የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዚአብሔር ይሰማል

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ      

                                               ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22/ 2007 ዓ/ም
በእግዚአብሔር እንደ መሰማት ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም፡፡ አንድ ንጉሥ ሊፈጽምልን አይደለም ጊዜ ሰጥቶን ሊሰማን ቢፈቅድ ደስታችን ወደር የለውም፡፡ “እኔ አለሁ” ቢለን ትምክሕታችን መግለጫ የለውም፡፡ እኛ እልፍ ካልን በኋላ ሊረሳው ይችላል፣ አለሁ ማለቱ ግን ያኮራናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ጊዜ ሰጥቶ የሚሰማን ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የልመናችንን ዋጋ የሚሰጠን አምላክ ነው፡፡ አለሁ ብሎ የሚሰወር ሳይሆን የሚገኝልን አምላክ ነው፡፡ ሰዎች ጆሮአቸውን ሊነሡን ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን በሞገስ ይሰማናል፡፡ የንግግር ችሎታ ስለሌለን ብዙ ዕድሎች አምልጠውን ይሆናል፤ እግዚአብሔር ግን ጥልቅ ስሜታችንን ይሰማዋል፡፡ በሕይወት ላይ ጥማታችን በጆሮው የሚሰማንና በልቡ ስለ እኛ የሚሰማው ወዳጅ ማግኘት ነው፡፡  እርሱ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የምናልፍበትን የኑሮ በረሃ ያየልን ደግሞም የሚራራልን ነው (ዕብ. 4÷15)፡፡

 

    በዓለም ላይ በልበ ሰፊነት የሚሰማን፣ በቸርነት የሚሰጠን ማግኘት በዘመናት ሁሉ ያልቻልነው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በልበ ሰፊነት የሚሰማንና ሕይወትን የለመንን መስሎን ሞትን ስንለምነው አርሞ የሚሰማን፣ ከለመነው በላይም አትረፍርፎ የሚያደርግልን ቸር አባታችን ነው፡፡ ሰዎችን መለመን አስቀድሞ ጭንቀት፣ ስንቀበልም ቀጥሎ ሰቀቀን አለው፡፡ በደስታ የምንለምነው፣ ሳንሰቀቅ የምንቀበለው ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ያስደስተናል፡- ስንለምነው በተስፋ፣ ሲሰጠን ደግሞ በቸርነት ስፍሩ ያስደስተናል፡፡ በእውነት ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ከሰዎች ብንቀበለው ኖሮ ሰዎቹ ደስተኛ ቢሆኑ እንኳ ሰቀቀኑ በገደለን ነበር፡፡ የእግዚአብሔር በረከት ግን ከራሳችን ንብረት በላይ የራሳችን ሆኖ ይሰማናል፡፡
