የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ኋላህ አትይ / ክፍል 1

                                                                ነሐሴ 28 2003

(ዘፍ. 19&17)፡፡

/ክፍል አንድ/
ካለፉት ዘመናት ይልቅ በዛሬው ዘመን የበዛው ኃጢአት ምንድነው? ብንባል ዝሙት፣ ሌብነት፣ ግድያ ብለን ልንጠቅስ፣ ይህንንም በቊጥር ስሌትና በመረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ከእኛ ዕይታ የተሰወሩ፣ የዘወትር አቋማችንን የሚያነቃንቁ የተሰወሩ ስህተቶች አሉ፡፡ ነቢዩ፡- “ ስህተትን ማን ያስተውላል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ” ያለው ለዚህ ነው (መዝ. 18÷12)፡፡ እነዚህ የተሰወሩ ኃጢአቶች ከሚፈጽማቸው ሰው ባሻገር ቆመው ያሉ አይደሉም፤ በውስጡ ያሉ፣ በኑሮው የሚገለጡ ኃጢአቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደሚገዙት እንኳ አያውቅም፡፡ በሚፈጽማቸውም ጊዜ የሕመም ስሜት የላቸውም፤ ስለለመዳቸውም ጽድቅ መስለው ይታዩታል፡፡ እነዚህን ኃጢአቶች ሰውዬው የሚኖርበት ማኅበረሰብ ስለተቀበላቸው የብዙኃን ውሸት እውነት መስሎ ታይቶት ሊሆን ይችላል፡፡ የቃሉና የቅዱስ መንፈስ ብርሃን የሚገልጣቸውን ስውር ኃጢአቶች ኅሊና ሊደርስባቸው አይችልም፡፡ ሰዎች መሳሳታቸውን የሚያውቁት ኅሊና የአደጋ ድምጽ ሲያሰማቸው ነው፡፡ ነገር ግን ኅሊና የተሰወረውን ስህተት ሁሉ የማወቅ አቅም የለውም፤ ኅሊና በኃጢአት ብዛትም ስለሚሞት የእውነት ሚዛን በመሆን ሁልጊዜ አያገለግልም፡፡ የኑሮአችን መመዘኛ ቃሉና ቅዱስ መንፈስ ብቻ ነው፡፡
          ኃጢአትን የምንፈጽመው መንፈሳዊ ዓይናችን ሲታወር ነው፡፡ ጭል ጭል የሚለውን ዕይታ ደግሞ ይበልጥ የሚያጨልመው በውስጣችን ያለው የተሰወረ ኃጢአት ነው፡፡ ነቢዩ፡- “ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ” (መዝ.18÷12) አለ፡፡ የማላውቀውን ነገር ግን የማደርገውን ኃጢአቴን አስወግድልኝ ማለቱ ነው፡፡ መንጻት የሚያስፈልገው የቆሸሸ ነገር ነው፡፡ ነቢዩ፡- ‹ኃጢአት ያልመሰለኝ ነገር እያቆሸሸኝ ነውና ስም ጠቅሼ ከማልናዘዝበት ርኲሰት ንጹሕ አድርገኝ› በማለት ይጸልያል፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ብቻ እንዳደረገልን የሚያውቀው ውለታ እንዳለ ሁሉ፤ እርሱ ብቻ እንዳደረግን የሚያውቀው ኃጢአት አለብን፡፡ የተገለጡ ኃጢአቶችን ያህል የተሰወሩ ኃጢአቶች ሰውን ያቆሽሻሉ፡፡ በቤት ውስጥ የት ቦታ እንዳለ የማይታወቅ ነገር ግን ቤቱን በክፉ ሽታ የሚያነቃንቅ ቆሻሻ አለ፡፡ ከተገለጠ ቆሻሻ ይልቅ የተሰወረ ቆሻሻ ለመወገድ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ቶሎ አግኝቶ ማጽዳት ስለማይቻል ያውካል፡፡ የተሰወረ ኃጢአትም ከተገለጠ ኃጢአት ይልቅ ለመጽዳት ጊዜ ይፈጃል፡፡ የቃሉ ብርሃን ካልበራልን በቀር ልንደርስበት አንችልም፡፡ ታማሚዎች ሁሉ በሽታቸውን አያውቁትም፡፡ አንዳንዱ በሽታም ሕመም አልባ ሆኖ መጨረሻ ላይ ይገኛል፡፡ ሕመም ያለው በሽታ ቶሎ መፍትሔ ሲያገኝ የተሰወረውና ሕመም አልባ የሆነው በሽታ ግን ክፉኛ ይጎዳል፡፡ ሕመም አልባ የሆኑ የተሰወሩ ብዙ የድርጊት ኃጢአቶች አሉ፡፡ በአቋራጭ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚከፈል ጉቦ ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ መቼ ታመውበት ያውቃሉ? 

