የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከስድስቱ ቀን ጦርነት ምን እንማራለን ?

“ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ አንተንም ለሚወድዱ ልማት ይሁን።” (መዝ. 120፡6 ።)

እስራኤላውያን በሮማውያን ደምሳሽነት መቅደሳቸውና ከተማቸው ፈረሰ ። ከግድያ የተረፉት በመላው ዓለም ተበተኑ ። ከ70 ዓ.ም. እስከ 1940 ዓ.ም. ለ1940 ዓመታት በመላው ዓለም እንደ ጨው ዘር ተበተኑ ። ስማቸው ተደመሰሰ ፣ እስራኤል የሚለው ከአገር ባሕር መዝገብ ተፋቀ ። ከዚህ በኋላ እስራኤል የሚባል ወገንና አገር አይኖርም ተብሎ ተስፋ ተቆረጠ ። እ.አ.አ ከ1935-1945 የነበረው የሆሎኮስት ጭፍጨፋ በሂትለር ርእዮት ፣ በናዚዎች ግብረ አበርነት ስድስት ሚሊየን የአውሮፓ አይሁዶች ተጨፈጨፉ ። ይህ ጭፍጨፋ የሰውን ዘር ታሪክ ያጠለሸ ፣ ለዓለም ጥቁር መልክ የሰጠ ፣ ፣ በፍልስፍና ፣ በብሔርተኝነት የተቃኘ ፣ አይሁድ የሚባልን ዘር ከምድር ላይ ማጽዳት አለብን ብሎ የተነሣ ነው ። ሆሎኮስት ማለት የተቃጠለ መሥዋዕት ማለት ነው ። የሥጋቸው ሞራ እየተገፈፈ ፣ አካላቸው እየጤሰ አየሩን በክሎታል ። አይሁዶች ጀርመን ላይ መኖር ከጀመሩ 1700 ዓመታት ቢሆንም እንደ ምድር ጉድፍ ፣ ዛሬ እንደ መጣ ሰይጣን ተቆጥረው በአሽዊትስ ካምፕ ውስጥ አልቀዋል ። ይህ ቀን ለጀርመናውያን የታሪክ ጥላሸት በመሆኑ ግፉ እንዳይደገም ለጀርመን ወጣቶች ለማስተማር በየዓመቱ የሆሎኮስት ቀን በማለት ታከብራለች ፣ ለእስራኤልም ካሣ ትከፍላለች ።

ከናዚዎች ጭፍጨፋ የተረፉት ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ምድራቸው ተይዞ ነበር ። በሮማውያን ፣ በቱርኮችና በመጨረሻም በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የወደቀችው ምድረ እስራኤል ተረፈ እስራኤልን ለማስጠጋት አልቻለችም ። ይህን ግፍ አገናዝቦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1947 እ.አ.አ ምድሩን ለሁለት ከፍሎ ለአይሁድና ለፍልስጤም የሰጠ ቢሆንም ቅኝ ገዥዎቹ እንግሊዛውያን ግን በዓመት ከ15 ሺህ በላይ አይሁድ ወደ ምድሩ እንዳይገባ ገደብ ጥለው ነበር ። ፍልስጤምና በዙሪያው ያሉ ዐረቦች እስራኤል እንዳትቀላቀላቸው በብርቱ ይጠብቃሉ ። የትንቢት ቀጠሮ ደረሰና እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም. ግንቦት 14 ቀን በእኛ አቆጣጠር በ1940 ዓ.ም ግንቦት 6 ቀን ነጻ መንግሥት መሆናቸውን ፣ የተባበሩት መንግሥታትን ውሳኔ ጠቅሰው ተፈጥሮአዊ የመኖር መብታቸውን አገናዝበው መንግሥት ነን አሉ ። ቀኑ የፈጠነ ቢሆንባትም አሜሪካ ቅድሚያ እውቅና በመስጠት ሌሎችም በመቀበላቸው እስራኤል መንግሥት ሆነች ። ያ ሁሉ መጠላት ፣ መገፋት ፣ የምድር ጉድፍ ተብሎ መጠራት ዘመኑ ያበቃ መሰለ ። በዓለም ላይ እንዲህ ያለ ብቸኛ ሕዝብ አልነበረም ። አባታቸው አብርሃምን ክርስትናም እስልምናም ያከብረዋል ። እነርሱ ግን በዓለም ላይ የመጨረሻውን የጥላቻ ጥግ አይተዋል ።

