ከክርስቶስ ልደት በፊት በ59 ዓመት በጁልየስ ቄሣር ዘመን የተጀመረው ጋዜጣ በጣልያንኛ ስሙ “ጋዜታ” የ90 ዓመት ዕድሜውን ለማክበር ጠብ እርግፍ የሚልበት ሰሞን ነው ። በሰሌዳ ላይ ተለጥፎ ሕዝብ የሚያነበው በኩሩ ጋዜጣ “አክታ ዲዮረና” በልዩ እትሙ የሮማን መንግሥትና ሕዝብ ለማስደሰት እየጣረ ነው ። “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ” የሚለው አባባልም በብርቱ እየተነገረ ነው ። ሮማ ያልገዛችው ግዛት አልነበረምና ። ከሮም እስከ ኢንግላንድ ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ሩቅ ምሥራቅ ፣ ደግሞም እስከ ሰሜን አፍሪካ በክንዷ ያላንበረከከችው አይገኝም ነበር ። በኩሩ ጋዜጣም የቅኝ ግዛት ዜናዎችን ፣ አስገራሚ ክስተቶችን እየሰበሰበ ነው ። ታላቁ እስክንድር ባለመጽሐፍ የሆነውን ፣ አደረጃጀቱ የሰለጠነውን የአይሁድን እምነትና ክህነታዊ ሥርዓት እውቅና ሰጥቶት ስለነበር ከእርሱ በኋላ የመጣው የሮማ አገዛዝም ተቀብሎት ነበር ። ከምድረ እስራኤልም ልዩ ዜና ይጠበቅ ነበር፤ አንጾኪያ ፣ ቁስጥንጥንያ የሮማ መንግሥት ትልቅ መናገሻዎች ቢሆኑም ኢየሩሳሌም ደግሞ የበለጠ ታሪካዊ ግዛቱ ናት ። ይልቁንም በእስራኤል የተነሣው መሢሑ ክርስቶስ ዝናው ወደ ሮም ተሰምቶ በጥንቃቄ ይመረመር ነበር ። ሰላማዊነቱ ስለ ታወቀም የሮማ መንግሥት በቸልታ አልፎታል ። ከሮማ እውቅ ባለሥልጣናትም የእጁን ተአምራት የቀመሱ አሉ የሚለው ዜና በሮም ተሰምቶ ነበርና የመቶ አለቃውን ወደ ሮም መምጣት ጋዜጠኞች ሁሉ በጉጉት ይጠብቃሉ ።
የመቶ አለቃው ከረጅም ጉዞ በኋላ በሮም ወዳለው ቤቱ ደረሰ ። ከወትሮ በተለየ ብዙ የወሬ አነፍናፊዎች ይጠብቁታል ። የጋዜጣው ዕድሜ ዘጠና ሞልቷልና ለዚያ ልዩ እትም የእርሱ ቃለ ምልልስ በጣም ማራኪ ገጽ ያደርገው ነበር ። ይልቁንም በምድረ እስራኤል ያለ ሐኪም ቤት ይፈውስ ፣ ያለ ሆቴል ይመግብ ፣ ያለ ማደሪያ ብዙዎችን ያስከትል ስለነበረው ስለ ክርስቶስ የሚያውቀውን ምስክርነት እንዲሰጥ ይጠበቃል ።
የመቶ አለቃውም ብላቴናውን እንዴት እንደ ፈወሰለት ዜናው ሮም ድረስ በመሰማቱ ደስ ብሎታል ። ቅዱስ ማቴዎስን አግኝቶ የተራራው ስብከት እንደ ተፈጸመ በስምንተኛው ምዕራፍ ላይ ጻፍልኝ ብሎታል ። ቅዱስ ሉቃስንም አግኝቶ ሰባት ቊጥር የፍጹምነት ምልክት ናትና በሰባተኛው ምዕራፍ ላይ ዘግብልኝ ብሎታል ። አሁን ደግሞ በሮማ ጋዜጣ ላይ ዜናው የመውጣቱን ነገር ሲያስበው ልቡ በደስታ ተሞላ ። የክርስቶስ ተአምር አይሸሸግምና ። ጋዜጠኞቹም አዋከቡት ። “አንተና ክርስቶስን ምን አገናኛችሁ ?” በማለት በጫጫታ ውስጥ ጠየቁት ። “ያገናኘን ጣር ነው” ብሎ በጫጫታ ውስጥ መለሰ ። በልቡም፡- “ካልተወጋ ሰው መቼ ክርስቶስን ያመልካል” አለ ። የሮማ ቋንቋ ድምፁ ኃይል አለውና ሴቷ ጋዜጠኛ “እርሱን የለመንከው ስለ ባሪያህ ነው ይባላል ፣ ይህ የሮማን መንግሥት ክብር አይነካም ወይ ?” ብላ በጩኸት ጠየቀችው ። “አዎ ክብራችን ካልተነካ ክብሩን ማወቅ አይቻልም ። በሁለት ወገን ክብራችን ተነክቷል ። የመቶ አለቃው ከአንድ ምስኪን መምህር ዘንድ ደጅ በመጥናቱ ፤ ሁለተኛ ባሪያ እንደ ዕቃ በሚሸጥበት ግዛት ስለ ባሪያ በመማለዱ ክብሩ ተነክቷል ። ክብር ከሰማይና ከምድር ትርጉሙ ልዩ ነው ። ምድር ክብር የምትለውና ሰማይ ክብር የሚለው ይለያያል” በማለት መለሰ ። በጫጫታ ውስጥ ያለው ቃለ መጠይቅ ማስታወሻ ላይ ለማስፈር አላመች አለ ። በዚህ ጊዜ የተመረጡ “የአክታ ዲዮረና” ጋዜጠኞች ፀጥታ ባለው አጸድ ውስጥ የመቶ አለቃውን እንዲያነጋግሩ ተወሰነና ብዙዎች ተበትነው ሁለቱ ጋዜጠኞች ከመቶ አለቃውን ጋር ተቀመጡ ።
“በእስራኤል የተነሣውን ክርስቶስን ታውቀዋለህ?” በማለት አንደኛው ጋዜጠኛ ጠየቀ ። የመቶ አለቃው ግን በግርምት ፈገግ አለ ። ትንሽ ጥያቄም መስሎ ተሰማው ። “ክርስቶስ ያውቀናል እንጂ ገና አናውቀውም ፣ ባወቅነውም ቊጥር አለመታወቁ እየሰፋ ይሄዳል ፤ እርሱ ስለ እኛ ባለው እውቀት እናርፋለን እንጂ እኛ እርሱን በማወቃችን አንጠነቅቀውም” አለ ። “በመጀመሪያ እርሱን ባገኘኸው ጊዜ ምን ተሰማህ?” አለችው ሴቷ ጋዜጠኛ ። እርሱም፡- “ከክርስቶስ ጋር መገናኘት ከብርሃን ጋር እንደ መገናኘት ነው ። ብርሃን በጠባዩ ራቁትነትን ያሳያል እንጂ አይሸፍንም ። እርሱ ግን የሚሸፍን ብርሃን ነው ። ብርሃን የለበሰ ፣ በሰማይም በምድርም ያለ እርሱ ነው” በማለት መለሰ ። ሁለቱም ጋዜጠኞች ቃለ ምልልሱ አላረካ አላቸው ። መቶ አለቃው እንዲሁ ቢተርከው ተመኙ ። “ራስህን በክርስቶስ እንዴት አገኘኸው?” በማለት ጠየቁት ። እርሱም፡- “እንኳን እናቴ ሙታብኝ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” የሚለውን ብሂል ጠቅሶ የባለ ዝናውን ዝና መተርተር ጀመረ ።
የሮማ መንግሥት መቶ አለቃነት እንዲህ በቀላሉ የማይገኝ ነው ። ከአዝማደ መንግሥቱ አንዷን በማግባት ደጃዝማችም ፣ ፊታውራሪም መባል ይቻላል ። መቶ አለቃነት ግን ሙያና የጥረት ውጤት ነው ። ውትድርናዬን ሳስበው አመጋገቤ ፣ የሰውነት እንቅስቃሴዬ ፣ ታዛዥነቴ ፣ ትዕግሥቴ ሁሉ ተጠቃለው ያሉበት ነው ። ያለ ዓላማ ከመኖር በዓላማ መሞትን የሚያከብር ነውና ወታደርነቴን እወደዋለሁ ። ስሙም ወጥቶ አደር ማለት ነው ። በከተማ የሚያውደለድል ፣ ሀብታምና ቆንጆ ሴት የሚጠብቅ ሳይሆን ወጥቶ የሚያድር በመሆኔ ስሙም ግብሩም ኩራቴ ነው ። ለአገሬ ለመንግሥቴ ሕይወቴን የምሰጥ በመሆኔ ታላቅ ክብር ይሰማኛል ። የምኖረውም ሕይወት ለመስጠት ሳይሆን ወታደር የሆንኩት ገና ከጅምሩ ሕይወቴን ሰጥቼ ነው ። የተሠዋ ሕይወት አይፈራም ። የሞተ ሞትን አይሰጋም ። ንጽሕና ፣ ንቃት ፣ ማልዶ መውጣት ፣ ለሰላም ዋጋ መክፈል የወታደርነት መለያ ነው ። ተመልከት ዓላማህን ፣ ተከተል አለቃህን የሚለውን መመሪያ እወደዋለሁ ። በዓላማዬ መሠረት አለቃዬን የምከተል ነኝ ። እንዲህ ዓይነት ሥነ ሥርዓት ባይኖር ኑሮ ዓለም የጨምላቃ አስተዳደግ መድረክ ትሆን ነበር ። እናንተ በከተማ እንድትንጎማለሉ ወታደር በበረሃ ፣ በድንበር መቀመጥ አለበት ። ቤዛ ባይኖር ሕይወት አይቀጥልም ነበር ። ጨዋ ለመሆን አዳሪ ትምህርት ቤት ወይም ወታደርነት መልካም ነው እያሉ የሮማ ሰዎች ሲናገሩ ትሰማላችሁ ። እኔም ሰው ሁሉ ወታደር ቢሆን እመኛለሁ ። ብቻ ሰው ሁሉ ወታደር ባይሆንም ወታደር ሁሉ ግን ሰው ነው ።
የመቶ አለቃው ከመቀመጫው ብድግ አለ ። ጋዜጠኞቹም ከተመስጦ ሰመመን ነቁና ቆሙ ፤ እርሱ ግን፡- “እናንተ ተቀመጡ ፣ እኔ ግን ቆሜ የእርሱን ዝና ልተርክ” በማለት ስለ ክርስቶስ ለመናገር ፈለገ ። መሐል ባሕር ላይ እንደ ለቀቁት ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚሄድ ተጨነቀ ። እንደ ምንም ብሎ ትረካውን ጀመረ ።
“ሰዎች ሁለት ደግነት አለህ ይሉኛል ። የመጀመሪያው ባሪያህን እንደ ልጅህ ማየትህ ሲሆን ሁለተኛው ሰዎችን የምትወድና ካንተ በሚፈልጉት ነገር ቀድመህ መገኘትህ ነው ይሉኛል ። ሁለተኛውን አሳብ የሚሰነዝሩት አይሁድ ናቸው ። ምኩራብ ሠርቼላቸዋለሁ ። እኔ ለደስታዬ የሠራሁትን እነርሱ የዝናዬ ስም መጥሪያ አድርገውታል ። ለዝና የሠሩት ለደስታ አይሆንም ፣ ለደስታ የሠሩት ግን ለዝና ይሆናል ። ሁለት መቅደስ እንደ ሠራሁ ይሰማኛል ። አንደኛው የአይሁድ ምኩራብ ነው ። እርሱ ሰው ተሰብስቦ የእስራኤልን እምላክ የሚያመልክበት ነው ። ሁለተኛው መቅደስ ግን ራሱ እግዚአብሔር የሚያድርበት የሰው ልጅ ነው ። ባሪያዬን ያገኘሁት በሶሪያ ውጊያ ምርኮኛ ሁኖ ነው ። ምርኮኛ ሁሉ ወደ ሮማ መንግሥት ገብቶ ከዚያም በመሸጥ መንግሥቱ ያወጣው የጦርነት ወጪ ይካካሳል ። እኔም የማረክሁትን ገዝቼ ባሪያዬ አደረግሁት ። በሁለት ዋጋ የእኔ ሆነ ። ከሁሉ የሚያስደስተኝ ግን በፍቅር እንደገና ልጄ አደረግሁት ። ባሮች ሁሉ ሕመማቸው ጌቶች ናቸው ። ይህ ባሪያ ግን አባት ሲያገኝ ታማሚ ሆነ ። ዓለም በአንደኛው ጎኑ ቀዳዳ ነው ። ሕመሙ ያዝ ለቀቅ እያለ ቢዘልቅም አሁን ግን እየበረታ መጣ ። በቅፍርናሆምም ታላላቅ ተአምራትን መሢሑ እንደሚደርግ ብሰማም በየትኛው ማንነቴ በፊቱ እቆማለሁ እያልሁ አመነታ ነበር ። አንድ ቀን የብላቴናዬ ሕመም ጠንቶበት መላው ቤተሰብ ከእኔ ጋር ሲጨነቅ ድንገት ብድግ ብዬ ከቤቴ ወጣሁ ። በጎዳናውም የአይሁድ ረቢዎችም ከምኩራብ ወጥተው ለጉብኝት ወደ ምእመናን ቤት ሲሄዱ አየሁ ።