የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዋጋ አለኝ

“በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” 1ጴጥ. 1፡19 ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነበሩት ቶማስ ጃፈርሰን “ፕሬስ ከሌላት አገር” ወይም “አገር ከሌለው ፕሬስ” የቱን ትመርጣለህ ? ተብዬ ብጠየቅ ሳላመነታ የምመርጠው ነገር ቢኖር ሁለተኛውን ነው ካሉ በኋላ፡- “ፕሬስ ከሌለው አገር ፣ አገር የሌለው ፕሬስ ይሻላል” ብለዋል ። መንግሥት ያለ ፕሬስ ራሱን ማየት አይችልም ፣ ያለ ጋዜጠኞች ሊቆም አይችልም ማለት ነው ። ጋዜጠኝነት ሙያው ሲከበር ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ ነው ፣ ሙያው ሲቀል ደግሞ ነፍስን እየሸጡ መኖር ነው ።
ሰይጣንም ራሱን የሚያየው እንደ ጨለማው መንግሥት ነውና የራሱ ፕሬስ አለው ። የሰይጣን ፕሬስ ክፋት የሞላበት ወሬ ነው ። በዚህ ዓለም ስንኖር ከውስጣችን የምንሰማው ድምፅ አለ ። በዙሪያችንም የከበበን ወሬ አለ ። ሰይጣን ሰዎችን የሚዋጋባቸው ዋነኛ ነገሮች በውስጣችን ድምፅ በማሰማትና በዙሪያችን ወሬን በማራገብ ነው ። ሰይጣን ታላላቅ ውድመት የማድረግ ሥልጣን ቢሰጠው የሚያስቀረው ነገር ቢኖር ወረኞችን ነው ። ያለ ወረኞች ሰይጣን ግቡን መምታት አይችልም ። ሰይጣን በኢዮብ ላይ ብዙ ውድመት እንዳደረሰ መጽሐፍ ይነግረናል ። ብላቴናዎች ሁሉ ሲያልቁ አንዱ ግን ተረፈ ። ወደ ኢዮብም መጣ፡- እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።” ኢዮ. 1፡15 ። በዚህ የሰይጣን ጥፋት ለኢዮብ ወሬውን የሚያቀብል አንድ ሰው አልተነካም ። እሳት ከሰማይ ወድቃ በጎቹንና እረኞቹን ስትፈጅ አንዱ ወረኛ ግን አልተነካም ። ወደ ኢዮብ ዘንድ መጥቶ፡- እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።” የሚያስፈልጉት ብዙ አይደሉም ፣ አንድ ወረኛ በቂ ነው ። ከእሳቱ በላይ ጻድቁን በወሬ እፈታዋለሁ ብሎ ሰይጣን አሰበ ። በግመሎች ላይ አደጋ ሲደርስም አንዱ ወሬ ነጋሪ ተረፈ ። ወደ ኢዮብም መጥቶ፡- እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።” ኢዮብ. 1፡17 ። ሰይጣን ዋነኛ አሳቡ የኢዮብን ንብረት ማፍረስ ሳይሆን እምነቱን መናድ ነው ። እምነትን ከሚጎዱ ነገሮች አንዱ ወሬ ነው ። የኢዮብ ልጆች በዐውሎ ነፋስ በተገደሉ ጊዜ አሁንም አንድ ወሬኛ ተረፈ ። እርሱም ለኢዮብ፡- እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።” ኢዮብ . 1፡19 ። ኢዮብ ግን ያሸነፈው ወሬውን ባለማዳነቅ ነው ። ኢዮብ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ዘመን አልነበሩትም ነበር ። ከሀብትም ፣ ከአሽከርም ፣ ከልጆችም በፊት ግን እግዚአብሔር ነበረ ። ከቀን በኋላ በመጣ ነገር አምላኬን አላማርርም አለ ። ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ ፥ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን ።” ኢዮብ . 1፡21 ።