በዓለም ላይ ብዙ መከራዎች አሉ ቢባልም የመጀመሪያው፡- የሰው ፊት መሆኑን ብዙዎች ተናግረዋል፡፡ የሰው ፊት እሳት እንደሆነ የደረሰባቸው በዕንባ ገልጸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ፊት ግን ሕይወት ነው፡፡ ሰዎች እንደ መሆናችን ሌሎችን መለመንና በሌሎች መለመን አንወድም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለምኑ ብሎ ያዘዘን ልመናን የሚወድ አምላክ ነው (ማቴ. 7፡7)፡፡ ልመና በዘመናችን ጎጂ ባሕል ነው፣ የአገርንም መልክ ያበላሻል፡፡ እግዚአብሔርን መለመን ግን ራስን መቻል፣ ሥልጣን፣ ባለጠግነትም የማያስቀረው ፍላጎት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ጥገኞች ነን፡፡ የእርሱ ጥላም ከሠራናቸው መጠለያዎች ይልቅ የሚያስተማምን ነው፡፡ የራሳችን የሆነውን ንብረት እንኳ ለመጠቀም እናስባለን፡፡ እግዚአብሔርን ግን አምጣ የምንለው ሳናስብበት ነው፡፡ ከራሳችን ይልቅ የራሳችን የሆነው ጓዳችን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ከራሳችን ይልቅ ለራሳችን የቀረበን፣ የሚረዳን፣ የማይታዘበን ወዳጃችን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለነበርጠሜዎስ የመንገድ ዳር ለማኞች ጩኸት የቆመ ጌታ ነው (ማር. 10፡46-52)፡፡ እነበርጠሜዎስ ለዘመናት ሣንቲም ተመጽውተዋል፡፡ ኢየሱስ ጌታችን ግን የሣንቲም ሳይሆን የብርሃን ስጦታን ሰጣቸው፡፡ የችግሩን ወራጅ ሳይሆን ምንጩን ደፈነው፡፡ ለ12 ዓመት ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት ድምጽዋን ሳይሆን የልቧን መቃተት ሰማላት (ማር. 5፡25-32)፡፡ ሰዎች የሚሸሽዋት ሳለች ኢየሱስ ግን ቆመላት፡፡ እግዚአብሔር በእውነት ይሰማል፡፡ ያልሰማን የሚመስለን ለምነን የተቀበልነውን ስለምንረሳው ነው፡፡


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተቀመጡ ጣፋጭ ታሪኮች፣ ለዛሬው ክፍተታችን መልስ ከሆኑ ተአምራቶች አንዱ በነቢይት ሐና ሕይወት ውስጥ የተፈጸመው ነው፡፡ ሐና የማይቻለው ነገር በእግዚአብሔር የተቻለላት፣ እግዚአብሔርን የመጠበቅ ዋጋን የተቀበለች፣ የተቀበለችውንም መልሳ ለእግዚአብሔር የሰጠች ሴት ናት፡፡ እኛ ለብዙ ዘመን ጠብቀን የተቀበልነው ነገር እንደ ጣኦት ይሆንብናል፡፡ ሐና ግን የሁልጊዜ እምነቷ እግዚአብሔር ነበር፡፡ 1ሳሙ. 1÷ 1-2፡- “ በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፤ … ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ” ይላል፡፡ በዚያ ዘመን ሁለት ሚስት ማግባት በእስራኤል ተለምዶ ነበር፡፡ ይህ የእስራኤል የድካም ታሪክ እንጂ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ያስተማረን ለአንድ ወንድ አንዲት ሴት ብቻ ነው፡፡ ለአንድ ወንድ ብዙ ሴቶች ቢያስፈልጉ ኖሮ ለአዳም ብዙ ሔዋኖችን በፈጠረለት ነበር፡፡ ሕልቃና ሁለት ሚስት እንዲያገባ ያደረገው በሕይወቱ ከነበረበት አለመርካት የተነሣ ነው፡፡ ሁለት ሚስትም ሆኑ ልጆች የእርካታ መልስ መሆን አይችሉም፡፡ እንኳን ሁለት ሚስት የዓለም