የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ኋላህ አትይ / ክፍል 4

         
                                       የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ኅዳር ፲፰ / ፳፻፮ ዓ/ም
                              ወደ ቀድሞ አድራሻ መመለስ
                                                                  (ዮሐ. 21&1-14)፡፡
ከዓመታት በፊት አንድ ሰው ከውጭ አገር ገንዘብ ላከና ለእነ እገሌ ስጥልኝ አለኝ፡፡ አረጋውያኑ ለማየት በሚያሰቅቅ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ያ በጎ አድራጊ ሰው ከዛሬ ሠላሣ ዓመት በፊት ገና ትምህርት ቤት ሲሄድ እነዚያ አረጋውያን በድህነት ጨለማ ተውጠው ያያቸው ነበር፡፡ ከሠላሣ ዓመት በኋላ ወደ አገር ቤት ሲመለስ እነዚያ ድሆች በዚያ ድህነት ውስጥ ተዘፍቀው አያቸው፡፡ እርሱ ተማሪ ሳለም ረሀብተኞች ነበሩ፣ ትምህርቱን ጨርሶ፣ ከአገር ወጥቶ፣ አራት ልጆች ወልዶ፣ ትልልቅ ድርጅቶች አቋቊሞ ወደ አገሩ ሲመለስ እነዚያ ድሆች ግን ባሉበት ቦታ ረግተው ተቀምጠው ነበረ፡፡ ወደሚኖርበት የፈረንጅ አገር ሲመለስ እልፍ የማይለው ያ የድሆቹ ኑሮ ልቡን አራደው፤ በርኅራኄ ተነካ፡፡ እንቅልፍ አጣ፡፡ ከእነዚያ ጥቂት ድሆች ጋር ሃያ ድሆችን ጨምሮ በየወሩ መርዳት ጀመረ፡፡ በቀድሞ የረሀብ፣ የጨለማ አድራሻ መሆን ያሳዝናል፡፡ በሰንሰለታማ ረሀብ ለሚኖሩ ሰንሰለቱን የሚቆርጥ፣ በጨካኙ ረሀብ ላይ የሚጨክን ደግ ሰው ያስፈልጋል፡፡ በቀድሞ አድራሻ መገኘት ያሳዝናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ወደ ቀድሞ አድራሻ መመለስ ያሳዝናል፡፡ አግኝቶ ማጣት፣ ከብሮ መዋረድ፣ አምኖ መካድ፣ ጌታን ተከትሎ ጌታን መሸጥ፣ አብሮ በልቶ አላውቀውም ማለት እጅግ ያሳዝናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኋላ ስለ ተመለሱና ጌታን ከመከተል ዘወር ስላሉ ሰዎች ይናገራል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለት ጊዜ ተገለጠላቸው፡፡ እነርሱ ግን ልባቸው ከድቶ ስለ ነበረ ወደ ቀደመ ኑሮአቸው ለመመለስ፣ በደቀ መዝሙርነት የጀመሩትን ጉዞ በነጋዴነት በዓሣ ቸርቻሪነት ለመፈጸም ወደ ጥብርያዶስ ባሕር ኮበለሉ፡፡ የጎበዝ አለቃ፣ የከዳተኞች መሪ የሆነው የሁልጊዜ ቀዳሚው ጴጥሮስ ነው፡፡ ችኩልነቱ ለእምነትም ለክህደትም ይፈጥንበት ነበር፡፡ ጴጥሮስ ጌታችን በተያዘ ጊዜ ለብቻው ካደ፣ ጌታችን ተነሥቶ ሁለት ጊዜ ከተገለጠላቸው በኋላ ሌሎችን አስከዳ፡፡ አንድ አባት፡- ‹‹ክዶ ከማስካድ፣ ስቶ ከማሳት ጠብቀኝ›› ማለት ትልቅ ጸሎት ነው ይሉ ነበር፡፡
