የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ

ብዙ ብትወልድ እግዚአብሔር የሚባርክህ በአንዱ ነው ። አብርሃም ስምንት ወልዶ በአንዱ በይስሐቅ ተባረከ ። ዳዊት ብዙ ወልዶ በሰሎሞን ተባረከ ። ልጆችህ መልካቸው ለየራስ እንደሆነ ጠባይና ሙያቸውም ይለያያልና በማንነታቸው መንገድ በጥበብ ምራቸው ። የእናት ርኅራኄ ፣ የአባት ቆራጥነት ለአንድ ልጅ ሁለት ክንፎች ናቸው ። የእናት ርኅራኄ ብቻ ፈሪ ፣ የአባት ጭካኔ ብቻ ልጅን ደረቅ ያደርጉታል ። አስተዳደግ ሚዛናዊ ካልሆነ ልጅ አንድ ክንፍ ያለው ይሆናል ።
ወዳጄ ሆይ
መልክህ ከቤተሰብህ የተለየ ከሆነ የውጭ ሰዎች ሁሉ የዚያ ቤት ልጅ አይደለም ብለው ያልፉሃል ። ወንድሞችህና እህቶችህም አንተን ለማናደድ የሚቀልዱበት ርእስ ይሆናል ። ባደግህበት ቤት የሚመጡ እንግዶች ወንድሞችህንና እህቶችህን ስመው አንተን ሲያልፉህ ለጋ አእምሮህ የውጭ ልጅ ነኝ ወይ ? ብሎ መቀበል ይጀምራል ። ወላጆችህ ሲቆጡህና ሲመቱህ ሌላ ወላጅ ያለህ ይመስልሃል ። ነገር ግን ልዩ በመሆንህ ደስ ይበልህ ። ዓለምን ውብ ያደረጋት ልዩ ልዩ ነገር መኖሩ ነው ። የብቸኝነት ስሜት ሰበብ ፈላጊ ነውና ማንጎራጎርም ሱስ ነውና ተጠንቀቀው ።

ወዳጄ ሆይ
“የሚተኛ ሰው ዓሣ አይዝም” ይላሉ ። በማለዳ መንቃትን ፣ ለሥራ መሠማራትን ለልጆችህ አስተምር ። ልጆችህ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ድርሻ ገና በልጅነታቸው አስለምዳቸው እንጂ አንተ አትሥራላቸው ። የሰውን ዕድሜ ጣፋጭ የሚያደርጉት ትጉ ሠራተኝነትና አንድ ጉድለት ነው ። ትጉ ሠራተኝነት ለዛሬ እንቅልፍን ይሰጣል ፣ ጉድለትም ደግሞ ለነገ ተስፋ ይሰጣል ። እናት ስትሆኚ ልጅሽን አቅፈሽ መያዝ ትፈልጊያለሽ ፣ አባት ስትሆን ደግሞ ልጅህን ሜዳ ላይ ለቅቀህ ማንበብ ትሻለህ ። ልጁም ከእናቱ አባቱን ይወዳል ፤ ምክንያቱም ነጻነት ይሰጠዋልና ። ስለዚህ ወላጅ ስትሆኑ ለልጆቻችሁ ነጻነት ስጡ ። አሊያ ይጠሉአችኋል ።
ወዳጄ ሆይ
ሰዎች የሚገኙልህ አንተ በተገኘህላቸው መጠን ነው ። ከነተረቱም “ለገቢህ ተንገብገብ” ይባላል ። ገቢህ ማለት አለሁ የሚልህ ፣ እሳት ውስጥ ስትገባ አብሮ ገብቶ የሚያወጣህ ማለት ነው ። በክፉ ቀን ወዳጅ እንድታገኝ አንተም ሰዎችን በክፉ ቀን አለሁ በላቸው ። ተማክረው ያረጉት ጥፋት የልማት ያህል ነው ። ያለ ምክር የተደረገ መልካም ነገር በምክር ከተደረገው ጥፋት በላይ ሰዎችን አልጥም ይላቸዋልና መመካከርን ውደድ ። ኑሮህን በተረት አትምራ ። የሌሎችን ተሞክሮ እቤትህ ላይ ልሞክረው አትበል ። ምክርን ሁሉ አትቀበል ። ያልሞከርከውን ለሰው አትስጥ ። ስለማታውቃቸው ሰዎች በጎም ክፉም አትናገር ። ዘመን የወለደውን በጉልበት ሳይሆን በጸሎት እንደምትጥል እወቅ ። የባለሥልጣን ወዳጅ መሆን ሲያምርህ የአንገትህን ከረባት ሰይፍ እንዳደረግህ ተረዳ ።
ወዳጄ ሆይ
