የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከታላቅ ክብር በኋላ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ       
                                                                                ቅዳሜ ፣ ጥቅመት 15/ 2007 ዓ.ም.
            አገር እንዲመሩ በተቀቡ ቀን በጽኑ የታመሙ፣ በስደት የተገፉ ነገሥታትን በታሪክ እናውቃለን፡፡ ካልተቀቡበት ዘመን ይልቅ ያላጣጣሙት ንግሥና የሰሚውን ልብ ይሰብራል፡፡ የሰው ልጅ መራመድ የሚፈልገው ከከፍታ ወደ ከፍታ እንጂ ከከፍታ ወደ ዝቅታ ከዚያም ወደ ከፍታ ያለውን ጉዞ አይደለም፡፡ ሕይወት የማሳያ ሰሌዳ ቢኖራትና ብናያት ቀጥ ያለች ጉዞ ሳትሆን እጅግ ከፍታ፣ እጅግ ዝቅታን የምታፈራርቅ ማሳያ ናት፡፡ ዓለም በሁለት ነገሮች መዋቀሯን የተፈጥሮና የኑሮ ሂደት ያስተምረናል፡፡ ዓለም ብርሃንና ጨለማ፣ ሹመትና ሽረት፣ ደስታና ሀዘን፣ ተራራና ሸለቆ የሚፈራረቁባት መድረክ ናት፡፡ 
            የሰው ልጆች በጥረታቸው ወደ ከፍታ ማማ ላይ ከወጡ በኋላ የሚሠሩት ሌሎችን ለመጥቀም ሳይሆን ወንበራቸውን ለማስጠበቅ ነው፡፡ አንዴ ዝቅ ካሉ እንደገና የሚነሡ አይመስላቸውም፡፡ በእግዚአብሔር ቅብዐት ከፍ ያሉ ግን ዝቅ ቢሉም አቅም ጨምሮ ለመነሣት እንጂ ለመጥፋት አይደለም፡፡

            ከጊዜ በኋላ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች አለማየትን መልመድ እንደሚያቅት ብዙ ጊዜ ይናገራሉ፡፡ ከእነርሱ ይልቅ በልጅነታቸው ዓይናቸውን ያጡ እንደሚሻሉም ይመሰክራሉ፡፡ ብርሃንን ካዩ በኋላ ጨለማን መልመድ ይከብዳል፡፡ ታዲያ አንዳንዶች እንደገና የብርሃን ጸጋ ሲሰጣቸው ለእያንዳንዱ ሰዓት ዕይታም ቢከፍሉ ደስተኛ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በማዳኑ ይደርሳል። እንዲሁም ከሀብት ወደ ድህነት የወረዱ ሁሉን ሰው የሚቀየሙ፣ ብስጭትና ክፉ ንግግርን የተሞሉ ይሆናሉ፡፡ ከክብር ወደ ሽረት የመጡም አለምድ እያሉ ራሳቸውን በልዩ ልዩ ሱስ ይጎዳሉ፡፡ ከመንፈሳዊ ሕይወትም ወደ ዓለም የዘቀጡ አለምድ እያሉ በጭንቀት ይንገላታሉ፡፡ ብርሃን አልፎ ጨለማው እንደ መጣ፣ ጨለማው አልፎም ብርሃን ይመጣል፡፡ ሳይደክመው ይህን የሚለዋውጥ ጌታ በዙፋኑ ተቀምጧል፡፡ 
            ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነን ነቢዩ ዳዊት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ሊቃውንት እንደሚነግሩን ነቢዩ ዳዊት ከቤት ውጭ የተወለደ ዲቃላ ነበር፡፡ እርሱም ይህንን ብዙ ጊዜ ገልጧል፡-
            “እነሆ በዓመፃ ተፀነስሁ÷
            እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” (መዝ.50÷5)።
            “አባቴና እናቴ ትተውኛልና÷
            እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” (መዝ.26÷1ዐ)።
