F
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ
‹‹Love is the Answer no matter what the Question! ለየትኛውም፣ ለማንኛውም ጥያቄዎቻችን ፍቅር መልስ ነው!››
(ይህ ጽሑፍ ‹‹በፍቅር ለይኩን›› የተባሉ ጸሐፊ ‹‹በአዲስ አድማስ ጋዜጣ›› የቅዳሜ ሐምሌ ፲፬/፳፻፬ እትም ላይ ያወጡት ጽሑፍ ሲሆን ጽሑፉም ‹‹ዶ/ር ፈቃደ አየለ›› የተባሉ ጸሐፊ በዚሁ ጋዜጣ ‹‹ድምፂቱ፣ ለእነ እንዴት እንመን… ለሚሉ ወገኖች›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ያስነበቡትን መከራከሪያ አሳብ መሠረት በማድረግ ‹‹በፈጣሪ በማመንና በሀለዎተ-እግዚአብሔር›› ዙሪያ ጸሐፊው በፍቅር ለይኩን የራሳቸውን እሳቤና አስተያየት ያንጸባረቁበት መጣጥፍ ነው፡፡ እኛም ይህን ጽሑፍ ለብሎጋችን በሚመች መልኩ እንዲህ አዘጋጅተን ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ!)
አፄ ቴዎድሮስ ብዙ ከተባለለትና ከተጻፈለት አፍሪካዊው ‹‹ታላቁ ናፖሊዮን›› ካሰኛቸው ከጀግንነታቸው፣ ከጭካኔያቸው፣ ከፍርድ አዋቂነታቸውና ኢትዮጵያን ለማዘመን ከነበራቸው ታላቅ ራእይ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ስለ ፈጣሪ ህልውና ከቤተ ክህነቱ ተጠሪዎች ነን ባዮች ደብተራዎችና ካህናት ጋር ያደረጓቸው እንደ አንዳንድ የዋሃን አገላለጽ ‹‹ፈጣሪን መፈታተን›› ዓይነት ጥያቄዎችን እያነሡ ካህናቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንቶች በጥያቄ በማጣደፍ ያስጨንቁ ነበር ይባላል፡፡ እናም በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ በዙፋናቸው በተሰየሙበት ግብር ገብቶ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርሰቲያን፣ ካህናት በታደሙበት ግብዣ ላይ ንጉሡ አንድ ጥያቄ አነሡ እንዲህ ሲሉ፡-
‹‹ለመሆኑ እግዚአብሔር አለን… ካለስ ምን እየሠራ ነው…!? በማለት ጥያቄያቸውን ወርወር አድርገው የሊቃውንቱንና የካህናቱን መልሳቸውን ለመስማት ጓጉተው መይሳው ካሳ ከዙፋናቸው ላይ ተመቻቹ፡፡ ሊቃውንቱና ካህናቱ ሁሉ የመሰላቸውንና የንጉሥን ልብ ያሳርፋል ያሉትን መልስ ሁሉ ወደ አፄ ቴዎድሮስ መወርወር ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ ከእነዚህ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን ከሚሉ ሊቃውንትና ካህናት ዘንድ ንጉሥ ቴዎድሮስ ልባቸውን የሚያሳርፍ በቂ ምላሽ አላገኙም፡፡ እናም በቁጣ ሆነው ሊቃውንቱንና ካህናቱን በመገላመጥ ከግብር ቤቱ በራፍ ላይ ደበሎውን ለብሶ አኩፋዳውን ይዞ ከንጉሥ ገበታ የሚተራርፈውን እንጀራ የሚጠብቀውን አንድ ምስኪን የቆሎ ተማሪ ወደ ዙፋናቸው አስጠርተው ተሜ፡- ‹‹እግዚአብሔር አለን… ካለስ ለመሆኑ ምን እየሠራ ነው!? አሉት፡፡
ተሜም ለጥ ብሎ እጅ ከነሣ በኋላ ‹‹ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሡ! እግዚአብሔር መንግሥትዎን ያስፋ፣ ጠላትዎን ያጥፋ! ጃንሆይ እግዚአብሔርማ አለ እንጂ…! የቀን ተሌት ሥራውም ለእያንዳንዳችን መልካም ሆነ ክፉ ሥራችን ምላሽ/ብድር ሰፍሮ የሚመልስበትን ቁና ይሰፋል!›› በማለት መለሰ፡፡ ንጉሥም በተሜ መልስ እጅግ ተደንቀው ትክክል ብለሃል በማለት ያን ተማሪ እንደመረቁትና እንደሸለሙት በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ እግዚአብሔር አለ ወይስ የለም፣ ካለስ ምን እየሠራ ነው!? የሚሉ ጥልቅ የሆኑ በእግዚአብሔር ህልውና፣ የእጆቹ ሥራዎች ላይ የሚያሟግቱ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች ትናንት ተጠይቀዋል፣ ዛሬም ይጠይቃሉ፣ ምናልባት ወደፊትም እስከ ፍጻሜ ዓለም ይኸው ጥያቄው ይቀጥል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፤ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ያለ ነፍሱ በጥያቄ መዓት የተሞላች ጠያቂ ፍጥረት የለምና!
