የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከእኔ ጋር እንዴት ኖርህ ?

የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ! እንዴት ከእኔ ጋር ኖርህ ? እኔ አንተን ማመን አቅቶኝ ፣ አንተ እኔን አምነኸኝ እንዴት ከእኔ ጋር ኖርህ ? የጸናኸውን ዓለት ትቼ ስሄድ ፣ የባሕር ላይ ኩበት የሆንሁትን እንዴት እኔን መረጥህ ? ፍቅር ዳገት ሆኖብኝ ጥላቻ ከሚገዛኝ ፣ የወዳጄን የብዙ ዓመት ውለታ በአንድ ቀን ስህተት ከምደመስስ ፣ ሲያፈቅሩኝ እየተጠራጠርሁ ፣ ሲጠሉኝ ግን ከማምነው ፣ መልከ ብዙ ከሆንሁት ከእኔ ጋር እንዴት ኖርህ ? የተቀበልሁትን ሳላጣጥም ፣ ለጸለይሁበት መልሴ ምስጋና ሳላቀርብ መልሼ ሌላ አምጣ ከምልህ ፣ ቸልታ ከማበዛው ፣ ለጽድቅ ረጅም ቀጠሮ ከምሰጠው ፣ ለወንጌል ተኝቼ ለሣንቲም ከምነቃው ፣ ዘመናት ባለፉ ቍጥር ከበጎነት ከምቀንሰው ፣ የምችላቸው ላይ ክንዴን እያጸናሁ ፣ የማልችላቸውን ከማመልከው ከእኔ ጋር እንዴት ኖርህ ? በአሸዋ ገበታ ላይ መናህን ከምበላው ፣ በአንድ ልብ ወሬ እያዳመጥሁ በአንድ ልብ መጸለይ ከማልችለው ፣ በአዋጭ ስሌት ከእኔ ጋር መኖርህ ያከስርሃል ። በወዳጅነት ሚዛን ዘጠና ዘጠኙን ወዳጆች ትተህ አንዱን አጥፊ ፍለጋ መምጣትህ ያስወቅስሃል ። ገብቶ የማያልቀውን እኔነቴን መጠበቅ ያደክምሃል ።

ጌታ ሆይ እንዴት ከእኔ ጋር ኖርህ ? ካልበላሁ ከማልስቀው ፣ ያልከኝን ትእዛዝ እየሻርሁ ፣ ያልሁትን ጸሎት ለምን አልፈጸመም ብዬ ከማኮርፈው እኮ ከእኔ ጋር እንዴት ኖርህ ? ሽማግሌ ሳይገባብን ይህን ሁሉ ዘመን ፣ እኔ ስጮህ አንተ ዝም እያልህ ፣ እኔ ሳኮርፍ አንተ እያናገርህ እንዴት ከእኔ ጋር ኖርህ ? ጌታዬ ሆይ ለሕማም ለሞት አብቅቼህ ዛሬም አድሮ ጥጃ ነኝ ። የተሻለ ሰው ፈልግ ፣ ከማያድግ ችግኝ ጋር ፣ ከሁልጊዜ ሀሁ ፣ ከሁልጊዜ ዳዴ ጋር አትኑር ። አብረውኝ የተተከሉ ዛፍ ሁነው ፍሬአቸው ዓለሙን ሲያጠግብ እኔ ግን አድሮ ቃሪያ ከሆንሁት ፣ አቃጣይ ልጅ ጋር ምን ትሠራለህ ? ንጹሕ ልብስ እንጂ ንጹሕ ልብ ከማልወደው ፣ ቃሌ ለስልሶ ልቤ ከሻከረው ፣ በሰዎች ዕድል ደስተኛ ከማልሆነው ፣ እንግዶችን ለመቀበል ከመትጋት ይልቅ ከማኮርፈው ፣ ከሰጠኸኝ ላይ መስጠት ከተሳነኝ ፣ ራስ ወዳድነት ካጠቃኝ እንዴት ከእኔ ጋር ኖርህ ? ለካ ላትተወኝ መሐላ አለህ ። አንተ ከተውኸኝም የሚይዘኝ የለም ። በአማኑኤል ስምህ ፣ በቃል ኪዳን ፍቅርህ ከእኔ ጋር ስለሆንህ አትለየኝም ። ግን ልጠይቅህ ከእኔ ጋር እንዴት ኖርህ ?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