“እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ ።” 1ጢሞ. 2፡8
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነበሩት ቶማስ ጃፈርሰን፡- “ቊጣዬን ለማብረድ አንድ ሁለት ብዬ ካልቆጠርሁ በሕይወቴ የሚያጸጽተኝን ነገር አደርጋለሁ ብዬ እፈራለሁ” ብለዋል ። ቶማስ ጃፈርሰን ሲናደዱ ከአንድ እስከ አሥር ይቆጥሩ ነበር ። በጣም ሲናደዱ ደግሞ ከአንድ እስከ መቶ ይቆጥሩ ነበር ። በጣም ሲናደዱ መቊጠር እስኪደክማቸው ድረስ ይቆጥሩ ነበር ።
ዓለምን የገዙ ሰዎች በቊጣ ምክንያት ራሳቸውን መግዛት አቅቷቸው በታላቅ ጸጸት ውስጥ ወድቀዋል ። በወተት ላይ ያረፈች ትንሽ ነቁጥ ጎልታ እንደምትታይ በብዙ ትልልቅ ሥራዎቻችን ቊጣ ጎልታ ትታያለች ። ልፋታችንን ሁሉ ከንቱ ታደርገዋለች ። ሰዎች ስለ ብዙ ፍቅራችን ጥቂት ከመናገር ይልቅ ስለ ትንሽ ቊጣችን ብዙ ያወራሉ ። ቊጣ ጊዜያዊ ስሜት ሲሆን እየቆየ ሲመጣ ቂም ፣ እየከረመ ሲመጣ በቀል ይሆናል ። ቊጣ ትንሽ ዘወር ካልን የሚበርድ ነው ። ከአንድ እስከ አሥር ለመቊጠር ከደፈርን ቊጣ ይበናል ። ስሜታችን እያተኮሰ ፣ ውስጣችን እየጋለ ከመጣ ዘወር ማለት፤ ቊጣችንን ልንገልጽባቸው የምንችልባቸውን ስልኮቻችን ፣ ራስ መጠበቂያዎቻችን አብዝተን መራቅ መልካም ነው ። ነፋስ ነክቶን ስንመለስ ሌላ ሰው እንሆናለን ። “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” እንዲሉ ። ቊጣ እንዲያናግረን ስንፈቅድ መደምደሚያው እኛን ነፍሰ ገዳይ ማድረግ ነው ። ዘወር ስንል ደግሞ ብን የሚል ከንቱ ነገር ነው ። በተቆጡ ሰዎች ፊትም መፋጠጥ ተገቢ አይደለም ። ሌላውንም ከስህተት መጠበቅ አንዱ ቅድስና ነው ። ሌላውን እያረከሱ ፣ ሌላውን እያበሳጩ እኔ ተቀድሻለሁ ማለት ሐሰት ነው ። በቊጣ ላይ ላለ ሰው እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ ማለት እንኳ የበለጠ ማቀጣጠል ነው ። ሰዎችን ከማብረድ የሚናደዱበትን ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው ። ቊጣ ለአሁን ጀግና ለዘለቄታው ሰባራ ሰዎች ያደርገናል ።
የወንዶች ነገር ሊታሰብበት ይገባል ። የሴት ማኅበራት አሉ ። የወንዶች ማኅበራት ግን ብዙ የሉም ። ወንዶች ራሳቸውን ማየት ያስፈልጋቸዋል ። የዓለማችን የሚበዙት መሪዎች ወንዶች ናቸው ። ዓለም ግን የጦርነት ውድማ ከመሆን ፣ በደም አባላ ከመመታት አርፋ አታውቅም ። በወኅኒ ቤት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች እስረኞች ናቸው ። በታላላቅ የጭካኔ ተግባራት የተሰማሩ ፣ እንዲሁም ሌብነትን ሥራቸው ያደረጉ የሚበዙ ወንዶች ናቸው ። ዓለሙ የወንዶች ብቻ እስኪመስል ጀማሪም ፈጻሚም እየሆኑ ያሉ ወንዶች ናቸው ፤ በስህተት የማይማር ፣ ታሪክን የሚደግም የወንዶቹ ዓለም ነው ። ወንዶች እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩበት ፣ ሐቁን የሚያወሩበት ፣ በኪሳቸው ሳይሆን በአእምሮአቸው የሚያስቡበት መድረክ ያስፈልጋል ። ብዙ ወንዶች ከብስለት የራቁ ናቸው ። ሐዋርያው ወንዶችን አድራሻ አድርጎ መናገሩ በእውነት ተገቢ ነው ።
“እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ ።” 1ጢሞ. 2፡8
