የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከሁሉ በፊት

“እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ ።” /1ጢሞ. 2፡1-2 ።/
እግዚአብሔር በመኳንንት የሚፈርድ አምላክ ነው ። መኳንንት የሕዝብ ፈራጆች ናቸው ። እግዚአብሔር በሚፈርዱት ላይ የሚፈርድ የመኳንንት አለቃ ነው ። ነገሥታት ከበላያቸው ያለው ሕዝብ ሳይሆን እግዚአብሔር ነው ። ስለዚህ በቅን ሊያስተዳድሩ ፣ በርትዕ ሊፈርዱ ይገባቸዋል ። ይልቁንም ሥልጣን ኮንትራትና ኪራይ በሆነበት በዛሬው ዘመን አጭር ዘመናቸውን በክብር ሊፈጽሙት ይገባል ። ኮንትራት በመሆኑ የሚያልቅ ነው ፤ ኪራይ በመሆኑ አከራዩ ጌታ እንደ ፈቀደ የሚያረዝመው ነው ። ነገሥታት በአጭር የሥልጣን ዘመን ዘላለማዊ ታሪክን ወይ በደግ አሊያም በክፉ ይጽፋሉ ። ብዙ ሰው ለአንድ ቀን ምነው ሥልጣን በኖረኝ ይላል ። ለሥልጣን አንድ ቀንም ብዙ መሆኑን የሚያሳይ ነው ። ለንጉሥ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ትረዝማለች ፤ የሺህ ዓመት ልማትና ጥፋትም በአንድ ቀን ይፈጽማልና አንድ ቀን በሥልጣኑ ፊት እንደ ሺህ ዓመት ነች ። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጃፓን በሂሮሽማ ከተማ ላይ የተጣለው የአቶሚክ ቦምብ እ.አ.አ ነሐሴ 6 ቀን 1945 8፡15 ደቂቃ ላይ የወደቀ ሲሆን በዚህ ቅጽበት ከተማይቱ ወድማለች ፤ 70 ሺህ ሕዝብም ሞቷል ። የአቶሚክ ቦምቡ ባደረሰው የጨረር አደጋ ቀስ በቀስ 70 ሺህ ሰዎች አልቀዋል ። ይህ የነገሥታት የአንድ ቀን ውሳኔ የወለደው ነው ። የሥልጣን ዘመን አጭር ቢሆን እንኳ የሺህ ዓመት ቅራኔን ለመፍታት ይረዳል ፤ የሺህ ዓመት ጠባሳን ለማስቀመጥም አቅም ይሆናል ።

ንጉሥ ዳዊት፡- “ለንጉሥ ከቀን ላይ ቀን ትጨምራለህ” ይላል ። /መዝ. 60፡6 ።/ ይህን የሚናገረው በመገለጥ ብቻ ሳይሆን በንግሥናው ውስጥ በማለፍም ነው ። ንጉሥ ሁሉን ቢያዝም ለራሱ ግን አንድ ቀን መጨመር አይችልም ።በንግሥናው አንድ ቀን በዚህ ዓለም ላይ መቆየት ወይም ወደ ኋላ መቅረት አይችልም ። እግዚአብሔር ሁሉንም በሞት እኩል አድርጎታል ። ስላለህ አትኖርም ስላጣህ አትሞትም የሚባለው ለዚህ ነው ። ንጉሥ በአንድ ቀን ውስጥ ብዙ ጥያቄዎችንና ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ የሚውል ነውና አንድ ቀን ለንጉሥ ብዙ ናት ። በየቀኑ የዕድሜ ኮንትራት የሚታደስልን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ።  በዕድሜ ምጽዋት እኛና ንጉሡ አንድ ነን ።
 
