የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ኋላህ አትይ / ክፍል 5

        
                                ረቡዕ  ታኅሳስ 16 2006 /
                                       ፍለጋው ያደክማል
በብሉይ ኪዳን ወደ ኋላ ስለ ተመለሱ ሰዎችና ስለ ምርጫቸው ውጤት ስናነብ በአዲስ ኪዳን ግን በክርስትና እምነት ስለ መጽናት ግልጽ ትምህርትና ማስጠንቀቂያ ጭምር እናገኛለን፡፡ እነዚህ ማስጠንቀቂያዎችና ትምህርቶች ከሌሎች ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ጋር ጣልቃ ገብ ሆነው የተሰጡ ብቻ ሳይሆኑ ወጥ መልእክትም ሆነው ተሰጥተዋል፡፡ ይልቁንም ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያና በዕብራውያን መልእክቱ ወደ ኋላ የመመለስን መንስኤና ጉዳይ አብራርቶ ጽፎልናል፡፡ በአዲስ ኪዳን ላይ ወደ ኋላ ስለ መመለስና ስለሚያስከፍለው ዋጋ ተንቀሳቃሽ መጻሕፍት ሆነው የሚያስተምሩን ይሁዳና ዴማስ ናቸው፡፡ ይሁዳ መንፈሳዊ ዓይኑ ስለ ታወረ ገንዘብን ከክርስቶስ በላይ በማየት ከሐዋርያነት ጥሪው ራሱን አፈናቅሏል፡፡ ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች መንፈሳዊ ዓይናቸው የታወረ ነው፣ ከእግዚአብሔር መንግሥትም በልዩ ጭካኔ የሚለዩ ናቸው፡፡ ጨካኝ ሁሉ በራሱ ላይ መጨከን ይከብደዋል፡፡ በፍቅረ ንዋይ የተለከፈ ግን በራሱ ላይ የመንግሥተ ሰማያትን በር ዘግቶ የሚሄድ ጨካኝ ነው (ማቴ. 27፡1-10)፡፡ ከይሁዳ ቀጥሎ የምናገኘው ዴማስን ነው፡፡ ዴማስ የሚመጣውን ዘላለማዊ ዓለም ንቆ የአሁኑን ዓለም ወዶ ከዘመናዊነት ጋር ጋብቻ ፈጽሟል (2ጢሞ.4፡10)፡፡ የሁለቱም ፍጻሜ ግን አላማረም፡፡ ይሁዳ ታንቆ ሞተ፣ ዴማስ ስም አጠራሩ ጠፋ፡፡ 
ይሁዳ ማለት የስሙ ትርጉም ምስጋና ማለት ነው፡፡ የኃያል ነገድና የነገሥታት ዘርን የሚያመለክተው ‹‹ይሁዳ›› የሚለው ስም ነው፡፡ በዚህ ስም የተጠራው ከዳተኛው ሐዋርያ ግን ስሙን ሳይቀር በማርከሱ ዛሬ ልጁን ይሁዳ ብሎ የሚጠራ አባት የለም፡፡ ሰብእናውን ብቻ ሳይሆን ስሙን ጭምር ያረከሰ ሐዋርያ ነው፡፡ ወደ ኋላ ስንመለስ ስማችን ሳይቀር የሚጠላ፣ እንደ በሽታ የሚፈራ፣ ትውልድንም ያስታል ተብሎ የሚሰጋ ይሆናል፡፡ ዴማስም የአሁኑን ዓለም በመውደዱ በሥጋው ጨርሶ በነፍሱም ሲወቀስ ይኖራል፡፡ የጀመሩትን ዓላማ አለመፈጸም በብርቱ ያስነቅፋል፡፡ 
በክርስትና ውስጥ ‹‹ነበር›› ተብሎ ሲነገር ደስ የሚለው ለኃጢአት እንጂ ለጽድቅ አይደለም፡፡ ሰካራም ነበረ፣ ዓመፀኛ ነበረ ሲባል መለወጥን፣ አዲስ ሰው መሆንን የሚያሳይ በመሆኑ የሰማው ሁሉ ለምስጋና አንደበቱን ይከፍታል፡፡ ቄስ ነበረ፣ ሰባኪ ነበረ፣ ክርስቲያን ነበረ የሚለው ቃል ግን የቁም ሞትን የሚያረዳ በመሆኑ ልብን ያዝላል፡፡ እነ ይሁዳ እነ ዴማስ ሐዋርያ ነበሩ፡፡ አሁን ግን የሉም፡፡ በታሪክ መዳን የለም፣ ሩጫችንን በመፈጸም ግን ወደ ክብሩ እንገባለን፡፡ ይሁዳ ሐዋርያ ነበረ፣ ግን ገሀነም ወረደ፣ ፈያታዊ ዘየማን ሽፍታ ነበረ፣ ግን ወደ ገነት ገባ (ሉቃ. 23፡43)፡፡ 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንንም በማባበል ወደ ወንጌል አልጠራም (ዮሐ. 