ሰይጣን አማረልኝ ብሎ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ነበር ። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት” ኢዮብ . 1፡7 ። ሰይጣን ዘዋሪ ነው ። ሥራ ፈትና ምድርን ሁሉ ሲዞር የሚውል ነው ። ዘዋሪ ደግሞ ወረኛ ነው ። ስለዚህ ሰይጣን በየትኛውም ዘመን እንዳይጠፋ የሚንከባከበው አረም ቢኖር ወሬ ነው ። ወሬ ድንጋጤ ያመጣል ፣ የሰውን ተስፋ ይመታል ፣ ጅምሮች እንዳይቀጥሉ ያደርጋል ። የተሰለፈን ጦር ይበትናል ፣ ንጹሕ ልብን ያቆሽሻል ፣ የፍቅር እይታን ይለውጣል ፣ ኅብረትን ያፈርሳል ። ወሬ የሰይጣን ትልቅ መሳሪያ ነው ። ወሬን የምናሸንፈው በእግዚአብሔር ቃል ነው ። ወሬ እንደ ሰይጣን ሥራ ፈትና ዘዋሪ ያደርጋል ። ወሬ ሰላምን ያውካል ።
በውስጣችን ከምንሰማቸው ድምፆች ፣ ሰይጣን በወሬኞች ከሚያሰማን አሉታዊ ንግግሮች አንዱ ዋጋ የለህም የሚል ነው ። ዋጋ የለህም የሚል ድምፅ በደረቁም ይመጣል ፣ ተቀባብቶም ይመጣል ። ሰው የመኖር አምሮቱ የሚጨምረው ለራሱ ዋጋ እንዳለው መንገር ሲችል ብቻ ነው ። ሰዎች ወደቀ ሲባል ተሰበረ ብለው ማውራታቸው ፣ በግነት ሰይጣንን ማገልገላቸው ፣ ክፉውን ነገር መደጋገማቸው እርግጥ ነው ። ይህንን ድምፅ ግን ልናስተውለው ይገባል ። ወሬ የሰይጣን ትልቅ የፕሬስ ድርጅት ነው ። ብዙ ሰዎች ሳያውቁት በዚህ ድርጅት ውስጥ ያለ ደመወዝ ይሠራሉ ። ሰይጣን ያለው ሀብት ገሀነመ እሳት በመሆኑ ያንን እንዳያካፍላቸው መፍራት ይገባቸዋል ።
ዋጋ የለህም ለሚለው ድምፅና ወሬ ሐዋርያው ጴጥሮስ መልስ ይሰጣል ። “በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ይላል ። ዋጋ የለህም የሚለውን ድምፅ የሚያመጣው አለማወቅ ነው ። ስናውቅ ግን በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተገዛን እንረዳለን ። መዋጀት ማለት በዋጋ መግዛት ማለት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ የመግዣ ገንዘቦች እንዳሉ ሐዋርያው ጠቅሷል ። እነዚህም በዋናነት ሦስት ናቸው ፡-
1-  ብርና ወርቅ
2-  እንስሳት
3-  ደም
የብርና የወርቅ ክፍያ ለሚገዛው ነገር የሚመጥነውን በመክፈል መውሰድ ነው። የእንስሳት ክፍያ ለካሣ አንዳንድ ጊዜ በልዋጭ የሚገበያዩበት ነው ። የደም ክፍያ ግን ለአገር ለወገን የሚከፈል የታላቅ ፍቅር መግለጫ ነው ። በደም ዋጋ የተገኘ ነገርም በቀላሉ የሚሰጥ አይደለም ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛን በብርና በወርቅ አይደለም ። በወርቀ ደሙ ገዝቶናል ። በእንስሳት መሥዋዕትነት ሳይሆን ውድ ነፍሱን በመስጠቱ አድኖናል ። ስለዚህም ተገዝተናል ። የተገዛ ነገር፡-