በብሉይ ኪዳን ከሚቀርቡት አምስት መሥዋዕቶች አንዱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው ። የኃጢአት መሥዋዕት የሚያቀርቡት ሰዎች ማንነትና የመሥዋዕቱ መጠን ተገልጦአል ። ዘሌዋ. 4 ይህን ይገልጻል ። አቅራቢዎቹ አራት ሲሆኑ፡- ካህኑ ፣ ማኅበሩ/ምእመናን/ ፣ መኰንኑና ዜጋው ናቸው ። ካህኑ የሚያቀርበው መሥዋዕት ወይፈን ነው ። ማኅበሩም ወይፈን ያቀርባል ። መኰንኑ ተባት ፍየል ያቀርባል ። ዜጋውም እንስት ፍየል ያቀርባል ። የወይፈን ዋጋ የዛሬው ዘመን ግርድፍ ግምት ብንሰጥ 10 ሺህ ብር ይሆናል ። ተባት ፍየል ሦስት ሺህ ብር ሲሆን እንስት ፍየል ሁለት ሺህ ብር ይሆናል ። የካህኑና የምእመኑ የኃጢአት መሥዋዕት አንድ ዓይነት ነው ። ምእመናን በካህናት ኃጢአት ሊጽናኑ ቢችሉም ሁለቱም የሚያቀርቡት ግን አንድ ዓይነት ዋጋ ነው ። ካህኑና ምእመኑ በአማኝነት አንድ ናቸውና ። የሚለያዩት በሥራ ድርሻ ነው ። ካህኑም ምእመኑም ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት በአማኝነት ነው ። የመኰንኑና የዜጋው መሥዋዕት ግን ቀለል ያለ ዋጋ ያለው ነው ። ቢሆንም ከዜጋው መኰንኑ የበለጠ ተጠያቂ ነው ። ከአገር መሪዎችና ከዜጎች በላይም ካህናትና ምእመናን ተጠያቂ ናቸው ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ወይም ምእመናን ስለ ነገሥታት ያለባቸውን ግዴታ እየተናገረ ነው ። “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ ።” 1ጢሞ. 2፡1-2
አንድ ክርስቲያን እንዴት መኖር አለበት ከተባለ እግዚአብሔርን በመምሰል ፣ በጭምትነት ፣ ጸጥና ዝግ ብሎ ነው ። ይህ እንዲሳካ ግን ለሰዎች ሁሉ ለነገሥታትና ለመኳንንት ልመና ፣ ጸሎት ፣ ምልጃም ፣ ምስጋናም ሊደረጉ ይገባል ።
እግዚአብሔርን መምሰል ከእግዚአብሔር የተወለዱ ሰዎች የሚያሳዩት መልክ ነው ። ሰው አስቀድሞ ሲፈጠር በአርአያ ሥላሴ ስለ ተፈጠረ የእግዚአብሔር የመልኩ ነጸብራቅ ነው ። ሰው ትንሹ ቅዱስ ፣ ትንሹ ጌታ ነው ። መስተዋት ንጹሕ ሲሆን ብቻ ብርሃን ያስተላልፋል ። እንዲሁም ንጹሕ ልብ ስንይዝ የእግዚአብሔርን መልክ ለዓለም እንገልጣለን ። ሰው የተፈጠረው እግዜር በምድር ተብሎ ሕይወቱ እንዲወደስ ነው ። የእግዚአብሔር መልክ ፍቅር ፣ ርኅራኄ ፣ ይቅር ባይነትና ምሕረት ነው ። ይህን እንዳንገልጥ ግን ብዙ ክፉ ሰዎችና ክፉ ነገሥታት እንቅፋት ሊሆኑብን ስለሚችሉ ለሰዎች ሁሉና ይልቁንም ለነገሥታት መጸለይ ይገባል ።
ጭምትነት የምእመናን መልክ ነው ። ጭምትነት የእግዚአብሔርን ክብር የዓለምን ከንቱነት ከመረዳት ይመነጫል ። ሲያዩት ደስ የሚያሰኝ ምእመን ጭምት የሆነ ነው ። ጭምት እግዚአብሔርን ተሸክሞ የሚዞር መሆኑ ይታወቃል ። ጭምት ለመሆንም ግን በዙሪያችን ያሉ ሰዎችና በበላያችን ያሉ ሹሞች ወሳኝ ናቸው ። በክፉ ሰዎች ተሳዳቢ የሚሆኑ ፣ በክፉ ነገሥታት ጫካ የሚገቡ አማኞች ጥቂት አይደሉም ። ስለዚህ ጭምት ሁኖ ለመኖር ስለ ሁሉ መጸለይ ይገባል ።
ጸጥታ ክርስቲያኖች የሚታወቁት ነው ።      ጸጥታ ድምፅ አለው ። ጸጥታ ይናገራል ። የሚናገሩ ሰዎች ጸጥታ ላይኖራቸው ይችላል ። ጸጥ ያሉ ሰዎች ግን እየተናገሩ ነው ። ጸጥታ የክርስቶስ ሰላም ምልክት ነው ። የሚጮኽ ውስጡ የሚጮኽበት ነው ። ጸጥ ለማለት ግን ዙሪያው ሰላም መሆን አለበት ። ስንቱ ጸጥተኛ እየጮኸ እንደሆነ እያየነው ነው ። ለዚህ መድኃኒቱ  ጸሎት ነው ።
ዝግታ የክርስቲያን መልክ ነው ። ክርስቲያንነት መታወቂያው ጠባይ እንጂ የአባልነት ደብተር አይደለም ። ቀደም ቀደም ማለት አደጋ አለው ። ችኮላ ረግጦ ሲያይ ፣ ዝግታ ግን አይቶ ይረግጣል ። በዝግታ ለመራመድም ሆነ ለመኖር ዙሪያውና መንግሥቱ ሰላም መሆን አለበት ። ለዚህም መጸለይ ግድ ይላል ።
ልብ አድርጉ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ የነበረው ንጉሥ ኔሮ ቄሣር ነው ። ሐዋርያውን አስሮ ከለቀቀው በኋላ ቀጥሎ ይገድለዋል ። ሐዋርያው ጸልዩ የሚለው ለዚህ ንጉሥ ነው ።
ከሁሉ በፊት ለነገሥታት ለሚመሩን ፣ ለመኳንንት ለሚያስተዳድሩን መጸለይ ይገባል ። እኛ በጸሎት ካልጋረድናቸው የሰይጣን ፍላጻ ያገኛቸዋል ። የሚያጠፉትም በአቅማቸው መጠን ነው ። ድንጋይ የያዘ ያንን ሲወረውር ኒውክለር የጨበጠም ያንኑ ይወረውራል ። ጥፋት እንደ አቅም ነው ። የነገሥታት ሰላም መሆን የሕዝብ ሰላም ነው ።
ለሰው ሁሉና ለነገሥታት የሚደረገው፡- ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም” ነው ። ልመና እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ነው ። ጸሎት እኛን ሲያዩ ሰላም እንዲሰማቸው ነው ። ምልጃ ከክፉ ሁሉ እንዲጠብቃቸው ነው ። ምስጋና ሰዎችንና ነገሥታትን የሰጠን እግዚአብሔር መሆኑን አውቀን በደስታ እንድናወድስ ነው ። ሰዎችና ነገሥታት በረከቶቻችን እንዲሆኑ ጸሎት ፣ ልመና ፣ ምልጃ ፣ ምስጋና ሊኖር ይገባል ።
እግዚአብሔር በብዙ በረከት ይባርካችሁ !
1ጢሞቴዎስ /23/
ታኅሣሥ 15 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