የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 3

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።

3- እናትን ማጣት

ውስጣዊ ቍጣ ወይም መራርነት ያላቸው ሰዎች አንዱ ምክንያታቸው እናትን ማጣት ሊሆን ይችላል ። አንድ ልጅ እናቱን በዚህ ዓለም ባያውቃት እንኳ በማኅፀን ዓለም ግን ያውቃታል ። አባት ቅጽበታዊ ሊሆን ይችላል ። እናትን ግን የዘጠኝ ወር ቤት ናት ። እናት ለልጅዋ ራስዋን ስለምትሰጥ የልጁን ክፍተት ለመሙላት ትሞክራለች ። አባት የሌለውን ልጅ እናት በፍቅርዋ የተወሰነ ታግዘዋለች ። አባት ግን እናትን የሚያስረሳ እንክብካቤ ለማድረግ ይቸገር ይሆናል ። ልጆቻቸውን በመሥዋዕትነት ያለ እናት ያሳደጉ ፣ ብዙ መልካም አባቶች እንዳሉ እናውቃለን ። ለእነዚህ አባቶች ክብር መስጠት ያሻል ። እናት ባልዋ ሲሞት ልጆችዋን ስለማሳደግ እንጂ ስለማግባት ላታስብ ትችላለች ። አባት ግን በአብዛኛው ሁለተኛ ትዳር ይመሠርታል ። በዚህ ጊዜ ፍቅሩ ወደ ሁለተኛይቱ ሚስት ይሆንና ልጆቹን ችላ ሊል ፣ በሚደርሰውም ወሬ ሊቀየምና ሊገፋቸው ይሞክራል ። እናት የሌለው ልጅ ይህን ክፍተቱን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ካልሞላለት ሆደ ባሻ ፣ ቶሎ የሚከፋው ፣ ልበ ሰባራ ፣ ለማልቀስ ቅርብ የሆነ ፣ እናቱን በመናፈቅ የተጎዳ ፣ አባቱን የሚቀየም ፣ እንጀራ እናቱን እንደ ጠላት የሚያይ ይሆናል ። በዚህ ምክንያት ውስጣዊ ቍጣ በልቡ ይፈጠራል ። ይህ ቍጣም አባቱን ብቻ ሳይሆን በአባቱ ዙሪያ ያሉትን እንዲቀየም ያደርገዋል ።

ሁለተኛ ትዳር መመሥርት ግድ በሚሆንበት ጊዜ አባቶች ማሰብ ያለባቸው ነገር አለ ። የልጆቻቸው የሆዳቸው ብቻ ሳይሆን የስሜታቸውም አሳቢ መሆን ያስፈልጋቸዋል ። የሚስትን ፍቅር ከልጅ ፍቅር ጋር ማምታታት ፣ ወሬ እየተቀበሉ ልጆችን መቅጣት አስፈላጊ አይደለም ። ብዙ መልካም የሆኑ ፣ ያልወለዱአቸውን ልጆች እንደ ራሳቸው አድርገው የሚያሳድጉ ቢኖሩም አባትና ልጅን መለየት ደስ የሚላቸው የእንጀራ እናቶችም ይኖራሉ ። ሁለተኛ ትዳር የመሠረተው አባት ልጆቹ እንዴት እየኖሩ መሆኑን በየዕለቱ መፈተሸ ይገባዋል ። ከጆሮው ይልቅ ዓይኑን ማመን አለበት ። ከሁለተኛ ትዳሩ የሚወለዱ ልጆችም በመካከላቸው ልዩነት እንዳይከሰት ፣ በቤት ውስጥ እስማኤልና ይስሐቅ እንዳይሆኑ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ። እገሌ የአባቴ ልጅ ፣ እገሌ የእናቴ ልጅ የሚለው ቋንቋ ደስ የማይልና በትውልድ መካከል ጠብ የሚዘራ ነው ። ሁለተኛ ትዳር ለመመሥረት ያሰበው አባት ሚስቱን በሞት ካላጣ በቀር ይቅር ቢባባልና የልጆቹን ክፍተትና ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ቢያሟላ መልካም ነው ። ሁለተኛ ትዳር በልጆችና በሚስት መካከል ፣ በሰንጣቃ ዓለት ውስጥ መኖር ነው ። ለደስታ የታሰበው ለሐሳር እንዳይሆን ደግሞ ማሰብ መልካም ነው ።

አንጀቴና ሆዴ ሁለት ተጣልተው ፣
አንተም ተው ፣ አንተም ብዬ እንዳልለው ፤
አንጀቴም አንጀቴ ፣ ሆዴም ሆዴ ነው ።

እናትን ማጣት በተለያየ መንገድ ይከሰታል ። በልጅነት የሚወልዱ እናቶች ኃላፊነት ላይሰማቸው ይችላል ። ልጃቸውን አያቱ ጋ ጥለው ሊጠፉ ፣ ሰው አገር ሊሰደዱ ይችላሉ ። ልጁም የተሻለ ነገር አግኝቶ ቢያድግም ያጣው ነገር ያለ ይመስለዋል ። የሰው ተፈጥሮ ደስታውን ከሌለው ነገር ውስጥ መፈለግ ነው ። ደስታ ግን ያለው ካለን ነገር ውስጥ ነው ። ባለጠጋ ሰው ያገቡና ልጃቸው የሀብታቸው እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ወልደው የሚረሱ እናቶች አሉ ። ወንድ ሲክድ እንጂ ሴት ስትክድ አይተን አናውቅ ይሆናል ። እኛ በአገልግሎት ብዙ እናቶችን እናያለን ፣ ለልጆቻቸው እንዲራሩ ብዙ እናቶችን ለምነን እናውቃለን ። አዎ እናት ልጅዋን መርሳትዋ አጠራጣሪ ነገር ይመስላል ። ይህ እንኳ ቢገጥም መፍትሔ አለና እናቱን ያጣው ልጅ እግዚአብሔር እናት መሆኑን ማወቅ አለበት ። ቃሉም፡- “ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።” ይላል ። ኢሳ. 49፡14-15 ። እናትን የሰጠ እውነተኛው እናት እግዚአብሔር ነው ። በዚህ ዓለም ያለው ታላቅ ዝምድና ፣ የእናትና የልጅ ግንኙነትም በሞት ይቀራል ። ሞትን የሚሻገር ፍቅር የአማኑኤል ፍቅር ብቻ ነው ።

እናትን በማጣት ውስጣዊ ቍጣ ውስጥ ያሉ ልጆች ፣ ልባቸውን ማስፋት ፣ አባታቸው ያለበትን አስጨናቂ ኑሮ ማሰብ ፣ ይቅርታ ማድረግና በፈረሰው ቅጥር በኩል ወደሚቆመው እግዚአብሔር መቅረብ ይገባቸዋል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