በእግዚአብሔር ፊት ከተገለጡ በእኛ ፊት ግን ከተሰወሩ ኃጢአቶች አንዱ የዘመናችን ወረርሽኝ ብለን የምንጠራው ከዳተኝነት ነው፡፡ ይህ የተሰወረ ኃጢአት ለብዙዎች ዘመናዊነት፣ ከወቅቱ ጋር የተገናዘበ አኗኗር፣ ተጣጣፊነት መስሎ ቢታይም በእግዚአብሔር ፊት ግን ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአትን በስሙ ካልጠራነው መቼም ከዚያ ኃጢአት አንላቀቅም፤ ዝሙትን መዝናናት፣ ስርቆሽን ቢዝነስ፣ ስካርን ወይን ያስተፌሥህ፣ ክዳትን እጥፍ ማለት ካልነው መቼም አንድንም፡፡ ከኃጢአት ለመላቀቅ ኃጢአትን በስሙ መጥራት ግድ ነው፡፡ ኃጢአት ስውርነቱ ዘላቂ የሚሆነው በስሙ መጥራት ሲያቅተንም ነው፡፡ አንዳንድ የተበላሸ የውሃ ማሞቂያ በሙቀት ይጀምራል፤ መውጣት በማይቻልበት ሰዓት ግን  መቀዝቀዝ ይጀምራል፡፡ ቀድሞ ባይሞቅ ሰውዬው አይገባም ነበር፤ ሲቀዘቅዝ ለማኩረፍም  በዓይን ውስጥ ሳሙና ገብቷልና አይቻልም፡፡ እየሳቀ መታጠብ የጀመረው ሰው እየተንቀጠቀጠ ይጨርሳል፡፡ እንደ ተበላሸ ማሞቂያ የዓለምን ፍቅር ገላጭ ያለ አይመስልም፡፡ በሙቀት ተጀምሮ በቅዝቃዜ ያበቃል፡፡ ከዳተኝነትም በሙቀት ጨርሶ በቅዝቃዜ የሚፈጽም የዓለም ወረት አካል ነው፡፡ ከዳተኝነትን ሊያብራሩ የሚችሉ ብዙ ሕያዋን መዝገበ ቃላቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በእምነት ከግብጽ ምድር ወጥተው ባለ ማመን ጠንቅ ምድረ በዳ የቀሩት የእስራኤል ልጆች የከዳተኝነት ምሳሌና ማብራሪያ ናቸው (ዕብ. 3&12-19)፡፡ ጉዞአቸውን መፈጸም ባለ መቻላቸው ከግብጽ መከራ አምልጠው በሲና በረሃ በሞት ተቀጡ፡፡ ጉዞአችንን ካልጨረስን የሚገጥመን የባሰ ነው፡፡ ከዕባብ ጉድጓድ አምልጠን ዘንዶ ጉድጓድ ውስጥ እንገባለን፡፡ ከፈርዖን ይልቅ ከዳተኛነታችን ይጎዳናል፡፡ ፈርዖን በመከራ፣ ከዳተኝነታችን በሞት ይቀጣናል፡፡ ፈርዖን ከደስታ፣ ከዳተኝነት ከእግዚአብሔር ይለየናል፡፡ ከዳተኝነት ከከፍታ ኑሮ ወደ ዝቅታ ወለል መውረድ ነው፡፡ በኅሊና፣ በእግዚአብሔርና በጎረቤቶቻችን ዘንድ ቀሎ መታየት ነው፡፡ ለዓላማው ያልታመነውን ሰው ማንም ይሆነኛል ብሎ ሊያጨው ይችላል?
ከዳተኝነት የጀመሩትን መልካም ጉዞ አቋርጦ የመመለስ ስህተት ነው፡፡ ከዳተኞችን በመጀመር ማንም አይጠረጥራቸውም፡፡ የሁልጊዜ መወቀሻቸው መፈጸም አለመቻል ነው፡፡ የጅማሬ ጀግና፣ የፍጻሜ ሽባ መሆን በሌሎች ፊት ብቻ ሳይሆን በኅሊና ፊትም ክብር የሚነሣ ነው፡፡ ካለፉት መንግሥታት ጋ ከልባቸው ሲሠሩ የነበሩ አዲስ መንግሥት ሲመጣም ተገልብጠው ከልባቸው ለመሥራት የጀመሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ለገዛ መንግሥታቸው ያልታመኑ ለእኛ አይታመኑም ተብለው ቅጣቱን ሁሉ የተቀበሉ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሰዎች ዛሬ እነርሱ ጋ መምጣታችንን ብቻ አያዩም፤ ከኋላ ባልጨረስነው ጉዞና በተኮላሸው ዓላማችን ይገመግሙናል፡፡ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ብዙ ጊዜ አይደላውም፤ ሁለተኛይቱ ሴት የፊተኛዋን እያሰበች በጥርጣሬና በጥንቃቄ ትመለከተዋለች፡፡ መንፈሳዊ ብትሆን እንኳ ካልቆረበና አሰርኩት ብላ ካላሰበች በቀር አትረጋጋም፡፡ ከዳተኛ አገር የለውም፡፡ በሄደበት ስፍራ ሁሉ ከዳተኛነቱ ያሳድደዋል፡፡ ከእግሩ ስሙ እየቀደመ መድረሻ ያሳጣዋል፡፡ ራሱን ገልጦ የበደላቸውን ይቅርታ ካልጠየቀ በቀር እንደ ጅብ በማያውቁት አገር ቁርበት አንጥፉልኝ ቢልም ለጊዜው ይወደዳል ቆይቶ ግን ይሰደዳል፡፡
በዓለማችን ላይ እጅግ ነፍሰ ገዳይ የነበሩ ሰዎች የቅርብ ረዳቶቻቸው እጅግ ታማኝ ሰዎች እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳናል፡፡ ነፍሰ ገዳዮች ታማኞችን እንጂ የሚመስሏቸውን ወደ ጓዳቸው አያስገቡም፡፡ እንዲሁም ከዳተኞች እጅግ የሚፈሩትና የሚሸሹት ከዳተኛውን ሰው ነው፡፡ ከዳተኞች የቅርብ የሚያደርጉት ሰው ቃል ኪዳን ያለውን ሰው ነው፡፡ ከዳተኞች ራሳቸው ከዳተኞችን የማይፈልጉ ከሆነ በከዳተኝነታቸው ራሳቸው ራሳቸውን እንኳ አልተቀበለውም ማለት ነው፡፡ ከዳተኝነት ከዳተኛው እንኳ መሳዩን የማይፈልግበት ገለልተኛ የሚያደርግ የኃጢአት ዓይነት ነው፡፡ ከዳተኛ ከዳተኝነትን በሌሎች ሲያየው ይጸየፈዋል፡፡ ለመተው ግን አቅም ያጣል፡፡ ከከዳተኝነት የሚያድነው ያ የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ከዳተኝነት እያወቅነው ብቻ ሳይሆን ሳናውቅም የሚገዛን ኃጢአት ነው፡፡
          ሰዎች፣ እግዚአብሔርን፣ ራሳቸውንና ወዳጆቻቸውን ሊከዱ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔርን መክዳት ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ ጣኦት፣ ከወንጌል ወደ ተረት፣ ከክርስትና ወደ ፈሪሳዊነት፣ ከድንግልና ወደ ዘማዊነት፣ ከቸርነት ወደ ንፍገት፣ ከፍቅር ወደ ቂም በቀል፣ ከስብከት ወደ ክህደት፣ ከእምነት ወደ ፍልስፍና መመለስ ነው፡፡
