የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 8

 

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና ።” ያዕ. 1 ፡ 20 ።

8) ጉድለት አለብኝ ብሎ ማሰብ

አንዳንድ ጊዜ ለውስጣችን የምንነግረው የጉድለት ስም አለ ። አለብኝ የምንለው ጉድለት ግን በርግጥ ላይኖር ይችላል ። ጥሩ መናገር የሚችሉ ሰዎች እኔ መናገር አልችልም ብለው ሲያዝኑ ይታያሉ ። በሌለ ችግር ተጨባጭ ጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች አሉ ። መልከ ቀና ናቸው ፣ ንጹሕም ናቸው ። ነገር ግን ራሳቸውን መልክ የለኝም ፣ ንጹሕ አይደለሁም ብለው የሚጠራጠሩ አያሌ ሰዎች አሉ ። በዚህ ምክንያት ራሳቸውን ብቸኛ ያደርጋሉ ፣ ከሰዎችም ገለል ብለው ይተክዛሉ ። ባልተጨበጠ ችግር የተጨበጠ ጉዳትን በራሳቸው ላይ ያስተናግዳሉ ። በእነዚህ ሰዎች ላይ ከመፍረድ ማበረታታት የበለጠ መልካም ነው ።

ሌሎችም ጠላት በእነርሱ ላይ ያሰማውን ትችትና ነቀፌታ አምነውት ራሳቸውን ችግር እንዳለበት ሰው ይቆጥራሉ ። በተለያየ ፍርሃት ውስጥ በማለፍም ለምሳሌ እንስሳትን ፣ ከፍታ ቦታዎችን ፣ ውኃን ፣ መኪና መንዳትን በመፍራት ምክንያት ውስጣቸው ብስጩ የሚሆንባቸው አሉ ። ሌላው ያደረገውን ባለ ማድረጋቸው ያዝናሉ ፣ በራሳቸው ደካማነት ይናደዳሉ ። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ፍርሃቶች ሰውን ሁሉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፣ በመሸሽ ሳይሆን ቀስ በቀስ በመላመድ የሚወገዱ ናቸው ።

የሰው ልጅ በሁሉ ነገር ሙሉ አይደለም ። ሙሉ ቢሆን ኖሮ አምልኮተ እግዚአብሔርን ያስቀር ነበር ። ሙሉ ቢሆን ኖሮ ሰዎችን ይገፋ ነበር ። ሙሉ ቢሆን ኖሮ ራሱን እንደ አምላክ ይቆጥር ነበር ። እግዚአብሔር ለሰውና ለመላእክት የሰጠው ቅዱስ ጉድለት አለ ። ያንን በደስታ መቀበል ይገባል ። ሳጥናኤል ይህን መረዳት አቅቶት አምላክነትን ሲሻ መልአክነትን አጣ ።

አንዳንድ የታወቁ ጉድለቶች በጸሎት ከጠየቅን ይሰጡናል ። ሌሎቹ ደግሞ ስለማያስፈልጉን አይሰጡንም ። የምንሻው ጸጋ ያለውን ጸጋ እንዳያጠፋው የማይሰጡን ሀብታት አሉ ። የቤተ ክርስቲያን እረኛ የሆነው አባት ሀብተ ፈውስ ቢሰጠው ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ጊዜ ሊያጣ ይችላል ። ነቢይ ትንቢት ቢናገር ሊሰማ ይችላል ። አንድ እረኛ ቢናገር ግን መንግሥትን ለመቃወም እንደ ተናገረ ሊተረጎም ይችላል ። ሌጣ ለሆነውና በማንኛውም ጊዜ ወደ ጫካው ሊገባ ለሚችል ባሕታዊ ትንቢትን ፣ አደራ ላለበት አባት ደግሞ ጥበብን የሰጠ እግዚአብሔር ድንቅ ነው !

ጉድለትን እንደ ሙላት መጠቀም ብዙዎችን ታላላቅ ቦታ ያደረሰ ነው ። ሕይወት ከዓይን ብሌን በላይ ነው ብለው ታላላቅ የዜማ ሰዎች ወጥተዋል ። ዓይነ ሥውርነታቸው ሳይገድባቸው የብዙዎችን የልብ ጨለማ የገፈፉ አሉ ። እጅና እግርን ማጣት አእምሮን ማጣት አይደለም ። ዛሬ ዘመን ሰልጥኖ ውጫዊ አካል ሳይሆን እውቀት ብቻ እንጀራ የሚያመጣ ሁኗል ። እግር የሌላቸው መኪና ይነዳሉ ፣ የማያዩ ሰዎች መራመድ ችለዋል ። ዘመኑ ከአካል ይልቅ ለእውቀት የቀረበ ነው ። ጉድለት የምንለው ነገር በራሱ ሙላት ሊሆን ይችላል ። ያንን በደስታ መቀበል አስፈላጊ ነው ። እኛ ያልተቀበልነውን ማንነት ሌሎች እንዲቀበሉት ማስገደድ አንችልምና ። በምድር ላይ ጉድለት የምንለው ነገር በሰማይ የሚጠቅም አይደለም ። የምድር ሙላት በሰማይ ባዶነት ነው ። ትልቁ ጉድለት በሥላሴ አለማመን ፣ የወልድን ቤዛነት አለመቀበል ፣ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን አለማግኘት ነው ።

በጉድለት ስሜት ብቻቸውን የሚሰቃዩ ሰዎች ሊለውጡት የሚችሉትን ነገር ዛሬ ቢጀምሩ ፣ ሊለውጡት የማይችሉትን ዛሬ እንደ ሙላት ቢያዩት ታሪክ መሥራት ይቻላል ። በእግዚአብሔር ግን ሁላችንም ሙሉ ነን ። ያለ እግዚአብሔር ያለ ሙላት ከጉድለት በላይ ያሰቃያል ። አዎ ውስጣዊ ቍጣ ጉድለት አለብኝ ብሎ ከማሰብ ይመጣል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