እስራኤል ነጻ መንግሥት ከሆነች በኋላ ለሁለት ጊዜያት ያህል ከዐረቦች ጋር ጦርነት ብታካሂድም የስድስቱ ቀን ጦርነት ግን እስካሁን ትኩስና ያልበረደ ትግል ሁኗል ። ዓለም በስድስት ቀን እንደ ተፈጠረ እስራኤልም በስድስቱ ቀን ጦርነት ተፈጠረች እስከመባል ደርሷል ። የስድስቱ ቀን ጦርነት ከሶቭየት ኅብረት የስለላ ተቋም የተገኘው “እስራኤል ሶርያን ልትወጋ ነው” ከሚል ሐሰተኛ መረጃ የመነጨ እንደሆነ ይነገራል ። ሶርያ የእስራኤል መንግሥት መሆን በብርቱ ያመማት ፣ የፍልስጤም ነጻ አውጪዎችንና የዐረብ አገራት ተዋጊዎችን የምታሰለጥን ፣ የሶቭየት ኅብረት የአካባቢው ቀኝ እጅ ተደርጋ የምትቆጠር ናት ። ይህ መረጃ እንደ ደረሳት ልወረር ነው ብላ ለመላው ዐረብ አቤት አለች ። በዚህ ጊዜ የግብጹ ገማል አብድናስር ጦራቸውን ክተት ብለው እስራኤልን እንነቅላታለን በማለት ሲና በረሃ ላይ ደረሱ ። መረጃው ስህተት መሆኑን ከሶቭየት ኅብረት ቢመጣም ፣ ጦርነት እንዳይካሄድ ቢፈለግም ገማል አብድናስር ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ በማለት እንቢ አሉ ። በዚህ ጊዜ በግብጽና በመላው ዐረብ ምድር የገማል ጀግንነት ፣ የቁርጥ ቀን ልጅነት በሰልፍ ታጅቦ ገናና ሆኖ ነበር ።

በሲናይ በረሃ ላይ የሰፈረው የግብጽ ጦር በመካከል የነበረውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ጦር በ48 ሰዓታት አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ ትእዛዝ ሰጠ ። ይህ ጦር ሁለተኛውን የግብጽ እስራኤል ጦርነት ተከትሎ በ1956 እ.አ.አ የተቀመጠ ነበር ። እስራኤልም የነጻነት በዓሏን እያከበረች ያለበት ሰሙን ነው ። ነጻ መንግሥት ከሆነች ገና 19 ዓመትዋ ነበር ። ሰኔ አምስት ቀን 1967 እ.አ.አ አቆጣጠር በእስራኤሉ የጦር መሪ ሞሼ ዳያን ቀድሞ የማጥቃት መርሕን በመከተል በማለዳ ጦርነቱ ተጀመረ ። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሌቪ ኤሽኮል በጦርነቱ አልተስማሙም ። የእርሳቸው አሳብ በዲፕሎማሲ እንጂ በጦርነት የሚገኝ ድል ዘላቂ ሰላም አያመጣም የሚል ነበር ። ነገር ግን የጀነራሎቹን ልብ ማሸነፍ አልቻሉም ። እስራኤል ከ200 የጦር ጀቶችዋ 188 የሚሆኑትን አሰማራች ። በሲና ያለውን የግብጽ የአየር ማረፊያ ደመሰሰች ። ቀጥሎ የሬድዮ መገናኛዎችን ከዚያም የጦር አውሮፕላኖችን ደመሰሰች ። በአየር ላይ ምንም የሚቃወም አካል አልነበረምና እግረኛው ፍጹም የበላይነትን ተቀዳጀ ። ገና በጠዋቱ ቁርስና ጨዋታ ላይ የነበረው የግብጽ ጦር ከአዛዦቹ ጋር እንኳ መገናኘት አልቻለም ።