ቆንጆ የሆኑትን ሺህ ሚስቶች ያገባው ንጉሥ ሰሎሞንም ይህ ሁሉ ከንቱ ድካምም መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለእርካታ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው እንጣበቃለን፡፡ መርካት ግን በክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያረካ ነገርን አይሰጠንም፤ ራሱን  እርካታን ይሰጠናል፡፡ እኛ የሚያረካ ሀብት፣ ሚስትና ልጆች እንፈልጋለን፡፡ እርካታ ግን ክርስቶስን በማግኘት ብቻ የሚታገሥ የሕይወት ጥማት ነው፡፡ የትዳር ዓላማው እግዚአብሔርን መተካትና መወከል አይደለም፡፡ ትዳር ያለ እግዚአብሔር የማይዘልቅ ነው እንጂ እግዚአብሔርን የሚተካ በፍጹም አይደለም፡፡
ብዙ ጊዜ በትዳር ውስጥ ያሉ ሰዎች ያለባቸውን የመንፈስ ጭንቀት ማንም አይረዳላቸውም፡፡ ሰው በትዳርና በልጆች መካከል የመጣል ስሜት ይኖረዋል ተብሎም ማንም አይገምትም፡፡ ባልም የሚስቱን፣ ሚስትም የባሏን ጭንቀት ላትረዳ ትችላለች፡፡ የጭንቀት አንዱ መንስኤ በጣም የጠበቅነውን ነገር በጠበቅነው መጠን ማግኘት አለመቻል ነው፡፡ ሰዎችም ከልጅነታቸው ጀምሮ ወላጆቻቸውም ከሚነግሯቸው ነገር በመነሣት ትዳርን የእርካታ ጥግ አድርገው ይስሉታል፡፡ ከገቡ በኋላ ግን የጠበቁትን ማግኘት ሲያቅታቸው መጨነቅ ይጀምራሉ፡፡ ችግሩ ያለው ከሴቷ ወይም ከወንዱ አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው ከግምታችን ነው፡፡ ከክርስቶስ የሚገኘውን ነገር ከሰዎችና ከሁኔታዎች መጠበቅ ወደ መንፈሳዊ ዝለት ያደርሳል፡፡ የሰው ልጆች ትልቁ ችግር ነገሮችን በልካቸው ማየት አለመቻል ነው፡፡ ይህ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ ጎጂ ነው፡፡ ሕልቃና ሕይወቱ የግልግል እንደሆነበት ቀጥሎ እናያለን፡፡ ሁለቱ ሚስቶቹ እርስ በርስ ሲጣሉ እርሱ ቆሞ የሚኖር ሆነ፡፡ ፍናና የልጆቹ እናት በመሆኗ ሊለያት አይፈልግም፡፡ ሐናም የሚወዳት ሚስቱ በመሆኗ ሊያጣትና ስትከፋ ሊያያት አይፈልግም፡፡ ሕልቃና እንዳሰበው አልረካም፡፡ የሳሎን ፖሊስ ሆነ እንጂ፡፡
ሕልቃና ከቃሉ ውጭ ሁለት ሚስቶች ያገባ ቢሆንም በየዓመቱ ግን ለእግዚአብሔር ለመስገድ ወደ ቤተ መቅደስ ይወጣ ነበረ፡፡ አንዲት ወጣት በአንድ ወቅት፡- “እግዚአብሔርን የምፈልግ ባለጌ ልጁ ነኝ” አለችኝ፡፡ አንድ አባት ጨዋና ባለጌ ልጆች አሉት፡፡ ሁለቱም ግን ልጆች ናቸው፡፡ ይህች እህትም በጥልቅ ስሜት እያለች ያለችው፡- እርሱ ያልካደኝ ግን የማላስደስተው ልጁ ነኝ፤ የእግዚአብሔር ያልሆንኩ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቷ ነው፡፡ ሕልቃናም በየዓመቱ ለመስገድ ይወጣ ነበር፡፡ ሌላም እህት በአንድ ወቅት፡- “እግዚአብሔርን የማላውቅ የእግዚአብሔር ሰው ነኝ” በማለት በዕንባ ነግራኛለች፡፡ ሕልቃና ኑሮው ጥሩ ባይሆንም እግዚአብሔርን ግን ይፈልግ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ ሲወጣም የሊቀ ካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ፡፡ እነዚህ ካህናት ለእግዚአብሔር ሕዝብ መዋረድ፣ ለታቦቱም መማረክ ምክንያት የሆኑ ዓመፀኛ አገልጋዮች ነበሩ (1ሳሙ.4 )፡፡
“ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋም ሁሉ ዕድል ፈንታቸውን ሰጣቸው ሐናንም ይወድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት እግዚአብሔር ግን ማኅፀኗን ዘግቶ ነበር” (1ሳሙ. 1÷4-5)፡፡ ሕልቃና የሐናን ስሜት የሚጠብቅ ባል ነበረ፡፡ ብዙ ባለ ትዳሮች አብረዋቸው ለሚኖሩ የምግብ ፍላጎታቸውን ይጠብቃሉ፣ ስሜታቸውን ግን አይጠብቁላቸውም፡፡ ስሜቱን የሰበርነውን ሰው በመረቅ በቅባት እንደማንጠግነው ማን በነገረን! ፍናና የልጆች እናት ነበረች፣ ሐና ግን መሐን ነበረች፡፡ የልጆች እናት መሆን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ የጥረት ሽልማት አይደሉም፡፡ ያልወለዱም የቅድስና ችግር ያለባቸው አይደሉም፡፡ እንደውም ቅዱሳን እንደ ነበሩ ከሣራ፣ ከርብቃ፣ ከራሔል፣ ከሐና፣ ከኤልሳቤጥ መረዳት እንችላለን፡፡ ልጆች መኩሪያ ሳይሆኑ አደራዎቻችን ናቸው፡፡ ከተለወጡ እኛን ብቻ ሳይሆን አገራቸውንም ያስደስታሉ፡፡ ካልተለወጡ ግን የእኛ ብቻ ሳይሆን የምድር ዕዳ ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔር ልጅን ይሰጣል እንጂ ሴት ልጅን አትሠራም፡፡ ልጅን ከሴት መጠበቅ ኃጢአት ነው፡፡ ልጅ እግዚአብሔር ከሰጠን ብቻ የምንቀበለው ነው፡፡ ሲከለክለንም ተመስገን ማለት ይገባል፡፡ መውለድ ብቻ ሳይሆን አለመውለድም መባረክ ነው፡፡ “አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ ዘምሪ” (ኢሳ. 54÷1)፡፡ “መካኖች ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ. 23÷28) ይላል፡፡ ባልተወለደ ይሻላል እንደ ተባለለት እንደ ይሁዳ ያለም ይወለዳልና እግዚአብሔር ሲከለክለን በምስጋና እንረፍ፡፡
የሐና መውጊያ
“እግዚአብሔር ማኅፀኗን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋም ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር …” (1ሳሙ. 1÷6 -7)፡፡
ሃና የምትወደው ባሏ ያመጣባት ጣውንት መውጊያዋ ነበረች፡፡ የባሏ ወዳጅ ለእርሷ ጠላቷ ነበረች፡፡ የምንወዳቸው ሰዎች አጠገብ የሚያደሙ ሰዎች አሉ፡፡ ጽጌረዳ አጠገብ እሾህ እንዳለ ሁሉ፡፡ ሐና ርቃ መራቅ የማትችለው መውጊያዋ ነበረች፡፡ መውጊያ ትክክለኛ ትርጉሙ ልንሸሸው የማንችለው፣ በአካላችን ወይም በአጠገባችን ያለ የማይመች ነገር ነው፡፡
