የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 2

ውስጣዊ ቍጣ የተለያዩ መነሻዎች አሉት ።

1- ያለመፈለግ ስሜት

ስልካቸው ቀኑን በሙሉ ባለ መጥራቱ “የሚፈልገኝ የለም” በሚል ስሜት ውስጣዊ ቍጣ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ብዙዎች ናቸው ። በዚህች ምክንያት ብቻ አእምሮአቸው የተቃወሰ ፣ ለምን እኖራለሁ ? ብለው ሕይወታቸውን የጠሉ ሰዎች ብዙ ናቸው ። እጮኛቸው ጋር ሊቀጥሉ ባለ መቻላቸው ያለ መፈለግ ስሜት ውስጥ የገቡ ፣ ለእኔ ያልሆነ ለማንም አይሁን ብለው አደጋ የሚያደርሱ አያሌ ናቸው ። እጮኝነት መጠናናት በመሆኑ ሊቀጥልም ሊቆምም የሚችል ነጻ ቀጠና ነው ። ሰዎች መቀጠል አልችልም የሚሉት እኛ ተፈጥሮአዊና ሞራላዊ ጉድለት ስላለብን ብቻ ሳይሆን የእኛን ፍቅር ፣ ፍቅር አልባው ልባቸው መሸከም ስላቃተው ሊሆን ይችላል ። ያለ መፈለግ ስሜት ውስጥ የገቡ ሰዎች ዛሬ ተዋውቀውት ነገ ካልደወለላቸው በዚያ ሰው ላይ ቍጠኛ ይሆናሉ ። ያለ መፈለግ ስሜት ለአገር ለወገን ደክመው ሲረሱ ፣ ከደከሙበት መንግሥት ጡረታ ሲነፈጉ የሚመጣ ነው ። ዕድሜ ዝቅም ከፍም ሲል ይህ ስሜት ይኖራል ። ወጣቶች ሌላው ላይ መኩራት ደስ ሲላቸው ሲኮሩባቸው ግን ይረበሻሉ ። ሽማግሌዎችም የገዛ አካላቸው እንኳ እየከዳቸው ነውና ሁሉ እንደ ረሳቸው ሊሰማቸው ይችላል ።

ወላጆች የልጆቻቸውን ድምፅ ሲያጡ ፣ ቀድሞ የሞቀው ቤት አሁን የሰው ረሀብ ሲገባበት ያለ መፈለግ ስሜት ይሰማቸዋል ። ያለ መፈለግ ስሜት ቍጣንና የእልህ ተግባርን እንዲፈጽሙ ያደርጋል ። ልጆቼ አይፈልጉኝም ብሎ አንድ አባት ትልቅ ቦታና ንብረቱን ሸጦ ለቤት ሠራተኛና በቅርብ ለረዱት ሰጥቶ ፣ ለራሱ መናኛ ቦታ ላይ ወድቆ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሲሞት አውቃለሁ ። ውስጣዊ ቍጣ የእልህ ተግባር ያስፈጽማል ። ሰው የሚያጠፋው እንደ አቅሙ ነውና የአገር መሪዎችም ሁሉም ጠላት የሆነባቸው ሲመስላቸው ውስጠዊ ቍጣ ላይ ይወድቃሉ ። በአገራችንና በቤተ ክርስቲያን የእልህ ተግባራት ያመጡት ዕዳ ትውልድ የሚከፍለው ሁኗል ። አገራችን የዓለም ባንክ ዕዳ ብቻ ሳይሆን የቀደሙት ትተውት የሄዱት የእልህ ዕዳም አለባት ።

2- ወላጅ አባትን ማጣት

ብዙ ወላጅ አባቶች ለልጆቻቸው ክፉ አይደሉም ። አባቶች ግን ክፉ ተደርገው እንዲሳሉ ይደረጋል ። ገንዘባቸው እየጣፈጠ አባትነታቸው ይጠላል ። ልጆችም በልጅነት አእምሮ አባትን እንደ ክፉ ማየት እያዳበሩት ያድጋሉ ። አባቶች ስለመቆጣታቸው እንጂ ለምን እንደ ተቆጡ ልጆች እንደ ገና መመርመር ያስፈልጋቸዋል ። የሚሰሙ ጩኸቶች የማይሰሙ ቁንጥጫዎች ውጤት ናቸው ። ሁሉ አባት ደግ ላይሆን ይችላል ፣ ሁሉ አባትም ክፉ አይደለም ። በቤታቸው ሰላም ሲያጡ ጠጪ የሚሆኑ ፣ የማልመጥ ሥራ ሲሠራባቸው ቤቴንም ልጆቼንም ከስሬአለሁ ብለው አጉል ተግባር የሚፈጽሙ አባቶች አሉ ። የተናገረ ሁሉ ትክክል ፣ ዝም ያለ ሁሉ ጥፋተኛ አይደለምና ሊጠና ይገባዋል ። እግዚአብሔር ልጆች በአባትና በእናት እኩል እንክብካቤ እንዲያድጉ ፈቅዷል ። ምክንያቱም ከአባት ጥንካሬን ፣ ከእናት ፍቅርን ስለሚያገኙ ነው ። ይህን ሚዛናዊና የመንፈስ ምግብ የሚያገኙት አባትና እናት በሰላም ሲኖሩ ነው ። አባት እንዲኖርም አገር ሰላም መሆን አለባት ። ብዙ አባቶች የሚሞቱት በጦርነት ነውና ።

እናት ምንም ጎበዝ ብትሆን የአባትን ቦታ መተካት አትችልም ። ልተካ ብትልም በቶሎ ትደክማለችና ልጆችዋ ለመርዳት ሲፈልጓት አትገኝም ። አባታቸውን የማያውቁ ፣ አባታቸውን በሞት የተነጠቁ ፣ አባታቸው የማይፈልጋቸው ልጆች የሰው አባት ባዩ ቍጥር ይቀናሉ ። አባታቸውን ቢያገኙ አሁን ካለው የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ ያስባሉ ። በዚህ ምክንያት የዝምታ ፍለጋው ፣ የልብ ሩጫው ሲያደክማቸው ውስጣዊ ቍጣ ውስጥ ይገባሉ ። ብስጩዎች ፣ ለእናታቸውና ለአሳዳጊዎች የማይመቹ ፣ የበቀለኝነት ስሜት የሚያዳብሩ ፣ ሰውን ሁሉ የሚጠራጠሩ ሁነው ያድጋሉ ። እግዚአብሔር አባትን ውስዶ እናትን ካስቀረ ጨርሶ አልከፋምና ተመስገን ማለት ይገባል ። አባትም እናትም ሞተው አሳዳጊ ከሰጠም ማመስገንና አሳዳጊዎችን ማክበር ያስፈልጋል ። ትልቁ ቁም ነገር መውለድ ሳይሆን ማሳደግ ነውና ። ደግሞም ይህ ሁሉ ባይኖር እግዚአብሔር አባትነቱ ከአባትም በላይ ነውና በእርሱ መደሰት ይገባል ። አለኝ ለማለት እንጂ የሚሞቱ አባትና እናትን የሰጠ ፣ የማይሞተው አባት እናት እግዚአብሔር ነው ። አባትን ማጣት ውስጣዊ ቍጣ ፣ ውጫዊ ግጭት ይፈጥራል ። የሁሉም ነገር መልስ ያለው ግን ሥላሴ ጋ መሆኑን ማሰብ ያስደስታል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