የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 4

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።

4- ብቻዬን ነኝ ብሎ ማሰብ

ሯጭ የሚመለከተውና የሚደግፈው ባይኖር ሊሮጥ አይችልም ። ሴትም የሚበላና የሚያደንቅ ባይኖር ለራስዋ ምግብ ለመሥራት ብዙም አትበረታታም ። እንግዳ ፣ መብላት ባንፈልግም እንድንበላ ያደርገናል ። የሚጠብቁን ሰዎች መኖራቸውም ጠንክረን እንድንሮጥ ያደርጉናል ። ሁሉ የእኔ ይሁን የሚል ስሜታችን ሰው ሁሉ እያለ እንጂ ሰው ሁሉ አልቆ አይደለም ። ሰው ሁሉ እንዲኖር እንፈልጋለን ፣ ሁሉ የእኛ እንዲሆንም እንፈልጋለን ። እነዚህ ሁለት አሳቦች ይቃረናሉ ። የተወዛገበ ኑሮ የምንኖረውም ምዕራብና ምሥራቅን ለማጨባበጥ በመፈለጋችን ነው ። ስለዚህ ሰው ሁሉ ይኑር ሁሉም ነገር የእኛ አይሁን ማለት አለብን ። ሁሉ የእኛ ከሆነ ሌላው ምን ይሁን  ብለን መጠየቅ አለብን ። ምንም ድርሻ ሳይኖረው ሊያልፍ ነው ። ሁሉ የእኛ ከሆነ ምንም ነገር የእኛ አይሆንም ። የሰው ልጅ ውድቀት ያለው ሁሉን በእጁ ጨብጦ ፣ በእግሩ ረግጦ መያዝ ሲፈልግ ነው ። የብቻነት ስሜት ውስጠዊ ቍጣን ይፈጥራል ። ብዙ ባሎች የሚስታቸውን መንፈሳዊነትና ዓለምን መናቅ የሚቃወሙት ብቻዬን ነኝ ፣ ለምሠራው ሥራ አድናቂና ደጋፊ የለኝም ብለው ሲያስቡ ነው ። በዚህ ምክንያት ምክራቸውን ከደጅ ያደርጋሉ ። በማያቋርጥ ሩጫም ዕድሜአቸውን ያሳጥራሉ ።

ብቻዬን ነኝ የሚል ስሜት በኃላፊነት ላይ ያሉትን በጣም የሚጎዳ ስሜት ነው ። ሲያጠፉም ሲያለሙም ዝም የሚባሉ መሪዎች መጨነቃቸው አይቀርም ። ሕዝብ ዝም ሲል የመቆንጠጫ ርእስና ዱላ የሚያዘጋጁትም ጩኸት ለመስማትና ለመረጋጋት ነው ። በአገዛዝ ዓለም ጸጥ ሲል መልካም አይደለም ይባላል ። ዝምታ ከጩኸት በላይ ያስፈራል ። የሚያስጮኹ ተከፋዮች በዚህ ዘመን የሞሉት ለዚህ ነው ። የማይነኩና የማያስፈልጉ ርእሶችን እየቀሰቀሱ ሕዝብን ማስጮኽ አንዱ የአገዛዝ ስልት ነው ። አላስተኛ ላሉ ቆንጣጮችም ደመወዝ ይታሰባል ። በኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ብቻዬን ነን የሚሉበት ጊዜ ብዙ ነው ። ሲሠሩ ዝም ያላቸው ሲያጠፉ ሲጮህባቸው ውስጣዊ ብስጭት ውስጥ ይገባሉ ።

በመንፈሳዊው አገልግሎት ብቻቸውን የሚሮጡ ሰዎች ካየን አንድም ራስ ወዳዶች አሊያም ሞክረው በሰዎች ተስፋ የቆረጡ ናቸው ። ክፉ ሰዎችን ስናይ ማን ክፉ አደረጋቸው ? ብሎ ማሰብም ከብዙ ፍርድ ይጠብቃል ። በርግጥ ምክንያት ቅዱስ አያደርግም ። ሰዎቹን ለመርዳት ግን መነሻን ማወቅ ይረዳል ። ሰዎች ለሥጋዊ ኑሮአቸው የሚሮጡትን ያህል ለመንፈሳዊ ነገር ቸልተኛ ናቸው ። ምእመናን የእግዚአብሔር ሥራ የእነርሱ ሕይወት የሚሠራበት መሆኑን ሲዘነጉ አገልጋዮች ማዘንና መቆጣት ይጀምራሉ ።

ብዙ ቸልተኛ ወንዶች ቤታቸውን በጨለማ ተለይተውት በጨለማ ይገቡበታል ። ሳይነጋ ይወጣሉ ፣ ከመሸ ይገባሉ ። የልጆቻው መልክ እስኪጠፋቸው በቤት ውስጥ የጠፉ አባቶች ይሆናሉ ። አንዳንድ ወርቅ ቤት ውስጥ ጠፍቷል ፣ ከቤት እንዳልወጣም እርግጠኛ ነን ። ግን ያደክማል ። ወንዶች እንዲህ የሚሆኑበት ጊዜ አለ ። ሚስቲቱ በባልዋ መረሳትዋን ተቀብላ ልጆች ግን አባት አልባ መሆናቸውን መቀበል ይከብዳታል ። በዚህ ጊዜ ወንድም ሴትም መሆኑ ሲታክታት መቆጣት ትጀምራለች ። ድሮም ቢሆን ብቻዬን ነኝ ፣ ወደፊትም ብፋታ ብቻነቱ አይከብደኝም ብላ ለራስዋ ትነግረዋለች ። ትዳር ግን ሲፈታ ብዙ ጣጣዎች አሉት ። በአጭሩ ለፍቺ ያበረታቷት ፍቺው ከተፈጸመ ከደቂቃ በኋላ ገሸሽ ይሏታል ።

የብቻነት ስሜት የብዙ ሰው ውስጣዊ ሕመም ነው ። ህልውናውን ጣዕም እያሳጣበት ይመጣል ። ሥራችንን ግን ቅዱሳን መላእክት እንደሚመለከቱት አስበን እናቃለን ወይ? ሰማይ ውሎአችንን ያየዋል ። ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፈለዋል ። መንገድ ለሚያጸዳውም እንደ ሥራው ሰማይ ይከፍለዋል ። በእግዚአብሔር ፊት ትንሽ የሚባል ድርሻ የለም ። የከዋክብት መኖር የሚታወቀው በጨለማ ውስጥ ነው ። ማንም የሚደግፈን በሌለ ሰዓትና ብቻዬን ነኝ በምንልበት ጊዜ ብዙ መሥራት አለብን ። ብቻነት ብቸኝነት አይደለም ። አዳም ብቻውን ነበረ ፣ ብቸኛ ግን አልነበረም ። እግዚአብሔር ያለው ብቸኛ አይደለምና ። ዮሐንስ መጥምቅ በምድረ በዳ ብቻውን ነበረ ፣ ሥራውን ግን በትክክል ሠርቷል ። ፍጹም ድሀ ሁኖ ባለጠጎችን አስጨንቋል ። ያለ ጦር መሣሪያ ንጉሥን አሸብሯል ።

ሥራችሁን ሥሩ ! ደመወዙ ወይ በምድር አሊያም በሰማይ ይከፈላል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