የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት

እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ታዋቂ እንጂ አዋቂ አያደርግም ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት የሥጋ ጫናን እያቀለለ ነፍስን ግን በሸክም ያጎብጣታል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ብዙ የማያውቁ ሰዎችን ለጥፋት ያነሣሣል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት የዘመናትን ችግር ለወገን ያመጣል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ብዙዎችን መምራት ሳይሆን መንዳት ይፈልጋል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ሌሎችን ለመሥዋዕትነት እያስተማረ እርሱ ግን ይዘገያል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት እርስ በርስ በመጠፋፋት ይደመደማል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት በጅምላ ትውልድን ይጨርሳል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ለጥፋቱ ድንበር የለውም ። ይህችን ዓለም እያስጨነቋት ያሉት ካልተማሩት ይልቅ ፊደል የቆጠሩት ናቸው ። የዓለማችን ሀብት በጥቂት ሰዎች እጅ እንዳለ ሁሉ የዓለማችን ሰላምም በጥቂቶች ክፋት ይታወካል ። ተምረው የደነቆሩና ያልተማሩ ሰዎች የዓለምን ዕድሜ ለማሳጠር በኅብረት ይሠራሉ ።
ምድራዊ እውቀት አስተዳደግን ያጠነክራል እንጂ አይለውጥም ። ምድራዊ እውቀት የማይታወቁና የማይዳሰሱ ጓደኞችን ሲያመጣ ሲጩኹ የሚደርስ ጎረቤትን ግን ያሳጣል ። ምድራዊ እውቀት ሕግን ሲያስከብር ፍቅርን ግን ያስወጣል ። ምድራዊ እውቀት ለዛሬው ዋጋ ሲሰጥ የትላንትን ግን እንዳልነበር ያደርገዋል ።
በዘረኝነት ያደገ ሰው እውቀት የበለጠ ዘረኛ ያደርገዋል ። ያልተማረ ሲገድል የተማረው ደግሞ ጥይት ያመርታል ። ያልተማረ ሲተኩስ የተማረ ደግሞ የባከነውን ጥይት ከሟች ቤተሰብ ይጠይቃል ።
እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ከራስ ጋር ያጣላል ። ብዙ ሱሰኞች የሚወለዱት ከእውቀት ስፍራ ነው ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ሞቶ መኖር ነው ። እግዚአብሔር የማይከብርበት እውቀት እምነት ሳይሆን ስሌት ያለበት ነው ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ትዕቢት እንጂ ትምህርት አይሰጥም ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ኀዘነተኛ የሚያደርግ ነው ። እግዚአብሔር በሌለበት እውቀት ውስጥ ብስጭት አለ ። አእምሮንም እውቀትንም የሰጠውን እግዚአብሔርን የማያከብር እውቀት ተሳዳቢ ያደርጋል። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት አመንዝራ ወይ ተቺ ያደርጋል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ግለኛ እንጂ ማኅበራዊ አይደለም ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ያልተማሩትን እንደ ፈጠራቸው አድርጎ ያስባቸዋል ። ስለዚህ ጦርነትን እየቀመረ ይሰጣቸዋል ። እግዚአብሔርን የማያውቅ እውቀት ሁሉንም ነገር የሚተምን ለገንዘብ እንጂ ለኅሊና እርካታ የማይኖር ነው ። እግዚአብሔርን የማያውቅ እውቀት ወላጅን የሚዳፈር ፣ “ምን እሰጣለሁ ?” ሳይሆን “ምን እቀበላለሁ ?” ብሎ የሚኖር ነው ።
እግዚአብሔርን ሳያውቁ የዓለምን እውቀት የሚያውቁ ሰዎች ክፋትና ስስት ያጠቃቸዋል ። ለድሆች ከማዘን በሚሰጥ ሰው ይበሳጫሉ ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት የሽማግሌን ገጽ የማያፍር ፣ ንጉሥን የማያከብር ፣ እግዚአብሔርን የማይፈራ ነውና በሁለት ሰይፍ የሚቀጣ ነው ። እግዚአብሔርን ገሸሽ ያለ እውቀት ግዙፍ ሰይጣን የሚያደርግ ነው ። ከባሕር አሸዋ የበዛ ፣ ከሰማይ ሰሌዳ የሰፋ እውቀት የነበረው ሰሎሞን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሲለይ እውቀቱ ሳያድነው ወድቋል ። እግዚአብሔርን ገሸሽ የሚል እውቀት እኔን ይድላኝ እንጂ ለትውልድ ደንታ የለኝም ይላል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ለእልህ ብቻ ይኖራል ። እውቀት ብቻውን አይለውጥም ፣ ምድራዊ ፍልስፍና ኃጢአትን ቀላልና ምክንያታዊ ያደርጋል። ራስንም ይቅር ማለት ይለማመዳል ። እግዚአብሔር የሌለበት እውቀት ጸጸት የሌለበት ነው ። ጥፋቱም ረቂቅና ትውልድን የሚበክል ነው ። ያልተማሩ ሰዎች የሚጣሉት ለዕለት ነው ፣ አዋቂ የሚባሉት ግን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ጥለው የሚሄዱ ናቸው ። ያልተማሩ የሚባሉት ጠባቸው ከግለሰብ ጋር ነው ፣ አዋቂ የሚባሉት ግን ከአገርና ከትውልድ ጋር የሚጣሉ ናቸው ።
እግዚአብሔርን ማወቅ መሠረት መሆኑን ረስተህ ችላ አልከው ። ዛሬ ሁሉን ጨብጠህ ደስታ የምታጣው መሠረት የሌለው ቤት ስለሠራህ ነው ። እግዚአብሔርን ነፍገህ ለልጅህ ምድራዊ እውቀትን ብቻ ሰጠኸው ፣ ልጅህን ግን አጣኸው ። ያንተ ስም እንዳይሰደብ ብቻ ልጅህን በሥነ ሥርዓት አስጨነቅኸው ፣ ነጻ ሲወጣ ግን የታመቀ ኃጢአቱን አፈነዳው ። እግዚአብሔርን ማወቅና ማፍቀር ብታስተምረው ልጅህ እስከ ሞትህ ድረስ ያንተ ይሆን ነበር ። ከእግዚአብሔር ነጥሎ ልጅን እውቀት ጋ መሸሸግ የሚያፈስ ጣራ ውስጥ ማስጠለል ነው ። እግዚአብሔርን ማወቅ ከትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲወጣ ተደረገ ። ለራሱ ጌታ መሆን አቅቶት ይኸው ትውልድ ወደቀ ። ስለ እግዚአብሔር መናገር ፈሪ ትውልድ ማምረት ነው ፣ ሃይማኖትም አደንዛዥ ዕፅ ነው ተባለ ፣ ይኸው በምድር ላይ ካጋጠሙን አራዊቶች በጥቂት የሚለዩ ልጆችን አፈራን ።
በዕድሜ ውስጥ የሚያስፈሩ እግዚአብሔርን የማይፈሩ ናቸው ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ለክፋቱ ከልካይ የለውም ። የተፈራራ ማኅበረሰብን መፍጠር ይቻላል ፣ የሚፋቀር ማኅበረሰብን መፍጠር ግን ልዩ እውቀት ይጠይቃል ።
እግዚአብሔር ማወቅ ፀሐይ ነው ፣ ምድራዊ እውቀት ሻማ ነው ። ፀሐይ በዳርቻ ሁሉ ትሰለጥናለች ፣ እግዚአብሔርን የሚያውቅ በሁሉ ቦታ ውድ ነው። ፀሐይ ለሁሉ ታበራለች ፣ እግዚአብሔርን ማወቅ ከዘረኝነትና ከራስ አጥር የሚያወጣ ነው ። ፀሐይ በነጻ ታበራለች ፣ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ለአገሩ ለወገኑ መሥዋዕት ይሆናል ። ፀሐይ ለራስዋ አታበራም፣ እግዚአብሔርን የሚያውቅም ከእኔነቱ ይድናል ። ፀሐይ ጨለማን ታሸንፋለች ፣ እግዚአብሔርን የሚያውቅም ፍላጎቱን ያሸንፋል ። ፀሐይ ስትወጣ አራዊትና ሽፍታ ይገባል ፣ እግዚአብሔርን ማወቅ ሲመጣ የትውልድ ሸለፈት ይገረዛል።
የጥበብ መዝገብ የሆነውን ክርስቶስን የማያውቅ ፣ እንዴት አዋቂ ይባላል ? እግዚአብሔርን ማወቅ ያለበት እውቀት ብዙ ከመናገር ብዙ ይሠራል ። ችግርን ከማድነቅ ወደ መፍትሔ ይፋጠናል ። ዘመኑ አጭር መሆኑን ተረድቶ ለትውልድ አንድ ነገር ያበረክታል ። መማር የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው ፡- አንደኛ፣ ማወቅ ሲሆን ሁለተኛ፣ ምሕረት ማግኘት ነው ። እግዚአብሔርን ማወቅ ምሕረት ማግኘት ነው ። ምሕረት ያገኘ እውቀትም ሌሎችን የሚወድና የሚያፈቅር ነው ። እግዚአብሔርን ማወቅ ያለበት እውቀት ራስን መግዛት ያለው ነው ። ሰላም አግኝቶ ሰላም የሚሰጥ ነው ። ክፉውን ወደ በጎ በሚለውጠው እግዚአብሔር የሚደሰት ነው ። እያወቀ እንዳላወቀ የሚኖር ነው ። ሃይማኖት ያለውና መታመኑ የጸና ነው ። ለአደራ የሚበቃና ሥራውን በትጋት የሚፈጽም ነው ። እግዚአብሔርን ማወቅ ያለበት እውቀት ትሑትና ገና ለማወቅ የሚኖር ነው  ።
አለባበስህ ተስተካክሎ ኑሮህ ከተዘባረቀ ፣ ሥልጣኔ ገብቶህ የሕይወት ውል ከጠፋህ ፣ ብዙ ደርጅቶችን እያስተዳደርህ ቤትህ ከሸፈተብህ ፣ አገር እየገዛህ መንፈስህ ካመጸብህ መፍትሔው እግዚአብሔርን አሁንም አሁንም ማወቅ ብቻ ነው ። እግዚአብሔርን ማወቅ በራሱ ደስታ አይሆንህም ፣ በእግዚአብሔር እንደ ታወቅህ ስታውቅ ያን ጊዜ በዘላለም እቅፍ ታርፋለህ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 4
ተጻፈ በአዲስ አበባ
መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