ራስን መክዳት ደግሞ ከመታዘዝ ምክንያት ማብዛት፣ ለሰዎች የሰጡትን ተስፋ ለመፈጸም ማንገራገር፣ ቃል ኪዳንን ማፍረስ፣ ውሳኔን ሽሮ ወደ ተፉት ዓለም መመለስ፣ ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡
ወዳጆችን መክዳት የጋራ ቃል ኪዳንን አለማክበር፣ አብሮ ወጥቶ ተጣጥሎ መግባት፣ እስከ ሞት የሆነውን ትዳር በፍቺ መጨረስ፣ መሐላን ማፍረስ፣ ሲወደዱ መጥላት፣ ሲታመኑ መክዳት፣ በቃልና በአድራሻ አለመገኘት፣ አመስግኖ መራገም፣ ቀርቦ ማሳደድ፣ ገበና አይቶ ማሳየት፣ አብሮ ተማክሮ በአደባባይ ምሥጢር ማውጣት ነው፡፡
ለነገሮች ሁሉ ዋጋቸው ምንድነው? እውቀት ብቻውን የእውቀት ዋጋ፣ ገንዘብ ብቻውን የገንዘብ ዋጋ አይደለም፡፡ የሚጠቅሙ ነገሮች በጥቅም እንዲቀጥሉ፣ ለተቀደሰ ዓላማ እንዲውሉ ታማኝነት ወሳኝ ነው፡፡ ከፀፀት ነጻ የምንሆነው በታማኝነት ብቻ ነው፡፡
ቅዱስ እንጦንስ፡- “ዓሣ ከባሕር ወጥቶ ረጅም ጊዜ ቢያሳልፍ እንደሚሞት መነኮሳትም ግልጽ ባልሆነና በቂ በማይባል ምክንያት ከዓለም ሰዎች ጋር ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ የውስጥ ሰላማቸውን ይነጠቃሉ፡፡ ስለዚህ ዓሣ በባሕር ውስጥ በሕይወትና በብርታት ሊመላለስ እንደሚችለው እኛም በባእታችን ሆነን ብንጸና በረከት እንሆናለን” ብሏል፡፡
በስፍራ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ያለ ስፍራው ያለ የሚጠብቀው ሞት ነው፡፡ ዓሣ ከባሕር ውጭ ሕይወት የለውም፡፡ ሕይወቱንና ተፈላጊነቱን አስከብሮ የሚኖረው ዘሩንም የሚተካው በዚያው በስፍራው ነው፡፡ ክርስቲያንም በስፍራው ሲሆን ብቻ ሕልውናውና ተፈላጊነቱ ይፀናል፡፡ ትውልዱንም በማየት የነገ ወራሽነቱን ያረጋግጣል፡፡ በየትኛውም መስክ በስፍራ መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርት የሚያፈራው መምህር ገንዘብ ቆጣሪ፣ ገንዘብ ቤቱ ሰባኪ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ሃይማኖተኛ፣ ሃይማኖተኛውም ፖለቲከኛ ከሆነ የሕይወት መተላለፍ ይከሰታል፡፡ በስፍራችን ካልሆንን ጸጋችን እየተላጨ ይመጣል፡፡ ከመጥቀምም ሌሎችን እንጐዳለን፡፡ ሰዎች ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ስጦታቸውንና ውጤታማ የሚሆኑበትን ጸጋቸውን ከድተዋል፡፡ ሰው ሊያጠምዱ የሚችሉ ብዙ አገልጋዮች ዕቃ ግዥ ሆነው ስናይ ዕለት ዕለት መክሰማቸው ለሚያውቃቸው ሀዘን ነው፡፡ ዕቃ ግዥው ሰባኪ ሲሆን ደግሞ ስብከት አበድሩኝ እያለ ሲጨነቅ ማየት ይህም ልብ ሰባሪ ነው፡፡ ተሰምቶት ሳይሆን ሰምቶ የሚያገለግል አገልጋይ እንደ ማየት ምን ክፉ ነገር አለ? ዛሬው ያለው ዝብርቅ ይህን ይመስላል፡፡ አንድ የአገራችን አባባል እንዲህ ይላል፡-
                              ዝንጅሮን በባሕር በገደል ላይ ዓሣ
                             መስቀል ለዛር ፈረስ ከበሮን ላንካሳ