ለመሆኑ በዓለማችን ታሪክ ውስጥ እንደ እኛው ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ‹‹እግዚአብሔር አለን… ካለስ ምን እየሠራ ነው?!›› በማለት የጠየቁ ግለሰቦች ወይም ፈላስፋዎች ነበሩ ይሆን? ከነበሩስ እንዲህ ዓይነቱን በፈጣሪ ህልውና ላይ የሚገዳደር ጥያቄ እንዲያጭሩና ባስ ሲል ደግሞ እንደ ፳ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀርመናዊው እውቅ ፈላስፋ ኒቼ ‹‹God is Dead!›› ወይም ‹‹እግዚአብሔር የለም፣ ሞቷል!›› የሚል አብዮት በእግዚአብሔር ህልውና እና በአማኞቹ ልብ ላይ እንዲያፋፍሙ ምክንያቱ/ምክንያታቸው ምን ይሆን በሚል በዚህ በፈጣሪ ህልውና ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥቂት ቁምነገሮችን ለማነሳሳት ወደድሁ፡፡
ለመሆኑ በምድራችን ታሪክ የሰው ልጆች የፈጣሪን ህልውና/መኖር ለመጠራጠር እንዲገደዱ የሚያደርጋቸው ምክንያቱ ምን ይሆን በማለት ራሴን ለመጠየቅ ተገደድሁ፡፡ በቅርቡ ‹‹ፍልስምና›› በሚል በጸሐፊ ተውኔትና በጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ የተዘጋጀ በተለያየ እውቀት ደረጃ፣ የሥራ ኃላፊነት፣ ሃይማኖት፣ አመለካከትና የሕይወት ፍልስፍና ውስጥ ያሉ ጥቂት የሀገራችንን ታዋቂ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ያደረገበትን መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሃይማኖት እና ስለ ፈጣሪ በተነሡ አከራካሪ እሳቤዎችና ፍልስፍናዎች ላይ መልስ ከሰጡ ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት የፍልስፍናው ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጹት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር ጥርጣሬ ካስነሱ ምክንያቶች መካከል ሲጠቅሱ፡-
በምድራችን ላይ ስለነገሰው መከራና ግፍ፣ ምድሪቷ ባለቤት የሌላት እስኪመስል የሰቆቃ፣ የእዬዬ፣ የእሮሮና የሥቃይ አውድማ ያደረጋትን አሰቃቂ ክስተት የታዘቡ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡ ፈላስፋዎችና የሥነ መለኮት ምሁራን በመጥቀስ ‹‹በእርግጥ የሰው ልጅ ሕይወትና ድኅንነት የሚገደው አምላክ ቢኖር እንዲህ አይሆንም በማለት እግዚአብሔር በምድሪቱ ዕጣ ፈንታም ሆነ በሰው ልጆች ሕይወት ታሪክ ውስጥ ምንም ድርሻ የሌለው አንዳንዴም ጨካኝ እና ስሜት አልባ›› ተደርጎ እንዲሳል ሆኗል በማለት ያብራራሉ፡፡ እግዚአብሔር አለን? ካለስ ይህ ሁሉ ክፋት፣ ዓመፃና ቀውስ ሲነግሥ በንጹሐን ደም ምድሪቱ ስትጨቀይ ፍቅር! ነው ተብሎ የተነገረለት አምላክ ለመሆኑ ምን እያደረገ ነው…!?
