የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወርቁ እንዴት ደበሰ!(ሰቆ.ኤር. 4÷1)

                                                           ቤተ ጳውሎስ እሑድ ግንቦት 19/2004 ዓ.ም.
ገና ሻዩን አዝዤ ወደ አፌ ላስጠጋው ስል ከወዲያ ማዶ ለመቆም የምትጣጣረውን መኪና እያየሁ ዓይኔ ተተክሎ ቀረ፡፡ መኪናዋን አላወቅኋትም፡፡ ዓይኔ ግን በእርሷ ላይ ቀረ፡፡ የሾፌሩ በር ተከፍቶ የወጣው ሰው ግን የማውቀው ወንድም ነበረ፡፡ ወዲያው ግን ማወቄ ወደ አለማወቅ ተለወጠ፡፡ እንኳን የእርሱን ህልውና የራሴን ህልውና ያጣሁት መሰለኝ፡፡ እውኑ ሕልም መሰለኝ፡፡ የጨበጥኩት የጉም ስፍር ሆነብኝ፡፡ ሻዩን ሳልቀምሰው አፌ እሬት ሆነብኝ፡፡ አጠገቤ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ሕልውናቸውን መቀበል ከበደኝ፡፡ ዓለም ለቅጽበት ውሸት፣ የአሳብ ቤት ሆነችብኝ፡፡ ዓይኔ እዚያች መኪና ላይ የተተከለው የቀጠርኩት ሰው መጣ ብሎ አይደለም፡፡ ራሴን ቀጥሬ ራሴን እየጋበዝኩ ነበር፡፡ ያም ሰው እንደሚያገኘኝ ፍጹም አላሰበም፤ ነገር ግን ቀጠሮው ሞላ፡፡ እንደዚህ ባንገናኝ እመርጥ ነበር፡፡ በዓለም ግን የሆነው እንጂ የመረጡት አይታይም፡፡ ወዳጅ የሆነ ሰው ሊያየውም ላያየውም የሚገባ ሁኔታ ነበር፡፡ ማየቱ ለማጽናናት፣ አለማየቱ ላለመሰበር ነው። የመጣው ትንሽ ኬክ ቢጤ ገዝቶ ሊበላ ነው፡፡
ወደ እኔ መጓዝ ጀመረ፣ ይበልጥ ልቤ ፈራ፡፡ ያላየኝን ሰው ቀድሜ ዓይቼ የአሳብ ፍልሚያ ውስጥ ገባሁ፡፡ ያየ ታጋይ ነው፣ ያላየ ምን አለበት! ይህ ወንድሜ ቁመናው ያማረ፣ አንገቱ የንጉሥ ሕለተ ወርቅ የመሰለ፣ መልኩ የብር እንኮይ፣ አለባበሱ የጥቅምት አበባ፣ ቆፍጣናነቱ የድሮ ወታደር፣ አነጋገሩ በሥልጣን የተሞላ፣ ለሚረግጠው የሚጠነቀቅ፣ ለሚለብሰው የሚጨነቅ፣ በአጠገብ ሲያፍ ሽቶው የሚያውድ ነበር፡፡ መኪናውን የያዘ እንደሆነ እንደ መኪና ሳይሆን ያለ አቅሟ እንደ ጀት ሁኚ እያለ ያስጨንቃታል። እንደ ንጉሥ ሞተረኛ ለራሱ ድምጽ እያሰማ በመኪናው ጥሩምባ አድባሩን እያወከ ይነጉዳል። ብዙም አልናገረውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ወደ መሬት ገና አልወረደም ነበርና ስለማንደማመጥ ነው፡፡ ከመፈለጉ የተነሣ ኩሩ፣ ከመወደዱ የተነሣ ውድ ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ ብዙ ዘመን ነገርኩት፡፡ እኔን ላለማስቀየም ብቻ በትዕግሥት ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን እሺታው የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ የአሁኗ ዓለም እንደ እርሱ ያታላለችው ሰው አልነበረም፡፡ እኔም ሰው ነኝና ደክሞኝ ተውኩት። ዛሬ ያየሁት ከብዙ ወራቶች በኋላ ነው፡፡ ያቺ የቡልጋ አልቃሽ ያለችው በጆሮዬ አቃጨለ፡-