                              ጌታዬ ብይንህ ተወላገደሳ
 ለሌሎች በረከት የምንሆነው በስፍራችንና በዓላማችን ስንሆን ብቻ ነው፡፡ አሊያ ስተን የምናስት ሰዎች እንሆናለን፡፡ ዛሬ እየተነቀፍን ያለነው በተናገርነውና ባነገብነው ዓላማ መጽናት ባለመቻላችን ነው፡፡ እንደ ቀደሙት ዘመናት ዛሬ ስለ ክርስቲያንነታችን፣ ስለምንኩስናችን አንነቀፍም፡፡ የክርስቲያን መዓዛ፣ የመነኲሴ ለዛ እየታጣብን ግን ነቀፋ በዝቶብናል፡፡ የዛሬው መከራችን እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ደግሞም በተናገራችሁት ነገር ለምን አልተገኛችሁም? የሚል ነው፡፡ ከደረጃችን አንሰን በመገኘታችን የመጣብን መከራ ነው፡፡ በእውነት ከዳተኝነት በምድር በሰማይ ስደተኛ ያደርጋል፡፡
ኃጢአት እንደ ነብር ዘሎ የሚያንቅ ነገር አይደለም፡፡ ኃጢአት ሂደት ነው፡፡ ይልቁንም ከዳተኝነትን ስናየው ቀስ በቀስ የሚገዛን ኃጢአት ነው፡፡ ዛሬ በዓመት አንድ ጊዜ ከእስልምና አንድ ሰው ተመለሰ ብለን እልል እናሰኛለን፡፡ በየዕለቱ ግን ስማቸውንና ሃይማኖታቸውን እየለወጡ ብዙዎች እንደሚለዩን አላስተዋልንም፡፡ ከክርስትና ወደ አረማዊነት መግባት ለሰሚው ግራ ቢሆንም ላድራጊዎች ግን ቀናና ቀላል ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣው ሰውም በአንድ በር ገብቶ ሲወጣ ግን በሦስት በሮች ነው፡፡ ብዙዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጡ ተመልሰው ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚያኖራቸው ፍቅር፣ ሰላምና ታማኝነት አጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ሊያቆየን የሚችለው የቤተ ክርስቲያን ራስ የክርስቶስ ፍቅር፣ ሰላሙና ታማኝነቱ ብቻ ነው፡፡ የክርስትናው ዳሩ የት ነው? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ነገር ዳር አለው፤ ሩጫ የራሱ የሆነ ዳር አለው፡፡ የሩጫ ዳሩ፣ የድሉ ገመድ ሊሆን ይችላል፡፡ የክርስትናስ ዳሩ የት ነው? ለሁሉም ነገር ‹‹ነበር›› ሊኖረው ይችላል፡፡ ለክርስትና ግን ‹‹ነበር›› አይስማማውም፡፡ የክርስትና የመጨረሻው ገመድ ያለው በሰማይ ነው፡፡ ከገመዱ በፊት ሩጫቸውን የሚያበቁ የድል ሽልማት የላቸውም፡፡ ዛሬ ለብዙዎች የክርስትና ዳር ጥሩ ትዳር መያዝ፣ ገንዘብ መጨበጥ፣ ሥልጣን ላይ መቆናጠጥ፣ ፈረንጅ አገር መሄድ ሆኗል፡፡ የቀደመ ፍቅራቸውን የተው፣ ዓይተው እንዳላየ የሚኖሩ፣ በመንፈስ ጀምረው በሥጋ የጨረሱ፣ ደብረ ታቦር ላይ ዘምረው ቀራንዮ ላይ የከዱ ብዙዎች ናቸው (ራእ. 2&4)፡፡