ዶ/ር ዳኛቸው እንደገለጹት በዚህ በምድራችን ትራጀዲ ዙሪያ የ፲፱ኛው መቶ ክ/ዘመን እውቅ ደራሲና ጸሐፊ የነበረው ሩሲያዊው ፊዮዶር ዶስቶቮስኪ ‹‹የኮን ማዞቭ ወንድማማቾች›› በሚለው መጽሐፉ ላይ ሁለቱን ወንድማማቾች ኢቫንና ኢሊዮቫ ሲያወያይ ፈላስፋው ኢቫን ለሃይማኖተኛው ኢሊዮቫ የሚከተለውን ፈታኝ ጥያቄ አንስቶለታል፡-
‹‹ኃጢአተኞች፣ ክፉዎችና አዋቂ ሰዎች ስቃይ ቢቀበሉ ይገባኛል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ስለምናየው የንጹሐን መገፋት፣ ጉስቁልና የሞላበት ትራጄዲ የሆነ ሕይወት፣ እልፍ የሚሆኑ ሕጻናት በከንቱ ስለሚያልቁበት ኢ-ፍትሀዊ ፍርድ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብ አይችልም፡፡ ንጹሐንን በሚመለከት እግዚአብሔር ያሻውን ለማድረግ የመግቢያ ትኬት የለውም፡፡››በማለት በፈጣሪ መኖር ላይ ያለውን ጥርጣሬ ግልጽ አድርጓል፡፡ ይህ ክስተት ለሃይማኖተኛው ለዲዮስቶቮስኪም ፈታኝ ጥያቄና መልስ ያጣበት የዘመናት እንቆቅልሽ እንደሆነ በሕይወት ዘመኑ በማስታወሻው ውስጥ አስፍሯል፡፡ ይኸው ብዙዎችን የዓለማችንን ሊቃውንቶችና ፈላስፋዎች ያመራመረ እንቆቅልሽ በሀገራችን ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ‹‹እውነት ከመንበርህ የለህማ!›› በሚል ቅኔው እንዲህ ተገልጧል፡-
‹‹ . . . ግን . . . ግን . . . ብላቴኖቹ ምን በደሉ
የማንን አደራ በልተው . . . የማንን አማን አጎደሉ
እምብርታቸው ያላረረ . . . አጥንታቸው ያልከረረ
ሰማይ በቀል እንደ ቋጠረ . . . ዕጣቸውን እየመነጠረ
መንገዳቸውን እያጠረ
እንደ ደራሽ ውኃ አግተልትሎ
በራብ አኮርማጅ ተልትሎ
ከእናት እቅፍ በግፍ ነጥቆ
ምሱን ሊቃመስ ተናጥቆ
ሲሰለፍብን በአጭር ታጥቆ
እያየህማ ዝም ካልክማ
እውነት . . . እውነት . . . ከመንበርህ የለህማ . . .!››
ምድራችን ስለተራበችው ፍቅር፣ ምሕረትና ፍትሕ እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ስለነገሠው መከራ፣ ዋይታና ሰቆቃ ነፍሳችን በእጅጉ እያነባች በዚሁ ሁሉ ምስቅልቅልና ቀውስ ውስጥ ‹‹እግዚአብሔር የት እንዳለና ምን እየሠራ እንደሆነ›› ግራ በመጋባት ፈጣሪን የምንጠይቅ ሰዎች በተለይ ራብ፣ ችጋር፣ የከፋ የእርስ በርስ ጦርነትና መከራ ዕጣ ፈንታችን እስኪመስል መገለጫችን ለሆንን ለእኛ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ግን ለምን… ለምን?በማለት ለዘመናት መልስ ያጣንበት እንቆቅልሻችን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ሰው የሰውን ሥጋ እስከመብላት የተደረሰበትን፣ ጻዕረ ሞት የከበባቸው የሚመስሉ ሕጻናት በሞት የተነጠቁ እናቶቻቸውን ጡት ሲጠቡ የታየበትና ዓለምን በዕንባ ያራጨ ዘግናኝ የራብ ታሪክ ውስጥ ደጋግመን ስለማለፋችን፣ እርስ በርስ ስለተላለቅንበት ጦርነት፣ ሕዝባችን በተለያየ ጊዜ በሞት ስለተቀጠፈበት ወረርሽኝ፣ እርዛት፣ መከራና ሀገራችን ስለምትዳክርበት የከፋ ድህነት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን ደካማ የሥራ ባሕል፣ ስንፍና፣ ነጻ አስተሳሰብንና የአሳብ ልዩነትን በሰላም የማስተናገድ ዲሞክራሲያዊና በቅንነት የመቀባበል ባሕል አለማዳበራችን፣ ሀገራችንን ያስተዳደሩ ነገሥታቱም ሆኑ መንግሥታት አምባ ገነንትና የፍትሕና የመልካም አስተዳደር እጦት…ወዘተ ስላለፍንበት ዘግናኝ ጉስቁልናችን፣ መከራችንና አሁንም ላለንበት ዝቅጠትና የከፋ ድህነት እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ቢገለጹም በአንጻሩ ደግሞ በሌላ በኩል፡-