ዮርዳኖስም የጦር ጀቶችዋን በመጠቀም እስራኤልን በአየር ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃች ። የእስራኤል አየር ኃይልና ጦር ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ራፋንና ቤተ ልሔምን ከዮርዳኖስ እጅ አስለቅቆ ገንዘቡ አደረገ ። አሮጌው ኢየሩሳሌምና አል-አቅሳ መስጊድም በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ገባ ። የዮርዳኖሱ ንጉሥ አል-አቅሳንና ኢየሩሳሌምን መጠበቅ የእኔ የዘርና የሃይማኖት ግዳጅ ነው ብለው ቢያምኑም ግብጽ ተነሡ ስትላቸው በመሳተፋቸው ተነጠቁ ። ከአራት ቀን ውጊያ በኋላ ሶርያ የጎላን ተራራን ምሽግ አድርጋ ሰሜን እስራኤልን መደብደብ ቀጠለች ። እስራኤልም ይህ ሰበብ አድርጋ ሶርያን ቀጠቀጠች ። በዚህም የስድስቱ ቀን ጦርነት ግብጽ 15ሺህ የሚደርስ ሠራዊት ፣ ዮርዳኖስ 6ሺህ ፣ ሶሪያ 2ሺህ ሠራዊት ሲያልቅባቸው ምርኮኛ 4ሺህ ይደርስ ነበር ። እስራኤልም 776 ሰው ተገደለባት ። 400 የሚሆኑ የዐረብ ጀቶች ሲጋዩ እስራኤል 46 አውሮፕላኖች ወድመውባታል ።

በዚህ የስድስቱ ቀን ጦርነት እስራኤል ግዛትዋን አሰፋች ። በደቡብ 300 ኪ.ሜ. በምሥራቅ 60 ኪ.ሜ. በሰሜን 20 ኪ.ሜ ያዘች ። በሌላ አነጋገር ከግብጽ የሲና በረሃንና የጋዛ ሰርጥን ፣ ከዮርዳኖስ ራፋን ፣ ምሥራቅ ኢየሩሳሌምንና ቤተ ልሔምን ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን ፣ ከሶርያ የጎላን ተራራን እስከ አሁን በእጅዋ አስገብታለች ። ገማል አብድልናስርም በሁኔታው አፍረው ሥልጣን ለቅቀዋል ። የሚገርመው የግብጽ ጦር ሲወድም በካይሮ እስራኤል ተደመሰሰች በሚል ዜና ጭፈራ ነበር ። ቴሌአቪቭ እንገናኝ የሚል ደስታ ሕዝቡ ያሰማ ነበረ ። በተቃራኒው እስራኤል ድል ብታደርግም ሕዝቡ ዝግጅቱን እንዳያቆመ የድሉ ዜና እንዳይነገር ታግዶ ነበር ። የስድስቱ ቀን ጦርነት በእስራኤል ድል አድራጊነት ቢደመደምም እስካሁን ሰላም አላመጣም ።

ከስድስቱ ቀን ጦርነት የምንማረው፡-

1- ሐሰተኛ መረጃ አገራትን ሊያፈርስ እንደሚችል
2- በጦርነት የሚገኝ ድል ዘላቂ ሰላምን እንደማያመጣ
3- ካፈርኩ አይመልሰኝ ማለት አገርን እንደሚጎዳ
4- ነገሮች ለበጎ ሆነው ግዛት ሊሰፋ እንደሚችል
5- የሰውን ፈላጊ የራሱን እንደሚያጣ
6- ሰላም ላጡ ሕዝቦች ሰላምን መለመን እንደሚያስፈልግ
7- የእስራኤልና የዐረብ ጦርነት ለመላው ዓለም ጠንቅ ይዞ እንደሚመጣ እንማራለን ።

እግዚአብሔር ሰላም ላጡ ሁሉ ሰላምን ይላክልን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