“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠ” (ዮሐ. 21÷1)፡፡ ጌታችን አሁን የተገለጠው በጸሎትና በጽሞና ለሚጠባበቁት ሳይሆን ከድተው ወደ ተጠሩበት ባሕር ወደ ጥብርያዶስ ለተመለሱት ደቀ መዛሙርት ነው፡፡ እርሱ የካዱትንም፣ የከዱትንም ይፈልጋል፡፡ የእንደ ገና አምላክ ነው፡፡ እንደ ገና ይፈልጋል፣ እንደ ገና ይጣራል፡፡ እኛ በራሳችን ተስፋ ብንቆርጥ እንኳ እርሱ በእኛ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ የጥብርያዶስ ባሕር ጌታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ያገኘበት ባሕር ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተስፋ ቆርጠው፣ እውነት እስከ መጨረሻው የተሸነፈች መስሏቸው ወደ ጥብርያዶስ ባሕር ኮበለሉ፡፡ ጌታችን ሁለት ጊዜ ቢገለጥላቸውም ልባቸው አልተመለሰም፡፡ የሸፈተን ልብ ተአምር አያስቀረውም፡፡ ስለዚህ ቀድሞ በተጠሩበት ስፍራ ተገኙ፡፡ ከመጠጥ ቤት ተጠርቶ መጠጥ ቤት መመለስ፣ ከዝሙት ስፍራ ተጠርቶ ወደ ዝሙት መመለስ፣ ከሐሰተኛ አኗኗር ተጠርቶ በሐሰት ስፍራ እንደ ገና መገኘት ከመንፈሳዊ ክብር ዝቅ ማለት ነው፡፡
“ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት በአንድነት ነበሩ፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ፡- ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ አላቸው፡፡ እነርሱም፡- እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን አሉት፡፡ ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም አላጠመዱም” (ዮሐ. 21&2-3)፡፡
የጥብርያዶስ ባሕር ሁለት ፀጉር ያበቀሉበት ቢሆንም ዛሬ ግን አልቀናቸውም፡፡ ሰባት ሆነው አንድ ዓሣ መያዝ አቃታቸው፡፡ ሕይወትን በራሳቸው አስተሳሰብ ለመምራት፣ በኅብረት ስምምነት ለማትረፍ ጌታን ጥለው ወጡ፡፡ ነገር ግን ምንም አላጠመዱም፡፡ ገጣሚው እንዲህ አለ፡-
ወይ ዓለም መውደድ መሞኘት
ጌታን ረስቶ ጌትነት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአንድ ወቅት፡- “የሰው ልጅ ከዛሬ ብዙ ሺህ ዓመት ጀምሮ በታሪክ እንደምንረዳው ከእግዚአብሔር ጥገኝነት ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፡፡ ያለ እርሱ ምንም ማድረግ፣ ምንም መሆን እንደማይቻል እናስተውል፡፡ እኛም ጥገኛ ላለ መሆንና ከእግዚአብሔር እጅ ለመውጣት በከንቱ አንድከም፡፡ ይልቅስ በእርሱ እንመን፣ በእርሱ እንደገፍ” ብለዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ያለ ጌታ ጌትነትን፣ ያለ ሕያው አምላክ መኖርን አቅደው ወደ ኋላ ተመለሱ፡፡ ሰው ተጠሪነት ያለውን ኑሮ አይወድም፡፡ ተጠሪነትን የመጥላት ባሕርይውን በእግዚአብሔርም ላይ ያሳያል፡፡ ራሱ ለራሱ አምላክ ለመሆን ይፈልጋል፡:
ሚዳቋ ከመሬት ጋር ተጣላች ይባላል፡፡ ከመሬት ጋር መጣላቷም ይገርማል፡፡ መሬት ተሸካሚ፣ መሬት የፍሬ መገኛ፣ መሬት ሀብት፣ መሬት ትዳር፣ መሬት ከባቴ አበሳ፣ መሬት መቀበሪያ ናት፡፡ ሚዳቋ ራሷ ጠይቃ ራሷ መልስ እየሰጠች ከመሬት ተጣላች፡፡ መሬት ታስፈልገኛለች ብላ አስባ አታውቅም፣ እኔ ለመሬት አስፈልጋለሁ በሚል አሳብ ተወጥራለች፡፡ ሚዳቋም ከዚህ በኋላ ካንቺ ጋር አልኖርም ብላ ከመሬት ለመለየት ሩጫ ጀመረች፡፡ ከመሬት ግን መለየት አልቻለችምና ልቧ ፈርጦ ሞተች ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ከመሬት ይልቅ የተሸከመን ነው፡፡ የፈጠረን፣ ያሳደገን፣ ለወግ መዓርግ ያበቃን ነው፡፡ ትዳር ሀብታችን፣ ገመናችንን