ሀገረ-እግዚአብሔር ተብላ በምትጠራ ምድር፣ ሕዝቦቿ በእጅጉ ሃይማኖተኛ ናቸው ተብለው ለሚነገርላት ኢትዮጵያ ይሄ ሀገሪቱ በዓለም መድረክ የጦርነትና የራብ ምድር ተደርጋ የመገለጹ እውነት ብዙዎችን እያሳቀቃቸው ዓይናቸውን ወደ ፀባዖት በማንሣት ጠዋት ማታ አንተን የምትማጠን ኢትዮጵያንና ሕዝብህን እንዲህ ለአሰቃቂ ሞትና ለቅጥ የለሽ መከራ የዳረግበህት ምክንያቱ ምን ይሆን… በማለት ፈጣሪን የሚሞግቱና የሚጠይቁ በርካታ ሰዎች ዛሬም ድረስ በመቅደሱ አሉ፡፡
በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ዘንድ ሀገሪቱ ስላለፈችበት ውጣ ውረድና አሁንም ስላለችበት ውሉ የጠፋ ስለሚመስል ችግር የሚቀርቡትን ጥናቶችና ትንታኔዎች ለማብራራት የጽሑፌ ዓላማ አይደለምና ብዙም ሳልርቅ በጽሑፌ መግቢያ ወዳነሣሁት ጭብጥ ልመለስ፡-በምድራችን ላይ ስለነገሠው ይህ ሁሉ ግፍ፣ መከራና ጉስቁልና፣ ስለ ሰው ልጆች ሥቃይ፣ ስለ ንጹሐን እልቂት፣ ስለ ድሆች ጩኸትና ዋይታ የሚገደው እግዚአብሔር አለን ካለስ ይህን ሁሉ ግፍ እያየ ለመሆኑ ምን እየሠራ ይሆን? ከላይ እንደገለጽኩት ሃይማኖተኝነት በሚጎላበት ሕዝባችን መካከል ክስተቶችን ከእግዚአብሔር ምሕረትና መዓት ጋር ማገናኘት በረጅም ዘመን ታሪካችን ውስጥ የምንታዘበው ሐቅ ነው፡፡
ለዚህ ይመስለኛል ፋሽስቱ ቢኒቶ ሞሶሎኒ ይሄንን የሀገራችንን ሕዝብ ሃይማኖተኝነት በሩቅ በዝና ሰምቶ ለኢጣሊያን ሕዝብና ለጦር ሠራዊቱ በሮም አደባባይ ባደረገው ንግግር፡- ‹‹ኢትዮጵያን አምላኬ የምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ ክንዴና ከብርቱ መዳፌ ያድነኛል ብላ ከሆነ ተስፋ ያደረገችው የእኔንም እግዚአብሔር ልጨምርላት እችላለሁ!›› በማለት በኢትዮጵያ አምላክ ላይ በናቡከደነጾራዊ ትዕቢትና ትምክሕት በምስኪኑ ሕዝባችን ላይ በማላገጥ ዲስኩር ማድረጉን የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡
እስቲ በጦርነትና በራብ ታሪካችን ውስጥ ‹‹ፈጣሪ የተሞገተበትን››እውነት የሚያጎሉ ሀገራዊ ክስተቶችን በጥቂቱ ልጥቀስ፡- እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ ሀገራችን ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት ዘመን የጣሊያን ጦር በሀገራችን ሰማይ ላይ ያሰማራቸውን የጦር አውሮፕላን የታዘበ የሀገሬ ሰው እነዛ በሰማይ ላይ እየተምዘገዘጉ የእሳት አሎሎ በሚተፉና የመርዝ ቦምብ እያዘነቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕጻን፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ እንደ መኸር እህል እያጨደ የከመረውን፣ በእነዚህ ሞትን በሚተፉ እንግዳ ፍጡሮች ግራ በመጋባቱና አውሮፕላኖች በሕዝባችን ላይ እንደ መዓት ያፈሰሱትን የመከራ ውርጅብኝ የተመለከቱ አንዲት የሸዋ መነኩሲት በሀለዎተ እግዚአብሔር/በፈጣሪ መኖር ላይ ጥርጣሬ ያጫረባቸውንና ይህ ሁሉ መዓት በምስኪን ሕዝቡ ላይ ሲደርስ እግዚአብሔር ዝም ብሎ ያያልን!? በሚል የሀገራቸውን አሰቃቂ የታሪክ ክስተትና እልቂት በቅኔያቸው ‹‹ፈጣሪን ወዴት ይሆን ያለህ!?›› በሚል እንዲህ በድፍረት ሞግተውት ነበር፡-