            ነቢዩ ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት ገብቶ እሴይን ልጆችህን አቅርብልኝ ሲለው ዳዊት ተረስቶ የነበረው እንደ ልጅ የማይቆጠር ዲቃላ ስለነበረ ነው፡፡ ብዙ አራዊት ባሉበት ምድረ በዳ ላይ የከብቶች እረኛ እንዲሆን በዚያ ዕድሜው የተጨከነበት የቤት ውልድ ስላልነበረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰው የጣለውን ያነሣል፤ አባትና እናት የተውትን ያሳድጋል፡፡ 




            እያንዳንዱ ሰው የሥላሴ ዕቅድ ነው፡፡ በአጋጣሚ ወይም በስህተት የተፈጠረ ማንም የለም፡፡ እያንዳንዳችን የወላጆቻችን ዕቅድ ሳይሆን የእግዚአብሔር ዕቅድ ውጤቶች ነን፡፡ ዲቃላውም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍጡር ነው፡፡ የተሳሳቱ ወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ፣ የተሳሳቱ ልጆች ግን የሉም፡፡ እግዚአብሔር ግንኙነቱ ከአስተዳደጋችን ጋር ሳይሆን ከእምነታችን ጋር ነው፡፡ ታላቁ ነቢይ ዳዊት፣ ታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን የስርቆሽ ልጆች ቢሆኑም እግዚአብሔር ታላቅ ሥራን ሠርቶባቸዋል፡፡
          
            ዳዊት እረኛ፣ ዘማሪ፣ ደራሲ፣ ነቢይ፣ ንጉሥ ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም ሲመሰክርለት፡- “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” ብሏል (ሐዋ. 3÷22)፡፡ ዳዊት መውደቅና መነሣትን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያስተናገደ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ባለመበደሉ አይደለም፡፡ በአመንዝራነት የወደቀ ወዳጁን ኦሪዮንን ያስገደለ ሰው ነው፡፡ ዳዊት ግን ልበ አምላክ የተባለው ፈጥኖ የሚጸጸት፣ ንስሐም የሚገባ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር በበደላቸው ፈጥነው በሚጸጸቱና ንስሐ በሚገቡ ሰዎች ይደሰታል፡፡ 
            ዳዊት ዲቃላ ብቻ ሳይሆን የቤቱም የመጨረሻ ልጅ ነበረ፡፡ ዲቃላ መሆንና የመጨረሻ ልጅ መሆን ሁለቱም የሚያስከፍለው ዋጋ አለው፡፡ ዲቃላ መሆን በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያሳጣል፡፡ ያች እናት ልጇን በዚህ ሁኔታ የምትወልደው ችግር ቢፀናባት፣ ብቸኝነትም አጥር የሌለው ቤት ቢያደርጋት ነው፡፡ ስለዚህ ልጇ በችግር ላይ የመጣ ችግር እንጂ በረከት ሆኖ አይታያትም፡፡ በኑሮዋ ምክንያትም ልጇን ትመረርበታለች፡፡ እየረገመች፣ ኅሊናውንም እየኮረኮመች ታሳድገዋለች፡፡ ችግሩ እያየለ ሲመጣ ያን ልጅ አባቱ እንዲወስደው ይደረጋል፡፡ አባቱም የሕግ ሚስቱን ለማሳመን ያቅተዋል፡፡ ስለዚህ ቤቱ በዚያ ልጅ ሰላም ያጣል፡፡ በዚህ ምክንያት ያ ልጅ በወንድሞቹና በእህቶቹ ዘንድ በጥሩ አይታይም፡፡  ያች የሕግ ሚስትም ባሏ ልጁን እያለ ቀልጦ እንዳይቀርባት ልጁ ይምጣ ብላ ትፈቅዳለች፡፡ ልጁንም እንደ ልጇ ለማየት እየተፈተነች የአባቱን ዕዳ ለልጁ ታሸክመዋለች፡፡ ልጁ ከልጆቿ እኩል እንዳይሆን ትበድለዋለች፡፡ ለልጅ የማይሰጠውን ኃላፊነት ታሸክመዋለች፡፡ በአባቱ ፊት እየወደደችው ለብቻው ታሰቃየዋለች፡፡ ስሟም የእንጀራ እናት ነው፡፡ ያገናኛቸው የተፈጥሮ ማሰሪያ፣ የፍቅር ኅብረት ሳይሆን እንጀራ ወይም የመኖር ጥያቄ ብቻ ነውና የእንጀራ እናት ትባላለች፡፡     
       