ሲወለድ ትልቅ የሆነ የለም ። ከጅምሩ ስኬትን መፈለግ የሰነፎች ጠባይ ነው ። መታገል የማይሻ ተአምራትን ሲናፍቅ ይውላል ። አንዳንዴ አቋራጭ መንገድ ከዋናው ይርቃል ። በጊዜው የሚሆን መልካም ነገር ከጊዜው በፊት ከሆነ ክፉ ነገር ያመጣል ። ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ሳይሆን ወገንህን ትልቅ ቦታ ለማድረስ ጣር ። በሬሳ ላይ ደስ ብሎት የሚመገብ እንደ ሌለ በረሀብተኛ ሕዝብ ላይም የቅምጥል ኑሮ አትመኝ ። ትልቅ ስም ያለህ ሳይሆን ትልቅ ሥራ ያለህ ሁን ። መፍትሔ ከሌለው ጎምላላነት መፍትሔ ያለው ኮሳሳነት የተሻለ ነው ። ማኅበረሰቡን ለመርዳት ከፈለግህ ርቀህ አትቀመጥ ። የማታውቀውን ሕዝብ አትረዳውምና ። አይመጣም ብለህ ከሚመጣ ፣ ይመጣል ብለህ ቢቀር ይሻላል ። ጥንቃቄ የሌለው አገር ድንገት ይናዳል ። አገር ሲሞት ማልቀሻም ይጠፋል ። በደረጃ መውጣት ልምድና ዕድገት አለው ፤ ዋጋ ስለምትከፍልም ታከብረዋለህ ። በአንድ ጀንበር ትልቅ ቦታ መድረስን አትውደደው ።
ወዳጄ ሆይ
ሙከራ የጥራት እናት ነች ። መሳሳት ከፈራህ አትሞክር ። ካልሞከርህ ሕይወትህ አይለወጥም ። ካልተራመድህ አትደናቀፍም ፣ ቁጭ ካልህ ተበላሽተህ ትቀራለህ ። እየሠሩ መሳሳት የማልማት ያህል ነው ። ከማይሠሩ አራሚዎች የሚሠሩ ተሳሳቾች ይሻላሉ ። እንዲህ ቢደረግ ከማለት እንዲህ ማድረግ የትልቅነት መገለጫ ነው ።
ወዳጄ ሆይ
መውጣት መውረድ አለውና ሰው አትበድል ። የሚገድሉ ወንጀለኞችን ያህል የማይፈርዱ ዳኞችም ገዳዮች ናቸው ። መውረድ መውጣት አለውና ተስፋን አትጣል ። ዓለም ተረኛ እንጂ ቋሚ ወዳጅ የላትምና አቦ ፣ አቦ ስትባል እባክህን ፍራ ። የእኔ የምትለው ከሄደ ያንተ አልነበረም ። የእኔ ብለኸው ያልሄደው ጌታ ግን ያንተ ነው ። ብቻህን ብትዘራም የምታጭደው ብዙ ሁነህ ነው ። መከር ሠራተኛ ፣ ማግኘትም ድሆችን ይፈልጋል ።
ወዳጄ ሆይ
ሰይጣን ሰዎችን የሚያዋርደው እንዳይናገሩ ዲዳ በማድረግ ነው ። መፍትሔ የሚገኘው በመናገር ነውና ሁኔታዎች ሲከብዱህ ከወዳጆችህ ጋር ተማከር ። ችግርህን ለመስማት ወዳጆችህ ቢሸሹህ ካንተ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳሉ ተረዳ ። ድብቅነት ውስጥ ውስጡን የሚጨርስ እሳት ነው ። አዲስ ነገር በዓለም ላይ የለምና ለወዳጆችህና ለመንፈሳዊ አማካሪዎችህ መናገርን አትፍራ ።
ወዳጄ ሆይ
በውስጥህ ያለውን ፍቅር ካልገለጥህ ወዳጅህ አያውቀውም ። እውቀትህን ካላካፈልህ በጨለማ ያሉትን አታበራላቸውም ። ራእይህን ካልገለጥህ ተከታይም ተቃዋሚም አታገኝም ። ያልተጻፈ መጽሐፍ አይገመገምም ፣ ያልታወቀ አሳብም ጠላት የለውም ። በውስጥህ ያለውን ቅሬታ ካላወጣህ ሰዎች ይቅርታ አይጠይቁህም ። ፍላጎትህን ግልጽ ካላደረግህ ሰዎች ሳያውቁ ያስቀይሙሃል ።
ምክር /20
ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