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፡፡
አምላክ ለአንተው ፍራ፣
በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡ በማለት እነዚህ በሰማይ የሚምዘገዘጉ የፋሽስት ጣሊያን ሠራዊት የሞት አበጋዞች በእውነት አንድዬ በዙፋንህ ካለህማ ግዛትህን እየተዳፈሩና የአንተንም ህልውናን ጭምር እየተፈታተኑ እንደሆነ ተመልከት ሲሉ ያሳሰቡበት ነው፡፡ ሌላው የደብረ ሊባኖስ ባለ ቅኔም ይህን ድፍን ኢትዮጵያን ጉድ ያሰኝ እነዚህ የጣሊያን ጦር የሰማይ በራሪ አካላት በሀገራችን ሕዝብ ላይ ሴት ወንድ፣ ሕጻን ሽማግሌ ሳይሉ የሚያዘንቡትን የሞት የእሳት ላንቃ ታዝበው እንዲህ ተቀኝተው ነበር፡-
ከኢትዮጵያ ጸሎት ጣሊያኖች በለጡ፣
በአርባ ዘመናቸው ክንፍ አውጥተው መጡ፣
ፈጣሪ ተጠንቀቅ ወዳንተም እንዳይመጡ፡፡
የዚህ ቅኔ መነሻው ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው የጸለዩት በዚህ በረጅም ጸሎታቸው፣ ተጋድሎአቸውና ትሩፋታቸውም የተነሣ ከፈጣሪ ዘንድ ክንፍ ተሰጥቶአቸዋል ተብሎ የሚተረክላቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ባለ ቅኔው በዘመናቸው ሃይማኖተኛ ነኝ ብሎ የሚመጻደቀው ሕዝባቸውና ኢትዮጵያውያን በጾምና በጸሎታቸው ያልታደሉትን ክንፍ ጣሊያን በአእምሮ ብልጠትና ስልጠት ከአድዋው ጦርነት አሳፋሪ ሽንፈት በኋላ በአርባ ዘመናቸው በረቀቀ ቴክኖሎጂ በሰማይ በሚበር ባለ ክንፍ አውሮፕላን መጥተው ሕዝቡን እንደፈጁና ሀገሪቱን ለመያዝ እንደበቁ ያመሰጠሩበት፣ የራሳቸውንና የሕዝባቸውን ሃይማኖተኛነትና ለሺህ ዘመናት ሀገረ-እግዚአብሔር ተብላ የምትጠራውን ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገቡበትና የተቹበት ቅኔ ነው፡፡
በ፲፱፻፸፯ቱ ክፉ የድርቅ ዘመንም በተለይ የሰሜኑ የሀገራችን ሕዝብ ባጋጠመው አሰቃቂና መላውን ዓለም ዕንባ ያራጨ ራብ፣ ጉልበቱ የበረታ የሀገሬ ጎበዝ እራሱንና ቤተሰቡን ከሞት መንጋጋ ለመታደግ እህል ፍለጋ ወደ ሸዋ ግዛት በስደት መጥተው ነበር፡፡ በዛም ድርቁና ራቡ ብዙም ያላጠቃው የሸዋ ሕዝብ በሰሜነኞቹ ላይ ባሳየው ያልተገባ ባሕርይና ኢ-ሰብአዊነት ሞራሉ የተነካበት የሰሜኑ ሕዝባችን እንደ ጀርመናዊው ፈላስፋው ኒቼ ሁሉ ‹‹ፈጣሪ ሞቶብን!›› እንዲህ ጊዜ ጥሎን እናንተም እንደ እግዚሔሩ ፊታችሁን ታዞሩብን፣ እንዲህ ትዘባነኑብን ሲል ምሬቱንና ብሶትን በግጥም እንዲህ ገልጧል፡-
እነዚህ ተጉለቶች
የእኛ እግዜር ሞቶብን!
የእኛ እግዜር መንኖ፣ የእነሱ ቆመና
ውሻ ‹‹ችስ!›› እያሉ አፈራረቁብን አንኮላና ቁና፡፡
ሀገራችን ስላለፈችበት ክፉ የራብ ዘመናትና የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት አሁንም እያለፈችበት ስላለው ጉስቁልና እና የከፋ ድህነት ምክንያት ፈጣሪ/እግዚሔሩ ወይም እኛ ስለምንጠየቅበት አግባብ አሳማኝ የሆነ መረጃና ትንታኔ ለማቅረብ በዚህ አጭር ገጽ የማይታሰብ ቢሆንም ወደ መነሻ አሳባችን ስንመለስ የሰው ልጆች በኃጢአታቸውና በበደላቸው የተነሣ ከሚመጣ ቁጣ፣ መከራና ጉስቁልና ባሻገር ‹‹ለኃጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል!›› እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል እግዚአብሔር በንጹሐን ላይ ስለሚደርሰው ግፍና በደል በተመለከተ ግን ለመሆኑ እግዜሩ ምን ምላሽ አለው?
