የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከዓለቱ ጋር መስማማት

 

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!

ወንድሟ በአደጋ የሞተባት ሴት እንዲህ ብላ የልቅሶ ሙሾ አቀረበች ይባላል፡-

“እስቲ ልነሣና ሙሾ ላውጣለት ፣

ለዚህ ለወንድሜ ለቀረው ከዓለት ።”

የቅኔው ሰሙ ከዓለት ላይ ወድቆ መሞቱን ሲገልጥ ወርቁ ደግሞ ካለ እኅት ፣ ካለ ዘመድ ብቻውን ለቀረው ወንድም የኀዘን መግለጫ ነው ። ካለት ከዓለት ማለት ሲሆን ደግሞም ካለ እኅት ማለት ነው ። ዓለት ብንወድቅበትም ይሰብረናል ፣ ቢወድቅብንም ይሰብረናል ። ይህ ለጌታችን ምሳሌ ሁኗል ። ማቴ. 21፡44 ። ጌታችን ባለማመን ብንቃወመውም ፣ አላውቃችሁም ቢለንም ሁለቱም ጉዳት ነው ። ዛሬ ይህን ዓለት በማያምን ልብ ብንቃወመው የወደቅነው በዓለቱ ላይ ነውና ይሰብረናል ። ንስሐ ካልገባን ደግሞ በመጨረሻ ቀን ዓለቱ በፍርድ ይወድቅብናል ። የጌታችን የክርስቶስ ኢየሱስን ፍርድ ለየት የሚያደርገው ምስክር የማይጠራበት ፣ የእምነት የክህደት ቃል የማይጠየቅበት ፣ የውሳኔ ቀጠሮ የማይሰጥበት ፣ መረጃና ማስረጃ የማይሰበሰብበት ፣ ይግባኝ የማይባልበት ፣ ዘላለማዊ ቅጣት ያለበት ነው ። ይህ ዓለት ለሚያምኑት የሚከተላቸውና የሚያረካቸው የበረሃው ዓለት ነው  ። 1ቆ. 10 ፡ 1-5 ። 

መከተሉ አለመለየቱን ያመለክታል ። እርሱ አይለየንም ። እስከ መጨረሻው ድረስ በእኛ ተስፋ አይቆርጥም ። እርሱ ለደግነቱ ማለቂያ ፣ ለፍለጋው ማረፊያ የለውም ። በመጥራቱ የማይጸጸት ነው ። በፍለጋውም የማይደክም ነው ። እገሌ ልቡ ጠንካራ ነው እንዴት ያገኘዋል ብለን ብናስብ ለመንገዱ ፍለጋ የሌለው ነው ። የሁሉ ፈጣሪ ፣ ልብ አውቃ ነውና ማንን በምን ቋንቋ እንደሚያነጋግር ያውቅበታል ። የት ቦታ ሲመቱ አቤት እንደሚሉ ያውቃል ። እርሱ የሚከተል ዓለት ነው ። የሚመራው ብሩህ ደመና ፣ የሚከተለው ዓለት ነው ። የሚከተል ከኋላ ያለ ነው ። እግዚአብሔር ከፊት የሚመራ ፣ ከጀርባችን የሚጠብቀን ፣ ከቀኝ ከግራ ወዳጅ ሁኖ የሚከበን ነው ። ሕልም አይተነን ስናስፈታ ፈቺዎቹ “በጀርባዬ መጣብኝ ያልከው በጀርባ የሚመጣ ጠላት ነው እግዚአብሔር ያውጣህ” ይሉናል ። ጠላት ከጀርባ ይመጣል ። የጀርባ ጠላታችንን ብቻ ሳይሆን የጀርባ አካላችንን እንኳ አይተነው አናውቅምና ዓለቱ ክርስቶስ ሊከተለን ይገባል ። እስራኤልን የሚከተል ዓለት ነበረ ። የዓለት ግድግዳን የትኛውም ጦር አይበሳውም ። ጦርን ያጥፋል እንጂ በጦር አይበሳም ። የእኛ ከለላ እንዲህ ነው ፤ ደስ ያለው አሁን በልቡ ቆሞ ፣ በሕሊናው ተንበርክኮ ፣ በነፍስ ጩኸት እልል ይበል ። 

