የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከግፈኞች ጋር አትተባበር

“በምድር ላይ ብቻህን ብትቀር እንኳ ከግፈኞች ጋር አትተባበር ።” ማኅተማ ጋንዲ

ውግዘት የምንለው ነገር አጥፊውን ሰው ከቤተ ክርስቲያን ፍቅር ፣ ከምእመናን ኅብረት በመለየት መቅጣት ነው ። እንደ ውሻ በማባረር ስሙን በማሳነስ ሳይሆን እንደ ሰው በማክበርና ጊዜ ሰጥቶ አሳቡን በመጠየቅ የሚፈጸም ውሳኔ ነው ። ያ ሰው የሚቀጣው በስድብና በነገሥታት ዱላ ሳይሆን ፍቅርንና ኅብረትን በማጣት ነው ። ጠፍቶ እንዲቀር ወይም አስወጥቶ በር መዝጋት ሳይሆን ውግዘት በፍቅርና በኅብረት ረሀብ ቀጥቶ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ማድረግ ነው ። ቤተሰባዊ ቅጣት እንጂ ውግዘት የበቀል በትር አይደለም ። ያለ በቂ ምክንያት የሚያወግዝም ራሱ የተወገዘ ፣ የኣላውያን ወዳጅ ፣ የአረማውያን ጓደኛ ነው ። ክርስቶስ የሞተለትን ሰው በማባረሩ የክርስቶስን ደም የረገጠ ነው ። በቤተ ክርስቲያን ፍቅሩ በሽንገላ ፣ ኅብረቱ በአድማ ከተተካ ውግዘቱ በቂ ቅጣት መሆን አይችልም ። የሄደውም ለመመለስ አያስብም ። የተሻለ ክፉ እየፈለገ ፣ ራሱን እየደለለ ይኖራል ። ቢሆንም ውግዘት የሚፈራው መለየት ፣ መውጣት ፣ ብቻ መሆን ስላለው ነው ። እንደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፖፑ አይሳሳትም አንልም ፣ በማይሳሳቱ የሃይማኖት መሪዎች እየተመራን አይደለምና ኦርቶዶክሳዊነት ሁልጊዜ የመታረም ሕይወት ነው ። የተወገዘም ርጉም ፣ ያወገዘም ቡሩክ አይደለም ። ውግዘት በጥቅም ፣ በጥላቻ ፣ በጉቦ ፣ ለፖለቲካ በማደር ፣ በቡድን ስሜት ፣ በጎሠኝነት ሊከናወን ይችላል ። ውግዘት መክሮ ዘክሮ አልመለስ ያለውን ልጅ በፍቅር የመቅጣት ሥርዓት ነው ። ዓላማውም አስወጥቶ በር መቆለፍ ሳይሆን እስኪመለስ መጠበቅ ነው ። ታዲያ ውግዘትን በመፍራት እውነትን ሐሰት ማለት ፣ መገለልን በመስጋት ከእግዚአብሔር መለየት አይገባም ። ሰማይን በምድር ፣ ቤተ ክርስቲያንን በዕድር መለወጥ ስሌትን አለማወቅ ነው ። ግፈኞች በቅንዓት ተነሣሥተው ፣ ቅንዓታቸውን የሃይማኖት ካባ አልብሰው እናውግዝ እናጥፋ ቢሉን ከግፈኞች ጋር መተባበር አይገባንም ።

“ጊዜ የሰጠው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል” ይባላል ። ወቅታዊ ርእስ ፣ ስሜት እውነት እንዲመስል ያደረገው ወሬ ፣ ሁሉ የተስማማበት ጥበት ፣ እንደ መጨረሻው ቀን አድርጎ የሚነጋገርበት ክፋት ወደ እኔ ኑ ይላል ። ሌላው ግሎ መቀዝቀዝ ፣ ብዙኃኑ ተስማምቶ እኔ አልስማማም ማለት ለሥጋዊ ፍርሃት ከባድ ነው ። ልዩ ሰው ላለመሆን አዎ አዎ ማለት ፣ ላለመገለል ግፍን ማድነቅ ፣ ዕድሩን እቁቡን ላለማጣት ሕሊናን መሸጥ ፣ ብቸኛ ላለመሆን ትልቁን ጌታ መጣል አይገባም ። በማኅፀን ዓለም ብቻችንን ነበርን ፤ እናታችን ሳታየን ያየን የነበረው እግዚአብሔር ነው ። በመቃብርም ብቻችንን እንቀበራለን ። ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እንሆናለን ። ይህችን የመተላለፊያ ዓለም ፣ የመሻገሪያ ድልድይ ለማትረፍ ብለን ነፍሳችንን ማሰቃየት አይገባንም ። ማኅበረሰብ ነጻ ብሎን ሕሊና እስረኛ ከሚለን ፣ ሕሊና ነጻ ብሎን ማኅበረሰብ ቢያስረን ይሻላል ። ለመለየት ብለን አንድ ነገርን ማድረግ እብደት ነው ። ልዩ ሰው መሆን የታይታ ጥማት የሚወልደው ነው ። ልዩ ሰው መሆንን ስንመርጥ ልዩ መከራ ይገጥመናል ። ድሀን ሁሉም ሲረግጠው ፣ ብቸኛውን ሁሉም ሲያሳድደው እንቢ ብለን ከተገፋው ጋር መቆም ያስፈልጋል ። ይህ መገለልን ያስከትላል ። ሳይረዳን የራቀን ሰው የተረዳን ቀን ይመጣል ። ትልቁ ብቸኝነት ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር መራቅ ነው ።