ሸፋኝ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ብንለይ የምንጎዳው እኛ ነው፡፡ በአየር ብናኮርፍና አየር መሳብ ብናቆም የሚጎዳው አየሩ ሳይሆን እኛ ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ብንጣላም ተጎጂዎቹ እኛ ነን፡፡ ከእርሱ መለየት አይቻለንም፡፡ በሰማይ በምድር አለ፡፡ ከእርሱ ርቀን ላንርቅ ባንሞት መልካም ነው፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ተለይተው ወደ ተጠሩበት ወደ ጥብርያዶስ ቢሄዱም አንዳች አላተረፉም፡፡ እንዲሁም እኛ ጌታችንን ከመከተል ወደ ኋላ ብንል የሚገጥመን ባዶነትና ጨለማ ነው፡፡ ወደ ኋላ ስንመለስ ዓለም እንኳ በሙሉ ልብ አትቀበለንም፡፡ የምትቀበለን እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ ስደተኛ ነው፡፡ ብዙዎች ከክርስትና ኮብልለው ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡ ሌሎች የሚያደርጉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም መመሳሰል ቢፈልጉም ዓለም ግን፡- “ድሮ እኮ አማኒ የነበረ ነው፤ ላይዘልቅበት ገብቶ ነው” ትላለች እንጂ ቂሟን አትረሳም፡፡ ክርስቶስ ጋ ደርሶ ለመጣ ሰው ዓለም ሙሉ ልቧን አትሰጠውም፡፡ የምታኖረው እየሰደበች ነው፡፡ 
በእውነት ክርስቶስን የቀመሰ ሰው በሌላ የዓለም ነገር መርካት አይችልም፡፡ ድሮ እንኳ የሚያረካው ኃጢአት አሁን አያረካውም፡፡ እውነትን አውቋልና፡፡ የጠፋው ልጅ ከእርያ አሠር እንኳ ለመጥገብ ይመኝ እንደ ነበረ እናነባለን (ሉቃ. 15&16)፡፡ የእርያ አሰር ለሰው ምግብ መሆን አይችልም፡፡ የእርያ አሰር የአረማውያን እርካታ የሆነው ዘፈን፣ ዝሙት… ነው፡፡ የጠፋው ልጅ ዘፍነው ራሳቸውን በሚረሱ፣ ሰክረው በሚደነዝዙ ሳይቀር ይቀና ነበር፡፡ ምንም ኮብልሎ ዓለም ቢገባም እንደ ዓለማውያን ግን በኃጢአት መርካት አልቻለም፡፡ ዛሬም ብዙ አገልጋይ የነበሩ ሰክረው እንኳ ክርስቶስን እያሰቡ ያለቅሳሉ፡፡ ራሳቸውን ለመርሳት በኃጢአት ለመደሰት ይሞክራሉ ግን አልሆነላቸውም፡፡ ያ የጠፋው ልጅ መፍትሔ የሆነለት ወደ አባቱ መመለስ ብቻ ነው፡፡ ለዛሬዎቹም ኮብላዮች መፍትሔው መንገድ አጋምሶ ወደሚቀበለው ጌታ መመለስ ብቻ ነው፡፡ ጌታዬን ብዬ ከሰርኩ፣ ጌታን ጥዬ አተረፍኩ የሚሉ ሰዎችን ብንሰማ በእውነት እየዋሹ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንርቅ የገዛ ኅሊናችን እንኳ ይዋጋናል፡፡ ባዶነትንም እናመርታለን፡፡
ሰው ወደ ኋላ ሲመለስ የሚጨልምበት ከቀድሞው በላይ ነው፡፡ የሚያውቀው የእውነት ቃል እየተዘነጋው ይመጣል፡፡ በዙሪያው ሁሉ ድምፅ ይከበዋል፡፡ ሁሉም ሰው ስለ እርሱ የሚናገር እስኪመስለው በብዙ ቃላት ይወጋል፡፡ ደንባራና ፈሪ ይሆናል፡፡ በራስ መጨከን ማለት በክርስቶስ አለመጽናት ነው፡፡ እናንተስ በእርግጥ ከጌታችሁ ጋር ናችሁ? እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው ስትሉ እኔም ከእግዚአብሔር ጋር ነኝ ለማለት ትችላላችሁ? በሩን በፈጠረው ላይ አይዘጋምና ደግሞም ከዓለም ማባበል የእርሱ ተግሣጽ ይሻላልና ወደ እርሱ እንመለስ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