የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ኋላህ አትይ / ክፍል 6

                                                ዓርብ ጥር 16 2006 ዓ/ም

በአራተኛ ማርሽ እየበረረ ያለ መኪና ሲቀዘቅዝ ካቆመበት ከአራተኛ ሳይሆን ከአንደኛ ማርሽ ይጀምራል፡፡ ታሳቢና ማስተዛዘኛ ሆኖ ከሁለት እንኳ መነሣት አይችልም፡፡ ከቆመ እንደገና ከአንደኛ ማርሽ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ መኪና በቀን ውስጥ አንደኛና አራተኛን ሲነካ ይውላል፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ ተመሥርተን ብንሄድ ክርስትናንም ከፍ ባለ ሩጫ እየሮጥን ከሆነ ስንቆም የምንጀምረው ከአንድ ነው፡፡ በአገልጋይነት እየሮጥን ሊሆን ይችላል፤ ከቆምን ግን ከተገልጋይነት እንጀምራለን፡፡ ከፍ ባለ የሥነ መለኮት እውቀት እየፈጠንን ይሆናል፣ ከቆምን ግን ከንስሐ እንጀምራለን፡፡ በታላቅ መሪነት እየገሰገስን ይሆናል፤ ከቆምን ግን በጉባዔ ላይ በሚደረግ ይቅርታ እንጀምራለን፡፡ ከቀዘቀዝን ከአንድ መጀመራችን ግድ ነው፡፡ መሠረትን ሲመሠርቱ መኖር ከፍታን አለማየት እጅግ ከባድ ነው፡፡
በክርስትና ሦስት ዓይነት መንገደኞች አሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ፡- የንጉሥ ክርስቶስ  ደግነት፣ የርስተ መንግሥተ ሰማያት ውበት እየታያቸው ወደፊት የሚገሰግሱ ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ፡- በእግዚአብሔር ቤት ዕድሜ በማስቆጠር ብቻ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ዐጽመ ርስት ቆጥረው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሦስተኛዎቹ፡- ከክርስቶስ ሙሴን፣ ከወንጌል ኦሪትን፣ ከሰማይ ምድርን መርጠው ወደ ኋላ የሚሉ ናቸው፡፡
ክርስትና ቀላል የሚሆነው ወደ ፊት ሲገሰግሱ ነው፡፡ በጀመሩበት ፍቅር የማያልቀው የዓለም ወዳጅነት ነው፡፡ ክርስትና ግን የእውነት እንጂ የወረት መንገድ አይደለም፡፡ የክርስትናው ኃይል የሚርቀው ክደው ወደ ዓለም ለሚገቡት ሰዎች ብቻ ሳይሆን እያመነቱ በሚኖሩ፣ ቀን እስኪያልፍ ቤተ እግዚአብሔርን ከተጠጉትም ይርቃል፡፡ ክርስትናን በሥጋ ኃይላችን መኖር አይቻልም፣ መንፈሳዊውን ውጊያም በዓለም ባሸነፍንበት ጉልበት ድል መንሣት አይሆንልንም፡፡ ክርስትናን የምንኖረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ድልንም የምንወርሰው በሚዋጋልን በጌታችን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የቆረጡና የወሰኑ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡ ዕውቀታችንና ስሜታችን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ አይካፈልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የሚካፈለው ውሳኔአችን ወይም የተሰጠው ፈቃዳችን ነው፡፡ ክርስትና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ የምንኖረው ሕይወት ከሆነ፤ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የሚገኘው በመጽናት ነው፡፡ 