ሐና የልጅ ረሀብ የሚያዳፋት ሴት አልነበረችም፡፡ እንደ ፈቃዱ ብላ የምትኖር ደስተኛ ሴት ናት፡፡ ደስታዋ ግን ለብዙዎች ያማቸው ነበር፡፡ እነርሱ ጨብጠው ያላገኙትን ደስታ ሐና በጉድለት ውስጥ በመያዟ ምን ብለን እናስለቅሳት ይሉ ነበር፡፡ ፍናናዎች ዘመን ሳይገድባቸው ዛሬም አሉ፡፡ እንበልጣችኋለን እያሉ ግን በመብለጣቸው ሊረጋጉ ያልቻሉ በምንወዳት ቤተ ክርስቲያን፣ በምንወዳቸው ሰዎች አጠገብ የተቀመጡ ፍናናዎች ዛሬም አሉ፡፡ የሐና የደስታዋ ምንጭ ሊሰጥ ሲችል የከለከላት አዋቂው እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሷም በጸሎቷ፡- “እግዚአብሔር አዋቂ ነውና” ብላለች (1ሳሙ. 2÷3)፡፡ ሐና አለመውለዷን ተቀብላ የምትኖር ሴት እንጂ ልጅ የለኝምና ሕይወት ለእኔ ምንድነው የምትል ሰነፍ ሴት አልነበረችም፡፡ ለዚህም ማስረጃችን በመጀመሪያ ስለ ልጅ ያሰበችው ስለ ልጅ ማጣቷ ሲሰድቧት ነው፡፡ ሁለተኛ ልጅ ብታገኝ እንኳ ለእግዚአብሔር ለመስጠት እንጂ ለኮሩባት ለማሳየት አልናፈቀችም፡፡
ፍናና የልጆች እናት የሆነችው በጥረቷ መስሏታል፡፡ እግዚአብሔር ከልክሎ የሚነሣ፣ አሳይቶም  የሚወስድ መሆኑን ዘንግታለች፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ይዤዋለሁ ተብሎ በኩራት የሚያናገር ምንም ነገር የለም (1ሳሙ. 2÷3)፡፡ ፍናና ሐናን ታበሳጫት ነበር፡፡ የሐናን ማኅፀን የዘጋ ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር የዘጋውን ፍጡር መክፈት አይችልም፡፡ ጉድለትን ከተቀበሉት በራሱ ሙላት ነው፡፡ ሐና ተቀብላው የምትኖረውን ጉድለት እየቆሰቆሰች ጣውንትዋ ታስጨንቃት ነበር፡፡ ለብዙ ዓመታት ይህን አድርጋለች፡፡ ሰዎችን በተፈጥሮ ጉድለታቸው ስንተቻቸው በፈጠራቸው አምላክ ላይ ጠላት እንዲሆኑ እያነሣሣናቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሐናም በየዓመቱ የሚደርስባት ነገር ከበዳት፡፡ ያውም ለአምልኮ ወጥታ በመቅደሱ ፊት ለፊት ጉድለቷ የስድብ ርእስ ሲሆንባት ተከፋች፡፡ ዛሬም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንዲሁ የሚወጋጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓሉ ዓመታዊ የደስታ በዓል ቢሆንም ያ ቀን ለሐና የጾምና የሀዘን ቀን ነበረ፡፡ ሕልቃና ሊያጽናናት ሞከረ፡፡ ከዐሥር ልጅ እኔ እሻልሻለሁ አላት፡፡ ሐና የምትወዳቸውን ልጆች ስታሰብ የሚወዳትን ባሏን ማየት አልቻለችም፡፡ ገና ስለሚመጡ ልጆች ስታዝን የጨበጠችውን ወዳጅ እየገፋች ነው፡፡ በእውነት ከጐደላት ያላት ይበልጣል፡፡ ልጅ የትዳር በረከት እንጂ የትዳር መሠረት አይደለም፡፡ ልጅ የሁለቱ ፍቅር ውጤት እንጂ የፍቅራቸው ምክንያት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ተደፍረውም ሲወልዱ እናያለን፡፡ የጋብቻ ቀለበት የሁለቱ መተማመን እንጂ የልጅ መንጋጋት አይደለም፡፡ ሰይጣን ግን የሰውን አፍ ተከራይቶ ጉድለታችንን ሊነግረን ይፈልጋል፡፡ በእውነት ከሚደረግልን የተደረገልን  ትልቅ ነው!
