የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 7

የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።

7- መታፈን

የሰው ልጅ በነፍሱ ለባዊነትን/ማሰብን ፣ ነባቢነትን/መናገርን ፣ ሕያውነትን/መኖርን የተቀዳጀ ትልቅ ፍጡር ነው ። የሰው ልጅን የማሰብ ፣ የመናገርና የመኖር መብት ነገሥታት አይሰጡትም ፣ ያስከብሩለታል እንጂ ። ሰው ሲፈጠር በነጻነት በመፈጠሩ የትኛውም ምስለኔ ተነሥቶ ዲሞክራሲ ሰጠሁህ ሊለው አይገባም ። እግዚአብሔር የሰጠውን ነጻነት በማስከበሩ የአምላክ ሎሌ ሁኛለሁ ብሎ መደሰት ይገባዋል ። ሰውን ሰው የሚያደርገው ማሰብ ነው ። አጭሩን ረጅም ፣ ውስኑን ስፉሕ የሚያደርገው ማሰብ ነው ። በአሳብ ሰማይ ይወጣል ፣ እመቀ እመቃት ይወርዳል ፤ በዳርቻዎች ይወናጨፋል ፣ ከአድማስ አድማስ ይዘላል ። አሳብ ደስ ይላል ። ማድረግ የማይችሉትን ማሰብ ይቻላል ። የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት አስቀድሞ በልበ ሥላሴ የታሰበ ነው ። አሳብ ፈጣሪ ነው ። አሳብ የሚታዩ ሥልጣኔዎች መገኛ ነው ። ማሰብ ባይኖር ለውጥ አይኖርም ነበር ። ሰው ከእንስሳት ልዩ የሚባለው ካለበት ኑሮ የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ በመራመዱ ነው ። ይህም ማሰብ ነው ። የደረሰበትን ችግር እንዲሁ የሚቀበል ሳይሆን መፍትሔ ፈላጊነቱ ሰውን ከእንስሳ ልዩ ያደርገዋል ። ሙቀት ሲገጥመው ማቀዝቀዣ ይሠራል ። እግዚአብሔር ለበረዶ አገሮች የሚነድ እሳት አልፈጠረም ፣ ማሞቂያ መሥራት የሚችል አእምሮ ግን ሰጥቷል ። ችግር ብልሃትን ያመጣል ። ያላደግነው ምቹ አየር ላይ ስለተቀመጥን ነው ። ክረምት ከበጋ አንድ ዓይነት ልብስ የሚያስለብስ አየር ንብረት ላይ ሁነን እንዴት ብለን እንሠራለን !

ከማሰብ የቀጠለ መናገር ውብ ነው ። አስበው የሚናገሩ የፈረሰ አገር ይሠራሉ ፣ ሳያስቡ የሚናገሩ የተሠራ አገር ያፈርሳሉ ። ምላስ የበደልዋን ዋጋ እስካሁን ተቀብላ አታውቅም ። እርስዋ ተናግራ በከንፈር መጋረጃ ትጋረዳለች ፣ በጥርስ ቅጥር ትከበባለች ። እርስዋ በተናገረች እጅ ይሰበራል ፣ እርስዋ በተሳደበች እግር ይቆስላል ። ምላስ መልክዋም የእሳት ነው ። ስንቱን ታቃጥለዋለች ። እሳት ግዙፉን ቤት ያሳንሰዋል ፣ ተራራውን አመድ ያደርገዋል ። ምላስም ንጉሡን ጳጳሱን ሲያዋርድ ይውላል ። በዚህ ዘመን ምላስ ጸጥ ብትል ዓለም ይድን ነበር ።

ለመናገር ማዳመጥ ፣ ማንበብ ፣ ማሰብ ፣ መመጠን ፣ መተመን ፣ ግቡን ማየት ያስፈልጋል ። “ከአፍ የወጣ ካፋፍ” እንዲሉ የተናገርነውን ብንጸጸትበት እንኳ አሳቡን የገዛው ግን ይዞ ሊያውክበት ይችላል ። እግዚአብሔር ለባዊ አምላክ ፣ ዘላለማዊ ምክር ያለው ሲሆን ነባቢም ነው ። በቃሉ ይፈጥራል ፣ ያሳልፋል ፤ ያድናል ፣ ይገድላል ። የእኛም የፍጡር ቃል ብንንቀውም ሲተክልና ሲነቅል ይውላል ። የብዙ ሰው ሕመም በምላስ መወጋት ነው ። ስድብ ሐሜት ለወርዋሪው ቀላል ፣ ለሚቀበለው ግን ሕመም አለው ።

