ሌላው ችግር እዚያው ድረስ መሄድን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሬሳ አይመጣምና፡፡ እስኪመጡ ብለን የማንጠብቃቸው ካሉበት ስፍራ ሄደን የምንቀሰቅሳቸው፣ የምንጸልይላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ብቻ እያንዳንዱ ሰዓት ለፍቅርና ለመልካም ነገር አጋጣሚ ነውና እግረ መንገዳችንን ለምድር ፈውስ እንሥራ! ከታላላቅ ጉባዔዎች ይልቅ ጸጋ ሲፈስ እናያለን፡፡ ስሙ በተጠራበት ለመገኘት የማያስችለው ጌታ ስሙን ስንጠራ፣ የምናገኛቸው ሁሉ መልካም መጠጊያ እንዳገኘ ከሽሽት ሥቃያቸው ሲድኑ እናያለን፡፡
 በአንድ ወቅት እያዘንኩ በአውቶብስ ውስጥ ተሳፍሬ ስሄድ እግሬ እንኳ ተስተካክሎ ባልቆመበት ስፍራ የሚያቆም ቃል ሰማሁና በመልስ ገባሁ፡፡ አንድ ሰው ለአንድ እህት፡- ‹‹እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ያለ መውጊያ አልተመለከም፤ ሰዎች ካልተወጉ አያመልኩትም›› ሲል የእኔ ጥያቄ ተመለሰ፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሰማሁትን ችግር መቋቋም አቅቶኝ ሳለ አንድ መነኩሴ አንዲት ሕጻን ልጅን እስኪ ጥቅስ ንገሪኝ ሲሏት፡- ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ›› ስትል ልቤ ስንጥቅ አለ፡፡ ችግር ያልኩትም እንደ ወደቀ አመንኩኝ፡፡ እግረ መንገድ ስንት ዘመን ተሠራን፡፡ እግረ መንገድ እኛም እንሥራ! ታክሲ ላይ የተለጠፉ ጥቅሶች ለስንት ሰው መጠገን እንደሆኑ፣ ዓለም ያሰከረቻቸው አያሌዎች እንደተረጋጉ እናውቃለን፡፡ መንገድ አሳዩን ለሚሉ በትሕትናና በጥሩ አስረጂነት ብንጠቁማቸው ለካ ሰው አላለቀም ብለው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይሄዳሉ፡፡ በጨለማው ሰዓት የጊቢአችንን መብራት ብናበራው ለራሳችን ባበራነው መብራት በመንገዱ የሚያልፉ እየመረቁን በድፍረት ይራመዳሉ፡፡ በልተን ከሚተርፈን ምሳ ላይ አንዱን ወዳጅ ብንጋብዘው ሲያስበው ይኖራል፡፡ መቀመጫችንን ብንለቅላቸው በመከበራቸው ብዙዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ ትምህርት አልገባ ያላቸውን መምህሩ ሲወጣ በእኛ ቋንቋ ብንገልጥላቸው ሲያመሰግኑን ይውላሉ፡፡ አጠገባችን ያለውን ሰው ከያዝነው ቆሎ ብናሳትፈው ቀጥሎ የቤቱን ገመና ይዘረግፍልናል፡፡ ከቢሮ ይልቅ ባለጉዳዮች በጎዳና ላይ አሉ፡፡ ከዐውደ ምሕረት ይልቅ ተሰባኪዎች እገረ መንገድ ይገኛሉ፡፡ የምናስፈልግበትን ቦታ እንድንለይ፣ ሥራችንን በታማኝነት እንድንሠራ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያግዘን

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።