የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 1

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።

ሱናሚ ከባሕር ወለል ላይ በእሳተ ገሞራ ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰት ፣ በከፍተኛ ፍጥነትና ከፍታ የሚበርር የማዕበል ፣ ማዕበል ነው ። አደጋውን ስናየው በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ከተሞችንና መዝናኛ ቦታዎችን ወዳለመኖር የሚለውጥ ፣ የባሕሩን እንስሳ መሬት ላይ የሚተፋ ፣ የመሬቱን ንብረት ወደ ባሕር የሚከት ድንገተኛ መቅሰፍት ነው ። ይህ ውስጣዊ ማዕበል ፣ የማዕበል ማዕበል የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል ። የሚያደርሰውን ጉዳት በሚዛን ማስቀመጥ አይቻልም ። እሳተ ገሞራና የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያመጣው ይችላል ። እንደ ሱናሚ ያለ ውስጣዊ ማዕበል በሰው ውስጥ ይፈጠራል ። ይህ ማዕበልም ከተቀበረ ቍጣ የሚወጣ ፣ ለህልውና ምክንያት በማጣት የሚከሰት ነው ። ራስን አናውጦ በዙሪያ ያሉትን ሰዎችና ንብረትን የሚያወድም ሊሆን ይችላል ። ለውስጣዊ ማዕበል መነሻ የሚሆነው ውስጣዊ ቍጣ ምንድነው ? ስንል ለዘመናት በውስጣችን ሲብላላ የኖረ ፣ ነገር ግን ያልተፈወሰ ሕመም ነው ። ህልውናን መጠራጠር ፣ የሚኖሩበትን ምክንያት ማጣት ለዚህ ማዕበል መፈጠር ምክንያት ይሆናል ።

ውስጣዊ ቍጣ ከላያቸው የተረጋጉ በሚመስሉ ሰዎች ልብ ውስጥ ሲብላላ የሚኖር ነው ። እነዚህ ሰዎች ይህን እሳት ተሸክመው ከላያቸው ግን የውኃ ባሕርይ ተላብሰው ይኖራሉ ። ይህን በእሳት ላይ ያለ ቀዝቃዛ ባሕርይ ሊያመጡ የቻሉት በተለያየ ምክንያት ነው ። የመጀመሪያው ከልጅነት ጀምሮ እርሱ ወይም እርስዋ “ጨዋ ፣ ትዕግሥተኛ ፣ መልስ የማይሰጡ ፣ የእግዜር በግ” እየተባሉ ስላደጉ ከዚህ ውዳሴ ከንቱ ባሻገር ፈውሳቸውን ሊፈልጉ አልቻሉም ። ሁለተኛው ምክንያት ያሉበት ኃላፊነት ራስን ደብቆ መኖርን የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል ። በዚህ መንፈሳዊ እውቀትና ኃላፊነት ላይ እንዴት ይቆጣሉ ? እንዳይባሉ ውስጣቸውን አምቀው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ። ሦስተኛው ምክንያት የውስጥ እንፋሎታቸውን ቢያወጡ አንታመንም ብለው ማሰባቸው ነው ። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ ስለተባሉ ፣ ስለሚያገለግሉ ፣ ብዙዎችን ስለሚያጽናኑ ጉዳታቸው አመኔታ የሚያገኝ አይመስልም ። “እገሌ ተጨነቀ ቢባል ማን ያምናል ?” እያሉ ሰዎችም ያዳምቁላቸዋል ። ውስጣዊ ኩርፊያቸውን በቀልድ ሸፍነው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ። በዚህ ምክንያት ለውስጣዊ ማዕበል ይዳረጋሉ ። አራተኛው ምክንያት በልጅነታቸው እናታቸውን ወይም አባታቸውን አጥተው ምነው ባገኘኋቸው በሚል ስሜት የወላጆቻቸውን ሥዕል በመሳል የደከማቸው ስለሆኑ ውስጣዊ ቍጣ ይፈጠርባቸዋል ።

ውስጣዊ ቍጣ ያለባቸው ሰዎች የዕለት ታማሚዎች አይደሉም ። ዛሬ በድንገት ቢለወጡብን ምክንያቱ እኛ ሳንሆን የኖረውና የተዳፈነው እሳት ሊሆን ይችላል ። ይህ ውስጣዊ ቍጣ ሲፈነዳ ሁለት ዓይነት አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ ። የመጀመሪያው፡- ራስን መጉዳት ነው ። ራስን መጉዳት በኃጢአት ፣ በተለያዩ ልምምዶች ሊሆን ይችላል ። የተከለከሉ ነገሮችን ማነው ተዉ የሚለኝ ? በሚል ስሜት ያደርጋሉ ። እንደ እነርሱ የተጎዱ ሰዎችን ጓደኛ ማድረግ ይሻሉ ። ቍጣው ኃይለኛ በመሆኑ ሁሉንም ነገር ለማድረግ ወደ ኋላ አይሉም ። ለጥፋታቸውም የተለያዩ ሰዎችን ተጠያቂ ስለሚያደርጉ የጸጸት ስሜት የላቸውም ። ትክክል አይደላችሁም የሚላቸው መርህ ቢመጣ እንኳ ሕይወት ከትክክልና ከስህተት ያለፈ ምሥጢር አላት ብለው ያምናሉ ። ሁለተኛው፡- ውስጣዊ ቍጣ ማዕበል ሲፈጥር ሰዎችን መጉዳት ሊከሰት ይችላል ። ክስተቱም ሁን ብሎ ሰዎችን ማጥቃት ፣ ስለ ሰዎች ክፉ ክፉ ብቻ ማሰብ ፣ ማንም ሰው የሚቀርበኝ ሊጎዳኝ ነው ብሎ መጠንቀቅ ፣ የሌላውን ስምና ክብር ማጉደፍ ነው ። አለፍ ሲሉም የትዳር ጓደኛና ልጆች ላይ አደጋ ሊያመጡ ይችላሉ ። ሳይታከም የኖረው ያ ቍጣ ለንብረት ግዴለሽ ፣ ለወጪም የማይሳሳ ሰው አድርጎ ያንን ሰው ብኩን ያደርገዋል ።

አንዳንዳችም ይህን ቍጣ በመንፈሳዊ ቅድስና ስም ሊሸፍኑት ይሞክራሉ ። ቍጣቸውንም ቅዱስ ቍጣ ሊያሰኙት ይፈልጋሉ ። ሰዎችን ለማንቀጥቀጥ በተጠንቀቅ የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ። ከሰላማቸው ጋር ሳይገናኙ መኖር ለራሳቸውም ለቀረቡአቸውም ስቃይ ነውና ።

እኛስ ውስጣዊ ቍጣ ይኖርብን ይሆን ?

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 24 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