የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወርቀ ደሙ

“በውድ ልጁም ፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን ፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት ። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ።” ኤፌ. 1 ፡ 7-8 ።

እግዚአብሔር የጸጋ አምላክ ነው ። ጸጋውም ባለጠጋ ነው ። እግዚአብሔር አለ ፣ ጸጋው አለ ፣ የጸጋው ባለጠግነት ደግሞ አለ ። እግዚአብሔር የነገር ሁሉ ሥር መሠረት ፣ ጅማሬ ሳይኖረው ሁሉን ያስጀመረ ነው ። ጸጋው ሥጋና ነፍሳችንን ያገኘንበት ፣ ተበላሽተን እንደገና የተሠራንበት አምላካዊ መግቦት ነው ። የጸጋው ባለጠግነትም መንፈስ ቅዱስን የተቀበልንበት ፣ የአገልግሎት ስጦታዎችን ያገኘንበት ፣ ቤተ ክርስቲያንን /መንፈሳዊ ቤተሰብን ያተረፍንበት ፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬና ስጦታዎችን ያገኘንበት ፣ ተቆጥሮ በማያልቅ ፣ በሰፊ እጅ የተሰፈረ መኖሪያችን ነው ። በምድር ላይ ባለጠጋ ተብለው የሚጠሩ አሉ ። እውነተኛው ባለጠጋ ግን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ናቸው ። በምድር ላይ ሦስት ነገሮች ገዥዎች ናቸው ። እውቀት ፣ ሥልጣንና ሀብት ። እውነተኛው እውቀት እግዚአብሔርን ማወቅ ነው ፣ ከመንግሥት ሥልጣንም የክህነት ሥልጣን ይበልጣል ። ሀብተ መንፈስ ቅዱስም ከቁሳቁስ ይልቃል ። እግዚአብሔርን በማወቅ ውስጥ ራስን መግዛት አለ ። በአገልግሎት ውስጥም የጨለማውን ኃይል ማሸነፊያ ሥልጣን አለ ። መንፈሳዊ በረከትም ሰጥተን የማያልቅብን ብዙ ሀብት ነው ። ስለዚህ ምእመናን ገዥዎች ናቸው ። እውቀት ፣ ሥልጣንና ሀብት አላቸውና ።

ባለጠጋ ተብሎ የሚጠራ ሰውን እናስታውስ ። ቤት ንብረት ያለው ሰው ባለጠጋ ይባላል ። ባለጠጋ መባሉ የተሰጠው እንጂ የባሕርይ ገንዘቡ አይደለም ማለት ነው ። በእውነትም ዕራቁቱን ወደ ምድር መጥቶ ዕራቁቱን ይመለሳል ። የትላንት ባለጠጎች የዛሬ ድሆች ናቸው ። የዛሬ ድሆችም የነገ ባለጠጎች ናቸው ። የተራ ዓለም እንጂ ቋሚ ዓለም አይደለም ። ተረኛ ባለጠጋ ፣ ተረኛ ትልቅ ሰው ይታያል ። ተራው ሲያበቃ ለቀጣዩ ጥሎ ይሄዳል ። ሲያጣውም ይገባኛል ብሎ አይከራከርም ። ዓለም የእኔ የማትባል ናት ። ሲገዙና ሲነዱ የነበሩ በእስር ቤት ፣ በስደት ዘመናቸውን ሲገፉ ይገባኛል ብለው ግን ሲካሰሱ አይታዩም ። በሕይወት መኖራቸውንም እንደ ዕድል ቆጥረውት ታሪካቸው የልጆች ማሳደጊያ ተረት ይሆናል ። የነበራቸው ሁሉ የባሕርይ ገንዘባቸው ሳይሆን የመንገድ ስንቃቸው ነበር ። ሰው ስንቁን ሊጨርስ ይችላል ፣ ጣቶቹን ግን አይጨርስም ። ቤቱን ትቶ ይሰደዳል ፣ ኩላሊቱን ትቶ ግን አይሰደድም ። የባሕርይ ገንዘብ ከህልውናው ጋር የሚኖር ነው ። ገንዘብ የመንገድ ስንቅ ነው ። ሀብታምነትም ለጊዜው ነው ፣ እውነተኛ ሀብት ክርስቶስ ብቻ ነው ። ይዘው ሲገኙ እንጂ ነበረኝ ቢሉ ማንም አያምንም ። ዓለም ስትሄድ አሻራ እንኳ ሳትተው ነው ። ሲረታ የማያውቅ ሞኝ ፖለቲከኛ ነው ።