            ያ የውጭ ውልድ የሆነው ልጅ በጥሩ ቢያዝ እንኳ ደህና እንቅልፍ አይወስደውም፣ ሰውነቱም አይጠረቃም፡፡ ምክንያቱም እናቱ ጦሟን ስታድር ይታየዋልና፡፡ ለእናቱ እንጀራ እየሰረቀ በልብሱ ውስጥ ደብቆ የሚሄድ ወጣት አውቅ ነበር፡፡ እርሱ በአባቱ ቤት በጥሩ እየኖረ ነው፡፡ አባቱ ልጆቹን በጣም ይንከባከብ ስለነበር ያች የእንጀራ እናት መጐዳት አልቻለችም፡፡ ከሦስቱ ልጆች አንዱ ግን ለእናቱ እንጀራ ይዞ በየሌሊቱ ይገሰግስ ነበር፡፡ እናቱ በደንብ ይራቡ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እንጀራ ሠርቆ ሲወጣ ተይዞ ተገረፈ፡፡ ለአባቱ ስሞታ ሲነገርም አባቱ አዝኖ ምነው ታዲያ አንቺስ ብትረጃት እናቱ እኮ ተርባበት ነው ብሎ አለቀሰ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ በየወሩ ኩንታል ጤፍ ይላክላቸው ጀመር፡፡ ይህንን በዓይኔ ዓይቻለሁ፡፡ ዳዊት ዲቃላ ነበረ ስንል ይህን ሁሉ ስቃይ እንደሚያስተናግድ ገና በጠዋቱም ብዙ ሸክም እንደሚሸከም መዘንጋት የለብንም፡፡ ዳዊት የመጨረሻ ልጅም ነው፡፡ 
            የመጨረሻ ልጅ መሆን ቅብጠት የሞላበት መስሎ ይሰማን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብርቱ ኃላፊነትና ጭንቀት ያለበት ነው፡፡ በርግጥ የአባትና የእናት ኃይላቸው የመጨረሻው ልጅ ዕድሜ ላይ ስለሚበርድ የመጨረሻ ልጅ አይገረፍ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማደጉን ሁሉም ሰው የማይቀበለው፣ ሁልጊዜም እንደ ልጅ የሚታይ፣ በዕድሜ የገፉ የወላጆቹ ኃላፊነት እርሱ ላይ የሚወድቅበት፣ ትላላቆቹ ሁሉ አይታዘበንም እያሉ የሚያማክሩት ነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻው ልጅ ከዕድሜው በፊት ይበስላል፣ የቤተሰቡ ጥሪት/ሀብት/ ከተሟጠጠ በኋላ ስለሚደርስም ብዙ ችግሮችን ያስተናግዳል፡፡ ታላላቆቹ የሚሆኑ እህትና ወንድሞቹም የወላጆቻቸውን አሳብ በመጨረሻው ልጅ ላይ ጥለው ትዳራቸውን ያጠናክራሉ። ለዚያም ልጅ ከሆዱና ከልብሱ አልፈው ለኅሊናው አያስቡለትም፡፡ እነዚህ የመጨረሻ ልጆች ከፍተኛ የሆነ የልብ ጥንካሬን ቢያዳብሩም ከማንም የበለጠ ትግል ውስጥ ግን ያልፋሉ፡፡ ዳዊትን ስናስብ ስሙን ብቻ ሳይሆን ትግሉንም ብናስብ ለትምህርት ይሆንልናል፡፡
            እግዚአብሔር የመረጠው ይህንን ዳዊትን ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ምንም የሚመኩበት የሌላቸውን ድሆችን ቀና አድርጎ መመኪያ ይሆናቸዋል፡፡ የእኔ ተራ መቼ ይሆን? እያሉ የሚጠባበቁትን የድል ጽዋቸውን ያስጨብጣቸዋል፡፡ በመንግሥት ስለተበደሉ ዜጎች ብዙ እንሰማለን፤ በገዛ ወላጆቻቸው የተገፉ እንደ ዳዊት ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ቀና በማድረግ እግዚአብሔር ስሙን ያከብራል፡፡ አንድ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበሩ የድሮ ባላባት 12 ልጅ ወልደው ከደጅ አንድ ልጅ ወለዱና ወደ ቤታቸው አመጡት፡፡ እንጀራ እናትም ያን ልጅ በመብል ይበድሉት ነበር፡፡ ባላባቱም፡- “ይህ ልጅ በላ ወይ?” ብለው ሚስታቸውን ሲጠይቁ ሚስቲቱም፡- “ኋላ ይበላል” በማለት ይመልሳሉ፡፡ የሁልጊዜ መልሳቸው “ኋላ ይበላል” ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እኒያ ባላባት ልጃቸውን ጠርተው፡- “ልጄ ኋላ ትበላለህ” አሉት፡፡ ጊዜ ተለዋውጦ ያ ልጅ እጅግ ባለጠጋ ሆነ፡፡ 12 ወንድሞቹም የእርሱ ባለሟሎች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር የእንጀራ እናቱን ቃል ትንቢት እንደሚያደርግለት እኒያ ባላባት ያምኑ ነበር፤ ትንቢቱም ተፈጸመ፡፡ የኋላ እንጀራ አገኘ፡፡ እግዚአብሔር ቀኝ ኋላ ዙር በማለት ይሠራል፡፡ ያን ቀን የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆናል፡፡ በዳዊት ሕይወት የሆነው ይህ ነው፡፡ መገፋት ከዙፋን፣ መናቅም ከቅብዐት ያደርሳል፡፡ እኛ ከመልካሙ መልካም ማውጣት እያቃተን እናለቅሳለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ክፉ ከመሰለው ነገር ውስጥም መልካም ማውጣት ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ነገርን ሲቀያይር፣ ባለ ዙፋንን ትቢያ ላይ ሲያስቀምጥ፣ ከአመድ አንሥቶም በመንበር ላይ ሲያስቀምጥ አይከብደውም፡፡ የነቢይት ሃና ጸሎት፡- ‹‹አትታበዩ÷ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና÷ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና ከአፋችሁ የኩራት ነገር አይውጣ … ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋልና …” (1ሳሙ. 2÷ 3-8) ይላል፡፡
            እግዚአብሔር አባቱ የረሳውን ዳዊትን፣ እናቱ ከኑሮዋ የተነሣ የጣለችውን ብላቴና፣ ዱር ቤቱ የነበረውን ስደተኛ አስበው፡፡ የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ያለ ምርጫ፣ ያለ ሕዝብ ድጋፍ መረጠው፡፡ 1ሳሙኤል ምዕራፍ 16 ይህንን ታሪክ ያብራራልናል፡
            ከእግዚአብሔር የተላከው ነቢዩ ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት በሄደ ጊዜ የእሴይን የመጀመሪያ ልጁን መልከ ቀና ቁመቱ ሎጋ የሆነውን ኤልያብን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር የመረጠው ይህን ነው አለ፡፡ ነቢይ ሳይቀር የተሳሳተበት የኤልያብ ቁመናና መልክ ምን ዓይነት ይሆን? እግዚአብሔር ግን ሰውን በሰው ዓይን አይመርጥም፡፡ እግዚአብሔር የሚያየው ከሰው ዓይን ዘልቆ ነው፡፡ ነቢዩንም፡- “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው” (1ሳሙ. 16÷7)፡፡
            ከዚያን ጊዜ እስከ ዛሬ መስፈርታችን ውጫዊ ነው፡፡ መልክና ቁመና ይስበናል፤ መልከ ቀና የሆነ ሰባኪ፣ ባለውቃቢ ሳይቀር ተከታዩ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አስተሳሰብን ያያል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ውበት የቆዳ ሳይሆን የልብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መስፈርቱ እንደ ሰው መስፈርት ቢሆን ኖሮ ክርስቲያን ለመሆን ባልበቃን ነበር፡፡ እኛ ቆንጆ መኪናን እንኳ መልክ የለሽ የምንላቸው ሰዎች ይዘው ካየን እንበሳጫለን፡፡ ቆንጆ ለቆንጆ እንላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን አፈር የሆነውን የሚናደውን ግንባታ ሳይሆን ዘላቂ የሆነውን፣ የማይሞተውን፣ የማይደክመውን እውነት ከሰው ልብ ላይ ይፈልጋል፡፡ የውበት መለኪያው ልብ ነው፡፡ መልከ ቀና ግብረ ጠማማ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ዓይተናል፡፡ መልካቸው ላይ ብዙ ጊዜ ሲያጠፉ አሊያም ቆንጆ ናችሁ ሲባሉ ስለ ባሕርያቸው አላሰቡበትም በአብዛኛው ስናይ መልከ ቀናዎች አመላቸው የሚለበልብ ሳማ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ጉዳዩ ከቆዳችን ጋር ሳይሆን ከልባችን ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ኤልያብን ናቀው፡፡ እሴይ ልጆቹን ሁሉ በቅዱስ ቅባት ፊት አሳለፈ፡፡ እግዚአብሔር ግን የመረጠው አልተገኘም፡፡ እሴይ መቼም ዳዊትን አይመርጠውም ብሎ ዳዊትን አላቀረበውም፡፡ ዳዊት በዱር በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡ ሌላ ልጅ ካለህ ጥራ ሲባል የግዱን ዳዊትን ጠራው፡፡ ዳዊትም  በናቁት ወንድሞቹ ፊት፣ ቁራሽ በተከለከለበት ቤት ውስጥ ቅብዐ መንግሥት ተቀባ፡፡
            እግዚአብሔር ዳዊትን በማይመች ምድረ በዳ ውስጥ እያሰለጠነው ነበር፡፡ በቤት ውስጥ ከሚያድጉት፣ ምግብ እየተመረጠ ከሚቀርብላቸው ይልቅ ጠንካራ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሠራዊት ነውና ከጣፋጭ ይልቅ በመራራ፣ ከሳሎን ይልቅ በምድረ በዳ ሰለጠነ፡፡  አንድ በዳር አገር የሚኖር ሰባኪ ስልክ ደወለልኝና፡- “ያለሁት በምድረ በዳ ነውና እዘንልኝ” አለኝ፡፡ እኔም ወዲያው የእግዚአብሔር ደስታ ልቤን ሞላውና የመጣውን መልእክት ነገርኩት፡- “መንግሥት ወታደሩን የሚያሰለጥነው በከተማ ሳይሆን በበረሃ ነው፡፡ እግዚአብሔር እየሠራህ ነውና ደስ ይበልህ” አልኩት፡፡ ያም ሰው ሕይወቱ ከዚያች ሰዓት በኋላ እንደ ተለወጠ ሲመሰክር ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር በማይመች የሕይወት ቀጠና ልጆቹን ያሰለጥናል፡፡ አንዲት እህቴ ስትናገር እንዲህ አለች፡- “እግዚአብሔር በሕይወታችን ሥራ ሲጀምር በማፍረስ ነው” አለች፡፡ አዎ የምንመካበትን ነገር ሁሉ ጥሎ፣ የከበቡንን በትኖ ሥራውን መሥራት ይጀምራል፡፡ ባላችሁበት ደሳሳ ጎጆ ላይ ፎቅ ለመሥራት ብታስቡ ሥራውን የምትጀምሩት በማፍረስ ነው፡፡ ዛሬ ከአጠገባችሁ የፈረሱ ወዳጆች፣ የፈረሱ መመኪያዎች ካሉ ደስ ይበላችሁ! እግዚአብሔር ትልቁን ሥራ የሚሠራው በማፍረስ ነው፡፡ ዳዊት በምድረ በዳ የሚሠለጥን የእግዚአብሔር ሠራዊት ነበር፡፡
            ነገ የሕዝብ ጠባቂ ስለሚሆን ሥራውን የጀመረው በጎች ከመጠበቅ ነው፡፡ እረኝነት ማለት ምን ማለት መሆኑን በደንብ ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔር የሚያሳልፈን የሕይወት ገጠመኞች ነገ ለሚሾመን ሥፍራ ልምድ የምናካብትባቸው መሆናቸው ይገርማል፡፡