1-  ባለቤት አለው ። የሚቆረቆርለት ፣ የሚዋጋለት ባለቤት ያለው ነገር ቢኖር የተገዛ ብቻ ነው ። እኛም በክቡር የክርስቶስ ደም የተገዛን ነንና ባለቤት አለን ። ባለቤታችንም ክርስቶስ ነው ። እርሱ ስለ እኛ ይቆረቆራል ፣ እርሱ ስለ እኛ ይዋጋል ።
 
2-  ዋጋ አለው ። የተገዛ ነገር ዋጋ አለው ። ዋጋ የከፈለለት ወገንም አለው ። የተገዛው ነገር የራሱንም ዋጋ አያውቅም ፣ የገዛው ብቻ ያውቃል ። ገዢው ብዙ ድካሙን አፍስሶ ይገዛዋል ። ክርስቶስም ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ መስቀል ተሸክሞ በደሙ ገዝቶናል ። ዋጋችንም እግዚአብሔር ነው ። ዋጋ የለኝም ማለት ክርስቶስ የለኝም ማለት ነው ።
3-   አፍቃሪ አለው ። ነጋዴው ከቤቱ ሲወጣ ያ ዕቃ ዛሬ ከእጄ በወጣልኝ በማለት ነው ። ገዥው ደግሞ በእጄ ባስገባልኝ በማለት ነው ። ነጋዴው መገላገል ሲፈልግ ገዥው ደግሞ ይዞ መግባት ይፈልጋል ። ያልወደደውን የሚገዛ የለም ። የገዛን ጌታም ይወደናል ።
4-   ጥበቃ አለው ። የተገዛ ነገር ገዥው ነፍሱን ከፍሎ ይጠብቀዋል ። ሌባ ቢመጣ ተናንቆ ያስጥለዋል ። ተገዝተናልና እኛም አምላካዊ ጥበቃ አለን ።
5-   ማስቀመጫ አለው ። የተገዛ ነገር የሚቀመጥበት ስፍራ አለው ። እኛም ተገዝተናልና ቤተ ክርስቲያን መኖሪያችን ናት ።
6-   ለገዛው ይኖራል ። የተገዛ ነገር ከመገዛቱ በፊት ተቀባብቶ የተቀመጠ ነበር ። ከተገዛ በኋላ ግን ያገለግላል ። ሲቆሽሽ ይታጠባል ። ቀባብቶ ቢያስቀምጠው ነጋዴው እንዲሄድለት ይፈልጋል ። ቢቆሽሽና ቢያገለግልም ገዥው ግን ይወደዋል ። ብንደክም ፣ ብንዝልም የሚወደን አለ ።
7-   የተገዛው ለአገልግሎት ነው ። እኛም በክርስቶስ ሞት የዳነው ወይም የተዋጀነው ለማገልገል ነው ። እርሱ ሲገዛን ካልሳሳ ፣ ለማገልገልም መሳሳት የለብንም ። 
ጌታችን የገዛው ሙት የሆነውን ይህንን ማንነት ነው ። ወደ ሞት እየሄዱ ላሉ ሰዎች ደም መስጠት ሕይወት መስጠት ነው ። ክርስቶስም ደሙን አፍስሶ ሕይወትን ሰጥቶናል ። እኛ ገዥ ብንሆን ኑሮ ይህን ማንነት አንገዛውም ነበር ። መቃብርን ልደት ማድረግ የሚችል ጌታ ግን ገዝቶታል ። አዎ ዋጋ የለኝም አትበሉ ፣ ዋጋችሁ ትልቅ ነው ። እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።
ጌታ ሆይ ያልከው ላይቀር መጨነቄ ከቶ ለምንድነው ? ድካሜና ሩጫዬ ዕረፍት አልሰጠኝም ። ዕረፍት የሰጠኝን ቃልህን ማክበር ይሁንልኝ ። ዋጋ ቢስነት እንዳይሰማኝ ልቤን በዋጋዬ ልክ ሙሉ አድርግልኝ ። ሁልጊዜ በጸናው ማንነት አንተን ማስከበር ይሁንልኝ ። በአማኑኤል ስምህ ፣ በፈሰሰው ደምህ ፣ በእንተ ማርያም እምህ አሜን ።
የዕለቱ መና 14
ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