“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።
6- ፈልጎ ማጣት
ይህን ዓለም ስንመለከተው ሳይፈልጉ ብዙ የሆነላቸው ሰዎች እንዳሉበት ሁሉ ፈልገው አንድን ነገር ማግኘት ያልቻሉ ብዙዎች ናቸው ። ሳይፈልጉት ሁሉም ነገር የሆነላቸው ሰዎች የሚያምራቸው ነገር ዝቅ ያለው ቦታ ፣ የረከሰው ግብር ነው ። ብዙ ልዑላንና ልዕልቶች ራሳቸውን የቤተ መንግሥት እስረኛ አድርገው ይቆጥሩ ነበር ። ዛሬም በሩቅ ሲታዩ የሚቀናባቸው ፣ እነርሱ በተራቸው በሌሎች የሚቀኑና የድሆችን ኑሮ የሚናፍቁ ናቸው ። አንዱ ቁሳዊ ጉድለት ሲገጥመው ሌላው ደግሞ ውስጣዊ ጉድለት ያጠቃዋል ። በወርቅ ማንኪያና ሹካ የሚመገቡ የነገሥታት ልጆች የውጭውን ኑሮ በመናፈቅ ክብርን አሽቀንጥረው ሲጥሉ ፣ በድብብቆሽ ኑሮም ራሳቸውን ሲጎዱ ታይተዋል ። በደጅ ያለው እንዴት ይህን ኑሮ ይጥላሉ? እያለ ሲገረምባቸው እነርሱ ደግሞ ሰማይን ጣራው ፣ ምድርን ግቢው አድርጎ በሚኖረው ድሀ ይቀኑ ነበር ። ዓለም በሁለት ጎንዋ ቢገላበጡባት የምትቆረቁር ናት ። ይህችን ዓለም በበቃኝ የተገላገላት እግዚአብሔርን ያወቀ ሰው ብቻ ነው ። አንዱ ባንዱ ሲስቅ ብቻ ሳይሆን አንዱ ባንዱ ሲቀና ጀምበር ይጠልቃል ።
ለዘመናት አንድን ነገር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ ፣ ያ ነገር በቀረቡ ቍጥር እየራቃቸው ሲመጣ ይስተዋላል ። የምንፈልጋቸው ነገሮች ቶሎ አለመሆናቸው የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ይችላል ። የመጀመሪያ ዋጋ የከፈልንበት ነገር ጣዕም ስላለው ነው ። በክብር የምንይዘው ነገር ብዙ ዘመን ደጅ ያስጠናን ነገር ነው ። በዚህም ትዕግሥትንና የነገሮችን ዋጋ እንማራለን ። ሁለተኛው ፈልገን የምናጣው ያ ነገር ቢሆን ከጥቅም ይልቅ ለእኛ ጉዳት ስላለው ነው ። የያዕቆብ ሚስት ራሔል ደስታዋን ሁሉ ልጅ ላይ ወስና ስለነበር ከያዕቆብ ደግነት ክፉ ልጅ ሳያምራት አልቀረችም ። በዚህም በመልክዋ ፣ በመወደድዋ ፣ በነበራት ትልቅ ክብር ማመስገን አልቻለችም ። ለደስታዋ መራቅ ያዕቆብን መክሰስ ጀመረች ። ከእኅትዋ ጋርም አጉል ፉክክር ውስጥ ገባች ። እግዚአብሔር ልጅን ያዘገየባት ግን ለምን መሆኑን እርስዋ ራስዋ ሳትገነዘብ አልፋለች ። ሁለት ልጆች የወለደችው ራሔል ብንያምን ስትወልድ በወሊድ ምክንያት ሞተች ። ዘፍ. 35 ፡ 16-19 ። ያዕቆብም ኀዘን ተረፈው፣ ዮሴፍና ብንያምም በእናት ፍቅር ስስ ሆኑ። በጊዜው የሚሆኑትን ታግሦ መጠበቅ፣ አይሆንም የተባልነውን በምስጋና መቀበል የመንፈሳዊነት ልኩ ነው።
ከእግዚአብሔር በስጦታ የምንቀበለው እንጂ በመብትና በይገባኛል የምናገኘው ምንም ነገር የለም ። ልጅነታችንም የጸጋ ነው ። ብዙ የሕይወት ስብራት የሚያመጣብን ነገር “ይህን ካላገኘሁ እሞታለሁ” ብለን ችክ ያልንበት ነገር ነው ። በረከት ሲመጣ ሕይወት ሊጠፋ ይችላል ። ወርቅን በነሐስ መለወጥ ማለት ይህ ነው ። በዕድሜም በክርስትናም እየበሰልን ስንመጣ ብዙ ነገሮችን እንሰጋለን ። ፈቅደህ ስጠኝ ማለትን እንለማመዳለን ። እግዚአብሔር ባልቀደመበት መራመድን እንፈራለን ። የማጣት በረከትን ፣ የመገፋት ዕድገትን እናጣጥማለን ። ፍላጎታችንን እየሰጋን በእግዚአብሔር የፈቃዱ ሚዛን እንለካዋለን ።
ሰው ውስጡ ቁጡ ከሚሆንበት ነገር አንዱ ፈልጎ ማጣት ነው። የፈለግነው ቢሆንም ዓለም ጎዶሎ ነው። በጌታ ደስ ይበለን!!!
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን