የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከልክ ማነስና ከልክ ማለፍ

አንድ ታሪክ ሲተረክ እንሰማለን፡- ጌታ ለዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንድ ትእዛዝ ሰጠ ፡- “ሁላችሁም አንድ ድንጋይ አንሡ” አላቸው ። ሁሉም በእጃቸው ሙሉ ፣ በአቅማቸው ድንጋይ አነሡ ። ይሁዳ ግን ትንሽ ጠጠር አነሣ ። ጌታም፡- “ዳቦ ይሁንላችሁ” ብሎ ሲናገር ዐሥራ አንዱ ጠግበው በሉ ፣ ይሁዳም አንድ ጉርሻ አገኘ ። ከዕለታት በአንዱ ቀንም ጌታችን ትእዛዝ ሰጠ ፡- “ሁላችሁም ጠጠር አንሡ” ሲል ይሁዳ ካለፈው ተምሬአለሁ በሚል ስሜት ቶሎ ብሎ ትልቅ ድንጋይ አነሣ ። ደቀ መዛሙርቱ ግን በልካቸው አነሡ ። ጌታም ወርውሩት አላቸው ። ደቀ መዛሙርቱ አርቀው ወረወሩ ። ይሁዳ ግን የያዘው ትልቅ ድንጋይ ነውና አርቆ መወርወር አልቻለም ። ጌታም፡- “ዕድሜአችሁ እንደዚህ ይርዘም” ብሎ መረቃቸው ይባላል ።
ይሁዳነት ምንድነው ? ይሁዳ ስሙ እንጂ ግብሩ ያልተጠላ ሰው ነው ። ይሁዳ ደቀ መዝሙር ነበረ ፣ ይሁዳ ሐዋርያ ነበረ ተብሎ የሚነገርለት በነበር የቀረ ሰው ነው ። ይሁዳነት ጀምሮ አለመጨረስ ነው ። ጀምሮ አለመጨረስ ብዙ ምክንያቶች አሉት ። ስልቹነት የመጀመሪያው ነው ። ሁለተኛው የፈተናዎች መደራረብ ነው ። ሦስተኛው የገንዘብ ፍቅር ነው ። ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር የጀመረውን መጨረስ አልቻለም ። ገንዘብ መርዝና ክፉ ሥር የተባለው ከደቀ መዝሙርነት ጥሪ የሚያስቀርና ጌታን የሚያሸጥ መሆኑ ስለ ታየ ነው ። ሰው አንደበቱንና የገንዘብ አመለካከቱን መንፈሳዊ ካደረገ ሌሎች ፈተናዎች ከባድ አይደሉም ።
ይሁዳነት ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ መሠረት መልካምነት ለራስ መሆኑን አለመገንዘብ ነው ። ይሁዳ ሁሉም በልኩ ሲያነሣ እርሱ ግን ትንሽ ጠጠር አነሣ ። ጥጋቡ ግን ባነሣው መጠን ሆነ ። መልካምነት ለእግዚአብሔር ጥቅም  ወይም ለሰዎች የሚደረግ አይደለም ። መልካምነት ለራስ ነው ። ይሁዳ ከመጠኑ አንሶ አነሣ ። በልካችን ያህል መገኘት የበረከት ምሥጢር ነው ። በልጅነታችን የምናነሣውን መጠን ዘንድሮም ማንሣት አለብኝ ማለት ተገቢ አይደለም ። ባለማወቃችን ዘመን እንደ ኖርነው ዛሬ ተምረን መኖር የለብንም። በመማርና ባለመማር መካከል ልዩነት ማሳየት አለብን ። ድሮ ትንሽ በነበረን ጊዜ የምንመጸውተውን አምስት ሣንቲም ዛሬ ብዙ ገንዘብ አግኝተን መድገም አይገባንም ። በተሰጠን ልክ መኖር አለብን ። ብዙ የታወቁ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ድሮ በሚኖሩበት የገንዘብ መጠን አሁን እየኖሩ የቀረውን ግን ለድሆች ይሰጡ እንደነበር ታሪካቸው ተጽፎአል ። በልካችን ማንሣት ተገቢ ነው ። ድሮ በትንሹ የምንከፋ ከሆንን አሁን ግን ልበ ሰፊ መሆን አለብን ። በእውቀታችን መጠን ይቅርታችንም ማደግ አለበት። በዚህ ዓለም ላይ ለሰዎች ያለማቋረጥ የምንሰጠው ነገር ቢኖር ለድሆች ምጽዋት ፣ ለበደሉን ደግሞ ይቅርታ ነው ። መስጠት ለራስ ነው ። ሁሉ ገንዘባችንን አይፈልግ ይሆናል ፣ ይቅር የማንለው ሰው ግን የለም ።
በልካችን አለማንሣት ረጅም ርቀት እንዳንወረውር ያደርገናል ። የምንፈልገውና የሚያስፈልገንን በውል ማወቅ ያቃተን ዘመን ላይ ነን ። የምንጨነቀው በትክክለኛ ነገር ላይ አይደለም ። ከአቅማችን በላይ ባነሣናቸው ድንጋዮች ነው ። ድሮ አሳንሰን ብናነሣ የምንበላው ነው የቀነሰው ። አሁን አብዝተን ስናነሣ ግን ዕድሜአችን እያጠረ ይመጣል ። ድህነት አልፎ እንኳ መሄዱን ማመን ያቃታቸው ሰዎች ስግብግብ ሁነዋል ። ቊጥር መቆሚያ የለውምና በቃ ካላልነው አያበቃም ። ኑሮአችን ለሕይወታችን ዋጋ መክፈል ሲገባው ሕይወታችን ለኑሮአችን ዋጋ አየከፈለ ከሆነ ያሳዝናል ። መቼ ነው የሰጠንን ነገር እየቆጠርን የምናመሰግነው ? መቼ ነው ከቤተሰባችን ጋር ንጹሕ ጊዜ የምናሳልፈው ? መቼ ነው በሕይወታችን መልካም የዋሉልንን ሰዎች የምናመሰግነው ?
በርግጥም ይሁዳ ለጌታ ውድ ሽቱ ሲነሰነስለት ትንሹን ድንጋይ አነሣ ። ይህ ሁሉ ማባከን ነው አለ ። ሌላው ላደረገው መልካምነት እርሱ ደከመው ። በፈተና በሚጸናባት በዚያች ሌሊት ትልቅ ድንጋይ አነሣ ። ፍቅረ ንዋይ ግን ዕድሜውን አሳጠረው ። ይሁዳ ለማይበላው ገንዘብ ጌታውን ለወጠ ። አዎ ከልክ አለማነስ በረከት ነው ። ከልክ አለማለፍ ዕድሜን የሚቀጥል ነው ።
ይሁዳ በሚባረክበት ምሽት ተረገመ ። በተማረው ልክ ሳይሆን ትንሽ አነሣ ። ደቀ መዛሙርቱ ግን ጸንተው ጌታን ባያከብሩት እንኳ ንስሐ ገብተው ምሕረቱን አከበሩት ። ይሁዳ ትልቅ ድንጋይ ፣ ከዳተኝነትና ፍቅረ ንዋይን ይዞ የተጠራበት ቦታ ላይ ተቀበረ ። ሐዋርያት ግን ረጅም ዘመንና ሩቅ አገር አገልግለው ጌታቸውን አከበሩ ። ተራራ የሚወጡ መኪናዎችን አስቡ ። ተጎታች ያላቸው ያጣጥራሉ ፣ ተጎታች የሌለው ግን ቶሎ ይወጣዋል ። መንፈሳዊ ሕይወትም ትጥቁ አጠር ላለው ቀላል ሲሆን ከነተጎታቼ ለሚል ግን ከባድ ነው ።
ልዑል እግዚአብሔር በኃያል ክንዱ ይደግፋችሁ ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሚያዝያ 19/2010 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