ሐና ግን ዛሬ ቁርጥ ልመናዋን በእግዚአብሔር ፊት ሳላቀርብ እህል አልቀምስም ብላ ተነሣች፡፡ በጽኑ ልቅሶ፣ በብርቱ ጩኸት፡- “አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ÷ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ÷ እኔንም ባትረሳ÷ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ÷ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እስጠዋለሁ÷ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች” (1ሳሙ. 1÷11)፡፡ ሐና ተቀብላ ከእግዚአብሔር ፊት ለመኮብለል የምታስብ ሴት አይደለችም፡፡ የሰጣትንም ይዛ ለመመካት የምትሞክር አይደለችም፡፡ የሰጣትን ለሰጣት ጌታ ለመስጠት የምታስብ ናት፡፡ የሰጠንን ለመስጠት የተቸገርን እግዚአብሔር ያስበን! ሐና በእኔ አለመውለድ እኔ ብቻ ሳልሆን ልጅ ከልካዩ አንተም ተነቅፈሃል መቻልህን በእኔ በደካማዋ ላይ ግለጥና ምስጋናውን ለራስህ ውሰድ፡፡ እኔም የሰጠኸኝን ሳይሆን ሰጪውን ይዤ እኖራለሁ፡፡ የሰጠኸኝን ለአንተው እሰጣለሁ ማለቷ ነው፡፡ ታላላቅ ሥራዎችን እግዚአብሔር በእኛ ላይ እንዲሠራ እንመኛለን፡፡ የምንመኝበት ዓላማ ግን ለመከበር ወይም የናቁንን ሰዎች ለማበሳጨት ነው፡፡ ነገር ግን ክብሩ ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን፡፡
ሐና በእግዚአብሔር ፊት ብዙ ሰዓት እያለቀሰች ስትጸልይ ካህኑ ዔሊ የሰከረች መስሎት ስካሩ እስከ መቼ አይለቅሽም? አላት፡፡ ሰዎች በእኛ ላይ የሚናገሩት አብዛኛው በግምት ነው፤ የሚያሳዝነው በገዛ ግምታቸው ማልቀሳቸው ነው፡፡ ካህኑም አለመስከሯን ካረጋገጠ በኋላ እንደ ዘበት መረቃት፡፡ እግዚአብሔር ግን የዘበት ምርቃቱንም እውነት አደረገው፡፡ ሰዎች እንደ ዘበት ይመርቁናል፡፡ እስቲ ያድርግልሽ፣ አምነዋለሁ የምትዪው እስቲ ይድረስልሽ በማለት ከፊታቸው ዞር እንድንል የማባረሪያ ምርቃት ይሰጡናል፡፡ እግዚአብሔር ግን የእውነት ያደርገዋል፡፡
ቃሉም፡- “ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች፤ በላችም ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም” ይላል (1ሳሙ. 1÷18)፡፡ ማልቀስ ማዘን ለእግዚአብሔር እስኪነግሩ ነው፤ ለእርሱ ከነገርን በኋላ ዋስትና አለን፡፡ እግዚአብሔር የሰማው ችግር በቁጥጥር ሥር የዋለ ችግር ነው፡፡ ሐናም እግዚአብሔር የዘጋውን ከፍቶ ልጅ ሰጣት፡፡ ዘግይታ የወለደችው ግን የአገር መፍትሔ የነበረውን ሳሙኤል ነቢይን ነበር፡፡ በችኰላ ያልበሰለ በረከት ከመቀበልና ከመታመም ጠብቆ የበሰለ በረከትን መቀበል መልካም ነው፡፡ ሐናም ጡት እስኪተው ድረስ ያን ልጅ አሳደገችው፡፡ የእኔ አይሆንም ብላ ወስዳ አልጣለችውም፡፡ የእግዚአብሔር የወደፊት አገልጋይ ነውና ተንከባከበችው፡፡ የወደፊቱን የመቅደስ አገልጋዮች መንከባከብ እንዴት መልካም ነው! አገልጋዮችን መንከባከብ ዋጋው ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ነው፡፡ በተዘዋዋሪም አገልግሎቱን መንከባከብ ነው፡፡ ሳሙኤል ትልቅ ነቢይ፣ ትልቅ መስፍን፣ ለእስራኤል ነገሥታት እንዲሆኑ ሳኦልንና ዳዊትን ቀብቶ ያነገሠ፣ ሰው በጠፋ ቀንም ሰው ሆኖ የተገኘ ነው፡፡ የመጠበቅ ዋጋው ይህ ነው፡፡
ወገኖቼ! እግዚአብሔር ይሰማል፡፡ ቁርጥ ልመናን ያደምጣል፡፡ ለእኛ ብቻ የሚበቃ ሳይሆን ለአገር የሚተርፍ መልስን ይሰጠናል፡፡ ዛሬ የምትፈልጉትን ጉድለታችሁን፣ መሰደቢያችሁ የሆነውን ሸለቆአችሁን በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ንገሩ፡፡ የጸለያችሁትን መዝግቡት፡፡ እግዚአብሔር በመልሱ ያሳርፋችኋል፡፡ በጠላቶቻችሁ ፊት ለፊትም በዘይቱ ይቀባችኋል፡፡ እግዚአብሔር ይሰማል!   

ያጋሩ