ፈላስፋዎቹ እንዳሉትስ ይህን ሁሉ ግፍ፣ መከራና ኢ-ፍትሐዊነት ታግሦ ዝም ብሎ የሚያይ ‹‹ፈጣሪ/አምላክ አለ ቢባል እንኳን እንዳለ አይቆጠርም ወይም እግዚአብሔር ጭራሹኑ የለም!››የሚለውን መደምደሚያ እስቲ ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ እውነት አንጻር እንመልከተው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የፈጣሪን ህልውና ከመካድ ባለፈ እንዲህ ዓይነቱን ‹‹ፍርደ- ገምድል እግዚአብሔር›› ከሆነ አምላክ ብለን ስናመልክና ስንገዛለት የኖርነው በእውነት ተሳስተናል እናም ይህን እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት በማለት በምሬትና በብስጭት የተናገረች ሴትን ታሪክ እናገኛለን፡፡
በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እጅግ ቅን፣ ጻድቅ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ተብሎ የተነገረለት ኢዮብ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው እጅግ ተመችቶት በሀብትና በዝና ዙፋን ላይ ተንደላቆ ከቤተሰቡና ከወገኑ ጋር እጅግ ደስ ብሎት የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ግና ይህ በሀብትና በዝና ምንጣፍ ላይ ሲራመድና ሲንቀባረር የነበረ በእግዚአብሔር አንደበት ‹‹ጻድቅና ቅን!›› ተብሎ የተመሰከረለት ሰው በአንድ ጀምበር ሀብት ንብረቱን፣ ቤተሰቡንና ጤናውን አጣ፡፡ በአንድ ጊዜ ሰማይ ምድሩ ተደፋበት፡፡ የልጆቹ እልቂት የሀብት ንብረቱ መውደም፣ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በቁስል ንዳድ በመመታት በትል መወረሱ፣ በመርዶ ላይ መርዶ፣ በሐዘን ላይ ሐዘን የተከታተለበት ኢዮብ ሐዘኑ ቅጥ አጣ፣ በታላቅ ድምጽም ጮኾ አለቀሰ፣ ከክብር ሰገነቱ ወርዶ በአመድ ላይ ተቀምጦ በራሱ ላይ ትቢያን ነስንሶ የተወለደበትን ቀን በምሬት እንደረገመ ታሪኩ በመጽሐፈ ኢዮብ በሰፊው ተጽፎለታል፡፡
ጻድቁ ኢዮብ የመከራውና የዚህ ሁሉ መዓት ውርጅብኝ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጥሯል፣ ደክሟልም፡፡ ምነው ቃሌ በአለት ላይ ቢጻፍ ብሎም ተመኝቷል፣ እንደውም ምናለ በእኔና በአምላክ ፊት የሚቆምና ክርክራችን የሚዳኛ ዳኛ በተገኘ ሲልም ተማጽኗል፡፡ ኢዮብ አንቱ በተባለበት ምድር የከበሬታ ስፍራ ያገኘ ፍርድንና ፍትሕን ለማድረግ የሚሟገት ሰው፣ መልካሙን ስጠብቅ ክፉን አገኘሁ፤ በእውን ድሀውን ገፍቼ፣ ፍርድ አጉድዬ ነበር እንዴ፣ ለችግረኛውና ለምስኪኑስ አባትና ጠበቃ አልነበርኩ በማለት ስለ እራሱ ተሟገተ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ የአካሉ ክፋይ ረዳቱ የምትሆነው ይህን በቃላት ሊገለጽ የማይችል የመከራ ዶፍና ውርጅብኝ የታዘበችው ሚስቱ የአካሉ ክፋይ እንዲህ አለችው፡-
‹‹አሁንም በታማኝነትህ እንደጸናህ ነውን… እግዚአብሔርን ስደብና ሙት!›› ስትል ልብን በሌላ የኀዘን ሰይፍ የሚመትር፣ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ነፍሱን የሚበረብር ንግግር ተናግራው ከእንግዲህ አልተገናኘንም ወዳጄ በማለት እንደ ዋዛ በዛ የመከራና የጭንቅ ቀውጢ ዘመን ሚስቱ የአካሉ ክፋይ እንኳን ጥላው እብስ አለች፡፡ ኢዮብ ይህን አሰቃቂ ክስተት፡- ‹‹ሚስቴም እስትንፋሴን ጠላች፣ የእናቴም ማኅጸን ልጆች ልመናዬን ጠሉ፡፡ ቤተሰቦቼ፣ ወዳጆቼና የሴት ባሪያዎቼ እንደመጻተኛ ቆጠሩኝ፣ በዓይናቸውም ፊት እንደ እንግዳ ሰው ሆንሁ፡፡›› (ኢዮ ፲፱፣፲፯) ሲል በምሬትና በሐዘን ስሜት ይገልጸዋል፡፡