እግዚአብሔር የሥጋና የነፍስ ባለቤት ነው ። ሆድን ፈጥሮ እንጀራን አይነሣም ። ነፍስንም ፈጥሯልና ቃሉን ይልካል ። በመግቦቱ አድልኦ የሌለው ሥጋና ነፍስን ፈጥሮ የሚያኖር ነው ። እውነተኛው ባለጠግነት ግን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ነው ። ሰባኪው ደሀ ቢሆን ፣ ካህኑ ምስኪን ቢሆን ትልቁን ሀብት ግን ይዘዋል ። ናኝተውት የማያልቅ ሀብት ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ነው ።

ጸጋው መዳናችን ነው ። በዚህ ውስጥ ብዙ ሀብታት አሉ ። መንፈስ ቅዱስ ባይተዋርነት እንዳይሰማን ወደ እኛ የመጣው ድኅነት በመፈጸሙ ነው ። የሙት ልጅ ስሜት እጓለማውታነት እንዳያሰቃየን መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነው ። እርሱ በበረሃ የተገኘ የሕይወት ምንጭ ነው ። ቤተ ክርስቲያንም የጸጋው ባለጠግነት መገለጫ ናት ። በቤተ ክርስቲያን ሰዎች በየዕለቱ ከነፍስ እስራት ይፈታሉ ። ዓለም ሁሉ የኰነነው በቤተ ክርስቲያን ግን ጸሎተ ንስሐ ይደገምለታል ። ብቻዬን ነኝ ለሚለው ብዙ ወንድሞችና እኅቶችን በቤተ ክርስቲያን ያገኛል ። እንደ ክርስቶስ የሚያዛምድ የለም ። ይህ መንፈሳዊ ዝምድና ቀሎባቸው ወንድም እኅቶችን የሚገፉ ወዮላቸው ።

“በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን” ይላል ። ቤዛ ክፍያ ከሆነ የተከፈለው ደግሞ ደሙ ነው ። የደም ክፍያ በየዘመናቱ አለ ። የደም ክፍያ ለአገር ፣ ለህልውና ይከፈላል ። ክርስቶስም የገዛን በብር ሳይሆን በንጹሕ ደሙ ነው ። አንድ ወርቅን እናስታውስ፡- ይህ ወርቅ በነጋዴ እጅ ሳለ ተወልውሎ በመስተዋት ይቀመጣል ። በገዥው እጅ ግን የአካሉ ዘመድ ሁኖ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀበት ይኖራል ። ነጋዴው ቢወለውለው ሊሸጠው ነው ፣ የማለዳ ጸሎቱም “ከእጄ በወጣልኝ” የሚል ነው ። ወርቁን ሳይሆን ወርቁ የሚያስገኘውን ነገር ይፈልጋል ። ስለዚህም ከማይወደው ጋር ያ ወርቅ ተወልውሎ ይኖራል ። ገዥው ግን አብሮት ቢጎሳቆልም ጌጡ ፣ የቃል ኪዳን ምልክቱ ፣ የስጦታ ልኩ አድርጎ ይይዘዋል ። ለመታጠብ ሲያወልቀው ለደቂቃ እንኳ አያምነውም ። ወርቅ ይሰለባልና አታውጡት የሚባለው ከመሰሰት የተነሣ ነው ። ይህ ወርቅ ፀሐይና ዝናብ ቢፈራረቅበትም የሚኖረው ከሚወደው ጋር ነው ። እኛም ከሚሸጡን ጋር በዓለም ተወልውለን ፣ በውዳሴ ከንቱ አንቱ ተብለን ኖረናል ። ምነው በሄደልን እያሉን በፊት ለፊታችን ግን አትለየን ከሚሉን ጋር ፣ የእኛ ሳይሆን የእሴታችን አፍቃሪዎች ከሆኑ ጋር አሳልፈናል ። የገዛን ክርስቶስ ግን ፀሐይና ዝናብ ቢኖረውም በእውነት ይወደናል ። እርሱ አካሉ አድርጎናል ። “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በሚል ኪዳን ይዞናል ።

በደሙ ዋጋነት ፣ በቤዛነቱ ደረሰኝ የተቀበልነው የኃጢአታችንን ስርየት ነው ። ብዙ ሰው በሱስ ውስጥ የሚኖረው ስርየትን ስላላገኘ ለመርሳት ብሎ ነው ። ስርየት በመጠጥም ፣ በወርቅም አይገኝም ። በወርቀ ደሙ ዋጅቶ ፣ የነፍስ ዕረፍት የሰጠን ጌታ ስሙ ቡሩክ ቅዱስ ይሁን ። አሜን ! የሚሰማ ሁሉ አሜን ይበል !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /15

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም.

ያጋሩ