ባሕልና ልማድ የሰው ልጆችን ረጅም ታሪክና ድካም የሚገልጥ ያልተጻፈ ግን የሚኖሩት መጽሐፍ ነው ። ባሕሉና ልማዱ ብዙ መልካም ነገር ያለው የብዙዎች ብቻ ሳይሆን የትውልዶች ስምምነት ነው ። ማኅበረሰቡን አስተሳስሮ ያቆመ በመሆኑ ባሕልና ልማድ መልካም ነው ። ሁሉም ባሕልና ልማድ ግን ጥሩ ነው ማለት አይቻልም ። ባሕልና ልማድ አንዱ ሲሽረው ሌላው ነጋሢ ደግሞ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት ከፍ ያደርገዋል ። ባሕልና ልማድ እውነትንና የሰው ልጆች የደረሱበትን ተጨባጭ ሥልጣኔ የሚገፋ መሆን የለበትም ። ባሕልና ልማድ የሰው ልጆችን እኩልነትና ክብር የሚጋፋ መሆን የለበትም ። ባሕልና ልማድ ጤናንና የአካልን ደኅንነት የሚሽር መሆን የለበትም ። ባሪያና ጨዋ የሚል ባሕል ፣ አጋንንትን የሚያነግሥ ልማድ ፣ የሰውን ጤና የሚጎዳ ተግባር ፣ አንዱን ዝቅ የሚያደርግ ምሳሌም ሆነ ጥቅስ ሊወገዝ ይገባዋል ። ባሕልንና ልማድን ስንከተል የእግዚአብሔር ቃል ምን ይላል ማለት አለብን ፣ ዘመኑን የመጠነ እውቀትን የተላበሰ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልገናል ። የሰውን ጤናና አካላዊ ክብር የሚጠብቅ መሆኑን መመርመር ያስፈልጋል ። ብቻዬን እቀራለሁ ብሎ በመስጋት አጉል ባሕልና ልማድን መከተል አይገባም ። ከአንድ በላይ ትዳር ልማድ ሆኗል ። ልማድ ስለሆነ ግን የሚከበር መሆን የለበትም ።

በምድር ላይ አንድ ዘር አለ ። እርሱም የአዳም ዘር ነው ። ሌላው ግለሰብ ፣ ቤተሰብ ፣ ጎሣ ፣ ነገድ እያለ የሚያድግ ስብስብ ነው ። ነገደ ካም በማለት አፍሪካንና እስያን ፣ ነገደ ሴም በማለት እስራኤልና ዐረብ ኢትዮጵያን ፣ ነገደ ያፌት በማለት አውሮፓን እንጠራለን ። ቅርንጫፉ ቢበዛም ግንዱ ግን አንድ ነው ። አንድ እግዚአብሔር ያበጀን ነን ። ሁለት አዳሞችን ያልፈጠረው የሰውን መገኛ ከአንድ ምንጭ ያደረገው ለአንድነታችን በማሰብ ነው ። መላእክት አንድ ጊዜ በብዛት ሲፈጠሩ ሰው ግን አንድ ሁኖ ተፈጥሮ በየጊዜው የሚባዛ ነው ። በተለምዶ ዘረኝነት የምንለው ጎሠኝነት የሰውን ልጅ ከትልቁ ቤተሰብ የሚያወጣ ፣ የሚኖርበትን ዓለም የሚያጠብ ነው ። የመጨረሻው ዘመን መገለጫ ጎሠኝነት ነው ። የሰይጣን ቀጥተኛ ወኪል የሆነው አውሬው ጎሠኝነትን ያራምዳል ። “በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው” ይላል ። ራእ. 13 ፡ 7 ። መለያየትን ያመጣል እንደ ማለት ነው ። ጌታችንም፡- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና” ብሏል ። ማቴ. 24 ፡ 7 ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚነሣው በጎሠኝነት ስሜት ነው ። የሕዝብ ለሕዝብ እልቂት ያድግና መንግሥት ለመንግሥት ደግሞ ይዋጋል ። የትንቢት መፈጸሚያ እየሆነ ያለ ሰው ካለ ፣ የአውሬ ተከታይ ሊባል የሚገባው ጎሠኛ ወይም ዘረኛ ሰው ነው ። ከቤተሰብ ካገር ልጅ ላለመገለል ብሎ ሃይማኖቱን ሳይቀር ችላ ብሎ ጎሠኛ የሆነ ብዙ ሰው አለ ። ትላንት ክርስቶስን በሰበከበት አፉ አሁን ስለ መንደር ሲያወራ ሐፍረት የማይዘው አያሌ ነው ። ብቻዬን እቀራለሁ ብሎ ዘረኛ የሆነ ሰው አለ ። ስለዚህም ግፍን በደልን ያደንቃል ። ብቻችንን ብንቀር እንኳ ዘረኛ መሆንን መጠየፍ ይገባናል ።

ብቻቸውን ላለመቅረት የሚዘርፉ ፣ በመጠጥ የሚናውዙ ፣ በጊዜ ወደ ቤት ለመግባት ፈልገው የሥራ ዕድል አላገኝም እያሉ መጠጥ ቤት ከባለጠጎች ጋር የሚያመሹ ፣ ኃጢአትን የሚያደንቁ ፣ እግዚአብሔር ለጠላው ነገር እውቅና የሚሰጡ ፣ የእነርሱ ጎሣ ያደረገውን ግፍ ጽድቅ ነው ብለው የሚያሞካሹ አያሌ ናቸው ። የሕንዱ የነጻነት ታጋይና መሪ ማኅተማ ጋንዲ ያሉትን መከለስ ይገባል፡- “በምድር ላይ ብቻህን ብትቀር እንኳ ከግፈኞች ጋር አትተባበር ።”

የብርሃን ጠብታ 28

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።