ኢዮብን ለማጽናናት ከሩቅ የመጡ ወዳጆቹም መጽናኛ ቃል ሳይሆን በቁስሉ ላይ ጥዝጣዜን የሚጨምር የምላስ ጅራፋቸውንና የቃላት ውርጅብኛቸውን በየተራ እየተቀባበሉ ያወርዱበት ጀመር፡፡ አንድ የሰራኸው ኃጢአትና በደል ቢኖር እንጂ መከራ እንዲሁ ከሰማይ አይወርድም ሲሉ በኀዘን የደከመችና ተስፋ የቆረጠች ነፍሱን በእጅጉ አጎሳቆሏት፣ አሳቀቋትም፡፡ ኢዮብ ግን በዚህ ሁሉ ሥቃይና መከራና ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ ‹‹ብሞትም እንኳን እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፣ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ!›› (ኢዮ ፲፫፣፲፭) ሲል ለነፍሱ ተናገራት፡፡
ኢዮብ በታላቅ የጥያቄና የእንቆቅልሽ ማዕበል ውስጥ ነፍሱ ከወዲህና ከወዲያ እየተላጋችም ቢሆን በታማኝነቱ ጸና፡፡ ኢዮብ ምንም ‹‹ጻድቅና ቅን›› ተብሎ በአምላኩ የተመሰከረለት ሰው ቢሆንም በመከራው ዘመን ‹‹እግዚአብሔር የት ነህ ያለኸው!?›› ሲል በምሬት ጠይቋል፡፡ የሚደንቀው ነገር በስተመጨረሻ የኢዮብን ጥያቄ እግዚአብሔር በጥያቄ ነበር የመለሰለት እንዲህ ሲል፡-
‹‹…እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ እጠይቅሃለሁ አንተም ተናገረኝ፤ በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን? እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጎደጉዳለህን? በታላቅነት ተላበስ በክብርና በግርማም ተጎናጸፍ፡፡ የቁጣህን ፈሳሽ አፍስስ፣ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው፡፡ ትዕቢተኛውንም ዝቅ ዝቅ አድርገው፣ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው፡፡ በአፈር ውስጥም በአንድነት ሰውራቸው፣ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን፡፡ በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ…፡፡›› (ኢዮብ ፵፣፮-፲፬)
እናም በፍጻሜው ኢዮብ ያለው ነገር ቢኖር ‹‹እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ፤ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ አሳብህንም የሚከለክለው እንደሌለ አውቅሁ፡፡›› በማለት በአምላኩ ፊት ተጸጸተ፡፡ በመከራው ፍጻሜ እግዚአብሔር በምሕረትና በበረከት ኢዮብን እንደጎበኘውና በደስታና በሐሴት ዕድሜን ጠግቦ እንደሞተ ይኸው የኢዮብ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
እንደ ኢዮብ ሁሉ በራሳችን/በግል ሕይወታችንም ሆነ በቤተሰብ ይሁን በሀገር ደረጃ መልስ ስላጣንበት ምድራችን ስለተራበቸው ፍቅር፣ ምሕረትና ፍትሕ ኃጢአተኞችና ክፉዎች ስለሰለጠኑበት ሁኔታ እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ስለነገሠው መከራ፣ ዋይታና ሰቆቃ ነፍሳችን በእጅጉ እያነባች በዚሁ ሁሉ ምስቅልቅልና ቀውስ ውስጥ እግዚአብሔር የት እንዳለና ምን እየሠራ እንደሆነ ግራ በመጋባት ፈጣሪን የምንጠይቅ ሰዎች በኢዮብ ሕይወት እንደታየው እግዚአብሔር መልሶ እኛኑ ስለ ኃይሉ ፍጹምነት፣ ስለ ታላላቅ የእጆቹ ሥራዎች፣ ስለማይመረመር ፍርዱና ምሕረቱ በመጠየቅ አፋችንን በመገረም አስይዞን ያለ እርሱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ምንኛ ምስኪንና ጎስቋላ መሆናችን በመግለጽ በፍቅር ኃይል፣ በእምነት ዓይን፣ በማስተዋል ልቡና ሥራውን በአንክሮ እንድናስተውል ያሳስበናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ሕይወት ታሪክ ጉዞ ውስጥ በግለሰብ፣ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚያከናውናቸው ክስተቶች ብንጠይቅም ብንመራመርም ልንደርስበት ስለማንችለው የእውቀቱ፣ የጥበቡ፣ የማስተዋሉና የፍርዱ ነገር ሲናገር፡-