ክርስቶስ ከሚከፍለው ዋጋ ይልቅ ላነሰ ለዓለም ዋጋ ብዙዎች ራሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለፖለቲካ ጥይትን ንቀው አደባባይ የወጡ፣ በወኅኒ ለዘመናት የማቀቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹‹ከዚህ ሕይወት መውጣት አይችሉም፣ ልክፍት ነው›› እስኪባልላቸው እነርሱን ከርእዮተ ዓለማቸው ማውጣት ጭንቅ ነው፡፡ ግን ዋጋቸው ምድራዊ ነው፤ ዋጋቸው ትንሽ ነው፡፡ ለትንሹ ነገር ትልቅ ዋጋ የከፈሉት፣ ለትልቁ ነገር ትንሽ ዋጋ የምንከፍለውን እኛን እየከሰሱን ይመስለኛል፡፡ የበለጠ አይቶ ያነሰ መኖር መቼ ያበቃል? የሚል ሙግት ሊነሣብን ይገባል፡፡
በአገልግሎት ዘመናችን ብዙዎችን በእግዚአብሔር ቤት ተቀብለናል፡፡ ጭካኔአችን እኛን ለሚመስለው አገልጋይ እንጂ ለምእመኑ ሩኅሩኅ ነን፡፡ ከሚያለቅሱት ጋር አብረን አልቅሰናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስእለት ለመናገር የሚመጡ የዓመት ደንበኞች ናቸው፡፡ በዓል በሌለ ቀን ግን ለስእለት እንዲያበቃኝ ወደ እግዚአብሔር ለምኑልኝ የሚሉን ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ ክረምት ጅረት በሚፈሰው ዕንባቸው ልባችንን ያቀለጡት፣ የራሳቸውን ተናግረው እኛ ስንነግራቸው መቀበል ያልሆነላቸው፣ ቊስላቸው እስኪጠግ ዓመታት የወሰደባቸው ብዙ አልቃሾች ዛሬም ይታወሱናል፡፡ ሕፃን ልጅ እናቱን አለቅሽም እያለ ገበያና ሥራ እስኪከለክል እንዳላስቸገረ፣ ሲያድግ ደግሞ እናቱን አትጠብቂኝ እያለ እንደሚፎክር እኛም አለቅ ያሉን፣ በእሹሩሩ የተኙልን፣ ልቅሶአቸውን የጋበዙን ልቅሶ ያለቀ መስሏቸው ዛሬ ስንፈልጋቸው ሊያገኙን እንደማይሹ እናያለን፡፡ ይህ ማደግ ነው ወይስ መቀጨት? አዎ ብዙዎች ከድተው የበሉትን እንጀራ እየረገጡ ነው፡፡ ለሰው ልጅ የሚሻለው የቱ ነው? መከራ ወይስ ደስታ? መምረጥ ያዳግተናል፡፡ ራሳችንን አናውቀውም፡፡ በክዳት፡-
·         ሰብከን ያሳመናቸውን መልሰን እያስካድን ይሆን?
·     ክርስትናን በመቀበላችን፣ መንፈሳዊውን እውቀት በማወቃችን ተጸጽተን ምነው እንደ ድሮው በነበርኩ ብለን ይሆን?
·         ክርስቶስ የተሸነፈ መስሎን እንደ ጴጥሮስ ከሰቃዮች ጋር እሳት መሞቅ ጀምረን ይሆን?
·         ወደተፋነውና በአደባባይ ወደረገምነው ዓለም ተመልሰን ለብዙዎች መደነቂያ ሆነን ይሆን?
·         ሌሎችን የሚያደነዝዝ፣ የሚያረሳሳ ኃጢአት እኛን አላደነዝዝ እያለን ተጨንቀን ይሆን?
·         ከተገፉት ጋር ላለ መቆም የገፊዎች ወዳጅ መሆንን ጥበብ ነው ብለን አስበን ይሆን?
·         ከእግዚአብሔር የት ይራቃል? ያሰብኩት ጋ ልድረስ ብዬ ነው ደግሞም ንስሐ ይገባል፤ ሰው ሁሉ የሚያድገው በዚህ መንገድ ነው ብለን ይሆን? የዚህን ትምህርት ሁለተኛ ክፍል ሳንጠብቅ አሁን ራሳችንን እንመርምር ቃል ኪዳናችንን እናድስ፡፡ ደጁን በፍጥረቱ ላይ ወደማይዘጋው አምላክ አቤት እንበል፡፡ እግዚአብሔር ያግዘን!
                                             ‹‹ወደ ኋላህ አትይ›› (ዘፍ. 19&17)፡፡
ይቀጥላል…

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።