      ‹‹ምን ቆንጆ ቢሆኑ ቢረዝሙ እንዳክርማ
               መጠቅለል አይቀርም በነጠላ ሸማ››

ያንን ወንድሜን በሩቅ ሳየው ነዘረኝ፡፡ መልኩን ሳየው ደንገጥኩኝ፡፡ ያ ጥቁር መነጽር ለሌቦች ብቻ ሳይሆን መልካቸውን ለተሰረቁም እንዴት ጥሩ ነው! ጥቁሩ መነጽር በትልቁ ፊቱ ላይ ተለጥፏል፡፡ ዛሬ የሚያዩት አይጨነቁም፣ እንዲሁ የተሠራ ይመሰላቸዋል። ተሠርቶ መፍረሱን ላየሁት ለእኔ ግን አስደነገጠኝ፡፡ የሚያበረታኝን ጌታ አጽናኝ ብዬ ለመንኩት፡፡ ቅድም ያየኋት መኪና ሳትሆን መቃብር መሰለችኝ፣ ከውስጧም የወጣው ያ ቆንጆ ሳይሆን የሰነበተ አጽም ሆኖ ታየኝ፡፡ እውነቱን አለመቀበል እንዴት ሕመም ይጨምራል! መቀበል  ስላቃተኝ ወንበሩ ሊሸከመኝ አቅም ያጣ መሰለኝ፡፡ እውነቱ ግን እኔ ልቀመጥ አቅም ማጣቴ ነበር፡፡ ያ ጎበዝ ከዓመት በፊት ግንባታውን ላየ የሚወድቅ አይመስልም ነበር፡፡ ሰው ግን ለአንድ ቀን ትኩሳት የሚገብር ፍጹም ደካማ ፍጡር ነው።፡

ወደ አጠገቤ ሲቃረብ ተንሥቼ ለማምለጥ ጉልበት አጣሁ፡፡ ዓይን ለዓይን ስንተያይ ደነገጥን። እኔ እርሱን መቀበል አቅቶኝ እርሱ ራሱን መቀበል አቅቶት ደነገጥን፡፡ የቀድሞ መልኩን የማያውቁት በዙሪያዬ ሻይ ቡና የያዙት ያወቁት መሰለኝና እንዳይጠይቁኝ ተሰቀቅሁ፡፡ እርሱም እኔ መሆኔን ሲያውቅ ‹‹ይኸውልህ እንዲህ ሆንኩልህ›› ብሎ አለቀሰ፡፡ እኔም በሰው መሐል መነጋገር ስላልፈለግሁ አይዞህ አሁን ቶሎ ሂድ፣ አሁን እደውልልሃለሁ፣ አሁን አገኝሃለሁ አልኩት፡፡ እርሱ ግን የማምለጫ ምክንያት ያቀረብኩ ሳይመስለው አይቀርም። ሰው ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበታል፡፡ ‹‹ስነግርህ ሂድ›› አልኩት መኪናዋን አስነሥቶ አደባባዩን እንደ ዞረ ደወልኩለት። ቁም መጣሁ ብዬ ላልጠጣሁት ሻይ ከፍዬ ተነሣሁ፡፡ ወደ አፍ ያደረሱትን መጠጣትም እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው፡፡ ላልጠጡት መክፈልም በዓለም የተለመደ ነው፡፡
ተገናኝን ምን ሆነህ ነው አልኩት። ምን እንደሆን ማወቅም ለካ ከባድ ነው፡፡ ንግግሩን በፍጹም መሸነፍ በዕንባም ገለጠልኝ፡ ከውሸታም ወንዶች ውጭ ያ የሚያለቅሱ ወንዶች ስሜታቸው በጣም ሲነካ ብቻ ነው፡፡ ዝም ብለው የሚነፈረቁት በእውነቱ ሳይሆን በማልቀስ ብዛት መታመን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዕንባ ድራማ ሕዝብ የሚያስከትሉ ብዙ ሰባኪዎች አሉ። ትልቅ ማዕረግ ያላቸው ሆነው ካለቀሱ ደግሞ በመንገድ ጠራጊዎቻቸው ከብቃት ማዕረግ የደረሱ አባት ናቸው ይባላል፡፡ የዕንባን ትርጉም ጌታ ያውቀዋል፡፡ ይህ ወንድሜ ግን ከማየው ሁኔታ አንጻር ማልቀሱን ወድጄዋለሁ፡፡ ዕንባው እንደ ቋንቋ ይረዳዋል፣ ደግሞም ይቀለዋል፡፡