ያ የሚከተለው ዓለት ሕያው ዓለት ነው ። ያ ዓለት የሚያረካ ዓለት ነው ። ያ ዓለት በበትር ሲመቱት ያለ ሕጉ ምንጭ የሚያፈልቅ ነው ። ዓለቱ በትሩን መስበር ሲገባው በትሩ ዓለቱን እንዲሰብረው ፈቃድና ጊዜ አገኘ ። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ። ዓለት ክርስቶስም መስቀሉን መስበር ሲችል መስቀሉ እርሱን ሰቅሎ ለዓለም አሳየው ። ያልተሰቀለ ነገር አይታይምና ሁሉ አይቶት እንዲድን ተሰቀለ ። አርማና ሰንደቅ ነውና ፣ መኩሪያ አገራችን ፣ መመኪያ ንጉሣችን ሊሆን ተሰቀለ ። ይህን ዓለት ሊያምኑት ፣ ሊጠጉት ፣ ሊደበቁበት ይገባል ። ያ ሰው ግን ዓለቱ ላይ ወድቆበት ሞተ ። በክርስቶስ የማያመኑ የሚሞቱት ዓለቱ ላይ ስለሚፈጠፈጡ ነው ። እርሱ የሕይወት ምንጭ ነው ። ዓለት ብርታቱ በመስቀል ተመትቶ የሕይወት ውኃ ፈለቀልን ። ብዙ ዘመን የተከተለን ነው ። ስንሸሸው የተከተለን እርሱ ነው ። የሚከተለው ዓለት በበረሃው ዓለም ድፍረት ነው ። እኛን የሚነካን ከዚህ ዓለት ጋር የሚጋጭ ነው ። ሥልጣን ብርታት ኃይል እስከ ዛሬ ያልረታው የዘላለም ጽናት ነው ። የሚከተለው ዓለት የኋላ አጥር ፣ የኋላ እሸት ነው ። እርሱን የጠበቁ እነ አብርሃም የማታ በረከት ፣ የሠርክ መብራት አግኝተዋል ። ዓለቱን ሊድኑበት ሲገባ ወድቀውበት የሚሞቱ ብዙዎች ናቸው ። ሊለቀስላቸው ይገባል እንጂ ሊለቀስባቸው አይገባም ። 

በዓለት ላይ ወድቆ የሞተው ያ ሰው የሞተው ለአንድ ጉዳይ ሳይሆን ለብዙ ጉዳዮች ሞቷል ። የሚወዱትን አጥቷል ። የሚጠሉትም ሞቷልና አይጎዳንም ብለው ይቅር ብለውታል ። ሊያሙት የሚፈልጉም “ሙት አይወቀስ ፣ ድንጋይ አይነከስ” ብለው አልፈውታል ። በዓለቱ ላይ የወደቀው ያ ሰው እኅት ፣ ወንድም ፣ አባት ፣ እናት አጥቷል ። ዓለቱ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የሚጋጩም ብዙ መንፈሳዊ ዘመዶችን ያጣሉ ። ከቅዱሳን ጋር ባለ አገሮች መሆናቸው ያከትማል ። ጉዳታቸውን የትኛውም የኢንሹራንስ ተቋም ሊክሰው አይችልም ። ክርስቲያን ስንሆን ዘጠና ዘጠኝ ነገድ የሚሆኑ ቅዱሳን መላእክት ወዳጆቻችን ይሆናሉ ። ልብ አድርጉ መላእክት ኅብረት የሚያደርጉት ከአባት ከእናት ልጅ ጋር ፣ ዘር በመቋጠር አይደለም ። ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ሥጋዊ የልደት ትስስር የላቸውም ። ፍቅራቸው ግን በምድር ላይ ካለ ከእናትና ከልጅ ፍቅር ይበልጣል ። የቅዱሳን መላእክት ፍቅር ልዩ ነው ። ንስሐ ስንገባ ታላቅ ደስታ የሚያደርጉት ስንወድቅ ታላቅ ኀዘን ስለተሰማቸውና ስለጸለዩልን ነው ። ሉቃ. 15፡7 ። ዓለቱ ላይ ወድቆ የሞተ ወይም ክርስቶስን ተቃውሞ መንፈሳዊ ሕይወትን ያጣ ሰው ይህን ሁሉ ዘመድ ይከስራል ። ከአዳም ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ያለው የሰው ዘር አንድ ነገድ ነው ። መላእክት ዘጠና ዘጠኝ ነገድ ናቸው ። ይህን ሁሉ ወዳጅ ማግኘት ትልቅ ሀብት ነው ። ከአቤል ጀምሮ ድል የነሡ የቅዱሳን ኅብረትም ክርስቲያን ስንሆን እንዛመዳቸዋለን ። 

እስቲ ልነሣና ሙሾ ላውጣለት ፣

ለዚህ ለወንድሜ ለቀረው ከዓለት ፤

መስቀሉ በሚታወስበት በዚህ ቀን በመንፈሳዊ ነጻነትና ድል የሚያከብሩ ፣ ከዓለቱ ክርስቶስ ጋር በንስሐ የታረቁ ብቻ ናቸው ። መስቀል ቅርጹም ኅብረት ነው ። ወደ ላይና ወደ ጎን ነው ። ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ጎን ከሰዎች ጋር መተሳሰር ነው ። ከዚህ ሕይወት ለጎደለው ወንድም አልቅሱለት ። የሞተ ይለቀስለታል እንጂ አይለቀስበትም ።

ታላቁን የክርስትና ኅብረት የምናገኘው ከዓለቱ ጋር ስንስማማ ነው ።

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ ። ዛሬም መስቀሉ ተቀብሯልና እናውጣው ። መስቀል ሰላም ነው ። መስቀል የሰው ክብር ነው ። መስቀል ቀና ብሎ መሄድ ነው ። መስቀል መስማማት ነው ። መስቀል ጦርን ማረሻ ፣ ቀስትን መኮትኮቻ ያደረገ ነው ። ከመስቀሉን ብርሃን ያሳትፈን ።

የብርሃን ጠብታ 8 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