‹‹የእግዚአብሔርን ባለጠግነት ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፣ ፍርዱ የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፡፡ የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?›› በማለት በአድናቆት ተናግሯል፡፡ የሁሉን ቻዩን የፈጣሪን አሠራር ወደማወቅ ፍጹም የከበረ እውቀት፣ ማስተዋልና ጥበብ ለመድረስና ለጥያቄዎቻችን ሁሉ ምላሽ ለማግኘት በፍቅር ሰረገላ መሳፈር እንዳለብንና በዚህ መለኮታዊ ፍቅር ውስጥም እምነታችንን ፍጹም ለማድረግ የሚያስችል ተስፋ፣ ጸጋ፣ ኃይልና ብርታት እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
በዚህ መለኮታዊ ፍጹም ፍቅር ውስጥ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ እንዳለና ወደ እግዚአብሔር ፍጹም እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል የምንደርስበት ብቸኛ መንገድም ፍቅር መሆኑን እግዚአብሔር ራሱ በፍቅር ስለ ፍቅር እኛን ሆኖ ከኃጢአት በስተቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ ተፍትኖ ሰው ሆኖ መንገዱን አሳይቶናል፣ የማያዳግም መልስም ሰጥቶናል፡፡ ክርስትናም የዚሁ የአምላክ ፍጹም ፍቅር፡- ውበት፣ ኃይል፣ ጸጋና የሰው ልጆች ሁሉ እንቆቅልሽና ምሥጢር የሚገለጽበትና መልስ የሚገኝበት ሕይወት ሆኗል!
‹‹Love is the Answer no matter what the question! ለማንኛውም ሆነ ለየትኛውም ጥያቄዎቻችን ፍቅር ምላሽ ነው! ፍቅር ደግሞ እግዚአብሔር ነው!›› መጽሐፍ፡- ‹‹እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው!›› እንዲል፡፡ ስለዚህም በፍቅር ውስጥ ለሁሉም ጥያቄዎቻችን መልስ፣ ለሕይወት እንቆቅልሽም ነፍስንና መንፈስን የሚያሳርፍ ፍቺ አለ፡፡
ፈላስፋዎቻችን እንደሚሉት ሳይሆን ፍቅር የሆነው የዓለማት ፈጣሪና ገዢ እግዚአብሔር ስለ ሰው ልጆች መከራና ግፍ አጥብቆ ይገደዋል፣ በክፉዎችና በኃጢአተኞችም ላይ በጽድቅና በእውነት የሚፈርድ አምላክ በሰማይ በዙፋኑ ላይ አለ፡፡ የሀገራችን የቆሎ ተማሪ እንደገለጸውም እግዚአብሔር በእውነት አለ እንጂ!ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን መጠን ዋጋችንን ይከፍል ዘንድ ለብድራታችን ምላሽ የሚሆን የእያንዳንዳችንን ቁና በመስፋት ላይ ነው፡፡ በእውነትም በጥበቡ በእውቀቱና በማስተዋሉ አቻ የሌለው ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር ሁሉን በጽድቅና በእውነት የሚዳኝበትን ቁና እያዘጋጀ፣ እየሰፋ ነው፡፡ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ‹‹የዙፋንህ መሠረት ፍርድ፣ እውነትና ምሕረት ናቸው!››ብሎ እንደዘመረው፡፡
የእግዚአብሔር ቅዱስና ሕያው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን መጠን ሊከፍለን፣ ዕንባችንን ከዓይኖቻችን ሊያብስ፣ ምድሪቱን የተራበችውን ፍትሕን፣ ፍርድንና ምሕረትን ሊያሰፍን በቅዱሳን መላእክቱ ታጅቦ በአባቱ ክብር ይመጣል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ፡-
ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳኖች በሰዎች መካከል ነው፣ ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፡፡ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሐዘንም ቢሆን ወይንም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፡፡ የቀደመው ስርዓት አልፏልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፡፡ በዙፋኑም የተቀመጠው ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ፡፡ አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና! ማራናታ!
ሰላም! ሻሎም!