አዎ ክርስትና ቀላል ነው፡፡ ክርስትና ቀላል ነው ብለን ስንናገር ክርስትና ከባድ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎች ይቃወሙን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ መጥቶ መዳን ተፈጽሞ፣ መቃብርና ሲኦል ተሸንፎ፣ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ፣ ቤተ ክርስቲያን ተመሥርታ፣ ቀሳውስት ጳጳሳት ተሹመው፣ ሊቃውንት ምሥጢር አስፋፍተው፣ የእምነትን ገድል የፈጸሙ ብዙ ጻድቃንና ሰማዕታት ምስክርነታቸው ከብቦን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተናኝቶልን ክርስትናን መኖር ቀላል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሕይወትና በረከት ባልነበረበት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት፣ ገነት ተዘግታ ራሱን እግዚአብሔርን ብቻ ያመለኩት፣ መንፈሰ እግዚአብሔር በራቀበት፣ ቤዛነት ባልተፈጸመበት፣ ሰው ማኅደረ ሥላሴ ባልሆነበት ዘመን፣ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ሰዎች እንኳ እግዚአብሔርን ማምለክ ከባድ ነው አላሉም፡፡ እንደውም፡- “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ& እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ& መቅደሱንም እመለከት ዘንድ” (መዝ.72፡28፤ 26÷4) ብለዋል፡፡
በርግጥ ክርስትና ቀላል የሚሆነው ወደ ፊት ሲገሰግሱ ብቻ መሆኑን ጌታችን ተናግሯል፡- “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ ቢመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” ብሏል (ሉቃ. 9÷62)፡፡ በሬዎች ጠምዶ፣ ቀንበር አጋድሞ፣ ሞፈር ዘርግቶ፣ ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ ማለት በሰማይና በምድር፣ በሰዎችና በገዛ ኅሊና ያስወቅሳል፡፡ ኃይለኞች የነበሩ አንገታቸውን ደፍተውልን፣ ዓመፀኞች የነበሩ ተማርከውልን፣ በገዛ መንገዳቸው ጠፍተው የነበሩ ባመላከትናቸው ጎዳና ፈሰውልን፣ ድምጻችንን እየሰሙ ወደፊት ለመንጎድ ዝግጁ ሆነውልን ሳለ፣ እኛ ግን ወደ ኋላ ካልን አሳዛኝ ነው፡፡ እውነተኛ አዝማች ከፊት ይቀድማል እንጂ አስከትቶ ከቤቱ አይውልም፡፡ አዝማሪ ግን አነቃቅቶ ጦርነቱ ሲፋፋም ይመለሳል፡፡ ዛሬም ብዙዎችን አስከትተው እነርሱ ግን ከቤታቸው የዋሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ያያቸውም፡- ‹‹ጡሩምባ ነፊ ቀብር አይወጣም›› እያለ ይተቻቸዋል፡፡ እርሱ በለፈፈው ልቅሶ፣ ሰው በዕንባ ሲራጭ፣ ደረት እየተደበደበ ሲናድ ጡሩምባ ነፊው ግን ጠላ ቤት ቁጭ ብሎ ይሳከራል፡፡ ዛሬ እየሆነ ያለው እንዲህ ነው፡፡ ልጁ ተወልዶ ልጁን ሳያዩ እንደሚሞቱ እናቶች የለፉበትን አገልግሎት ፍሬውን ሳያዩ በቁማቸው ያሸለቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በፊት ለፊት በር አስገብተው በኋላ በር የወጡ አያሌ ናቸው፡፡ እነርሱ ያመጧቸው የእሳት ትንታግ ሆነው ሲያገለግሉ ያየው ታዛቢ፡- ‹‹የአመድ ልጅ እሳት›› እያለ የሟቹን ልጅ ሕልውና ያደንቃል፡፡ ምድራውያኑ እንኳ አጋግዬ አልመለስ በማለት ግፋ በለው ሲሉ መንፈሳውያኑ ግን የሰበኩትን እውነት ክደው ወደ ዓለም ከሄዱ አሳዛኝ ነው፡፡ 
በሬዎቹን የጠመደው፣ ለቀንበር ዝቅ ያደረጋቸው፣ ሞፈሩን የዘረጋውና ዕርፉን የጨበጠው ገበሬ ማረሻው መሬት ውስጥ ከገባ በኋላ እያዜመ ይሰቀስቀዋል፡፡ ዕርፉን ከነቀለ ግን መጓዝ ይቀርና ሸክም ይሆንበታል፡፡ ክርስትናም ወደፊት ሲሄዱ ድል ነው፣ ወደ ኋላ ሲመለሱ ግን ሸክምና ዕዳ ነው፡፡ የክርስትናችን ኃይል የእግዚአብሔር ደስታ ከሆነ እግዚአብሔር ደስ የሚለው ወደፊት በሚገሰግሱት ነው፡፡ ቃሉ፡- “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው÷ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ÷ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” (ዕብ. 10 37-38) ይላል፡፡ ወደ ፊት ስንሄድ የእግዚአብሔር ደስታ ኃይል ይሆነናል፡፡ 
የክርስትናው ሁለተኛ ተጓዦች ባሉበት የሚረግጡ ናቸው፡፡ ወደ ኋላ የመመለስን ያህል ባሉበት መርገጥም አደገኛ ነገር ነው፡፡ ክርስትናው ለእነዚህ ግማሽ ዋጋ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ክርስትና የታሪክ ክብር ሳይሆን ሆኖ መገኘትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሐናና ቀያፋ ዘመናቸውን በሙሉ በቤተ መቅደስ የኖሩ፣ የካህናት ዘር ናቸው፡፡ ነገር ግን ፈያታዊ ዘየማን የወረሳትን መንግሥተ ሰማያት አልወረሱም፡፡ ሽፍታ የገባበትና ካህናት የወጡበት ይህች መንግሥተ ሰማያት ምንድናት ብለን መመርመር አለብን፡፡ 
ውኃ ወደፊት ሲጓዝ እየጠራ ይሄዳል፡፡ ወደፊት የሚገሰግሱም ራሳቸውን እያደሱ፣ በኃይል እየበረቱ የክርስትናውን የድል ገመድ ይጨብጣሉ፡፡ ውኃ ከረጋ ግን ራሱንና የሚጠቀሙትን ይበክላል፡፡ እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤት የረጉ፣ የዚያን ጊዜ ዝማሬ፣ የዚያን ጊዜ ስብከት እያሉ የትዝታ ወተት የሚጋቱ፣ የሞቀውን ልብ የሚያቀዘቅዙ፣ በትጋት የሚሮጠውን፡- ‹‹እኛም ስንጀምር እንደ አንተ ነበርን›› እያሉ የሚያሸማቅቁ፣ አትገቡም አታስገቡም የተባሉ የበር ላይ ጋሬጣ ናቸው፡፡ ቃሉ፡- በቤት ውስጥ የጠፉ ድሪሞች ይላቸዋል(ሉቃ. 15፡8-10)፡፡ ባሉበት መርገጥም ሆነ ወደ ኋላ መመለስ ሁለቱም አንድ ነው፡፡ 
ጳውሎስ ሐዋርያ፡- ‹‹አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውንም የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና›› (ዕብ. 6፡4-6) በማለት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ ልብ አድርጉ! ማስጠንቀቂያ ማስፈራሪያ አይደለም፡፡ ከገደል በፊት ያለ የትራፊክ ምልክት ማስፈራሪያ አይደለም፡፡ ዋጋ ሳይከፍሉ፣ ገንዘባቸውን ወይም ሕይወታቸውን ሳይከስሩ መማር ለሚፈልጉ ሁሉ ማስተማሪያ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ኃጢአታቸው ንስሐ የለውም አልተባለም፡፡ እነርሱን ለንስሐ መጋበዝ ግን ከባድ ነው፡፡ ከባድ የሚያደርገው ትንሹ ዕውቀታቸው ነው፡፡ ስንነግራቸው ‹‹የምትለውን ዐውቀዋለሁ፣ እኔም የቲዎሎጂ ተማሪ ነበርኩ፣ እኛ ያልሮጥንበት አገልግሎት የለም፣ እገሌን ታውቀዋለህ የእኔ ተማሪ ነበር . . . ›› እያሉ የንስሐን ድምፅ ስለሚገፉ እነርሱን ለንስሐ መጋበዝ ከባድ ነው፡፡
በተከታታይ ባቀረብናቸው መልእክቶች የሚያመነቱ ልቦችን ለማስጠንቀቅ፣ የጠፉትን በደወል ድምፅ ለመጥራት ሞክረናል፡፡ እኛም ያለንበትን በመመርመር ወደ ኋላችን ከማየትና ክርስትናን ቀምሰን እንዳልቀመሰ ከመሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን!
ሁሉን የምታሸነፍ የምትረታ
ዘላለማዊ ነህ የእኛ ጌታ
                                         ሰባኪ ዘማሪ ቢክድህ
        አንተ አትለወጥም ሕያው ነህ
ተፈጸመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