የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ

ለአንገትህ ወርቅ ሲያምርህ ለጭንቅላትህ ደግሞ እውቀትን ተመኝ ። ሐሜት የሰይጣን ልኳንዳ ነው ፣ የሚወራረደውም የወንድም ሥጋ ነው ። በስድብ የሚገድሉ አልገደልንም ብለው ይጽናናሉ ። የሌሎች ስለት እንዳመመህ ያንተም ጦር ሌሎችን እንደሚያሳምም አትርሳ ። የማይታየው ጥላቻ የሚታይ ግድያን ይወልዳል ። ትልቅ የጦርነት ውድማ የታወከ ልብ ነው ። አሳብ ዘር ፣ ተግባር ፍሬ ነው ። የሚበቅለው የዘራነው እርሱ ራሱ ነው ። ለመብለጥ ማነስ ሕጉ ነው ። ጥበብ ከድቶህ ለውበት አትጨነቅ ። የከበረን ነገር በከበረ ቦታ አስቀምጠው ፣ ወዳጅህንም በልብ አኑረው ።

ወዳጄ ሆይ
ለመርዳት ብዙ ማወቅ ሳይሆን ትንሽ መራራት በቂ ነው ። ችግር ትንታኔ ሳይሆን መፍትሔ ይፈልጋል ። ብልህ ያለውን ይዞ ይጸልያል ። ከጨለማ በኋላ ብርሃን ቢመጣም የሚያዩት የጸኑት ናቸው ። ክፉ ቀኖች ንብረትህን እንጂ ጠባይህን እንዳይቀሙህ ተጠንቀቅ ።
ወዳጄ ሆይ
እያንዳንዱ ቀን ክፋትንም ደግነትንም የምናነብበት መጽሐፍ ነው ። መኖር ብዙ ጉድ ያሰማል ፣ እግዚአብሔር ግን ሕይወትን ያድሳል ። ችሎታ ታማኝነት ከሌለው ከንቱ ነው ። ከሁሉ የበለጠ ሌባ አንተነትህን የሰረቀብህ ነው ። የዘረፋ ሀብት በዘራፍ ያልቃል ። የእኔ መቸገር ምክንያቱ የእገሌ ማግኘት ነው ብለህ አታስብ ።
ወዳጄ ሆይ
የማያፈቅር ተፈቃሪ ሁልጊዜ ባለ ዕዳ ነው ። ዓለም የቆንጆዎች ሳትሆን የሰው ልጆች ናት ። እያዩ አለማየት ከእግዚአብሔር ያጣላል ። ልብስ የአቅምህ እንጂ የጠባይህ መለኪያ አይደለም ። ወዳጅ የምታገኘው ወዳጅ በሆንከው መጠን ነው ። ሳትወድ መወደድን መፈለግ ካልዘራህበት ማሳ ለማጨድ መውጣት ነው ። መያዣ ለሌለው ሙልጭልጭ ሰው ልብህን አትስጥ ። ከእብደት ጋር ለተጋባ ሰው ጸልይ ። የማይጠነቀቅን ተጠንቀቀው ። ተስፋህ ተስፋ ለቆረጡት የሚያቀጣጥል ችቦ ይሁን ።
ወዳጄ ሆይ
መኖርም መሞትም አትችልም የሚሉ ሰዎች ሲገጥሙህ ለሥላሴም ሰማይን የለቀቅነው በቸርነታችን ነው ማለታቸው አይቀርም ። ፍርድ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ነው ። የሰላም ገመድ የማያስረውን የፍርድ ገመድ ያስረዋል ። ሐሰተኛ ፍርድ ተበቃይ ልቦችን ያፈራል ። ያማረ ቤት ያለ ብርሃን ውበቱ አይታይም ፣ ወጣትም ያለ ቅንነት አይደምቅም ። የታሰሩ ልቦች የታሰሩ አገሮችን ይፈጥራሉ ። አልቀው የሚያበሩልንን ዝም ካልን ያለቁ ቀን ይጨልምብናል ። ራስ ወዳዶች በሰላም የሚኖሩት ደጎች እስካሉ ድረስ ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ምን ያህል አፈቅራለሁ የሚለውን ለምትለካው ያፈቀርከውን ሰው ስህተቱን በታገሥከው መጠን ነው ። አድር ባይ ብዕሮች ለዘመኑ ጣዖት የሚያጥኑ ናቸው ። ፍቅር የተቀበለውን እንጂ የሰጠውን አይቆጥርም ። የገበያ ቸርነት ማስታወቂያው ሲደበዝዝ ተመላሽ ይሆናል ። በዓለም ላይ ፍቅርን መቀበል የማይችል ልብ ትልቅ ወኅኒ ቤት ነው ። ዘረኝነት ራስን አስሮ ማሰቃየት ነው ።

ወዳጄ ሆይ
ብዙ ዕድሜ ሳይሆን ብዙ ሥራ እንዲሰጥህ አምላክህን ለምን ። ከሳሾችህ እንዲያፍሩ ሁልጊዜ በንስሐና በተግባር ላይ ሁን ። ገንዘብ በሌለበት ቦርሳ ይኖራል ፣ ፍቅርም ያለ ንብረት ይቀጥላል ። ሲጠጣ የሚደሰት ካልጠጣ ኀዘነተኛ ነው ። የሱስ ላይ ፕሮጀክት ሱሱ ሲያልቅ ያበቃል ። ሥራውን ያልጨረሰ ከሞት መደበቅ ይፈልጋል ። በመጨረሻ መጸጸትና በአምላክ ፍርድ ፊት መቆምህ አይቀርምና በልበ ደንዳናነት ሌሎችን አትጉዳ ።
ወዳጄ ሆይ
ሐኪም ይታመማል ፣ ሰባኪም ይሳሳታል ፣ አባትም ሞኝ ይሆናል ፣ ጎበዝም ይደክማል ፣ ኃያልም በሰው እጅ ይወድቃል ፣ ብልህም ከሞኝ በላይ ስህተት ይፈጽማል ። እግዚአብሔር ብቻ ያው ሁኖ ይኖራል ። የቱንም ያህል ብትከብር ከዚህ በፊት ከከበሩት አትበልጥም ። “የቼዝ ጨዋታ ሲያልቅ ንጉሡም ንግሥቲቱም ወደ ሳጥን ይገባሉ” ይባላል ። የቼዝ ዓለም ሲያበቃ የከበሩም የተዋረዱም ሁሉም ጥርኝ አፈር ይሆናሉ ።
ደስ ብሎህ ዋል ።
ምክር 23
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