አለመናገር ጨዋነት አይደለም ። “እርሱ ጨዋ ነው ፣ ምንም አይናገርም” ሲሉን መደሰት አይገባንም ። ዝም ቢሉ አፍ ይሸታል ። ጨዋነት የሚናገሩበትን ቦታና ጊዜ መለየት ነው ። “ጨዋ ነው አይናገርም” የሚሉን እየተናገሩልን መኖር የሚፈልጉ ፣ ካልመራናችሁ የሚሉን ናቸው ። ንግግር የልምምድ ውጤት ነው ። ማልቀስ ብቻ የሚችለው ፣ አባ ፣ እማ ብቻ ማለትን የሚያውቀው ሕፃን ሲያድግ እንደ ፖለቲከኞቹ ይለፈልፋል ። አለመናገር እንደ ጨዋነት በሚታይበት ቤት ውስጥ ያደጉ የመታፈን ስሜት ይሰማቸዋል ። አሳባቸውን መግለጥና መብታቸውን መቀበል ሲያቅታቸው ውስጣዊ ቍጣ ይነቀንቃቸዋል ። ቍጠኛ ይሆናሉ ፣ ለምንም ነገር ዱላ ይመዝዛሉ ወይም በጭንቀት ራሳቸውን ይቀጣሉ ። ብዙ የትዳር ጓዶች እኔ ብቻ ልናገር በማለት የራሳቸውን ባሩድ ተኩሰው ሌላውን ተቀበል ብቻ ብለው ይሄዳሉ ። መታፈን ቍጣን ይወልዳል ። አምባገነን መሪዎችና የሃይማኖት አስተዳዳሪዎች በማፈን ለመግዛት ይሞክራሉ ። በጊዜው ቢተነፍስ እንደ ፍል ውኃ ይፈውስ የነበረው አሳብ ፣ በመታፈኑ እሳተ ጎሞራ ሁኖ ይፈነዳል ። በዚህ ምክንያት ሁሉም የጥፋቱ ተጋሪ ይሆናል ።

ዝም ብለው ሲሰሙን ከመደሰት ንግግርን ማለማመድ ፣ አሳባቸውን መጠየቅ ይገባናል ። አስተማሪ ፈተና የሚያዘጋጀው ዝም ብሎ ይሰማው የነበረውን ተማሪ ለማናገር ነው ። አሳቦች መጨቆን የለባቸውም ። የንግግር የመጻፍ መብቶች ተፈጥሮአዊ ናቸውና ልጓም ተደርጎላቸው ሊከበሩ ይገባቸዋል ። ተቹን ተብለው ለመተቸት የሚከፈላቸው ተቋማት በሰለጠነው ዓለም አሉ ። ሳንከፍለው ያላየነውን ነገር የሚያሳየን ሊከበር ይገባዋል ። ብቻ የመታፈን ስሜት ቍጣን ይወልዳል ። ሰዎችን እንስማቸው ፤ ከእኛ የተሻለ አሳብ አላቸው ። እኛ ያላየነውን የማየት አቅም አላቸው ። ቶማስ ጃፈርሰን፡- “ያለ ፕሬስ ከሚኖር መንግሥት ፣ ያለ መንግሥት የሚኖር ፕሬስ እመርጣለሁ” ብለዋል ይባላል ። የእኛ አገር ንግግር በአብዛኛው ግለሰባዊ ሕይወትን ማጥቃት ነውና አሳብ የበላይ መሆን ያቅተዋል ። የቀደሙ ነገሥታት ሕዝብ ዝም ሲል ይጨነቁ ነበር ። መናገሩን ይፈልጉታል ማለት ነው ። በቁንጥጫ ማናገርና በነጻነት ማናገር ልዩነት አለው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