የጻድቃንን ጥበብ መታዘዝን ፣ ዓለሙን ከሠራው ጋር መስማማትን እንዳልመርጥ ፣ አላሳልፍ ያልከኝ እልኸኝነት ከፊቴ ገለል በል ። በሄደበት ሁሉ ጌታዬን እንዳልከተል ደስታዬን የምትዋጋ ፤ በቤተ ልሔም ልደቱ የድሀ ልጅነቴን ፣ በግብጽ ስደቱ በወገን መገፋቴን ፣ በናዝሬት ዕድገቱ የቀደመ ታሪኬን ፣ በዓርብ መከራው የተዛባ ፍርዴን እንዳልቀበል የምታደርገኝ አንተ እኔነት ከፊቴ ገለል በል ። የተጠሩትን በር ላይ ቆሜ እንድመልስ ፣ የተመረጡት ላይ ጭቃ እንድለጥፍ ፣ የተወደዱትን እንዳጠለሽ የምታደርገኝ አንተ ቅንዓት ከፊቴ ገለል በል !
የሞላውን ምስጋና እንዳጎድል ፣ የበዛውን ውዳሴ እንዳሳንስ ፣ የተደረገልኝን እንዳላይ ፣ የተሰቀለውን ጌታ እንዳላስተውል የምታደርገኝ አንተ ማጉረምረም ከፊቴ ገለል በል ። ለታመነልኝ አምላክ እንዳልታመን ፣ የወደዱኝን እንድጠላ ፣ ያከበሩኝን እንዳዋርድ ፣ የቀረቡኝን እንድርቅ ፣ ትላንተ የሰጡኝ ላይ እንድጨክን የምታደርገኝ አንተ ከዳተኝነት ከፊቴ ገለል በል !
በእግዚአብሔር መቻል እየተጠራጠርሁ ፣ በራሴ መቻል እንድታመን የምታደርገኝ ፣ የተዋረደውን ሰዋዊ ፍልስፍና ከመለኮት መገለጥ ጋር ቁመት የምታለካካኝ አለማመን ሆይ ከፊቴ ገለል በል ። ድንቅ ያደረገውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን እንዳቃልል ፣ ደሙን እንዳላከብር ፣ ሞቱን እንዳልናገር ፣ ትንሣኤውን እንዳልመሰክር የምታደርገኝ አንተ ይሉኝታ ከፊቴ ገለል በል ። ስለ አቋም ትቼ ስለ አቋቋም ፣ ስለ ማወቅ ችላ ብዬ ብዬ ስለ መታወቅ ፣ ሥራን ጠልቼ ስፍራን እንድወድ የምታደርገኝ አንተ ከንቱነት ከፊቴ ገለል በል ። በቂም ቋጥረህ ዓይኔን ያጨለምህ ፣ በበቀል አሰማርተህ የአምላኬን ምሕረት ያስረሳህ ፣ የመላእክትን ወዳጅነት ሳይሆን የሰውን ሸርታታነት እንዳስብ የምታደርገኝ አንተ ዓለማዊነት ከፊቴ ገለል !
ጌታ ሆይ ! አንተ በሰማይ ታከብረኛለህና ፣ ሥራዬን ጨርሼ በምድር አከበርሁህ ለማለት አብቃኝ ። የሚሰማ ሁሉ አሜን ይበል !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም