የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከቀደምህ ልከተልህ

ከፊት የቀይ ባሕር ፣ ከኋላ የፈርዖን ሠራዊት ያስጨንቀኛል ፤ ብሄድ ገደሉ ፣ ብመለስ እሳቱ ያስፈራኛል ። ጋረድ ኢየሱስ ሆይ ከቀደምህ ልከተልህ ። የተዘጋጀልኝን ቀን ሳልዘጋጅ ተጋጥሜ መቋቋም አቅቶኛል ፤ ብችለው እንኳ “እንዴት?” የሚለው ጥያቄ አቅም ይነሣኛል ። ለመድረስ መራመድ ፣ ለማሸነፍ መዘርጋት የማያሻህ ጽኑ መለኮት ሆይ ከቀደምህ ልከተልህ !

የምኖረው ኑሮ የተማርኩትን ፣ ፈተናው ያሳየኸኝን ተአምር ያስረሳኛል ። ጎርፉ ሊጠርገኝ በሞትና በጭንገፋ ጀርባ ላይ ተጭኖ ይመጣብኛል ፤ ነፋሱ ሊነቅለኝ በወሬ ፈረስ ላይ ሁኖ ደረስሁ ይለኛል ፤ ወጀቡ ደስታዬን ሊያርቀው በከዳተኞች ላይ ሆኖ ይረብሸኛል ። በሚመስል ነገር ጠላት ያታልለኛል ፣ በማያድን ወሬ ጊዜዬን ይበላብኛል ። ላንተ ስኖር ብዙ ወጥመድ ይታየኛል ። አማኑኤል ሆይ ፣ ከቀደምህ ልከተልህ ! ለመማሬ የመጣው ለማማረር ሆነብኝ ፣ ለእምነት የሰጠኸኝ የብልጠት መሣሪያ ሆነኝ ፣ የጽድቁን ሥራ የውዳሴ ከንቱ ማትረፊያ አደረኩት ። አንተን ብቻ ስል ከራሴም ከሰውም እጣላለሁና ከቀደምህ ልከተልህ !

ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ራሴ ግን ሐቀኛ መስሎ ይሰማኛል ። ኃይለኞች የሁልጊዜ ኃይለኛ መስለው ይታዩኛል ። የተመሠረተው “ቢፈርስስ?” የሚል ስጋት አቅሌን ያስተዋል ። የተለወጡ “ቢክዱስ?” እያልሁ ፍርሃት ይንጠኛል ። አባት ልጅ ሲሆን ፣ ልጅ አባት መሆኑ መሰል ፣ ለሁሉ ማሰብ ይዳዳኛል ። ሁሉን ትቶ በእምነት መከተል ፣ መስቀልን በደስታ መሸከም ለዚህ ሥጋዬ ይከብደዋልና አዶናይ ሆይ ከቀደምህ ልከተልህ!

ባሕረ አሳብ ውስጥ ሆኜ ዋኝቼ መዝለቅ አልቻልኩም ፣ አንዱን ስህተት በሌላ ስህተት ማረም አላረካኝም ፣ ብርሃንን ጠልቶ የውሸት ወዳጅነት አቅም አልሰጠኝም ። የሆኑ ነገሮችን በሚመስሉ ነገሮች መለወጥ ዕረፍት አልሆነኝም ። እንዳስተማርከኝ እውነት ፣ እንዳሳየኸኝ ፍቅር መኖር እሻለሁና ከቀደምህ ልከተልህ ! አንተ ቃልህን የማትለውጥ ወዳጅ ፣ አንተ ሰውዬውን ሠርተህ ሥራውን የምትሠራለት ውብ ዓለም ፣ አንተ ወደ ዓለም ሁሉ የላክህ የወንጌል ባላባት ፣ ርስተ ብዙ ነህና ከቀደምህልኝ ልከተልህ ! የናፈቀህ ሁሉ አሜን ይበል ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