6፡68)፡፡ ወንጌል የሚያስከፍለውን ዋጋም በግልጽ ተናግሯል (ሉቃ. 14፡25-33)፡፡ መንገዱ የመስቀል መንገድ መሆኑን አልሸሸገም፡፡ በጎዳና ላይ ስንሄድ መስቀለኛ መንገድ ላይ አደጋ ይበዛል፡፡ እንዲሁም ክርስትና የመስቀል ጉዞ በመሆኑ ብዙ ትግሎች አሉት፡፡ ፍጻሜው ግን የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ “ዓለም ከኋላዬ፣ መስቀል ከፊቴ” በማለት የምንጀምረው ጉዞ ነው፡፡ ጌታችን የመስቀሉን ጎዳና ብቻ አልተናገረም፡፡ ራሱም ምሳሌ በመሆን በቀራንዮ በር ገብቶ በጎልጎታ ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ የዓለም ጉዞ በጎልጎታ (የትንሣኤ) በር ገብቶ በቀራንዮ (የመከራ) በር መውጣት ነው፡፡ የክርስትና ጉዞ ግን በቀራንዮ (የመከራ) በር ገብቶ በጎልጎታ (የትንሣኤ) በር መውጣት ነው፡፡ 
ጌታችን በተያዘ ጊዜ በዚያች ምሽት ብዙዎች ወደ ኋላ ተመልሰዋል፡፡ የሁሉም ሰው ፈተናው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ይሁዳ ወታደርና ችሎት ፈተናው አይደለም፡፡ አልቅሶ ፍርድ ማሳት ያውቅበታል፡፡ ገንዘብ ግን ትልቅ ፈተናው ነበረ፡፡ ልቡ ለገንዘብ ይርዳል፤ ገንዘብን ለማግኘት አምላኩን ያጣል፡፡ ጴጥሮስ ደግሞ ገንዘብ ፈተናው አይደለም፡፡ ታዲያ በዚያች ሰው ሁሉ እንደ ስንዴ በሚበጠርባት ሌሊት ግማሹ በፍርሃት፣ ግማሹ በገንዘብ ተፈታ፡፡ የክርስቶስን መንፈሳዊ ሀብትነት ላልተረዳ ገንዘብ ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔርንም የማይፈራ፣ የማያስፈራው ያስፈራዋል፡፡ በሰዓታት ጸሎት ላይ፡- 
“ወርቅ ዘተመክዓበ፣ ወመድፍን ዘተረክበ፣ ምናን ዘበዝኃ፣ ወመክሊት ዘረብኃ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ”
ትርጓሜ፡- “የተከማቸ ወርቅ፣ ተሰውሮ የተገኘ የሀብት ማከማቻ፣ የበዛ ትርፋችን፣ የበረከተ መክሊታችን ኢየሱስ    ክርስቶስ ነው” ይላል፡፡
የወርቅ ክምችት ዕረፍት ይነሣል፡፡ የክርስቶስ ሀብትነት ግን ያሳርፋል፡፡ የአልማዝ መዝገብ ያስጨንቃል፡፡ የክርስቶስ መክሊትነት ግን ለዘላለም ያጽናናል፡፡ ይሁዳ ከጌታው ጋር ሦስት ዓመት ኖረ፣ ከገንዘብ ጋር ግን አንድ ቀን አልኖረም፡፡ ዕድሜ የሚያረዝመውን ሀብት፣ ዕድሜ በሚያሳጥረው ሀብት ለወጠ፡፡ ያውም ለሚበትነውና ለማይበላው ሀብት ከጌታው ተለየ፡፡ የማያልፈውን ሀብት በሚያልፈው ሀብት የለወጡ፣ የሚያሳርፈውን በሚያሰቅለው ሠላሣ ብር የለወጡ እነ ይሁዳ እንዴት ከሰሩ! አወይ ገበያ አለማወቅ! ወርቅ ሰጥቶ መደብ ይዞ መመለስ፡፡ እውነተኛውን ወርቅ ጥሎ ቅቡን ይዞ መግባት
ወደ ኋላ ማለት ባለቤቱ እንኳ የማይገነዘበው ሰይጣን እያንዳንዷን ጥቃቅን ግድፈት እንድንለምዳት እያደረገ ወደ ትልቅ ክህደት ውስጥ እንድንገባ የሚያደርገን ነው፡፡ መኪና ወደፊት በሚሄድበት ፍጥነት ወደ ኋላ አይሄድም፡፡ አማኒም በአንድ ጊዜ አይክድም፡፡ የክህደት ጉዞ የሚያንደረድር ሳይሆን የሚያንሸራትት ነው፡፡ ሰይጣን ያለንበትን ሁኔታ እንድንለምደው እያደረገ ወደ ጥልቅ ውድቀት ይወስደናል፡፡ ሰው መሞት ሲጀምረው ከወደ እግሩ መቀዝቀዝ ይጀምራል፡፡ እንዲሁም አማኒው ወደ መንፈሳዊ ሞት እያዘገመ ነው የምንለው እግሩ ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ ሲጀምር ነው፡፡ እንቁራሪት የሚበሉ ሰዎች የፈላ ውሃ ውስጥ አይከቷትም ይባላል፡፡ ከቀዝቃዛው ውሃ ውስጥ ይከቷትና እሳት ላይ ይጥዷታል፡፡ ውሃው ለብ ሲል ቀዝቃዛውን ሳደንቅ ነበር ለካ ለብ ያለው ጥሩ ነው እያለች ለብታውን ትቀበላለች፡፡ እንዲህ እያለች እያንዳንዱን የግለት መጠን እየተላመደች  በመጨረሻ ፈንድታ ትሞታለች ይባላል፡፡ ከጅምሩ የፈላ ውሃ ውስጥ ቢከቷት ዘላ ትወጣለች፡፡ እንድትለምደው እያደረጓት ግን ይገድሏታል፡፡ እንዲሁም አማኒውን በአንድ ጊዜ ካድ ቢሉት ዘራፍ ይላል፡፡ ቀስ በቀስ ግን እንዲክድ የማላመድ ሥራ ይሠራለታል፡፡ በእውነት አሁንም ከጌታችን ጋር ነን?  
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐሥራ ሁለት ዓመት ብላቴና ሳለ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከአሳዳጊው ከዮሴፍ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፡፡ ከበዓል የሚመለሱ መንገደኞች በኅብረት መጓዛቸው የተለመደ ነው፡፡ መንገዱ እንዲቀላቸው፣ ወንበዴ እንዳይደፍራቸው በኅብረት ይጓዙ ነበር፡፡ ታዲያ በዓሉን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ወደ ገሊላ ሲጓዙ፡-            “ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፡፡ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር፡፡ ከመንገደኞች ጋር ያለ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ ከሦስት ቀንም በኋላ … አገኙት” (ሉቃ. 2&41-51)፡፡
ኢየሱስን ከአጠገብ መነጠል አይገባም፡፡ ሁልጊዜ እርሱ ከእኛ ጋር እንዳለ፣ እኛም ከእርሱ ጋር እንዳለን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ያለ ኢየሱስ አንድ ቀን ከተጓዝን ኢየሱስን ለማግኘት ሦስት ቀን እንደክማለን፡፡ ከእርሱ ጋር ለአንድ ቀን እንኳ መለያየት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንድ ቀን አለመጸለይ፣ አንድ ቀን ቃሉን አለማግኘት፣ አንድ ቀን ኅብረት አለማድረግ ወደነበሩበት ለመመለስ ያደክማል፡፡ እናቱ ድንግል ማርያምና ዮሴፍ ገሊላ ደርሰው እንደገና እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ የጨረሱትን ጉዞ እንደ ገና ጀመሩ፡፡ ልባቸው ሰላም እያጣ የት ይሆን እያሉ ተንከራተቱ፡፡ በእውነት በነጻ ያገኘነውን ጌታ ቸል ካልነው የምናገኘው በዋጋ ነው፡፡ ፍለጋው ያደክማል፡፡ ውድቀቱን በወደቁት መማር እንጂ ሲሞክሩት ያራቁታል፡፡ በእርግጥ በጉዞአችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር አለ? እርግጠኞች መሆን ይገባናል፡፡ 
                                                                                    
                                                                                     ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