‹‹ይኸውልህ ብዙ ዘመን መከርከኝ እግዚአብሔር ግን ሰበረኝ፣ ልታይ ልታይ ባልኩባት ከተማ የት  ልደበቅ ብዬ አልኩ፡፡ እንደ ትላንት ሥራ ውዬ በስኬቴ ተደስቼ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ጠዋት ስነሣ በላብ ባሕር ውስጥ ተዘፍቄአለሁ፡፡ ማነው ውሃ የደፋብኝ አልኩ፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በቤቱ የለም። እንደ ምንም ከአልጋ ተነሥቼ ወደመስተዋቱ ስሄድ እንደዚህ ሆኛለሁ፡፡ የማየውን መቀበል አቅቶኝ ራሴን ሳትኩ … ጓደኛቼ ሁሉ፣ ትላንት የሚፈልጉኝ ሲያዩን መንገድ አሳብረው ይሄዳሉ፣  እኔ ለተጎዳሁት እነርሱ ለምን ሸሹኝ›› በማለት ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ እኔም ከዚያ ወዲያ ውሎ አዳሬ ከዚያ ወንድም ጋር ሆነ፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ በጠና ታሞ ሐኪም ቤት ገባ፡፡ ወደ እግዚአብሔር አለቀስን። በልዩ ተአምር ከሞት አመለጠ፡፡ ፍጹም ዳነ። ያ የቀድሞ መልኩ፣ የቀድሞ ነገሩ ምርኮው ተመለሰለት፡፡ ተኳለ፣  ተዳረ። እንደገና እስከዚህች ብዕር ድረስ አልተያየንም፡፡
ያ የብር እንኮይ፣ ያ የተባዘተው ጥጥ፣ ያ ተወዳጅ፣ ያ ቁመተ ሎጋ፣ ያ አነጋገረ ሥልጡን፣ ያ ክቡር ዘበኛ ምነው እንዲህ ረገፈ! በደንብ ሠርቶ በደንብ ያፈረሰው ያ አንዱ እጅ ይሆን? እኔ ምን አውቃለሁ፡፡ ፀሐፊ ሁሉ መልስ አለው ብላችሁ አትወትውቱኝ፡፡ እኔም የራሴ ጥያቄ አለኝ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አዋቂ ነው፣ አይሳሳትም›› የሚለው የእምነት ቃል ብቻ ያሳርፈናል፡፡ ያንን ወንድም ባሰብኩ ጊዜ ከኤርምያስ ጋር፡- ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ?›› ብዬ አለቀስኩ (ሰቆቃወ ኤር.4÷1)፡፡
ሰው ከነ መልኩ አለመሞቱ፣ ሰው ከወዳጁ ጋር አለማርጀቱ፣ ሰው በክብሩ አለመቆየቱ፣ ሰው በቅንነቱ አለመክረሙ፣ ሰው በጨዋነቱ አለማርፈዱ፣ ሰው በሩኅሩኅነቱ አለመሰንበቱ በእውነት እንዴት ያሳዝናል፡፡ ሰው ምን ነካው አይባልም፣ የሚነካው ብዙ ነው፡፡ ሰው በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በቀኑም ስንት ጊዜ ያብዳል! ሰው እንዲህ ነው፣ እኔ እንዲህ ነኝ፡፡ ክፋት ግን ከራስ ይልቅ በሰው ላይ ሲያዩአት እንዴት አስቀያሚ ናት፡፡ ጦጣ በራስ አናት ላይ ዳባሽ ናት። በሰው አናት ላይ አስቂኝ ናት። ያዘልኳት ጦጣ ታባብለኛለች፣ ያዘሉት ጦታ ታስቀኛለች፣ እናንተ ሆይ እንደ እኔ ከተሰማችሁ ከእኔ ጋር ትግባባላችሁ፡፡
ወርቁ እንዴት ደበሰ! ከዓመታት በፊት መልኩ የረገፈውን ወንድሜን ሳየው ወርቁ እንዴት ደበሰ! አልኩኝ። ከዓመታት በኋላ ጠባያቸው የረገፈውን አባቶቼንና ወንድሞቼን ሳይ ወርቁ እንዴት ደበሰ! አልኩኝ፡፡ ልብ አድርጉ! ሕንጻው መሠረቱ አይደለም፣ በመሠረቱ ላይ ያደገ ጡብ ነው። የዛሬው ጠባይም የሰውዬው መሠረቱ አይደለም፣ ወርቅ ነበረ ዛሬ ግን ደበሰ!
      አልቃሻው አባት አስለቃሽ ሆነ
      መካሪው ወንድም አስጨናቂ ሆነ
      የጽድቅ ተማሪው የክስ ፀሐፊ /እኩይ ፍልስጣ/ ሆነ
      መንገድ መሪው አደናጋሪ ሆነ
      የዝማሬው ማኅበር የወጋሪዎች ልብስ ጠባቂ ሆነ
      አገልጋይ የሚሰለጥኑ ተደባዳቢ ማምረት ጀመሩ
      ለመጽደቅ የመጡ ለኩነኔ ሆኑ
      በጸሎት የተጀመሩ ጉባኤዎች በጠብ ተጠናቀቁ
      ለጸሎትም መክፈቻው በስመ አብ ለጥን        ቆላም በስመ አብ ሆነ
      ጸጋዬ መሳደብ ነው፣ የማገለግለው እየወጋሁለት ነው የሚባልበት ዘመን መጣ፡፡
      ሐዋርያ የነበሩ አባቶች በገንዘብ ፍቅር ሐናንያ ሆኑ/የሐዋ. 5፡1/
      በማንም አልፈርድም ይሉ የነበሩ የክስ ዶሴ ሰብሳቢ ሆኑ
      ከልብ ሰው የሚወዱ የጥላቻ ሠራዊት ሆኑ
ኤርምያስ በዚያ በምርኮ ዘመን፣ መቅደሱ በተቃጠለበት፣ የኢየሩሌም ቅጽር በፈረሰበት ወራት፡- ‹ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ!›› ብሎ እየተደነቀ አለቀሰ (ሰቆ. 4÷1)፡፡ መገረም ያስቃል፣ መገረም ያስለቅሳል፣ የሚያውቁት እንደማያውቁት መሆኑ፣ በወጣበት መሰላል ለመውረድ ሲቸኩል ያንን ክቡር ሰው ማየት ያስገርማል፡፡
የክርስቶስን የመስቀሉን ነገር የሞቱን ፍሬ ማዕከል አድርገው የሚሰብኩ፣ ጥቂት እንደ ሰበኩ በፍቅሩ የሚያነቡ፣ ሲቃውን መቋቋም አቅቷቸው ስብከት ያቋረጡ የነበሩ ዛሬ የክርስቶስን ስም አንሰማም እያሉ የከሳሽ አወዳሽ ሲሆኑ፣ ሰባክያኑን ‹‹በክርስቶስ የተለከፋችሁ እብዶች ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ አታውቁም›› በማለት ሲናገሩ መስማት ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ!›› ያሰኛል። ቤተ ክርስቲያንን የወደድነው አባቶቻችንን ዓይተን ነው፣ ልባችን የተሰበረው በቃላቸው ትምህርት ነው። አስጀምረውን ሲሰወሩ በእውነት ያሳዝናል።
ወዳጅ ብለን በልባችን የጻፍናቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ሲቀርቡ የሚያረኩ፣ ሲጣሩ ልብን የሚነኩ፣ ሲሰጡ የሚያስደስቱ፣ አምጣ ሲሉ ደስ የሚያሰኙ… እነዚያ በወርቅ የጻፍናቸው በከሰል ጥቁረት በልባችን ላይ ዛሬ ተጽፈው ስናይ፡- ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ!›› ያሰኛል። ማን ነበር የተሳሳተው? እነርሱ ወይስ እኔ? አላወቅኋቸሁም ወይስ አላወቁኝም? እንድንል አድርገውናል። ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ!››
ሕይወቱ የሚማርከኝ፣ ስለ ማንም ክፉ ሲሰማ እኔ ግን እገሌን መልካምነቱን ነው የማውቀው ይል የነበረ አንድ አገልጋይ አሁን የከሳሾች አለቃ ነው። ዓለምን ስለመናቅ ያስተማረኝ ዛሬ ግን ገንዘብ ለሚባል ጣኦት ይሰግዳል፡፡
 ስለ ሁሉም ነገር በጸሎት መፍትሔ አለ ይሉ የነበሩ ዋናው መረጃ ነው። ዋናው የፓርቲ አባል መሆን ነው። ‹‹ወፍራም ዱላ ባይመቱበት ያስፈራሩበት›› ሲሉ ስንሰማ ወርቁ እንዴት ደበሰ ያሰኛል። ደርጉ እንደ መጣ በአንድ ትልቅ ጉባዔ ላይ የምናውቀው ያ ጎበዝ ሰባኪ ቄሱን ሁሉ አስቀምጦ ጳጳሱን ሁሉ አስቀምጦ እንግዲህ እስከ ዛሬ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ እያልን ስብሰባ እንከፍት ነበር ከአሁን በኋላ ግን በስመ ሌኒን ወማርክስ ወኢንግልስ አሐዱ ሶሻሊስት ብለን እንከፍታለን አለ።  ቤተ ክህነቱ ንስሐ አለበት። ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ!››
በልጅነታችን ወደ እግዚአብሔር ቤት  ያመጡን፣ መልሰን ያገለገልናቸው እነዚያ ባለውለታዎቻችን መልሰው ከቤተ ክርስቲያን አሳደውናል። ወልዶ መብላት፣ የድመት ግብር መቼ ይቀር ይሆን?  ደክመን ያሳመናቸውን ደክመን ማሳደድ ምን ይባላል? ለወንጌል ያልተበጀተ ገንዘብ ለውግዘት ሲበጀት  እንደ ባላቅ እየከፈሉ እርገሙልኝ ማለት ምን እንበለው? /ዘኁል. 22፡4/
በሥነ ጽሑፋቸው ያስደነቁን የክርስቶስን ፍቅር በልባችን የተከሉብን ለዓለም ጥያቄ መልሱ ክርስቶስ መሆኑን ነግረው ያሳረፉን ዛሬ ግን መፍትሔው ፖለቲካ ነው፣ መልሱ የእነ እገሌ መሞት ነው ሲሉን ስንሰማ ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ!›› ያሰኛል፡፡
ስናዛቸው ያረኩን የነበሩ፣ በፊታቸው ስንራቆት የማናፍራቸው፣ ምሥጢራችንን የማወቅ መብት አላቸው ያልናቸው ዛሬ ግን የውኃ ሽታ ሆነው፣ ያለ ምክንያት ተጣልተውን ሲሸሹን ስናይ ‹‹ወርቁ እንዴት ደበሰ›› ያሰኛል፡፡
ስለ እውነት የሚቆረቆሩ፣ ስለተገፉ ያለቅሱ የነበሩ የተገፉትን የሚያድኑበት ወንበር ሲሰጣቸው እግዚአብሔርን አመስግኛለሁ፡፡ እነርሱ ግን በአለንጋ የተገረፉትን በጊንጥ የሚገርፉ በጭካኔ የሚወዳደሩ ሆነው አየሁና ወርቁ እንዴት ደበሰ አልኩ፡፡
ከንጹሑ ወርቅ ይልቅ ቅቡ ድምቀት አለው። ሲያበራም ልዩ ነው። ይህ መልኩ ግን አይቆይም። ከዚህ በፊት የደመቀ እስከማይመስል  መልኩ ይጠፋል። ወርቁ ግን በትክክለኛው መልኩ እጅግም ሳያበራ እጅግም ሳይደበዝዝ በመልኩ ይኖራል፡፡ ጥሩ ወርቅ መልኩን አይለውጥም፡፡ ነገር ግን ጥሩው ወርቅ እንዴት መልኩ ተወለጠ እስክንል መልኩ የሚገረጣበት ዘመን አለ፡፡ ቅቡ እንደ ለቀቀ፣ ወርቁም ይደብሳል! አስመሳዮች ብቻ ሳይሆን እውነተኞችም ይለወጣሉ፡፡
በምርኮ ዘመን፣ መቅደሱ በፈረሰበት ቀንና ቅጥሩ በተቃጠለበት ወራት ይህ ይሆናል፡፡ ምርኮ ከአገር ከመንደር መውሰድ ወደ ሌላ አገር ወደማያውቁት ፍጻሜ መንጎድ ነው። ይህ ዘመን የምርኮ ዘመን ነው። በየዕለቱ አእምሮአችንን የሚይዘው ነገር ወደየትኛው ፍጻሜ እንደሚወስደን ሳናውቅ እየተከተልነው ነው። ዘመኑ መቅደሱ የፈረሰበት ካህናት ያለቁበት ነው፡፡ መቅደሱ የንግድ ሥፍራ ሲሆን ካህናቱ በወይን ሲደለሉ ያ ዘመን ክፉ ነው። ንጉሡ ዳኝነት ሲያጣ ካህኑ በማለዳ ሲሳከር ያ ዘመን አስጨናቂ ነው፡፡ ይልቁንም ጳጳስ ያፀናውን ግብር ንጉሥ የሚያቀልበት፣ አባት አሳደደኝ እያለ ልጅ ፍርድ ቤትን የሚማጠንበት ዘመን ክፉ ነው፡፡ ቅጽር የፈረሰበት ሥነ ምግባር የወደቀበት የሰው ኅሊና በብልግና የተደፈረበት ዘመን ነው። ወርቁ የሚደብሰው፣ ጥሩው ወርቅ መልኩን የሚለውጠው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ያለንን መጠበቅ፣ ያላቸው ለተወሰደባቸው መጸለይ እንዴት መልካም ነው!
                 እግዚአብሔር ወደ እውነተኛው መልካችን ይመልሰን!

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።