            ነገር ግን ዳዊት ከቅብዐት በኋላ ትልቅ ፈተና መጣበት፡፡ በቤተሰብ የነበረው ትግል አገር የማይበቃው ሆነ፡፡ ከአባት ጋር የነበረው ሙግት ከንጉሥ ጋር ጀመረ፡፡ ከጥቂት ወንድሞች ጋር የነበረው ሰልፍ ከእስራኤል ሠራዊት ጋር ሆነ፡፡ ፈተናው በክብሩ መጠን ከፍ አለ፡፡ ሳኦል ሊያስገድለው በእስራኤል ምድር ሁሉ አሰሳ ቀጠለ፡፡ ከታላቅ ቅብዐት በኋላ ታላቅ ስደት መጣ፡፡ አንገት ደፍቶ ሁሉን እሺ ብሎ በእረኝነት ታሪኩን ለመደምደም የወሰነው ውሳኔ ሐሰተኛ ሰላም፣ ከታሰበለት ደረጃም የሚያስቀር ነው፡፡ በማዕበል ውስጥ አልፎ ግን ከከፍታው ይደርሳል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከሞቀ ጦርነት ውስጥ ከተተው፡፡ ምክንያቱም ያለ ጦርነት ድል የለምና፡፡
            ዳዊት ገና በልጅነቱ፣ የበጎች እረኛ ሳለ እግዚአብሔር የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ቀባው፡፡ ዳዊት አሁን ቢቀባም ዙፋኑን ለመውረስ ግን የዓመታት ትግሎች ከፊት ለፊቱ ይጠብቁት ነበር፡፡ በዳዊት ሕይወት ላይ እንዳየነው የእግዚአብሔር ቅብዐት የተቃዋሚ ኃይል አያሸንፈውም፡፡ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ ሳኦልና ሠራዊቱ ያሳድዱት፣ ሸለቆ ለሸለቆ ያንከራትቱት ጀመረ፡፡ የዳዊትን መቀባት ሳኦል በዓይኑ አላየም፣ በጆሮውም አልሰማም፡፡ ነገር ግን ዳዊት ወራሹ እንደሆነ ውስጡ ነግሮታል፡፡ ዳዊት ከቤተሰባዊ ጦርነት የተላቀቀ ቢመስልም ብሔራዊ ጦርነት ውስጥ ግን ገባ፡፡ አንድም ቀን ድሉ በእጁ እንዲሆንለት አልፈለገም፡፡ ሳኦል ሁለት ጊዜ በእጁ ቢወድቅም መግደል እየቻለ በነጻ አልፎታል (1ሳሙ. 26)፡፡ ዳዊት አስቀድሞ ተቀብቻለሁ በማለት የጎበዝ መሪ ሆኖ አለመውጣቱ ሲገርመን አሁን ደግሞ ድልንና ፍርድን ከሰማይ አምላክ መጠበቁ እጅግ ይገርማል፡፡ እግዚአብሔር ሲፈርድልን እንጂ ለራሳችን ስንፈርድ ደስታ የለውም፡፡
            ከታላቅ ቅብዐት በኋላ ታላቅ ስደት ተነሣ፡፡ ይህ የሕይወት ግፊት ግን ለወደፊቱ ሥራ የሚያዘጋጅ ነበር፡፡ ሳኦልም ሞተ፣ የእስራኤል ሠራዊትም ተበተነ፡፡ ስደተኛው ዳዊት በገሀድ ተቀባ (2ሳሙ. 5፡1-5)፡፡ እግዚአብሔር ያለው አልቀረም፡፡ ጠላት ግን በመንገድ ቀረ፡፡ ቅብዐት ወዲያው ዙፋን አይከተለውም፡፡ ብዙ ጦርነት ይቀሰቅሳል፡፡ አጥፊዎችን ለማጥፋት ያነቃቃል፡፡ በጓዳ ብንቀባም፣ በአደባባይ ግን ጦርነት ይነሣብናል፡፡ በዚህ ውስጥ ታላቅ ትዕግሥት ከማድረግ ጋር፡-
1.     የእግዚአብሔርን መድረክ መጠበቅ እንጂ ተቀብቻለሁ ብሎ ፎክሮ መውጣት ማንንም ስፍራ ልቀቁልኝ ብሎ መግፋት አይገባም፡፡
2.    ስኬቶቻችንን የግል ጥረታችን ውጤት አድርገን እንዳንመለከት፣ በአወዳሾችም ዜማ እንዳንታበይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
3.    አሳዳጆቻችንን ጊዜ አገኘሁ ብለን መበቀል አይገባንም በቀል የእግዚአብሔር ነው፡፡
4.    ድል ያለው በወንድነት በመጋፈጥ ብቻ ሳይሆን በመሰወርም ነው፡፡ ስለዚህ የመሰወርን ጊዜ ማክበር ይገባናል፡፡
5.    እግዚአብሔር ሁሉን አሳልፎ ባከበረን ቀን ሁሉን ትተን ምሕረት ልናደርግ ይገባናል፡፡ ከታላቅ ቅብዐት በኋላ ታላቅ ስደት ቢሆንም አንጠፋም፡፡ በአውራው ጎዳና፣ ወደ ቤተ መንግሥትም በሚያመራው መንገድ ላይ ነንና ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ሌባ የሚያሳድደው ሀብትን ዓይቶ ነው፡፡ ምንም የሌለውን አያሳድደውም፡፡ ጠላትም ስደት የሚያበዛብን ቅብዐቱን ዓይቶ ነውና ልባችን ሐሴት ይሞላ!
                            
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