እነርሱም ምንም እንኳ አይሁድ ካልሆነ ጋር በገደብ የሚቀራረቡ ቢሆኑም እኔ ግን ስለምወዳቸው ይወዱኝ ነበር ። ሮማዊነቴን ዘንግተው አይሁዳዊ እመስላቸው ነበር ። ፍቅር አገርና ጎሣን ያስረሳል ። ፍቅር ግዛቱ እግዚአብሔር በሚገዛበት ሁሉ ነውና ጥበት አይስማማውም ። ምን ሆነሃል? የመቶ አለቃ ሲሉኝ እኔም ከእንቅልፍ እንደ መንቃት ብዬ ደህና ነኝ አልኳቸው ። እነርሱም ወዲያው ገባቸው ። ከብዙ ሰው ጋር በመኖራቸው የሥነ ልቡና አዋቂ ሁነዋል ። ብላቴናህ ሕመሙ ጠናበት ? አሉኝ ። እኔም አዎ አልኳቸው ። መቼም ስለ ወዳጅ እሬት ይላሳል ። እኛ ባናምንበትም ፣ ወንበራችንን ሊፈነቅል የመጣ ቢመስለንም ያ ኢየሱስ የተባለው እንዲፈውስልህ እስቲ እንጠይቀው ሲሉኝ እባካችሁ ብዬ መሬት ላይ ወደኩኝ ። በዚያ ቀን አንድ ለምጻምን ፈውሶ የመንደሩ ሰው ሁሉ ግብዣ አድርጎለት በቅፍርናሆም ነበረ ።
የምኩራብ አለቆችን ከፊት አስቀድሜ እኔ ከኋላ ራቅ ብዬ ወደ መሢሑ ሄድሁ ። ‘ይህን ልታደርግለት ይገባዋል ፣ ብላቴናው ታሞበታል ። ሕዝባችንን ይወዳል ፣ ምኩራብም ሠርቶልናል’ አሉት ። ክርስቶስም ‘ልክ ናችሁ ፖለቲካውን ለማርጋት ሕዝቡን ሳይወድ ምኩራብ የሚሠራ አለ’ አላቸው ። እነርሱም በደመ ነፍሳቸው እውነት መናገራቸውንና እርሱም የሰማቸው መሆኑን አስተዋሉ ። ክርስቶስም ቀጠለ፡- ‘ፍቅር ያለውም ምኩራብ መሥራትን አይተውም’ በማለት ፍቅር አካል እንዳለው ተናገረ ። ቃሎቹ እያስገመገሙ ወደ ልቤ ይመጡ ነበር ። እርሱ ግን እነርሱን አልፎ ወደ እኔ መጣ ። እኔም ችግር አደባባይ ያውላልና ፣ ችግር ክብርን ያስጥላልና መለፍለፍ ጀመርሁ ። ‘ጌታ ሆይ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል’ ብዬ ለመንሁት ። ‘ባሪያህን ልጄ በማለትህ የፍቅር ሰው ነህ ። ባሪያና ጌታ የሚለውን ቃል የፈጠረው የሰው ዓመፀኛነት ነው ። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው እኩል አድርጎ ነው ። በአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ ፣ በአያቱ ድሀ ያልነበረ ሀብታም የለም ። ቦታ መለዋወጥ ሲመጣ አንተ ባሪያ እርሱ ጌታ ሊሆን ይችላል’ አለኝ ።”
ሁለቱም ጋዜጠኞች በመቶ አለቃው የሚነገረውን የክርስቶስን ቃሎች ለመስማት ድንገት ብድግ ብለው ቆሙ፡- ‘መሢሑ ሥጋዊ አካልም ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን የዛጉ ልቦችን አዳሽ ነው’ አሉ ። በመቀጠል፡- ‘ለባሪያህ ስለ ነበረህ ፍቅር ካደነቀህ ለጌትነትና ለቅምጥል ኑሮ የመጣ አይደለም’ አሉ ። እርሱም የጀመረውን አሳብ ሳይረሳ ለመቀጠል አንገቱን አወዛውዞ የዚያን ቀን ትርክት መተንተን ቀጠለ፡-
ይቀጥላል