የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከዘላለም እስከ ዘላለም – ከጽንፍ እስከ ጽንፍ

 “ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን ፤ አሜን ።” 1ጢሞ. 1፡17
ተስፋ ያደረግናቸው ሕልም እልም ሲሆኑ ፣ ያስቀመጥናቸው ከቦታቸው ሲታጡ ፣ ሁልጊዜ የሚገኝ ነገር ሲናፍቀን ፣ ቀና ብለን ስናይ በፍቅር የሚያይ ሲያምረን ፣ ሁሉን ደግ ነገሮች ማሰብ አቁመን ሁሉን ክፉ ነገሮች እንደ አሁን ማሰብ ስንጀምር ፣ የአምላክ የፍቅር እጅ ሳይሆን የጠላቶች የክፋት ጡጫ ሲሰማን ፣ የእግዚአብሔር ድምፅ ደብዝዞ የሰዎች ጥላቻ ሲያስተጋባብን ፣ የሚያየንና የምናየው እንደ አማረን ሲቀር ፣ እኔ ነኝ የተሳሳትሁት ወይስ ዘመኑ ነው ብለን ግራ ስንጋባ ፣ ከእኛ ጋ ተሰልፈው ሲዋጉልን የነበሩ እዚያ ጋ ተሰልፈው ውጊያ ሲከፍቱብን ፣ አለቀ ስንለው መሙላት ሲጀምር ፣ የሞላው ሲጎድል ፣ የፍቅር አገሯ የት ነው ? የታማኝነት መገኛዋ ወዴት ነው? ስንል ፣ የገዛ ድምፃችንን መልሰን ስንሰማ ፣ አሉታዊነት እንደ መጋኛ ሲያጣምመን ፣ ግራ ዘመም ሁነን ሁሉን በዜሮ ስናባዛ ፣ እጠላሃለሁ የሚለውን ድምፅ እያመንን “እወድሃለሁ” የሚለውን ድምፅ ስንጠራጠር ፣ ስልኮች ደውለን በመጀመሪያ ጥሪ ካልተነሣ ወዲያው ወዳጅ ስንሰርዝ ፣ ልጆቻችን ፍጹማን ካልሆኑ ብለን እኛ የሌለንን ከእነርሱ ስንፈልግ ፣ ጓጉተን የገዛነው በማግሥቱ መሰልቸት ሲጀምር ፣ ያበላናል ያልነው ቀርቶ ባላሰብነው መንገድ እንጀራ ስንቆርስ ፣ ባሰብነው ቀርቶ ባሰበው ስንውል ፣ ተረኛ እንጂ ቋሚ ነገር ስናጣ አንድ ነገር እንጠይቃለን ። ዘላለም የሚኖር ምንድነው ?

ዘላለም የሚባል ልጅ ሞቶ ሲለቀስ አንደኛው ጎራ “ዘላለም” እያለ ስሙን ሲጠራ ሁለተኛው የአልቃሾች ምድብ “ስም ብቻ” እያለ ይመልሳል ። ዘላለም የሚል ቃል በምድር ላይ ሲሰየም ስም ብቻ ይባላል ። ዓለም በገደል አፋፍ ላይ የተሠራች ቤት ናት ። ዓለም ስም ብቻ ናት ። የታሰሩ ባለሥልጣናትን ፣ ያበዱ ሊቃውንትን ፣ የጠፉ መንደሮችን ፣ የሰጠሙ ከተሞችን ፣ ብቻቸውን የቀሩ ሰዎችን ስናይ ዓለም ስም ብቻ ናት ። እነዚያ እንዳለፉ እኛም እናልፋለን ማለትን ስንተው ፣ ተንቀሳቃሽ ሬሳ መሆናችንን ስንዘነጋ ዓለም በእውነት ከንቱ ነው እንላለን ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ዝም የማታሰኝ ወንጌልን ተወዳጅቶ እኛንም ለፍላፊ አደረገን ። ይህን ሁሉ የሚያስወራን ከዘላለም እስከ ዘላለም እያለ መናገሩ ነው ። ዘላለም የሚለው መነሻ ላለውና የማትሞት ነፍስ ለተሰጠችው ለሰው ቢነገርም ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚባለው ግን መነሻና መድረሻ ለሌለው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀጸል ነው ። አልፋ ቢባል የሚቀድመው የሌለ ፣ መጀመሪያ የሌለው ሁሉን መጀመሪያ ያሰኘ ቀዳማዊ ነው ። ዖሜጋ ቢባል የሚከተለው የሌለው ፣ ለሁሉ ፍጻሜ ፣ የድንበር ድንጋይ ያስቀመጠ ደኃራዊ ነው ። ከዘላለም እስከ ዘላለም መባል ለእርሱ ብቻ ይሁን ። ሰዎች እንዲያገኙ ይመረቃሉ ። እግዚአብሔር ግን ሁሉ ገንዘቡ ነውና ይመሰገንበታል ።
ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የአንደበት ርእስ ፣ የጆሮ ቀለብ የነበረው ግኝት ዛሬ ላይ ተረስቷል ። የአምናው የሳይንስ ድምዳሜ ዛሬ ላይ በአዲስ እውቀት ተለውጧል ። ከዓመታት በፊት ሣር ቅጠሉ ያረገደላቸው ዛሬ አፈር ትቢያ ሁነዋል ። የአምናው ተሸላሚ ዛሬ ተነጥቀዋል ። ፀንቶ የሚኖር ቢፈለግም እየጠፋ ፣ ቢገኝም ልብረር ልብረር እያለ የሰው ልብ ዓለምን ባለማወቅ ስቃይ ውስጥ ገብቷል ። ሞትን ብንረሳው አይረሳንም ፣ ባንወደውም ዕለት ዕለት የምንሄደው ወደ ሞት ነው ። የምንፈልገውን ቀርቶ የማንፈልገውን እንሰማለን ። ያቀፉን ሲገፈትሩን ፣ የጠሉን እንደ ገና ይወዱናል ። ዓለም በጣም ተለዋዋጭ ናት ። ከዘላለም እስከ ዘላለም ተብሎ የሚነገርለት በህልውናው ፣ በአካሉ ፣ በስሙ ፣ በጠባዩ ፣ በባሕርዩ ፣ በልዩ ሦስትነቱ ፀንቶ ለሚኖረው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ።
ሐዋርያው ይህንን ምስጋና ለእግዚአብሔር ያቀረበው እንደ ሕግ የሞተው እርሱ እንደ ወንጌል ስለዳነ ነው ። “እንደ ሕግ ማን ጸድቆ ፣ እንደ ወንጌል ማን ተኮንኖ” የሚባለው ለዚህ ነው ። በወንጌል ውስጥ የሚያስፈልገው እምነት ነውና ። ሌጣው እምነት ሳይሆን ወላዱ እምነት ነው ። በቸርነቱ ለተቀበለው በቤቱም አገልጋይ አድርጎ ለቆጠረው ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባል ። “ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን ፤ አሜን ።”
ምስጋና እግዚአብሔርን በነገረ መለኮት እውቀት ሳይሆን በአምልኮ መንፈስ ማብራራት ነው ። ምስጋና እንደ መምህራን ቆሞ መናገር ሳይሆን ሰግዶ ማወደስ ነው ። እንደ ረበናት ተቀምጦ መተንተን ሳይሆን እጅ እየነሡ ማደሪያውን ማሰስ ነው ። ሐዋርያው እግዚአብሔርን የገለጠበት ውብ መግለጫዎች፡-
·        ብቻውን
·        አምላክ ለሚሆን
·        የማይጠፋ
·        የማይታይ
·        የዘመናት ንጉሥ የሚል ነው ።
ብቻውን፡- እግዚአብሔር ብቸኛ አይደለም ፤ ብቻውን ያለ ነው ። ይህን ንግግር ለአዳም ሲናገር እናነባለን ። “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ።” ዘፍ. 2፡18 ። አዳም እግዚአብሔር ነበረውና ብቸኛ አልነበረም ። ብቻውን ግን ነበረ ። ይህን ያህል እውቀትና ጥበብ የሞላበት አዳም ብቻውን ቢሆን የተሰጠው ጥበብና እውቀት ብክነት ይሆን ነበር ። ስለዚህ ፍቅርን ፣ በጎነትን እንዲቸር እርሱም የሚቸረው እንዲያገኝ ሔዋን ተፈጠረችለት ። እግዚአብሔር ከሚነገርለት ነገር አንዱ “ብሑተ ህላዌ”  ወይም “ብቻውን ነዋሪ” ነት ነው ። እግዚአብሔር ለመኖሩ በሌላ አይደገፍም ። ድጋፉም ምሰሶውም እርሱ ነው እንጂ ሌላ ድጋፍና ምሰሶ የለውም ። እገዚአብሔር ጥበቡ ፣ ኃይሉ የብቻው ነው ። የሊቃውንት ጥበብ ከመምህራን ፣ የነገሥታት ኃይል ከሠራዊት ይመነጫል፤ እግዚአብሔር ግን ብቻውን ጥበበኛና ኃያል ነው ። ይህን አጠራር ብቻውን የሚለውን ሙገሳ ሐዋርያው ይወደዋል ። ምስጋናውን ማንም ሳይጋራው ብቻውን የሚመለክ ጌታ ነው ። /ሮሜ 16፡27፤ 1ጢሞ. 6፡16 ።/ እርሱ ብቻ ምስጉን ፣ እርሱ ብቻ የማይሞት ፣ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ነው ።
አምላክ የሚሆን፡- አምላክነትን የከጀሉ ፣ መመለክን የፈለጉ አያል ናቸው ። ከሳጥናኤል እስከ አዳም ፣ ከፈርዖን እስከ ሮም ቄሣሮች መመለክን በአዋጅ ፈልገዋል ። አምልኮ ግን አምላክነት ያሻዋል ። መመለክ የፈለጉ ሁሉ የያዙትንም ክብር አጥተው ቀርተዋል ። “የቆጡን አወርድ ብላ የብብትዋን ጣለች” የተባለውም ለእነርሱ ሳይሆን አይቀርም ። እግዚአብሔር ግን አምላክ ነው ። የአምልኮ ወራሽ እርሱ ብቻ ነው ። የሠራነውን ጣዖት ሳይሆን የሠራንን አምላክ ማምለክ መታደል ነው ።
የማይጠፋ፡- ነገሮችን ከቦታቸው ስናጣቸው ያስደነግጣሉ ። ከተሞች እንኳ በሥልጣኔ ስም ሲጠፉ ትዝታ ያለባቸው ሰዎች ይተክዛሉ ። ትላንት የነበሩ ዛሬ የሉም ። ዛሬ አደባባዩን የሞሉት ነገ ይጠፋሉ ። የማይጠፋው ግን እርሱ ብቻ ነው ።
የማይታይ፡- ፎቁን ስናይ መሠረቱን ግን አናይም ። የሚታየውን ፎቅ የተሸከመው ግን የማይታየው መሠረት ነው ። እግዚአብሔር መሠረት ነውና አይታይም ። የሚታዩትንና የማይታዩትን የፈጠረና የተሸከመ ነው ።
የዘመናት ንጉሥ፡- ከሁለት ጊዜ ምርጫ በላይ የሚገዙ ጤነኛ አይደሉም እየተባለ ይነገራል ። ዘመናዊነት የስምንት ዓመት ነገሥታትን እያስገኘ ነው ። አንዳንዶችም በመጀመሪያው አራት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቅቃሉ ። በአንድ ቀንም ከሥልጣን የወረዱ በታሪክ ተመዝግበዋል ። የሰባት ቀን ንጉሥም በአገራችን አይተናል ። እግዚአብሔር ግን የዘመናት ንጉሥ ነው ። “ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ” የተባለለት ነው ።
በቸርነትህ ይህን ቀን ላሳየኸኝ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና ላንተ ይሁን ፤ አሜን ።
1ጢሞቴዎስ /19/
ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.

ያጋሩ