በስፍራው ሁሉ ማለቱ ድንቅ ነው ። ጸሎት በሁሉ ጊዜና በሁሉ ቦታ ነው ። የማይጸለይበት ጊዜና ቦታ የለም ። በደሳሳ ጎጆ ብቻ ሳይሆን ባማሩ ቤተ መንግሥቶችም ጸሎት አስፈላጊ ነው ። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገርም ጸሎት አስፈላጊ ነው ። በቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በቤታችንም ጸሎት ወሳኝ ነው ። በሰላም ጊዜ ጸሎት ፣ በክፉ ጊዜ ቡጢ ማንሣት የብዙ ወንዶች መገለጫ ነው ። ወንዶች በእግዚአብሔርና በጡንቻቸው ያምናሉ ። በእግዚአብሔር ብቻ አምነው ሊጸልዩ ይገባል ። ልብ በሉ በስፍራው ሁሉ ። አንዳንድ አገልጋዮች በመድረክ እኛ ባለ ጥቁር ቀበቶ ነን ብለው ሲናገሩ ሰምተናል ። ድሮ እገሌ የተባሉ ብርቱ አስማት አላቸው ሲባሉ ይፈሩ ነበር ። አሁን ደግሞ ከእግዚአብሔር ይልቅ በእርግጫ የሚኮሩ እያፈራን ነው ። በስፍራው ሁሉ ማለት በሰላም ለመጣው ቡራኬ ፣ በነገር ለመጣው አበርክኬ እቀጣለሁ የሚል ስልት ሊኖር አይገባም ማለት ነው ። በእውነት የራሳቸው የገራፊ ቡድን ስላላቸው አገልጋዮች ስንሰማ ይህን የሐዋርያውን ምክር አላነበብነውም ወይ ? ያሰኛል ። ክርስቶስ ሕይወቴ ነው የሚሉ ለሰማዕትነትም ዝግጁ ናቸው ፣ የማይጠፋ ብርሃን ከክርስቶስ አግኝተዋልና ። በአደባባይ “አገልግሎት ሕይወቴ ነው” የሚሉ ሰዎች ውስጣዊ ንግግራቸው፡- “በሕይወቴ የመጣውን በሕይወቱ እመጣበታለሁ” የሚል ነው ። ክርስቶስ ብቻ ሕይወት ካልሆነልን ከቊጣና ከክፉ አሳብ አንድንም ።
“አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ” ይላል ። ቊጣ የመጸለይ አቅማችንን ይጋፋል ።መጸለይም ከቊጣ ያድናል ። ቊጣ እኔ አስተካክለዋለው ማለት ነው ። መጸለይ እግዚአብሔር ያበጀዋል ማለት ነው ። “አንተው አብጀው ፣ አስቤም አልፈጀው” የሚባለው ለዚህ ነው ። ክፉ አሳብ መጠራጠር ነው ። መጠራጠር በአሳብ ማዕበል ያንገላታል ። እርምጃ እንዳይወስዱ እርግጠኛ አይደለም ። አርፈው እንዳይተኙ ልብ ተከፍሏል ። መጠራጠር አጉል ነዋሪ ያደርጋል ። መጸለይ ግን ራስንና ጉዳይን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ነው ። ጸሎት ሰላም ይሰጣል ።
“የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ ።” ለብዙ ዘመናት ግራ እጃችንን እያወጣን እናሸንፋለን ብለን ፎክረናል ። በግራ እጃችን ስንፎክር ኑረን ይኸው ግራ ገብቶናል ። እጆች በሁለት ነገር ይነሣሉ ። በድል ስሜትና በመማረክ እውነት ነው ። አሸንፋለሁ ወይም እናሸንፋለን የሚል እጁን ያነሣል ። ተማርኬአለሁ የሚልም እጁን ያነሣል ። እጆች እናሸንፋለን ብለው ሲነሡ ከመቀደስ መርከስ ይጀምራሉ ። እጆች ዕፀ በለስን ቆረጡ ፣ እጆች አቤልን በድንጋይ ቀጥቅጠው ገደሉ ። እጆች በክፉ አሳብና በቊጣ ሲነሡ የሚያደርሱት ጥፋት ታላቅ ነው ። እጆች ለጸሎት ሲነሡ ፣ ለምጽዋት ሲዘረጉ ግን ማዳን ይችላሉ ። ደግሞም ይቀደሳሉ ።
ሁለት ጊዜ ተንበርክከን ይሆናል ። አንድ ጊዜ ትምህርት ቤት ፣ ሁለተኛው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይችላል ። ትምህርት ቤት የተንበረከክነው ለቅጣት ነው ። ቤተ ክርስቲያን የምንበረከከው ግን ለበረከት ነው ። እጆቻችን የቊጣንና የመጠራጠርን መልእክት ለማድረስ ሳይሆን ለጸሎት ሊዘረጉ ይገባል ። ብዙ ወንዶች በቊጣ ተነሥተው ሚስታቸውን ይጎዳሉ ። ሚስት ላይ መሰንዘር በጣም መጥፎና የማይረሳ ነገር የሚተዉ በመሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። አንድ የሂንዱ አባባል፡- “ሚስትህን በአበባም እንኳ አትምታት” ይላል ። ወንዶች በክፉ አሳብ ወይም በመጠራጠር ሲነሡ ሌላውን ሰው ያጠቃሉ ። የአገራችን ሰው በሦስት ነገር ቀናተኛ ነው ። በሴት ፣ በመሬትና በአገሩ ። ወንዶች ሚስታቸው ላይ ጥርጥር ሲገጥማቸው መጸለይ ያስፈልጋቸዋል ። በገጠሩ ሚስቴን ትክ ብለህ አየሃት በማለት የሚገድሉ አያሌ ናቸው ። ሚስቴን ተመኝተሃታል በማለትም የሚገድሉ ብዙ ናቸው ። ወንዶች ቊጣን ከቤታቸው ፣ ጥርጥርን ከወዳጆቻቸው ሊያነሡ ይገባል ። ይህ ግን በራስ አቅም ብቻ አይሆንምና አጥብቀው መጸለይ ያስፈልጋቸዋል ።
እግዚአብሔር በትዕግሥት ይባርከን !
1ጢሞቴዎስ /29/
ታኅሣሥ 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.